የአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂዎች በአፍሪቃ | አፍሪቃ | DW | 24.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂዎች በአፍሪቃ

የአውሮፓ ፖለቲከኞች ወደ ሀገራቸው የሚመጡትን በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ተገን ጠያቂዎች የጦርነት እና የኤኮኖሚ ስደተኞች እያሉ ሲከፋፍሉ ይሰማል። በአሁኑ ወቅት ብዙ ሰዎች ከአፍሪቃ ድርቅ እና ረሃብን እየሸሹ ወደ ጎረቤት ሃገራት ይሰደዳሉ። ያካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ድርጅቶች እነዚህን ሰዎች የአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂዎች ስደተኞች ሲሉ ይጠሯቸዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:50
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:50 ደቂቃ

የአየር ንብረት ለውጥ

ሰሜን ኬንያ ውስጥ የሚገኘው የካኩማ የስደተኞች ጣቢያ ለአዲስ መጤዎች እየተስፋፋ እና እየተገነባ ይገኛል። ለዚህም ሲባል በቦታው የሚገኝ አንድ የህፃናት መጫወቻ ስፍራ አሁን ለስደተኞች ማረፊያ ቦታ እንዲሆን አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል። አፖሎኒአ ኦሚኖንግ የደቡብ ሱዳን የሎቱኮ ህዝብ ስደተኛ ናቸው። ወይዘርዋ በሃገራቸው በቆሎ እና ማሽላ ያመርቱበት የነበረው እርሻ በመድረቁ ምክንያት ወደ ኬንያ እንደተሰደዱ ይናገራሉ። የአምስት ልጆች እናት የሆኑት ወይአሚኖንግ እንደ አብዛኛው የደቡብ ሱዳን የሎቱኮ ህዝብ እርሻ እና ከብት እርባታ ላይ ጥገኛ ነበሩ፤« ተክዬ ነበር ነገር ግን ምንም ዝናብ አልጣለም። ሁሉም ነገር ደርቋል። በዛ ላይ ባለቤቴ በሞት ተለየኝ። የሚረዳኝ ማንም ሰው አልነበረም። ያኔ ልጆቼ የሚበሉት አግኝተው በጤና እንዲያድጉ ብዬ ከነርሱ ጋር ወደዚህ መጣሁ።»
ቀደም ሲል ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ይጥል ስለነበር ገበሬዋ በቆሎ ፣ማሽላ እና ቦሎቄ የሚዘሩበትን ቀን በትክክል ያውቁ እንደነበር ይናገራሉ። አሁን ግን ዝናብ ወይ ዘግይቶ ይመጣል አልያም መጠኑ ከፍተኛ ነው፣ ይላሉ ስደተኛዋ።


የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ባልደረባ ዱኬ ምዋንቻ እንደሚያስረዱት፣ «በ 1951 ዓ ም የፀደቀው የስደተኞች ውል በአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ ምክንያት ከቀያቸው የሚፈናቀሉ ሰዎች ስደተኞች አይደሉም» ሲል አስቀምጧል ። ምንም እንኳን በዚህ መሠረት ስደተኛ ባይባሉ እና የጥገኝነት መብት ባይኖራቸውም ድጋፍ አልነሳናቸውም ይላሉ ምዋንቻ« እነዚህን ሰዎች ወደ መጡበት አንመልሳቸውም። አብዛኛውን ጊዜ የሚመጡት ስደተኞች በርካታ ችግሮች ኖሯቸው ነው። ርሃብ እና ድርቅ ራሱ ብዙውን ጊዜ የግጭት መነሻ ነው።»
በርካታ ስደተኞች የተጠለሉበት የካኩማ ጣቢያ ራሱ ደረቃማ እና አቧራ የሞላበት በርሃማ ስፍራ ነው። በዚሁ ለ125,000 ሰዎች በተሰራው መጠለያ ጣቢያ ውስጥ 185,000 ይኖራሉ። አብዛኞቹም የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ሲሆኑ ለምን ተሰደዳችሁ ለሚለው ጥያቄ ለምሳሌ የጆሴፊን ጃሬማኖ ፈጣን መልስ፤ ርሃብ የሚል ነው። ቆየት ብለውም ወይዘርዋ አክለው ያብራራሉ፤« በመንደራችን በተደጋጋሚ ውጊያ ተካሂዶ ነበር። የተወሰኑ ሰዎች ተገደሉ። እና ትንሽ እስኪረጋጋ ድረስ ጫካ ውስጥ አምልጠን ተሸሸግን፤ ከዛ ነው ተመልሰን የመጣነው።»


የጆሴፊን ጃሬማኖም ባለቤት በደቡብ ሱዳኑ የእርስ በርስ ጦርነት ተገድለዋል። ወይዘርዋ እርሻቸውን የሚንከባከብ ሰው ማጣታቸው ብቻ ሳይሆን የዚህ ዓመቱ ድርቅ ከአራት ልጆቻቸው ጋር ድንበር ተሻግረው ወደ ካኩማ እንዲሰደዱ ዳርጓቸዋል። የተባበሩት መንግሥታት የተፈጥሮ አካባቢ ጥበቃ ድርጅት ኃላፊ አሂም ሽታይነር የስደተኛው ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ ከፍ እያለ መምጣቱን ተናግረዋል።« የአየር ንብረት ለውጡ እንደሚያመላክተው እና የዓለም የአየር ንብረት ምክር ቤት አስቀድሞ እንደጠቆመው፤ የደረስንበት ድምዳሜ ወደፊት በአየር ንብረት ለውጥ መዘዝ የሚሰደደውቁጥር በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር ነው። ዓለማችን ደግሞ ለዚህ ዝግጁ አይደለችም።»
ከለጋሾች በቂ ገንዘብ ስለማይገኝበካኩማ እና በሌላኛው የኬንያ ትልቁ የዳዳብ ስደተኞች ጣቢያ ለስደተኞች በሚሰጠው ምግብ ላይ ቅነሳ ተደርጓል። የUNHCR ባልደረባ ዱኬ ምዋንቻ በሚመጡት አመታት ሁኔታው ይበልጥ እንዳይባባስ ስጋት አላቸው።« የአየር ንብረት ለውጡ ትልቅ ፈተና ነው። በዚህ ምክንያት በርካታ ሰዎች ተፈናቅለዋል። በአዳጊው ዓለም ሀገራት ብቻ ሳይሆን በመላው የዓለማችን ክፍልም ብዙ ችግሮች ገና ሊፈጠሩ ይችላሉ።


ሊንዳ ሽታውደ / ልደት አበበ


አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic