የአዲሱ ሐገር አሮጌ ፈተና | አፍሪቃ | DW | 31.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአዲሱ ሐገር አሮጌ ፈተና

እነዚሁ ፖለቲከኞች የእስካሁኗም፤የወደፊቷም ደቡብ ሱዳን መሪዎችም ናቸዉ።የሥምምነቱ ሠነድ አንደኛዉ አንቀፅ « የተፈፀመዉን የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚያጣራ የእዉነት አፈላላጊ የእርቅና የፈዉስ ኮሚሽን ይዋቀራል።» ይላል።ሠብአዊ መብት ረጋጭ፤ ጣሹ፤ ሕዝብ አስጨራሽ፤ አሳዳጁ ማን ይሆን?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 14:57
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
14:57 ደቂቃ

የአዲሱ ሐገር አሮጌ ፈተና

ፖለቲከኞችዋ-ከሠሜን ጠላቶቻቸዉ ጋር ተዋጉ፤ አዋጉ፤ የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ያሏትን ነፃ ሐገር መሠረቱ።2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) ሥልጣን ያዙም።ሰወስት ዓመት አልቆዩም እርስ በራስ ተጣሉ።ተዋጉ፤ አዋጉ፤ብዙ ሺዎችን አስገደሉ፤ ሚሊዮኖችን አሰደዱ-አፈናቀሉ።በሃኛ ወራቸዉ ሠላም ለማዉረድ ተስማሙ።ታረቁ።ሥምምነት እርቃቸዉ መነሻ፤ የሐገራቸዉ እዉነት ማጣቃሻ፤ የወደፊት ጉዟቸዉ እንዴትነት መድረሻችን ነዉ።

በልማዱ ጦርነትን የሚያስቆም ዉል ሲፈረም በጦርነቱ ለተጎዳዉ ሕዝብ የተስፋ ሰበብ፤ የፌስታ፤ ደስታ፤ ፈንጠዝያ ምክንያት ነዉ።ደቡብ ሱዳን ሱዳን ግን ይሕ የለም።እርግጥ ነዉ ከትናንት በስቲያ ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ጁባ ዉስጥ የሠላም ስምምነቱን ሲፈርሙ እዚያዉ ጁባ የነበሩት የኢትዮጵያ፤ የኬንያና የዩጋንዳ መሪዎች ዕለቱን ለአካባቢዉ «አስደሳች ቀን» ማለታቸዉ ተጠቅሷል።

ለጁባ፤ለቤንቲዉ፤ ለአኮቦ ይሁን ለሌሎቹ አካባቢ ነዋሪዎች ግን የመሪዎቹ «አስደዳች ዕለት» ከወትሮዉ የተለየ አይደለም።የምሥራቅ አፍሪቃ የፖለቲካ ተንታኝ ፕሮፌሰር መድሕኔ ታደሰ-ሥምምነቱን ከተስፋ ይልቅ በጥርጣሬ፤ ከእፎይታ ይልቅ በቅሬታ እንዲያስተዉል የተደረገዉ ሕዝብ ለመደሰት አልታደለም።

አሳሳቢዉም ይኸዉ ነዉ።የጦርነት ዑደት።የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር ሥምምነቱን የፈረሙት ከአፍሪቃም፤ ከአዉሮጳም፤ ከዩናይትድ ስቴትስም አልፎ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት በማዕቀብ እንደሚቀጣቸዉ ካስፈራራቸዉ በኋላ ነዉ።የፀጥታዉ ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበር የናጄሪያዋ አምባሳደር ጆይ ኦጉዋ ኪር ስምምነቱን ካልፈረሙ የምክር ቤቱ አባላት ዩናይትድ ስቴትስ ያረቀቀችዉን የማዕቀብ ሰነድ ለማፅደቅ መዘጋጀታቸዉን አስታዉቀዉ ነበር።

«ፕሬዝደንት ኪር ሥምምነቱን ካልፈረሙ፤ የምክር ቤቱ አባላት ፈጣን እርምጃ ለመዉሰድ መዘጋጀታቸዉን ገልፀዋል።»

1955 የያኔዋ ሱዳን ነፃ ስትወጣ ዉስጥ ዉስጡን መብላላት የጀመረዉ የደቡብ ሱዳኖች የነፃነት ጥያቄ የአማፂ ቡድን ቅርፅ፤ መልክና ባሕሪ የያዘዉ በአስራ-ሁለተኛ ዓመቱ ነበር።1967ANYANYA (መርዛማዉ እባብ እንደማለት ነዉ) የቡድኑ ስም፤ አግሬይ ጃዳን ላዱ መሪዉ ሆኑ።ግን ብዙም አልቆዩ።ከቅርብ ረዳት፤ ተባባሪ፤ ጓዶቻቸዉ ጋር በገጠሙት ሽኩቻ ሾኬ ተመቱና በሁለተኛ አመታቸዉ ከሥልጣን ተባረሩ።

ጎርዶን ሙዎራት ማይዬን የመሪነቱን ሥልጣን ጠቀለሉእንደ ብዙ የአረብ ሐገራት ሁሉ ሱዳንን ለማዳከም ፀረ-ካርቱም ሐይላትን የምታደራጅ-የምታስታጥቀዉ እስራኤል ለደቡብ ሱዳኖቹ አማፂያን የምትልከዉን ትጥቅ ከቡድኑ መሪ ከጎርዶን ሙዎራት ማዬን ይልቅ ለቡድኑ ጦር ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ለጆሴፍ ላጉ ታስረክብ ገባች።ጆሴፍ ላጉ የአስታጣቂያቸዉን መልዕክት ለመረዳት ማሰላሰል አላስፈለጋቸዉም።ጦሩም ትጥቁም እጃቸዉ ከገባ የመሪነቱን ሥልጣን የማይጠቀልሉበት ምክንያት አልነበረም።

አለቃቸዉን ጎርዶን ሙዎራት ማይዬን በቀላሉ ፈንግለዉ የቡድኑን የመሪነት ሥልጣን ጨበጡ።1971።ባመቱ የሱዳን መንግሥትና አማፂያኑ አዲስ አበባ ዉስጥ የሠላም ሥምምነት ተፈራረሙ።ከጦርነቱ በተጨማሪ የመሪዎቹ መጠላለፍ፤ መሻኮት፤ መዋዋጥ ከሁሉም በላይ የዉጪ ጣልቃ ገብነት ግራ-ቀኝ የሚያላጋዉ የመርዛመዉ እባብ ትግልም አከተመ።1972

«መርዛማዉ እባብ» አፈር ልሶ ሲነሳ-ቁጥር 2 ከሚል ቅፅል ጋር አዲስ ስም፤ አዲስ አደረጃጀት፤ አዲስ ርዕዮተ ዓለም ቢበጅለትም በተለይም እስከ 1990ዎቹ ማብቂያ ድረስ ሁለት ትላልልቅ ነፃ አዉጪ ቡድናትን የመሠረቱት ፖለቲከኞች እርስ በርስ ያልተሻኮቱበት፤ አንዱ ሌላኛዉን ለመጣል ያላ ሴሩበት ዘመን ከነበረ ጥቂት ነዉ።ጎሳ፤ ጥቅም ሥልጣን የሚዘዉረዉን ሽኩቻ ለማጋጋም ደግሞ የሶሻሊስት-ካፒታሊስቶች፤ የአረብ እስራኤሎች፤ የሙስሊም ክርስቲያኖች ፍትጊያ ፤የአካባቢዉ ሐገራት ጠብ ከበቂ በላይ ነበር።

ደቡብ ሱዳን ከሰሜንዋ ተገንጥላ ነፃ መንግሥት ያወጀችበት ሥምምነት በ2005 እስከተፈረመበት ጊዜ ድረስ ለሠላሳ ዘመናት ያክል በተደረገዉ ጦርነት ከ2,5 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ አልቋል።በሚሊዮን የሚቆጠር ተሰዷል።የዉጪዉን ጫና እያስታመሙ፤ የዉስጡን ክፍፍል እያባበሉ ጦርነቱን ከፍፃሜዉ ያደረሱት ጆን ጋራግ በ2005 መሞታቸዉ ለእጩይቲ አዲስ ሐገር የሌላ ፈተና፤ነፃናት ለሚናፍቀዉ ሕዝብ የተጨማሪ መከራ አዲስ ጅምር ነዉ-የሆነዉ።

2011 ነፃ መንግሥት ያወጀችዉ የቀድሞዋ የሱዳን ግዛት የሐገርነት ቀርቶ የአዉራጃነት መዋቅር፤ የመሰረተ-ልማት አዉታር፤ ቢሮ ክራሲም አልነበራትም።የጋራንግ ወራሾችም አዲሲቱን ሐገራቸዉን ለሐገር ወግ፤ ለመንግሥትነት ማዕረግ፤ ሕዝባቸዉን ለሠላም ነፃነት ባለቤትነት ለማብቃት ከመጣር ይልቅ ሲሻቸዉ ከሰሜን ሱዳን፤ ሲያሰኛቸዉ እርስ በርስ ይላተሙ ገቡ።

