የአዲሱ መንግሥት አበይት ምጣኔ-ሐብታዊ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? | ኤኮኖሚ | DW | 06.10.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

የአዲሱ መንግሥት አበይት ምጣኔ-ሐብታዊ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?

ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በተያዘው ዓመት የመንግሥት ገቢን 600 ቢሊዮን ብር ለማድረስና በግብርናው ዘርፍ 592 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን ተናግረዋል። መንግሥት ከወጪ ንግድ 5.25 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት አቅዷል። ሥራ አጥነትን ማቃለል፤ የዋጋ ግሽበቱን በመቀነስ የኑሮ ውድነት ማስተካከል የመንግሥት ትኩረቶች ናቸው

አውዲዮውን ያዳምጡ። 07:52

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ የአዲሱ መንግሥት አበይት ምጣኔ-ሐብታዊ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው?

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ ላለፉት ሶስት አመታት የገንዘብ ምኒስትር ሆነው በመሥራት ላይ የሚገኙት አቶ አሕመድ ሽዴ በያዙት ሥልጣን ቀጥለዋል። ንግድ እና ኢንዱስትሪ ይባል የነበረው ተቋም ተከፍሎ ሁለት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ተቋቁመዋል።  ንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር የተባለውን ተቋም አቶ ገብረመስቀል ጫላ በምኒስትርነት የሚመሩት ሲሆን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን አቶ መላኩ አለበል ይመራሉ። 

የፕላን ኮሚሽን ወደ ፕላን እና ልማት ሚኒስቴርነት አድጎ ለሚቀጥሉት አምስት አመታት ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) እንዲመሩት ተሾመዋል። አቶ ላቀ አያሌው በገቢዎች ምኒስትርነታቸው፣ አቶ ዑመር ሑሴን በግብርና ምኒስትርነታቸው፣ አቶ ታከለ ዑማ በማዕድን ምኒስትርነታቸው ቀጥለዋል። 

የዋጋ ግሽበትን የመቆጣጠር ኃላፊነት የተጣለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለጠቅላይ ምኒስትሩ ተጠሪ ከሆኑ 20 ተቋማት መካከል አንዱ ሆኖ ቀጥሏል። የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዲሁም ወደ አገሪቱ ገበያ ለሚገቡ የቴሌኮም ኩባንያዎች ፈቃድ የሚሰጠው የኢትዮጵያ ኮሙኒኬሽን ባለሥልጣን በተመሳሳይ ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ምኒስትሩ ከሆኑ ተቋማት መካከል ይገኙበታል። 

ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እና ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሰኞ ባደረጓቸው ንግግሮች የኢትዮጵያ መንግሥት በምጣኔ-ሐብት ረገድ ትኩረት የሚያደርጉባቸውን አበይት ጉዳዮች ጥቆማ ሰጥተዋል። ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች የጋራ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ለዋጋ ውድነት እና ሥራ አጥነት መፍትሔ መፈለግ አዲስ የተመሠረተው መንግሥት ዋንኛ የኤኮኖሚ ትኩረቶች መካከል እንደሚገኙበት ተናግረዋል። 

Äthiopien Premierminister Abiy Ahmed stellt im Parlament sein neues Kabinett vor

ዐቢይ ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ በነሐሴ 2011 ዓ.ም. ይፋ የሆነው የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የኤኮኖሚ ማሻሻያ በቀጥታ የሚመለከተው የገንዘብ ሚኒስቴርን አቶ አሕመድ ሽዴ በምኒስትርነት መምራት እንዲቀጥሉ ተደርጓል

ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ "በኤኮኖሚያዊ ዘርፎች የሀገራችንን ማክሮ ኤኮኖሚ በማረጋጋት የተጀመረው ዕድገት ወደ ኋላ ሳይመለስ እንዲቀጥል የሥራ ዕድል ፈጠራን በማስፋፋት የተንሰራፋው ሥራ አጥነት እንዲቃለል፤ የዋጋ ግሽበቱን በመቀነስ የኑሮ ውድነት እንዲስተካከል፤ እንደዚሁም በተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ተግዳሮቶች የገጠሙ ጉድለቶችን በፍጥነት በማረም ሁለንተናዊ ዕድገት እንዲረጋገጥ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል" ብለዋል። 

ሣህለ ወርቅ "በሀገራችን እየጨመረ ለመጣው የዋጋ ግሽበት ብሎም የኑሮ ውድነት መንስኤ የሆኑ የአቅርቦት እና የፍላጎት አለመመጣጠን፤ ዝናብን መሠረት ያደረገ የግብርና ሥርዓት፤ የተዛባ የንግድ ሥርዓት ለማስተካከል በትኩረት ይሰራል። የኑሮ ውድነቱን በዘላቂነት ለመከላከል የገንዘብ እና የፊስካል ፖሊሲ ቁጥጥር ሥራ አጽንዖት ይሰጠዋል። የንግድ ሥርዓቱን የማስተካከል ሥራም የዚህ አመት የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል" ሲሉ አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያ ስታስቲክስ ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያሳየው በመስከረም ወር የዋጋ ግሽበት 34.8 በመቶ ደርሷል። የምግብ ነክ ሸቀጦች ዋጋ ከ37.6 በመቶ ወደ 42 በመቶ ሲያሻቅብ፤ ምግብ ነክ ያልሆኑ ሸቀጦች ዋጋ በአንጻሩ ከ20.8 ወደ 25.2 በመቶ ከፍ ብሏል።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመስቀል አደባባይ በተካሔደ በዓለ ሲመታቸው "ባለፉት አመታት የዋጋ ንረትን ከመቆጣጠር እና የኑሮ ውድነትን ከመቀነስ አንጻር የተወሰዱት እርምጃዎች የሚፈለገውን ውጤት እንዳላመጡ እና ደሀው የሕብረተሰብ ክፍል የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆኑን መንግሥት በውል ይገነዘባል" ሲሉ ተናግረዋል። 

