የአየር ንብረት ጉባኤ እና የአፍሪቃዉያን አስተያየት | ጤና እና አካባቢ | DW | 15.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

የአየር ንብረት ጉባኤ እና የአፍሪቃዉያን አስተያየት

ጀርመን በቦን ከተማ የምታስተናግደዉ በሃገራት መካከል የአየር ንብረት ለዉጥን ለመግታት የሚያስችሉ ርምጃዎች ለመዉሰድ የሚካሄደዉ ድርድር እና ጉባኤ ሁለተኛ ሳምንቱን ይዟል። ድርድሩ ከተጀመረ 23ኛ ዓመቱን በመያዙ ጉባኤዉ በእንግሊዝኛ ምህፃሩ COP 23 በመባል ነዉ የሚታወቀዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 12:32

ድርድሩ እስከ ዓርብ ይቀጥላል

በሦስት ዞኖች የተከፋፈለዉ የቦኑ ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ጉባኤ ማስተናገጃ መንደር ከመላዉ ዓለም የተዉጣጡ ተሳታፊዎችን ከነቋንቋዎቻቸዉ እያስተናገደ ይገኛል። በሀገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት የሚጀምረዉ ልዩ ልዩ ስብሰባ እና የቡድን ዉይይት በጋዜጣዊ መግለጫዎች እየታጀበ እስከ ምሽት ይዘልቃል።

የተመድ የአየር ንብረት ለዉጥ ተከታታይ ጉባኤ ላለፉት 21 ዓመታት የመከረበትን እና እልህ አስጨራሽ ድርድሮችን ያደረገበትን ሂደት መስመር የሚያስይዝ ስምምነት ፓሪስ ላይ ከወሰነ ወዲህ የተሻለ ርምጃ እያደረገ ነዉ የሚሉ ወገኖች አሉ። በአንፃሩ ዉሉን 169 ሃገራት መቀበላቸዉ አንድ ነገር መሆኑ የሚቀበሉ ሆኖም ግን ያንን ተግባራዊ ለማድረግ የሚደረገዉ ድርድር አሁንም ጊዜ እየወሰደ ነዉ በማለት ስጋት ብቻ ሳይሆን ትችትን የሚሰነዝሩም በርካቶች ናቸዉ።

በቦን ከተማ ከራይን ወንዝ ዳርቻ ላይ በሰፊዉ ተንጣሎ የሚገኘዉ ለአየር ንብረት ለዉጥ አንዳች መፍትሄ በጋራ እንዲፈለግ የሚሻዉ ጉባኤ የሚካሄድበት ስፍራም ይህንኑ የሁለት ወገን ክርክር እና ሙግት እያስተናገደ ይገኛል። ከባቢ አየርን የሚበክሉ ጋዞችን የመቀነስ፤ እንዲሁም በዚህ ምክንያት የመጡ የአየር ንብረት ለዉጥን መዘዞችን የመከላከል እና ከለዉጡም ጋር ተላምዶ የመኖር ስልቶችን እያፈለቁ እና እየመዘኑ መሟገቱ በመቀጠሉም ለመጪዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ፖላንድ ለምታስተናግደዉ ተመሳሳይ ጉባኤ የታሰበዉ እልባት ላይ መድረስ የሚቻል አይመስልም የሚል ስጋት ከወዲሁ እየተሰማ ነዉ።

የሚታየዉ ሁሉ የተለመደ እና ከበፊቱ የተለየ አይደለም ከሚሉት አንዷ የፆታ እና የአየር ንብረት ለዉጥ ተፅዕኖ ቅነሳ የተሰኘ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅትን በመወከል በዓለም የአየር ንብረት ጉዳይ ላይ በሚመክረዉ 23ኛዉ ዓመት ጉባኤ ተሳታፊ ናይጀሪያዊቱ ኤልዛቤት ቼዮ ናቸዉ። «ገና ዛሬ መምጣቴ ነዉ፤ ገና ከመምጣቴም ከሌሎች ወገኖቼ የተረዳሁት አፍሪቃዉያን ብዙም እንዳልተደሰቱ እና ቅር እንዳላቸዉ ነዉ፤ ምክንያቱም ዛሬም እንዲሁ ነገሮ በተለመደዉ መልኩ የሚሄድ መስሏል። ረዥም ጊዜ ተጎዞ ይህ 23ኛዉ ጉባኤ እንደመሆኑ ለምን ያደጉት ሃገራት በፓሪሱ ስምምነት መሠረት መራመድ እንዳልቻሉ ግልፅ አይደለም። ይህ ትልቅ ስጋት ነዉ። ምክንያቱም የአፍሪቃ ሃገራት እያንዳንዱ ሀገር ሊቀንስ የወሰነዉን የብክለት መጠንን በሚመለከት ቁርጠኞች ናቸዉ። ከዚያስ ምን ይሆናል?»

ከሳምንት በላይ በአየር ንብረት ድርድሩን እና ዉይይቱ በመሳተፍ ላይ ከሚገኙት የኢትዮጵያ ልዑካን መካከል አቶ ቢኒያም ያዕቆብ በኢትዮጵያ የአካባቢ ደን እና የአየር ንብረት ለዉጥ ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለዉጥ ተደራዳሪ እንዲሁም የሕግ ባለሙያ ናቸዉ። ረዥም ዓመታትን የፈጀዉ የአየር ንብረት ለዉጥ ድርድር ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን የሚዳስስ መሆኑን በማስታወስ በተለይ የአፍሪቃ ሃገራት ከድርድሩ ዉጤት ይፈልጓቸዋል ያሏቸዉን አበይት ጉዳዮች ጠቁመዋል።

በተለያዩ ጊዜያት በአየር ንብረት ለዉጥ ጉዳይ ድርድሮች የሚሳተፉት በኢትዮጵያ የአካባቢ ደን እና የአየር ንብረት ለዉጥ ሚኒስቴር የአየር ንብረት ለዉጥ ትግበራ ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ደባሱ ባይለየኝ በበኩላቸዉ ከእስካሁኑ ሂደት ረቂቅ መግባቢያ ሰነዶች ወደማዘጋጀቱ እየተመጣ መሆኑን ጠቁመዋል። በተለይ እሳቸዉ ከሚከታተሉት የካርቦን ገበያ ስልትን አስመልክቶ የሚካሄደዉ ድርድር መመሪያዎች እና ሕጎች ምን መምሰል አለበት ከሚለዉ ደረጃ ላይ እየተደረሰ መሆኑንም ገልጸዋል።

በምሳሌነትም በተለይ ብክለቱን ለመቀነስ የሚወሰዱ ርምጃዎችን የሚመለከተዉ ሰነድ ብቻዉን ወደ አንድ መቶ ሰባ ገጽ ገደማ እየደረሰ መሆኑንም አንስተዋል።  ለዚህም ዋናዉ ምክንያት ሃገራት የተለያዩ ሃሳቦችን ማቅረብ እንጂ በሃሳቦቹ ላይ ተነጋግሮ ሰነዱን ለመቀነስ የሚደረገዉ ጥረት ያን ያህል እንዳልሆነም ታዝበዋል። ከዚህ በመሳትም በሚ,ፈለገዉ ደረጃ እየተኬደ ነዉ ብሎ ለመናገር እንደማይቻልም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ናይጀሪያዊቱ ኤልዛቤት ቼዮም እንዲሁ አሁን ላለንበት ችግር ለዳረገን ከፍተኛ ብክለት ታሪካዊ ተጠያቂነት ያላቸዉ ሃገራት በቀዳሚነት ተገቢዉን ርምጃ መዉሰድ ሲኖርባቸዉ ይህን እያደረጉ አይደለም በማለት ይተቻሉ።

«አፍሪቃዉያንን ስንመለከት በተፈጥሮ ሃብት ላይ የተመረኮዘ ኑሮ ነዉ ያላቸዉ። እነሱ እዚህ ላይ ብቻ ቢያተኩሩ ምን ይገኛል? ታዳሽ የኃይል ምንጭ እየተባለ ነዉ መልካም ይሁን፤ የተፈጥሮ አካባቢያችንን ይጠብቅልናል። ግን ደግሞ ልማትን በተመለከተ እነዚህ ሃገሮች እንዴት ሊሆኑ ነዉ? ምንክንያቱም አሁንም ለልማት እንቅስቃሴያቸዉም አብዛኞቹ በተፈጥሮ ሃብት ላይ የተመረኮዙ ናቸዉ። እናም ይህ ነዉ የአብዛኛዎቹ የአፍሪቃ ሃገራት ስጋት።»

ከዚህ በመነሳትም ከጉባኤዉ የአፍሪቃ ሃገራት የሚፈልጉትን ያህል ዉጤት ያገኛሉ የሚል ተስፋ እንደሌለም አፅንኦት ይሰጣሉ። አቶ ደባሱ ግን ከዚህ ጉባኤ ዉጤት እንደማይጠበቅ ነዉ የሚያመለክቱት።

ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነዉ ናይጀሪያዊ በግብርና እንደሚተዳደር የሚናገሩት ኤልዛቤት ቼዮ፤ በተፈጥሮ ሃብት ላይ የተመረኮዘዉ የኑሮ ሁኔታዉ በአየር ንብረት ለዉጥ መዘዝ ችግር እየገጠመዉ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ችግር ደግሞ በእሳቸዉ ሀገር ብቻ ሳይሆን ራሷን ከፓሪሱ የአየር ንብረት ስምምነት ባገለለችዉ ዩናይትድ ስቴትስም በየመልኩ እየታየ እንደሆነ እና ማንም ቢሆን ከአየር ንብረት ለዉጥ መዘዝ ማምለጥ እንደማይችልም ያሳስባሉ። የሚባለዉ ሁሉ እዉነት መሆኑ እየታየ ግን በኢንዱስትሪ ያደጉት ሃገራት እንደአፍሪቃ ያሉ አኅጉራት ራሳቸዉን ከለዉጡ ጋር አላምደዉ መኖር የሚችሉበትን ስልት እንዲቀይሱ የሚረዱ ድጋፎች በፍጥነት የሚቀርቡበትን መንገድ እያመቻቹ አይደለም በማለት ይወቅሳሉ። አቶ ቢንያምም ይህን ሃሳብ ይጋሯቸዋል።

ጉባኤዉ በዚህ ሳምንትም ይቀጥላል። በነገዉ ዕለትም በሚኒስትሮች ደረጃ ድርድሩ ጀምሮ እስከ ዓርብ ዕለት ይቀጥላል። በሚኒስትሮች ደረጃ የሚካሄደዉን ድርድር ለመክፈትም የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እና ፕሬዝደንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር፤ የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ማኑዌል ማክሮ፤ የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬሽ እና ጉባኤዉን በፕሬዝደንትነት የምታስተናብረዉ ፊጂ ፕሬዝደንት ፍራንክ ባይኒ ማራማ ንግግር ያደርጋሉ። ጉባኤዉ ሲጠናቀቅም ሳይንቲስቶች፣ የዘርፉ ምሁራን እና የየሃገራቱ ተወካዮች ተደራድረዉ ከስምምነት የሚደርሱበት የፓሪሱን ስምምነት በተግባር የማዋያ ዝርዝር ሰነድ ሊወጣ እንደሚችል ይጠበቃል።

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

 

Audios and videos on the topic