የአዲሱ የተመድ ዋና ጸሃፊ የሰላም ጥሪ  | ዓለም | DW | 02.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአዲሱ የተመድ ዋና ጸሃፊ የሰላም ጥሪ 

አዲሱ የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉታሬዝ በአዲስ ዓመት መግለጫቸዉ ዓለም ለሰላም ቅድሚያ ልትሰጥ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል ። ለዚህም ሁሉም ርብርብ እንድያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። እሳቸዉ ይህንን ይበሉ እንጅ መጭዎቹ 5 የዋና ጸሃፊነት አመታት ለጉተሬዝ አልጋባልጋ እንደማይሆኑላቸዉና በርካታ ፈተናዎች እንደሚያጋጥሟቸዉ ከወዲሁ እየተነገረ ነዉ። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:30
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:30 ደቂቃ

አንቶኒዮ ጉተሬዝ


አዲሱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ ሥራቸውን በጀመሩበት በጎርጎሮሳዉያኑ ጥር 1 2017 ዓም በሰጡት ይፋዊ መግለጫ አለም ለሰላም ቅድሚያ ልትሰጥ እንደሚገባ ተናግረዋል። ላለፉት 10 አመታት በድርጅቱ ዋና ጸሃፊነት ያገለገሉትን ባንኪ ሙንን ተክተዉ ወደ ሥልጣን የመጡት የ67ቱ አመቱ አንቶኒዮ ጉታሬዝ በአለማችን የሰዉ ልጆች ክብር ፣ተስፋ ፤እድገትና ብልጽግና የሚወሰኑት በምንገነባዉ ሰላም ልክ  በመሆኑ ፤ሰላም ለአለም ግብና መመሪያ ሊሆን ይገባል ሲሉ
የመጀመሪያ በተባለዉ በዚሁ ይፋዊ መግለጫቸዉ አስረድተዋል።በመሆኑም  አዲሱ አመት 2017 የመቻቻልና የሰላም እንዲሆን እንዲሁም አስተማማኝ ሰላም 
በአለም ላይ እንዲሰፍን እያንዳንዱ ዜጋ፣መንግስታትና መሪዎች ልዩነቶችን ወደጎን በመተዉ ለሰላም ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
«ከዚህ ጦርነት ማንም አይጠቀምም።ሁሉም ተጎጂ ነዉ።በትሪሊየን የሚቆጠር ዶላር ማህበረሰብንና ኢኮኖሚን ለማዉደም ይዉላል።ይህ ኡደት አለመተማመንና ስጋትን 
ለትዉልድ ያተርፋል።ሁሉንም ቀጠናወች በማተራመስ ሽብርተኝነት ለአለማችን አዲስ ስጋት ሆኖ ሁላችንም ላይ ተጽእኖ አሳርፏል።በዚህ አዲስ አመት ሁላችሁንም የምጠይቀዉ የኔን የአዲስ አመት መፍትሄ  እንድትጋሩ ነዉ።እሲኪ ሰላምን እናስቀድም።2017 ትን ዜጎች ፤መንግስታትና ፤መሪወች ሁላችንም ልዩነትን ለማሸነፍ ጥረት እናድርግ።ሰላም ግባችንና መመሪያችን መሆን አለበት።»
የቀድሞዉ የፓርቹጋል ጠቅላይ ሚንስትር የአሁኑ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በሽብርተኝነትና የርስበርስ ግጭቶች 
ምክንያት የጥቃት ኢላማ የሚሆኑና በዚሁ ሳቢያ ህይወታቸው የሚያልፍ እና ንብረታቸው የሚወድም ንጹሃን ዜጎች ጉዳይም በእጅጉ እነደሚያሳስባቸዉ
በመግለጫቸዉ አመልክተዋል።

UN Hauptquartier New York Gebäude (imago/imagebroker)