ጠቅላይ ምኒስትሩ የዋጋ ግሽበቱ የበረታበትን "የሕብረተሰብ ክፍል ከጫና ለመታደግ በሚቀጥሉት አመታት መንግሥት የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚሰራቸው የኤኮኖሚ አስተዳደር ሥራዎች መካከል አንዱ የዋጋ ንረትን መግራት ይሆናል" ሲሉ ቃል ገብተዋል። 

ኢትዮጵያ ዐቢይ ሥልጣን ላይ በቆዩባቸው አመታት "መንግሥት መር" እየተባለ ከሚተቸው ምጣኔ ሐብታዊ አካሔድ ፈቀቅ የማለት አዝማሚያ አሳይታለች። ጠቅላይ ምኒስትሩ በንግግራቸው የአገሪቱ ምጣኔ-ሐብት በግሉ ዘርፍ የሚመራ እንደሚሆን ጥቆማ ሰጥተዋል። ዐቢይ እንዳሉት የመንግሥታቸው ሚና ገበያን መደገፍ ይሆናል። 

"ኤኮኖሚያችን በግል ዘርፍ ቀዳሚነት እና ገበያን በሚደግፍ መንግሥት አጋዥነት የሚመራ ተወዳዳሪ እና ከዓለም አቀፍ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ጋር የተሳሰረ፤ ፈጣን እና ፍትኃዊ ዕድገትን የሚያረጋግጥ፤ ለዜጎቻችን በቂ እና አስተማማኝ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ምጣኔ ሐብት እንዲሆን እንሰራለን" ብለዋል። 

የኢትዮጵያ የማምረቻ ዘርፍ ለሥራ ዕድል ፈጠራ አስተዋጽዖ እንዲያበረክት እና አገሪቱ ከውጭ ገበያ የምትሸምታቸውን "ስትራቴጂክ" ሸቀጦች ለመተካት መንግሥት በትኩረት እንደሚሰራ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ተናግረዋል። ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ "በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በኩል የነባር አምራቾችን ምርት እና ምርታማነት በማሻሻል እንደዚሁም ጥራት ያላቸው አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በመሳብ ዘርፉ ለሥራ ዕድል ፈጠራ አስተዋጽዖ እንዲያበረክት በትኩረት ይሰራል። በተጨማሪም ስትራቴጂካዊ የሆኑ የገቢ ምርቶችን የሚተኩ የማኑፋክቸሪንግ ውጤቶች እንዲስፋፋ ይደረጋል። የወጪ ንግድ ምርቶችን በብዛት፣ በጥራት እና በአይነት ማምረት እና የሀገር ውስጥ ባለሐብቱ በማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ ንዑስ ዘርፍ በስፋት እንዲሰማራ ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ለጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት የሚያደርገውን አስተዋጽዖ ማሳደግ እና የንዑስ ዘርፉ ከሀገሪቱ ዘላቂ ልማት የአረንጓዴ ኤኮኖሚ ልማት ስትራቴጂ ጋር የተጣጣመ ይሆናል" ብለዋል።

Sahle-Work Zewde

ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ መንግሥት ትኩረት ከሚያደርግባቸው ጉዳዮች መካከል የዋጋ ግሽበት፣ የኑሮ ውድነት እና ሥራ አጥነት እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ለዓለም ገበያ የምታቀርባቸውን ማዕድናት "በአይነት በመጠን እና በብዛት" በመጨመር ከዘርፉ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ማሳደግ ሌላው የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ተስፋ የጣለበት ዕቅድ ነው። የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪዎች የሚያሿቸው ማዕድናት "በሀገር ውስጥ እንዲቀርቡ ይደረጋል" ያሉት ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ "ከፍተኛ የማዕድናት ሐብት ባለባቸው አካባቢዎች እና አገራዊ ፋይዳዎቻቸው በላቁ የማዕድን ኩባንያዎች አካባቢ የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች እንዲቀረፉ በልዩ ትኩረት ይሰራል። በዘርፉ የተመራ የሰው ኃይል ልማት በጥራት እና በብዛት እንዲኖር፤ የተማረ የሰው ኃይል ልማት በጥራት እና በብዛት እንዲኖር ይደረጋል። ለባህላዊ እና አነስተኛ የማዕድን አምራቾችም ልዩ ትኩረት ይሰጣል"ብለዋል።

በግንባታው ዘርፍ የአገሪቱን ፍላጎት "የሀገር በቀል ኩባንያዎች እንዲሸፈን" እንደሚደረግ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ተናግረዋል። ዘርፉ ሰፊ የሥራ ዕድል እንዲፈጥር ማድረግም ሌላው የመንግሥት አቅጣጫ ነው። 

ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ እንዳሉት በ2014 ዓ.ም. የመንግሥት ገቢን ወደ 600 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ታቅዷል። ከዚህ ውስጥ 83 በመቶው ከታክስ ለመሰብሰብ የተወጠነ ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት ከወጪ ንግድ 5.25 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ማቀዱንም ፕሬዝዳንቷ ጠቅሰዋል። ይኸ ካለፈው 2013 ዓ.ም. ሲነጻጸር በመንግሥት መረጃ መሠረት በ1.7 ቢሊዮን ዶላር ገደማ የላቀ ነው። በፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ንግግር መሠረት በግብርናው ዘርፍ 592 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ለማምረት ዕቅድ ተይዟል።  

እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች