የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 18.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ

የዓለም መሪዎች በሚቀጥለ ወር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ምክረ -ኃሳብ ላይ ለመምከር እየተዘገጃጁ ነው። የአየር ንብረት ለውጥ የከፋ ከመሆኑ በፊት ከስምምነት ላይ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይሁንና ኢትዮጵያን ጨምሮ በደቡብ አፍሪቃ፤ሶማሊያና ኬንያን የመሳሰሉ የዓለም ክፍሎች የአየር ንብረት ለውጡ ተጽዕኖ እያሳደረ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:21
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
11:21 ደቂቃ

የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ

በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ 15 ሚሊዮን ዜጎችን ለረሐብ ማጋለጡን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል። የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ያወጣው ዘገባ ኤል-ኒኖ በተሰኘው የአየር መዛባት የተከሰተውን የኢትዮጵያ ድርቅ «አስከፊ» ሲለው «በአርብቶ አደር አካባቢዎች ከሚከሰተው የቀንድ ከብቶች ሞት በተጨማሪ በቅርቡ የተከሰተውን የምግብ እጥረት ቀውስ ያባብሰዋል።» ብሏል። የኢትዮጵያ መንግስት የተከሰተው ድርቅም ይሁን በዜጎች ላይ ያጠላው የረሐብ አደጋ ከቁጥጥሬ ውጭ አይደለም ቢልም ከፍተኛ መጠን ያለው የምግብ እህል ከውጭ አገራት «ገዝቼ እያጓዝኩ ነው» እያለ ነው። ኤል-ኒኖ የተሰኘውን የአየር ንብረት ለውጥ ተከትሎ የመጣው አደጋ ግን ለኢትዮጵያም ሌላ ስጋት ደቅኗል። የዓለም ጤና ድርጅት ኅዳር 7 ቀን 2008 ዓ.ም. ይፋ ያደረገው ‘የአየር ንብረትና ጤና’ የተሰኘ ዘገባየዓየር ንብረት ለውጡ የከፋ የጤና ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ሲል አስጠንቅቋል። «የከባቢ አየር ሙቀት መጨመር፤ከፍተኛ የሙቀት ወላፈን፤ዝናብ፤ጎርፍ፤የመሬት መንሸራተት» ሊከሰቱ ይችላሉ ያለው ዘገባው ካሁን ቀደም የነበሩ ተላላፊ በሽታዎችን የበለጠ አስቸጋሪ ሊያደርጓቸው ይችላሉ ብሏል። ዘገባው በጎርጎሮሳዊው 2030 ዓ.ም. 250,000 ኢትዮጵያውያን የጎርፍ መጥለቅለቅ ያሰጋቸው ሲልም አሳስቧል።

እንደ ዓለም አቀፉ የአየር ትንበያ ድርጅት(WMO) መረጃ ከሆነ የኤል-ኒኖ ክስተት ያልተጠበቁ ተጽዕኖዎች መፍጠሩን እስከ ጥር ወር ድረስ ይቀጥላል። የአየር ንብረት ለውጡ የሚያምሰው ኢትዮጵያን ብቻ አይደለም።

የአስር አመቱ ጆን ሌቺፓን 45 ዲግሪ ሴልሽየስ በሚደርሰው የቱርካና ሙቀት ያልተለመደ ቁርስ እየተጠባበቀ ነው። ከአጠገቡ የቤተሰቦቹ ፍየሎችና በጎች ከምህረት የለሹ ሙቀት መሸሸጊያ ፍለጋ ይራኮታሉ። የጆን ዋና ምግብ የፍየል ወተት ነው። አባቱ ሌሾርናይ ሌቺፓን በአስከፊው የአየር ጠባይ ምክንያት የቤተሰቡ አኗኗር እንደተቀየረ ይናገራል። በምግብና የመጠጥ ውሃ እጥረት ምክንያት የለት ተለት ህይወት ለቤተሰቡ ትግል ሆኗል።

በሰሜና ምዕራብ ኬንያ የሚኖሩት የቱርካና ሰዎች ከብት አርቢዎች ናቸው። ኑሯቿው ለቀንድ ከብቶቻቸው ውሃና የግጦሽ ሳር ፍለጋ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ እየተዘዋወሩ ነው። ይሁንና የሰሜናዊ ኬንያ የአየር ጠባይ የቀደመ ህይወታቸውን አመሳቅሎታል። ደረቅ ወቅቶች እየረዘሙ የዝናብ ሁኔታውም እየተቀያየረ ቸግሯቸዋል። የመጠጥ ውሃ እጥረቱ ተባብሷል። የአስር አመቱ ጆን ተንበርክኮ ከአንዷ ፍየል ጡቶች ወተት መጥባት ጀመረ።

«በአካባቢው በተከሰተው የውሃ እጥረት ምክንያት አብዛኞቹ እንስሶቻችን ሞተውብናል። አሁን አንዷን ፍየሌን ለአስር ዓመቱ ልጄ ለመስጠት ተገድጃለሁ። አዲስ ከተወለዱት ግልገሎች ጋር እየተጋፋ ወተት ይጠባል። መጀመሪያ ግልገሎቹ ከጠቡ በኋላ ከዛ ልጄ ይጠባል። በዚህ አይነት እስከ ማታ ድረስ ከብቶቹን ለመጠበቅ ጉልበት ይኖረዋል።» ይላል የጆን አባት ሌሾርናይ ሌቺፓን

በአስቸጋሪው ሙቀት ውስጥ የ48 አመቱ ኪገን በሞቱ የቀንድ ከብቶች መካከል ሆኖ የራሱን ይቆጥራል። ባራጎይ ከተባለው አካባቢ ወደ ኪሪሲያ የተጓዘው ጥቂት ዝናብ መዝነቡን ሰምቶ ነበር።

«የአየር ጠባዩ ሲቀየር እየተመለከትን ነው። ዝናብ ጠፍቶ ፀሐዩ በመበርታቱ ምክንያት በቂ ምግብ የለንም። የአየር ሁኔታው መቀየር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከእርሻ ማሳዬ ምንም ማግኘት አልቻልኩም»

በሞቃታማው በደቡብ አፍሪቃው ፎርዌይስ የገበሬዎች የገበያ ማዕከልም ቀኑ ሞቃታማና ጸሃያማ ነው። እዚህ ጥቁር- ነጭ፤ሽማግሌና ወጣት-ሁሉም ተሰብስቧል። አንዳንዶቹ ከዛፍ ጥላ ስር ተጠልለዋል። ከአግባቡ ታጭዶ ከታሰረ ሳር አሊያም ከዛፍ ጉቶ ላይም የተቀመጡ አሉ። እንደ ክሊንት ሐልኬት ሲዴል አይነቶቹ ገበሬዎች ለሃብታም የከተማ ሸማቾች ምርቶቻቸውን ለመሸጥ የመጡ ናቸው። ለክሊንት ሞቃታማና ደረቁ የደቡብ አፍሪቃ የአየር ጠባይ በደቡብ አፍሪቃ በጋ የተለመደ አይደለም።

«ከዚህ በፊት በዚህ የዓመቱ ወቅት ሁል ጊዜ ጠዋት ይዘንብ ነበር። ለግማሽ ሰዓት የሚዘንበው ጥሩ ዝናብ 10 ሚሊ ሜትር አካባቢ ይደርስ ነበር።»

እንደ ደቡብ አፍሪቃ የአየር ትንበያ ድርጅት በጁሐንስበርግ ከተማ በወርሃ ጥቅምት የሚዘንበው ዝናብ በአማካኝ 78 ሚሊ ሜትር መሆን ነበረበት። ይሁንና ባለፈው ወር የጣለው 17 ሚሊ ሜትር ዝናብ እነ ክሊንት ሐልኬት ሲዴል የሚፈልጉትን ያክል አይደለም። ነገር ግን ክሊንት ሐልኬት ሲዴል የራሱ የውሃ ጉድጓድ ስላለው የእርሻ ማሳውን ማጠጣት በመቻሉ እድለኛ እንደሆነ ይናገራል።

