የአየር ንብረት ለውጥ በጀርመን፣ | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 17.08.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

የአየር ንብረት ለውጥ በጀርመን፣

ከምድር ሰቅ በስተሰሜንና ደቡብ ፤ 23,5 ዲግሪ ድረስ ፣ «ትሮፒክ ኦፍ ካንሰር» ና «ትሮፒክ ኦፍ ካፕሪከርን» ድረስ በመሃል የሚገኘው የዓለም ክፍል አልፎ -አልፎ ከባህር ልክ 2,000 ሜትርና ከዚያ በላይ ከፍታ ካላቸው አካባቢዎች በስተቀር በአመዛኙ ሞቃት ነው፣

default

የአየር ንብረት ለውጥ በጀርመን፣ የአልፕስ ተራሮች፣

እምብዛም ተለዋዋጭ የአየር ንብረት ለውጥም አይታይበትም። በሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ከ 23,5 ዲግሪ ከፍ ብሎ የሚገኙት የየሜድትራንያን አካባቢ አገሮች፣ ከመሃልና ከሰሜን አውሮፓ ፍጹም የተለየ የአየር ንብረት እንዳላቸውም የታወቀ ነው። ክረምቱ ያን ያህል አያይልም ። የበጋ ወራቱ ግን ሞቃት ናቸው። ይሁንና ባለፉት ጥቂት ምዕተ ዓመታት ፤ የፕላኔታችን የአየር ሙቀት መጠን እየጨመረ ምምጣቱ፤ በራድ የሚባሉት የመሃል አውሮፓ አገሮችም ሙቀታቸው እየጨመረ መምጣቱ አልታበለም።

Ulf Buentgen የተባሉ የአስዊስ ጀርመናዊ የአየር ንብረት ተመራማሪ ፣ የአየር ንብረት በተለይ ከ 20ኛው ክፍለ ዘመን አንስቶ ይበልጥ እየሞቀ መምጣት የሜድትራንያን አዋሳኝ በሆኑ የኢጣልያና የፈረንሳይ አውራጃዎች የተለመዱ የከርሠ ምድር ፍሬዎች፤ 100 ኪሎሜትር ወደ ሰሜን በመዝለቅ በጀርመንና በምሥራቅ እስዊትስዘርላንድም በመብቀል መሆናቸውን ገልጸዋል። በተለይ እዚህ ላይ የተጠቀሰው በከርሠ ምድር ከሚገኙት ሥራሥሮች ወይም ድንች መሰል ፍሬዎች መካከል አንዱ እንደሚመስለኝ በአንዳንድ የኢትዮጵያ ክፍሎች የበሬ ገሃ (የበሬ ቂጣ፣ ርሚጦ) የሚሰኘው ጠፍጣፋ ድንች መሰል ፍሬ ነው። በብዙ የአውሮፓ ቋንቋዎች ተመሳሳይ ስም አለው ። እንግሊዝኛው ትራፍልስ ይለዋል። ጀርመኖች ትሩዑፈል ይሉታል። ጀርመንኛው ድንችን ካርቶፈል ነው የሚለው ። ይህም ቃል የተወሰደው፣ ታርቱፎ ከሚለው ከኢጣልያንኛው ነው። ድንችና የበሬ ገሃ፤ ከሞላ ጎደል በስምም በመልክም ተመሳሳይነት አላቸው። በጀርመን ሀገር ለመጀመሪያ ጊዜ በተለይ በደቡባዊው ጀርመን ትራፍልስ ተፈልጎ የተገኘው ትራፍልስ አሽትቶ መጠቆም በሚችል አንድ የሠለጠነ ውሻ ረዳትነት ነው። በዚህ ውሻ ረዳትነትም 2 ኪሎ የበሬ ገሃ ቆፍሮ በትኅተ ምድር ለማግኘት ተችሏል። በተደረገው ጥናት መሠረት እስካሁን በጀርመንና በምሥራቅ እስዊትስዘርላንድ ፤ በ 210 ጣቢያዎች ትራፍልስ እንደሚገኝ ታውቋል። ትራፍልስ ለቅንጦት ምግብ ማጣፈጫ የሚውል ሲሆን ፤ አንዱ ራስ ከአንድ ሺ ዩውሮ በላይ ሊሸጥ ይችላል። ባለፈው ኅዳር በማካዎ ካዚኖ አንድ ስታንሊ ሆ የተባሉ የናጠጡ ሃብታም ለ 2 ራስ ነጭ ትራፍልስ 330 ሺ ዩውሮ የከፈሉ ሲሆን ከዚያ 2 ዓመት ቀደም ሲል በተጠቀሰው ዋጋ 1,5 ኪሎ ግራም ትራፍልስ አግኝተው ነበር።

የእስዊሱ ሳይንቲስት ዑልፍ ቡዑንትገን እንደሚሉት፤ ትራፍልስ በጀርመን የተገኘበት ሁኔታ ለአየር ንብረት ለውጥ አንድ ዓይነት ምልክት ነው። ያም ሆኖ፤ ይህ እጅግ የከበረ ልዩ የምግብ ማጣፈጫ፤ ለመሃል አውሮፓ አገሮች በሳይንስና ኤኮኖሚ ሰፊ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ በሰፊው ጥናት ሊካሄድበት ይገባል ይላሉ። ትራፈልስ፤ ለኬክ ፓስታን ለመሳሰለው ብቻ ሳይሆን የሚውለው፤ የምግብ ዘይትና ቮድካም ይቀመምበታል።

የአየር ንብረት ለውጥን ካነሣን፤ ጀርመን ዘንድሮ የበጋ ወራት አየች ለማለት አያስደፍርም። የታዘቡ ኑዋሪዎች የሚሉትን ለጊዜው እንተወውና፤ የአየር ጠባይም ሆነ የአየር ንብረት ጠበብት የሚሉትን እናዳምጥ። «ኦፈንባህ » በተሰኘችው ፍራንክፈርት አካባቢ በምትገኘው ከተማ የሚገኘው የጠቅላላዋ ጀርመን የአየር ንብረት ነክ መ/ቤት ፣ መለስ ብለን ባለፈው ጸደይ በሚያዝያ ወር የሆነውን ላንዳፍታ እንስታውስ ይላል። በተጠቀሰው ከተማና የአየር ንብረት የምርምር ድርጅት፣ Gerhard Müller-Westermeier የተባሉት ተማራማሪ ፤ እንዲህ ይላሉ።

(1)«ሚያዝያ እጅግ ሞቃት ነበረ። ፀሐይ ታበራ ነበር፤ መሬቱም ደርቆ ነበረ። ባለፉት 5 ዓመታት በተለይ እ ጎ አ በ 2007 እና በ 2009 እንደታየው ማለት ነው። አማካዩ የጀርመን የሚያዝያ ወር የሙቀት መጠን 11,6 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሲሆን የዘንድሮው የ 4,2 ዲግሪ ብልጫ አሳይቷል። ስለሆነም የዘንድሮው ሚያዝያ (2011 ) እ ጎ አ ከ 1881 ዓ ም ወዲህ፣ ሁለተኛው እጅግ ሞቃት ሚያዝያ ለመባል በቅቷል። እ ጎ አ በ 2009 እና 2007 ካጋጠመው ብርቱ ሙቀት ቀጥሎ መሆኑ ነው»።

የአየር ጠባይ ዘገባዎች ወቅታዊውን የአየር ሁኔታና በቀጣይ ቀናት ጎልተው ሊታዩ የሚችሉትን ሲሆን የሚገልጹት ፤ የአየር ንብረት ይዞታ ተከታታዮች፣ በአንድ አካባቢ ለረጅም ጊዜ በሚፈራረቁ የአየር ጠባይ ይዞታዎች ላይ ነው የሚያተኩሩት። ብዙዎቹ፤ የአየር ጠባይ ተመራማሪዎች በሰፊው የአየር ንብረት ጉዳይ ተመራማሪዎችም ናቸው።

ስለሆነም ስለ አየር ንብረት ይዞታና በቀጣይነት ምን ሊመስል እንደሚችል ትንበያዎችን ለመግለጽ ይወዳሉ። የጀርመን የአየር ጠባይ ምርምር ድርጅት ፕሬዚዳንት ጌርሃርት አድሪያን---

4, « 2010 (እ ጎ አ )፤ ለአየር ንብረት ጥበቃ ጥሩ ዓመት አልነበረም። እ ጎ አ የመጀመሪያው 2011 አጋማሽም እንዲሁ! በ 2010 የዓለም ህዝብ ከሞላ ጎደል 31 ቢሊዮን ቶን CO2 ወደ ከባቢ አየር እንዲለቀቅ አድርጓል። መጠኑ አሳዛኝ ክብረ-ወሰን የያዘ ነው።»

የአየር ንብረት መለዋወጥ፣ በዓለም ዙሪያ ሲታይ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሙቀት መጨመርን እያስከተለ ነው። የውቅያኖስ የውሃ መጠን እየጨመረ ይሄዳል በምድር ዋልታዎች የተቆለለውም ሆነ የተጋገረው በረዶም ይሟሟል። የዚህን ሂደት ውጤት በጀርመን ሀገርም ማስተዋል ይቻላል ? በጀርመን ከታወቁት የአየር ጠባይ ዘጋቢዎች መካከል Sven Plöger----

5,«ባለፉት 100 ዓመታት፣ በጀርመን ሀገር የአየሩ የሙቀት መጠን በ 1,1 ዲግሪ ገደማ ከፍ ማለቱን ለመገንዘብ ችለናል። በመጀመሪያ ይህን የሚሰማ ሰው ያን ያክል ግምት አይሰጠውም። ነገር ግን ፣ ከመጨረሻው የበረዶ ዘመን ማክተም በኋላ፣ የፕላኔታችን የሙቀት መጠን ከ 4 እስከ 4 ተኩል ዲግሪ ሴንቲግሬድ ጭማሪ ማሳየቱ፤ በእርግጥ ፈጣን እመርታ ነው።»