የተመድ ዋና ጽሕፈት ቤት ኒዉ ዮርክ

«የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ ከሆንኩ  ከመጀመሪያዉ ቀኔ ጀምሮ  በልቤ ዉስጥ በከፍተኛ ደረጃ አንድ ጥያቄ አለ።በሚሊዮን የሚቆጠሩና በግጭት ዉስጥ ያሉ ህዝቦችን፣ በመካከላቸዉ ማንም ሳይኖር  በጦርነት የሚሰቃዩ  ፣በአደገኛ ሀይል የሚጠቁ ና  በአደገኛ ሁኔታ በጦር መሳሪያ የሚገደሉ  ሰላማዊ ሰወችን፤ሴቶችን፤ህጻናትንና ወንዶችን እንዲሁም ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዉ የድህነት  ኑሮ የሚገፉ ሰወችን እንዴት እንርዳ የሚል ነዉ።»
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ሆነዉ ለበርካታ አመታት ያገለገሉት ጉተሬዝ  ስለሰላም አበክረዉ ቢናገሩም ሽብርተኝነትና  የርስበርስ ግጭት የአለማችን ፈተናዎች ሆነዉ በቀጠሉበት በአሁኑ ወቅት  የሚጠብቃቸዉ ፈተናም ቀላል እንዳልሆነ ከወዲሁ እየተነገረ ነዉ።
የሶሪያ፤የየመን የሊቢያና የደቡብ ሱዳን የርስበርስ ግጭቶችና እንዲሁም አለም በሽብርተኝነትና በአየር ንብረት ለዉጥ ሳቢያ የገጠሟት ችግሮች  
የጉተሬዝ የዋና ጸሃፊነት አመታት ተግዳሮቶች እንደሆኑ ተዘግቧል።ልዕለ ሀያሏ አሜሪካ ለሚመሩት ድርጅት ያላት ድጋፍ አጠያያቂነት  በበሳል ፓለቲከኛነታቸዉና በዲፕሎማትነታቸዉ ለሚነገርላቸዉ ፓርቹጋላዊዉ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ሌላዉ ፈተና ነዉ ተብሏል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ለወሬና  ለጊዜ ማሳለፊ  ከማገልገል ዉጭ ፋይዳ የለዉም  ብለዉ የሚያስቡት የአሜሪካን ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ከተረከቡ በኋላ የሚወስዱት እርምጃ እያጠያየቀ ነው ። የተመድ ህልውና  22 በመቶ የድርጅቱን የጸጥታ ፣25 በመቶ ደግሞ  የሰላም አስከባሪ በጀት የምትሸፍነዉና ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት በእጇ በሆነዉ ዩስ አሜሪካ ለድርጅቱ  በምትሰጠዉ ድጋፍ ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ የአንቶኒዮ ጉተሬዝ የሰላም ጥሪና ተግባራዊነት ብዙዎችን ጥርጣሬ ዉስጥ ከቷል።

UN 70. Geburtstag - Generalsekretär Ban Ki-moon (picture-alliance/dpa/J. Lane)

ተሰናባቹ የተመድ ዋናጸሐፊ ባን ጊ ሙን


አዲሱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ጉተሬዝ በጎርጎሮሳዊዉ የዘመን ቀመር በጥቅምት 2016 ቃለመሃላ በፈጸሙበት ወቅት እንደተናገሩት 
ሁሉም መንግስታት መጭዉን የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጨምሮ አለም በገጠሟት ችግሮች ላይ በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ ቢያቀርቡም አሜሪካን አስቀድማለሁ የሚሉት ዶናልድ ትራምፕ ግን ለጉተሬዝ የሰላም ይቅደም ጥሪ ያሳዩት ፍላጎት  ዝቅተኛ ነበር ተብሏል።ለዚህም ይመስላል ጆን ቢልተን የተባሉ የአሜሪካዉ  የወግ አጥባቂዉ የሪፐብሊካኑ  ፓርቲ አባልና በተባበሩት መንግስታት የዩስ አሜሪካ አምባሳደር ለአሶሸትድ ፕሬስ እንደገለጹት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አሜሪካንና መጭዉን ፕሬዝዳንቷን ዶናልድ ትራምፕን በተመለከተ ጥሩ አማካሪ ሊኖራቸዉ ይገባል ብለዋል።
አምባሳደሩ አያይዘዉም ባንኪ ሙንን እንደተኳቸዉ የቀድሞዉን የድርጅቱ  ዋና ጸሃፊ እንደ ኮፊ አናን አንዳንዶች እንደሚሏቸዉ አለማዊ ሊቀጳጳስ ከሆኑ
ከትራምፕ ጋር ብርቱ ችግር ይገጥማቸዋል ብለዋል።በ1974 ጀምሮ ወደፓለቲካዉ አለም እንደገቡ የሚነገርላቸዉ ጉታሬዝ ግን በነዚህ ሁሉ ፈተናወች መሃል ሆነዉ ግጭትንና ቀዉስን አስወግዶ ሰላም ማስፈን  ቅድሚያ የሚሰጡት ተግባር እንደሆነ ይናገራሉ።ይሳካላቸዉ ይሆን ? ወደፊት የምናየዉ ይሆናል።

ፀሐይ ጫኔ

ኂሩት መለሰ
 

Audios and videos on the topic