«ይሁንና ብዙ ጉልበት የሚፈልግ ስራ ስላለብን በምርቶቻችን ዋጋ ላይ ጭማሪ ያመጣል። ምክንያቱም በዝናብ ላይ መተማመን ስለማንችል የእርሻ ማሳውን በየቀኑ የሚያጠጡ ሰራተኞች መቅጠር ይኖርብናል።»

የአየር ንብረት ለውጥ በይነመንግስታት (The IPCC) በአብዛኛው የደቡብ አፍሪቃ ክፍል በዚህ ወቅት መጣል የነበረበት የበጋ ዝናብ ወደፊትም እንደሚዘገይ አስታውቋል። የዓለም ሙቀት በ3 ዲግሪ ሴልሽየስ ይጨምራል ተብሎ በሚጠበቅበት በአሁኑ ወቅት ሳይንቲስቶች ደቡብ አፍሪቃ የበለጠ ሞቃታማና ደረቅ ትሆናለች እያሉ ነው።

የአየር ንብረት ለውጥ ከሚያስከትለው አሰቃቂ ውድመት ለመዳን በምዕተ ዓመቱ መገባደጃ የዓለም ሙቀት ከ2 ዲግሪ ሴልሽየስ በላይ መጨመር እንደማይኖርበት ሳይንቲስቶች ይጠቁማሉ። እስካሁን ወደ 35 የሚደርሱ አገሮች ወደ ከባቢ አየር የሚለቁትን የበካይ ጋዝ መጠን ለመቀነስ ቃል ገብተዋል። ይህ ግን በቂ አይደለም። የበካይ ጋዝ ወደ ከባቢ አየር ከሚለቁት መካከል ቀዳሚ የሆኑት ቻይና፤አውሮጳና አሜሪካ ለመቀነስ ቃል የገቡትም የሚጠበቅባቸውን ያክል አለመሆኑን በግራንትሐም የአየር ንብረት ለውጥና ከባቢ አየር ጥናት ማዕከል ቃል-አቀባዩ ቦብ ውድ ይናገራሉ።

የአየር ንብረት ለውጥ በይነመንግስታት የበካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስ በቂ አለመሆኑን አስጠንቅቋል። የልቀት መጠኑን መቀነስ ከተቻለ በኋላ ካርቦንዳይ ኦክሳይድን ከከባቢ አየር ማጥፋት ሁለተኛውና ሁነኛው መላ ነው ተብሏል።

ወደ ከባቢ አየር የሚለቀቀው የበካይ ጋዝ አስጊ የሆነው በብዛቱ በቻ ሳይሆን በአይነቱም ጭምር ነው። ከበካይ ጋዙ ቀዳሚው ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ሲሆን የ65 በመቶ ድርሻ አለው። ሚቴን 16 በመቶ፤ኒትረስ ኦክሳይድ ደግሞ 6 በመቶ ድርሻ አላቸው። የካርቦን ዳይ ኦክዳይድ ልቀት መቀነስና ከከባቢ አየር የማጥፋቱ ሂደት በጎርጎሮሳዊው 2055-2070 ባሉት አመታት ተመጣጣኝ ሊሆን እንደሚገባ የአየር ንብረት ለውጥ በይነመንግስታት ጠቁሟል። ሳይንቲስቶችም የሚቴንና ኒትረስ በካይ ጋዞች ልቀትና ከከባቢ አየር የማስወገድ ሂደት ከ2080 እስከ 2100 ባሉት አመታት ተመጣጣኝ ሊሆን ይገባል የሚል ስሌት አቅርበዋል።

«ሰዎች በ2020 ሊያደርጉት ይችላሉ ተብሎ የሚጠበቀውን መሰረት በማድረግ ስንመለከት በምዕተ-ዓመቱ ማብቂያ የምድር የሙቀት መጠን በ3 ዲግሪ ሴልሽየስ ወይም ከዛ በላይ ይጨምራል። ይህ በሚሊዮን አመታት ለመጀመሪያ ጊዜ ይሆናል። በምድር ለ 250,000 አመታት የኖረው የሰው ልጅ አይቶት የሚያውቀውም ባለመሆኑ ለመኖር አስቸጋሪ ይሆናል። የግሪን ላንድና ምዕራብ አንታርክቲካ የበረዶ ግግር ይቀልጣሉ። ሁለቱ በአንድ ላይ የባህር ጠለል በ13 ሜትር እንዲጨምር የሚያደር የውሃ መጠን ይዘዋል። »