እንደ ጦርነቱ ሁሉ ነፃነቱም ካርቱምን ለማዳከም፤ የዉጪ ሐይላትን ጥቅም-ለማስከበር፤ የነፃ አዉጪዎቹን የገዢነት ጉጉት ለማርካት፤ አዲስ የተገኘዉን ነዳጅ ዘይት ለመሻማት ካልሆነ በስተቀር ያቺ ግዛት መንግሥት የመሆን መዋቅር፤የመሠረት ልማት አዉታር፤ ቢሮክራሲም አልነበራትም።ፕሮፌሰር መድሕኔ እንደሚሉት ደግሞ የደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ግዛቲቱ መንግሥት ለመሆን የሚያስፈልጋትን ለማሟላት ቀርቶ ሕዝብን የመምራት ብስለት፤ ትዕግስት፤ ብልሐት፤ አመለካከቱም አልነበራቸዉም።አሁን ደግሞ ብሷል።

የደቡብ ሱዳን ሕዝብ የነፃነቱን መዝሙር በቅጡ አዚሞ ሳያበቃ፤ መሪዎቹ ዳግም የገጠሙት ዉጊያ አስር ሺዎችን አርግፏል።ከሁለት ሚሊዮን የሚበልጥ አፈናቅሏል-ወይም አሰድዷል።ከአራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን የሚበልጠዉን ምግብ አልባሳት አሳጥቷል።ጦርነቱ የርስ በርስ ብቻ አልነበረም።እስከ ነፃነት ዋዜማ ድረስ ከሰሜን ሱዳን ጋር እንደተደረገዉ ሁሉ በዉጪ ሐይላት የሚጋጋም ነበር።በኢትዮጵያ የሠላምና ልማት ዓለም አቀፍ ጥናት ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ አቶ አበበ አይነቴ።

ፕሮፌሰር መድሕኔ አከለበት።

እንደ ጦርነቱ ሁሉ የሠላም ስምምነቱም በተፋላሚ ሐይላት በተለይም በፕሬዝደንት ሳልቫኪር ፍላጎት የተረፈ አይደም። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ማስጠንቀቂያ፤ በአሜሪካኖች ዛቻ፤ በአካባቢዉ ሐገራት ጫና የመጣ ነዉ።በፕሮፌሰር መድሕኔ ቋንቋ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት የባራክ ኦባማ ሥም ሥላለበት ነዉ።

በጫና የተፈረመዉ ሰነድ-የዉጪ ሐይል ብሎ በደፈናዉ የገለፀዉ የዩጋንዳ ጦር በ45 ቀናት ዉስጥ ከደቡብ ሱዳን መዉጣት አለበት።ርዕሠ-ከተማ ጁባ ከጦር እንቅስቃሴ ነፃ ትሆናለች።የተፋላሚ ሐይላት ታጣቂዎች በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ በየ ጦር ሠፈሩ መክተት አለበት።

የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝደትነቱን ሥልጣን አማፂዎች (መሪያቸዉ) ይረከባሉ።በዘጠና ቀናት ዉስጥ ጊዚያዊ ብሔራዊ የአንድነት መንግሥት መመሥረት አለበት።ከሠላሳ ወራት በሕዋላ ምርጫ መጠራት አለበት።

አብረዉ መሥራት አቅቷቸዉ ፤ ጥቅም አጣልቷቸዉ ወይም የዉጪ ሐይል ገፋፍቷቸዉ እስካሁን ሲዋጉ፤ ሲያዋጉ፤ ሺዎችን ሲያስጨርሱ የነበሩት ፖለቲከኞች ስምምነቱን ገቢር የማድረጉ ፍላጎቱ፤ትዕግስት፤ ስምምነቱ ይኖራቸዉ ይሆን።ፕሮፌሰር መድሕኔ «በግዳቸዉ» ዓይነት ይላሉ።

በምሥራቅ አፍሪቃ በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) የደቡብ ሱዳን የሠላም ስምምነት አጣሪና ተቆጣጣሪ ሐላፊ አምሳደር ተፈራ ሻዉል እንደሚሉት ደግሞ ሰምምነቱን ገቢር ለማድረግ የዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ ነዉ።

ፕሮፌሰር መድሕኔ።አምባሳደር ተፈራ።

እነዚሁ ፖለቲከኞች የእስካሁኗም፤የወደፊቷም ደቡብ ሱዳን መሪዎችም ናቸዉ።የሥምምነቱ ሠነድ አንደኛዉ አንቀፅ « የተፈፀመዉን የሰብአዊ መብት ጥሰት የሚያጣራ የእዉነት አፈላላጊ የእርቅና የፈዉስ ኮሚሽን ይዋቀራል።» ይላል።ሠብአዊ መብት ረጋጭ፤ ጣሹ፤ ሕዝብ አስጨራሽ፤ አሳዳጁ ማን ይሆን? ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

Audios and videos on the topic