የአደይ አበባ ባህርያት እና ጥቅሞቹ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 13.09.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የአደይ አበባ ባህርያት እና ጥቅሞቹ

መስከረም መጥባቱን ተከትሎ ብቅ የሚለው የአደይ አበባ ለብዙዎች የዘመን መለወጥ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ አደይ አበባ ለምን በመስከረም አካባቢ ብቻ ይታያል? እውን በኢትዮጵያ ብቻ ነው የሚበቅለው? ከበዓል ማድመቂያ እና የቤት ማስዋቢያ በዘለለ ሌላ ጥቅም ይኖረው ይሆን?

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:41
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:41 ደቂቃ

አደይ አበባ የደም መፍሰስን ለማቆም ይውላል

አውሮፓውያን ከዘመን መለወጫቸው ሳምንት በፊት በሚከበረው የገና በዓል በወቅቶች መፈራረቅ የሚከሰተውን በረዶ በጉጉት ይጠብቃሉ፡፡ በረዶ ከጎደለ ቅር ይላቸዋል፡፡ በዓሉ ይደበዝዝባቸዋል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያንም ዘመን በሚለውጡበት መስከረም ወር ተፈጥሮ የምትለግሳቸውን አደይ አበባ በናፍቆት ይጠብቃሉ፡፡ ዙሪያው ገባውን በቢጫው አበባ ተውቦ ሲመለከቱ ያኔ አዲስ አመት ባተ ይላሉ፡፡ ወለል ግድግዳቸውን በአበባው ያስጌጣሉ፡፡ ልጃገረዶች “አባባዮሆሽ” ሲጨፍሩ አደይ አበባን ይዘው መዞራቸውም ያለ ነው፡፡ 

አደይ አበባ በኢትዮጵያውያን ያለውን ትልቅ ቦታ ለመረዳት አሁን በግንባታ ላይ ያለውን ብሔራዊ ስቴድየም መመልከት ይበቃል፡፡ ከእነስሙ እና ንድፉ አደይ አበባ ላይ የተንተራሰ ነው፡፡ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ የሆነው አደይ አበባ ከምን ዓይነት የዕጽዋት ዝርያ ይመደባል? መገኛውስ በኢትዮጵያ ብቻ ይሆን?  በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የዕጽዋት ባይሎጂ መምህር ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው ትንታኔ አላቸው፡፡

በኦሃዩ ስቴት ዩኒቨርስቲ የዕጽዋትና የብዘሀ ህይወት ተመራማሪ እና መምህር ፕሮፌሰር መስፍን ታደሰ ስለ አደይ አበባ እና እርሱ በሚገኝበት የሳይንስ ቤተሰብ ውስጥ ባሉ ዝርያዎች ላይ ሰፊ ጥናት ያካሄዱ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ስለሚገኙ ዝርያዎች ብዛት ተከታዩን ብለዋል፡፡ 

ባይደንስ መሰረቱ ሜክሲኮ ነው፡፡ ይህ ዝርያ (genus) በአሜሪካ፣ ሜክሲኮ እና ደቡብ አሜሪካ እንደሚገኝ የሚናገሩት ፕሮፌሰር መስፍን ይህም የሚያመለክተው ትልቅ መሆኑን ነው ይላሉ፡፡ እንደ የአጥኚዎቹ ዓይነት የቁጥር ልዩነት ቢታይም በዚህ ዝርያ ስር እስከ 300 ዘሮች እንዳሉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ 

ባይደንስ ማይክሮ ካርፓ በተባለ የሳይንስ ስም የሚታወቀው አደይ አበባ በሌሎች በእርሱ ዝርያ ስር ከተካተቱ እጽዋቶች የሚለዩት ባህሪያት እንዳሉት ሁለቱም ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ ዕጽዋቶች አንዳቸውን ከአንዳቸው ለመለየት መገለጫ ባህርያቸውን መመልከት እንደሚያስፈልግ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ይናገራሉ፡፡ የቅጠላቸው አዘረጋግ፣ የአበባቸው እና የፍሬያቸው ሁኔታ በመለያነት ከሚያገለግሉት ይገኝበታል፡፡ 

ፕሮፌሰር መስፍን በበኩላቸው የአደይ አበባን ልዩ መገለጫ ከዘር ወደ ዘር መተላለፉ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ሌሎች የዕጽዋት አይነቶች እድገታቸው ሲያበቃ ስራቸው እና ጥቂት ግንዳቸው የሚተርፍ ሲሆን አደይ አበባ ግን ዘሩ ብቻ በመሬት ውስጥ እንደሚቀር ያብራራሉ፡፡    

በኢትዮጵያ ስሙ የገነነው አደይ አበባ የዕይታ ጊዜው እንደስሙ ግዝፈት አይደለም፡፡ ተስፋ እና ደስታን ያንጸባርቃል የሚባለው ቢጫማ ቀለም ሀገር ምድሩን አልብሶ የሚቆየው ቢበዛ ለሶስት ወር እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ይህም የአደይ አበባ ሌላው መለያ ባህሪ እንደሆነ ፕሮፌሰር መስፍን ይገልጻሉ፡፡ አደይ አበባ ከሶስት ወር በኋላ የመሰወሩ ምክንያት ምንድነው? ፕሮፌሰር ሰብስቤ ከእንቅልፋችን ለመንቃት የምንሞላውን ሰዓት በማነጻጸሪያነት በመጠቀም ምክንያቱን ያስረዳሉ፡፡  

በዓመቱ መጀመሪያ ወራት በየቦታው የሚገኘው አደይ አበባ እንደው በየቦታው ከስሞ ከሚቀር ይልቅ ጥቅም ላይ መዋል ይቻል ይሆን፡፡ የኦሃዩ ዩኒቨርስቲው ፕሮፌሰር መስፍን ከ33 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ባካሄዱት ጥናት አደይ አበባ ከፋ እና አርሲ ውስጥ ለጥቅም እንደሚውል ደርሰውበታል፡፡  

አንዳንድ ጥናቶች አደይ አበባ ለስኳር በሽታ እና ለጭንቅላት ካንሰር ህክምና መዋል እንደሚችል ይጠቆማሉ፡፡ ኢኮኦፒያ የተባለ በኢትዮጵያ ያለ ድርጅት ከአደይ አበባ የተሰራ ክሬም ለገበያ እንዳበቃ ገልጿል፡፡ ክሬሙ ወንዶች ጺማቸውን ከተላጩ በኋላ የሚቀቡት ነው፡፡ ድርጅቱ ለሴቶች ያመረተው ክሬም ደግሞ ለማዲያት ማጥፊያነት እንደሚውል ከድርጅቱ የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ኂሩት መለሰ


 

Audios and videos on the topic