ወደ ጀርመን አየር ጠባይ እንመለስ። የተለያየው የአገሪቱ ተደጋጋሚ የአየር ጠባይ መነሻው ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ከአዞር ደሴቶች የሚነሳው ከፍተኛ የአየር ግፊትና የአይስላንዱ ዝቅተኛ ግፊት --የሁለቱ መጋጨት ወይም ግንኙነት የሚፈጥረው ነው። የአየሩ ግፊት ሲያይል ከምዕራብ በኩል የሚነፍሰው ነፋስ በራይንና በእሽፕሬ ወንዞች እስከ በርሊን አካባቢ ያለውን ቦታ ይቃኛል። ከምዕራብ በኩል ግፊቱ ሲቀነስ፤ ከምሥራቅ በኩል ይነፍሳል። ስለሆነም፣ የአየሩ ጠባይ ክፍለ-ዓለማዊነት ባህርይ ይኖረዋል። ከባድ ነው ማለት ነው። እስቬን ፕሎዖገር እንደተከታተሉት ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ ሁኔታው የተጠቀሰውን ነው የሚመስለው።

7,«የአየር ንብረት ጉዳይ ተመራማሪዎች ታዲያ አሁን የሚጠይቁት፤ የሰሜን አትላንቲክ የተለያየ ተደጋጋሚ የአየር ጠባይ፤ በአጠቃላዩ በአየር ንብረት ለውጣ ሳቢያ ተዛብቷል ወይ? ነው። ባለፉት ዘመናት፤ የሰሜን አትላንቲክ የተለያየ ተደጋጋሚ የአየር ጠባይ አልፎ-አልፎ ይዋዥቅ እንደበረ የተስተዋለ ጉዳይ ነው።»

የአየር ጠባዩ መዋዠቅ ደግሞ ያስከተለው መዘዝ አለ። የ 2011 ጎርጎሪዮሳዊው ዓመት ጸደይ በጣም ደረቅ ነበረ። በተለይ ለአርሶ-አደሮች ማለፊያ ዘመን አልነበረም። በሚመጡት 50 ዓመታት የአየር ንብረት ምን ሊመስል እንደሚችል ሳይሆን፣ የትንንሽ ድንች ይዞታና የውድ ዳቦ ጉዳይ ነው ብዙዎችን የሚያስጨንቃቸው። የአየር ንብረት ተመራማሪዎች ይህን የሰዎች አርቆ ያለማሰብ ችግር ነው በማለት ከማማረር አልፈው ህዝብ እንዲሰማው እያሉ ጠንከር ባሉ ቃላት ማብራሪያም ሆነ መግለጫ ይሰጣሉ።»ፕሎዖገር ፣ እንዲህ ዓይነቱ አስደንጋጭ ማሳሰቢያ ፣ በአየር ንብረት ዙሪያ የሚካሄደውን ውይይት ይጎዳ እንደሁ እንጂ አይጠቅምም ባይ ናቸው።

በአያሌ አዳጊ አገሮች የአየር ንብረት ለውጥ በጉስቁልና የሚኖሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን፤ በሰፊው የሀገር ውስጥ ስደተኞች ወይም ተፈናቃዮች እንዲሆኑ ማብቃቱና ዓለም አቀፍ መላ ካልተፈለገም፣ ይኸው ችግር፣ እንደ ብርቱ ድርቅና ረሃብ፤ የብዙ ሰዎችን ህይወት እንዳይቀጥፍ ያሠጋል ነው የሚባለው።

በዓለም አቀፉ የፍልሰት ጉዳይ ድርጅት፣ የፍልሰት ጉዳይ አመራር፤ የምርምርና የመገናኛ ክፍል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚሸል ክላይን ሶሎሞን እንደሚሉት ከሆነ ፤ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ በሚመጡት 25 እና 30 ዓመታት ውስጥ፣ 250 ሚልዮን ያህል ህዝብ ከመኖሪያ ቀዬው ሊፈናቀል ይችላል።

በዓለም ዙሪያ የተቃጠለ አየርን (CO2) ልቀት ለመቀነስም ሆነ ፣ ለመገደብ በታላላቆቹ ባለኢንዱስትሪ መንግሥታት መሪዎች የፖለቲካ በጎ ፈቃደኛነት እስካልታዬ ድረስ፣ ታዳጊ አገሮችንም በልዩ ልዩ ሥነ ቴክኒክ ለማገዝ ሰፊ ጥረት እስካልተደረገ ድረስ፤ ፕላኔታችን ፣ የኑዋሪዎቿን ኑሮ ማሻሻል ይቅርና አሁን ከገጠማት በባሱ ሰው ሠራሽ ችግሮች ይበልጥ አስከፊ ሁኔታ ቢደርስባት የሚያስገርም አይሆንም።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሰ