የአየር ንብረት ለውጥ የዓለማችን ፀጥታ ስጋት | ጤና እና አካባቢ | DW | 09.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

የአየር ንብረት ለውጥ የዓለማችን ፀጥታ ስጋት

ዓለማችንን የሚያሳስቧት የተፈጥሮ ሀብት መመናመን፣ የከፋ ድህነት፣ ረሀብ ወይም አሸባሪነት አለያም የጽንፈኛ አመለካከቶችን የመሳሰሉ አስጊ ሁኔታዎች በአሁኑ ጊዜ በአየር ንብረት ለውጥ ተባብሰዋል.

ናይጀሪያ ውስጥ ባለፉት 15 ዓመታት በግጦሽ መሬት ሰበብ በሚነሱ ግጭቶች ሰበብ ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወት አልፏል። የሞቱት ቁጥር በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የሽብር ጥቃቶችን የሚጥለው ቦኮ ሀራም የተባለው ቡድን ከገደላቸው በአራት እጥፍ ይበልጣል። መንስኤዎቹም የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተላቸው አስገዳጅ ሁኔታዎች ምክንያት ቀድሞ አርብቶ አደሮች ከብቶቻቸውን ለግጦሽ ያሰማሩበት የነበረውን መሬት ገበሬዎች ማረሳቸው ነው። ማትያስ ፎን ሀይን ያዘጋጀውን ኂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች።
የስቶክሆልሙ ዓለም አቀፍ የሰላም ጥናት እና ምርምር ተቋም በምህፃሩ ሲፕሪ የዘንድሮው ዓመታዊ ዘገባ ካተኮረባቸው ጉዳዮች ውስጥ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትላቸው ችግሮች የግጭት መንስኤu መሆናቸው ነው። የተቋም ሃላፊ ዳን ስሚዝ የአየር ንብረት ለውጥ እና ፀጥታ የተያያዙ ጉዳዮች መሆናቸውን ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል ።
«የአየር ንብረት ለውጥ ከማህበራዊ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ሁነቶች ጋር ተዳምሮ ግጭቶችን ለሚያባብሱ ሁኔታዎች አስተዋጽኦ ያደርጋል።»

በጎርጎሮሳዊው 2012 በዩናይትድ ስቴትስ የስለላ መሥሪያ ቤት ስር ያሉ አንዳንድ ድርጅቶች « ለዩናይትድ ስቴትስ ሥልታዊ ጠቀሜታ ያላቸው በርካታ ሀገራት በ10 ዓመታት ውስጥ በውሐ እጥረት እና በጎርፍ አደጋ እንደሚጠቁ የተነበየ ዘገባ አዘጋጅተው ነበር።ይህም የአለመረጋጋት ስጋትን እንደሚያባባስ ፤ሀገራትንም እንደ ሀገር መቀጠል ወደ ማይችሉበት ደረጃ ሊወስዳቸው እንደሚችል  እና ለአካባቢያዊ ግጭቶች አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ በዘገባው ተጠቅሷል። ይሁን እና የአየር ንብረት ለውጥ እና ደም አፋሳሽ ግጭቶች በቀጥታ ይገናኛሉ ብሎ መደምደም አስቸጋሪ ይሆናል የሚሉ ወገኖችም አሉ። በነርሱ አስተያየት ከዚያ ይልቅ ምናልባትም የአየር ንብረት ለውጥ ስጋቱን የሚያጎላ ሊባል የሚችል ነው። ይህን ከሚሉት አንዱ ዎርልድ ፍዩቸር ካውንስል የተባለው ድርጅት ባልደረባ ሮብ ቫን ሬት ናቸው። የአየር ንብረት ለውጥ ይበልጡን ስጋቱን የሚያባባስ ሆኖ ነው የሚታየው። ዓለማችንን የሚያሳስቧት የተፈጥሮ ሀብት መመናመን፣ የከፋ ድህነት፣ ረሀብ ወይም አሸባሪነት አለያም የጽንፈኛ አመለካከቶችን የመሳሰሉ አስጊ ሁኔታዎች  በአሁኑ ጊዜ በአየር ንብረት ለውጥ ተባብሰዋል። 
ዳን ስሚዝ በበኩላቸው ከድርቅ እስከ ጎርፍ ድረስ ያሉት የተፈጥሮ አደጋዎች የሚያደርሱት ተጽእኖ በደረሱበት አካባቢ ብቻ የሚወሰን አይሆንም ይላሉ። እጅግ የከፋ የአየር ንብረት ሁኔታ በዓለማችን የምግብ ዋጋ ላይ ተጽእኖ ያሳድራል። የዋጋ ንረት ደግሞ ግጭቶችን ወደ ከፋ ደረጃ ያሸጋግራል።
«በዓለማችን የምግብ ዋጋ ወደ ላይ ሲወጣ ሰልፎች ይካሄዳሉ። ብዙውን ጊዜ አመጾችም ይነሳሉ። 30 ወይም 40 በሚሆኑ ሀገራት  በተመሳሳይ ጊዜ  ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ አለመረጋጋቱ

Kenia Nationalpark Dürre (AP)

ይቀጥላል።» ስሚዝ እንደጠቆሙት የግጭቶች እና የአየር ንብረት ለውጥ ትስስር በሰሜን አፍሪቃ እና በመካከለኛው ምሥራቅ በግልጽ ይታያል። በጎርጎሮሳዊው 2ሺህ አጋማሽ በሶሪያ በደረሰው አስከፊ ድርቅ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ገበሪዎች በህዝብ ወደ ተጨናነቁ ከተሞች ለመሰደድ መገደዳቸውን ቫን ሬት ያስታውሳሉ።
«በርግጥም የውሐ እጥረት ደርሶ ነበር።ምግብም ተወዶ ነበር። እነዚህ ስቃዮች እና ማህበራዊ ቀውሶች ከቁጥጥር ውጭ ሆነው ዛሬ ወደ ምናየው ግጭት ተቀይረዋል።»
በርሳቸው አባባል ፓኪስታንን በመሳሰሉ ኒዩክልየር የታጠቁ ሀገራትም የአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂ ናቸው። ፓኪስታን በየጊዜው የጎርፍ አደጋ ይደርስባታል። በሀገሪቱ ጎርፍ ከሚያደርሰው አደጋ እና የሰዎች መፈናቀል ሌላ በኒዩክልየር ደህንነት ላይም ቀጥተኛ ተጽእኖ እንደሚኖረው ቫን ሪት ተናግረዋል። የአየር ንብረት ለውጥ በበርካታ አካባቢዎች የግብርና ምርት እንዲቀንስ አድርጓል። እናም ምን ሊደረግ ይችላል ተብለው የተጠየቁት የሲፕሪ ሃላፊ ስሚዝ በርሳቸው አስተሳሰብ በተመድ ስር ይህን ጉዳይ የሚከታተል ተቋም መመሥረት አስፈላጊ ነው። የጸጥታ ስጋቶችን ማጥናት ዋናው ተግባሩ የሚሆነው ይህ ተቋም የጥናቱን ውጤት ለተመ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት እና የሰብዓዊ እርዳታዎች አስተባባሪ ወይም ለዓለም የምግብ ድርጅት ያስተላልፋል። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ እነዚህ ድርጅቶች በሚቀጥሉት ዓመታት ከአየር ንብረት ጋር በተገናኙ የፀጥታ ስጋቶች ተጽእኖ ስር መውደቃቸው እንደማይቀርም ስሚዝ ገልጸዋል። 

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