የአየር ንብረት ጉባዔ አዘጋጅ ስብሰባ በቦን | ጤና እና አካባቢ | DW | 01.06.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የአየር ንብረት ጉባዔ አዘጋጅ ስብሰባ በቦን

ከ190 ሀገራት የመጡ የመንግሥት ተወካዮች የፊታችን ታህሳስ 2008 ዓም በፓሪስ ፈረንሳይ በሚደረገው የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ላይ የሚቀርበውን የስምምነት ረቂቅ ለማዘጋጀት ዛሬ እዚህ በጀርመን የቦን ከተማ ጉባዔ ጀመሩ።

በዚሁ 11 ቀናት በሚቆየው ድርድር ላይ አንድ አስማሚ ሀሳብ ይወጣል ተብሎ ባይጠበቅም፣ ለተፈጥሮ አካባቢ ተስማሚ የሆነ የአየር ንብረት ፖሊሲ ሊኖር እንደሚገባ የጀርመን የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ሚንስትር ባርባራ ሄንድሪክስ በጉባዔው መክፈቻ ላይ ተማፅነዋል።

« በያዝነው ምዕተ ዓመት ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ያካባቢ ጥበቃን የማይጎዳ የዓለም የምጣኔ ሀብት ያስፈልገናል። የዓለም የሙቀት መጠን ከሁለት ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንዳይበልጥ ለማድረግ የምናሳየው የጋራ ጥረታችን አበረታቺ እና ትክክለኛው ምልክት ነው። ዘላቂ የሆነ ስምምነት ለመድረስ ከፈለግን ይህን የአየር ሙቀትን የመገደቡ ሀሳብ በየብሔራዊ ዓላማችን ላይ ማካተት ይኖርብናል ብዬ አስባለሁ። »

የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሎውሮ ፋቢዩስም በስብሰባው የተወከሉት ሃገራት ገላጋይ ሀሳብ ላይ የመድረሱን ሂደት እስከመጨረሻ ደቂቃ እንዳያጓትቱ ጥሪ አቅረበዋል።

«የስብሰባው መንፈሥ አዎንታዊ ነው። እያንዳንዱ ተወካይ ስምምነት እንዲኖር የሚፈልግ ይመስለናል። ይህ በራሱ አዎንታዊ ነው። ይሁንና፣ ጥያቄዎቹ በጣም በጣም የተወሳሰቡ ናቸው፣ መገንዘብ ያለባችሁ ስምምነቱን መድረስ ያለባቸው 196 ቡድኖች መሆናቸውን እና በ196 ፓርቲዎች መካከል ገላጋይ ሀሳብ የመድረሱ ሂደትም ቀላል አለመሆኑን ነው። »

የተመድ ዋና ጸሐፊ ፓን ኪ ሙን እና የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር የፊታችን ዓርብ በቦኑ ጉባዔ ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። በዚህ ሳምንት መጨረሻ በደቡብ ጀርመን በኤልማው ጥንታዊ ቤተመንግሥት በሚካሄደው የቡድን ሰባት ዓቢይ ጉባዔም ላይ ከሚነሱት ዓበይት የመወያያ አጀንዳ መካከል የዓለም አየር ንብረት ለውጥ አንዱ ነው።

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