ከሁለት ሳምንታት በኋላ በፓሪስ የሚጀመረውና ለአስራ ሁለት ቀናት የሚዘልቀው የተ.መ.ድ. የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የዓለምንሁሉ ቀልብ ይስባል። በጉባኤው የበካይ ጋዝ ወደ ከባቢ አየር በመልቀቅ ቀዳሚ ይሆኑትም ሆነ ኢምንት ድርሻ የሌላቸው የአፍሪቃ አገራት ይታደማሉ። ባይረጋገጥም በፓሪስ ከዓለም አቀፍ የአየር ለውጥ ስምምነት ላይ ለመድረስ እቅድ ተይዟል። የደቡብ አፍሪቃው ገበሬ ሐልኬት ሲዴል ተደራዳሪዎቹ ቢሰሙ የሚወደው ጠንካራ መልዕክት አለው።

«በተቻለ መጠን በታዳሽ ሃይል ላይ ትኩረት ልናደርግ በስብሰባዎች የምንገባውንም ቃል ልንጠብቅ ይገባል። ደቡብ አፍሪቃና አፍሪቃ በሙሉ የገጠር ገበሬዎች፤ከአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ጫና መቋቋም የሚያስችል ቁሳቁስና ገንዘብ የሌላቸውን በማገዝ ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርብናል።»

በፓሪስ ምንም ይፈጠር ምን ኢትዮጵያ፤ኬንያና ደቡብ አፍሪቃን በመሰሉ አገሮች ላይ ተጽዕኖ ያሳደረውን የአየር ንብረት ለውጥ ማስቆም የሚችል አይሆንም። ነገር ግን ገበሬዎችና ሸማቾች በትክክለኛው ጎዳና ለሚደረግ ጉዞ የመጀመሪያ እርምጃ ሊሆን ይችላል ብለው ተስፋ አሳድረዋል።ቦብ ውድ ግን በፖለቲከኞች የሚመራው የፓሪስ ድርድር ተሳታፊዎች አርቀው እንዲያስቡ ይመክራሉ።

«ዋናው ምክራችን መሪዎች የበካይ ጋዝ ልቀታቸውን ቃል ከገቡት በላይ የሚያሳኩበትን መንገድ በእርጋታ ከፓሪስም ባሻገር እንዲያስቡበት ነው። የበካይ ጋዝ ልቀቱን ለመቀነስ የሚያስችሏቸውን መላዎች መዘየድ ይገባቸዋል። ተግባራዊ የማያደርጉትን ቃል እንዲገቡ አያስፈልግም።»

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በጎርጎሮሳዊው 1992 ዓ.ም ባደረገው የሪዮ ዲጄኔሮ ጉባዔ ነበር የአየር ንብረት ለውጥ ማዕቀፍ ያጸደቀው። ስምምነቱ የዓለም አገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመግታት ሃላፊነት እንዳለባቸው ቢያስገድድም አንዳች የድርጊት መርሃ-ግብር አልነበረውም። በጎርጎሮሳዊው 1997 የተደረሰው የኪዮቶ ስምምነት በአንጻሩ የበካይ ጋዝ ልቀትን በ5 በመቶ ለመቀነስ እቅድ የተቀመጠበት ነበር። ለእያንዳንዱ የበለጸገ አገር የሚቀንሱትን የበካይ ጋዝ መጠን በኮታ ያከፋፈለው ስምምነት ግን በወቅቱ «በማደግ ላይ ያሉ» ተብለው የሚታወቁትን እንደ ቻይና፤ ደቡብ ኮሪያና ሜክሲኮ ያሉ አገሮች አላካተተም። ስምምነቱም ከድርድርና ውይይት የተለየ ነገር ጠብ አላደረገም።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic