የአየር ንብረት ለዉጥና የአፍሪቃ ቀንድ | አፍሪቃ | DW | 09.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

የአየር ንብረት ለዉጥና የአፍሪቃ ቀንድ

በአፍሪቃ ቀንድ በቂ ዝናብ ባለመጣሉ የተነሳ በተከተለው ድርቅ ያካባቢው አገሮች የምግብ እጥረት ችግር እንዳጋጠማቸው ዘገባዎች ያሳያሉ። በዓለም በሚታየው የአየር ለውጥ ሰበብ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ድርቅ መዘዝ ሰዎች ለባሰ አደጋ ሳያጋልጥ በፊት አስፈላጊውን ቅደመ ዝግጅት ለማድረግ እንደሚሰሩ በየጊዜው ያስታውቃሉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:13
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:13 ደቂቃ

የአየር ንብረት ለዉጥ

ካለፉት ሶስት ወራት ጀምሮ የአፍሪቃ ቀንድ አገሮች፣ በአብዛኛዉ ደግሞ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የአየር ንብረት መዛባትን የሚያስከትለው የ«ኤል ኒኖ» ክስተት መዘዝ ሰለባ መሆናቸውን ዘገባዎች ያሳያሉ። ይህ የአየር ንብረት ለዉጥም ባለፉት 30 ዓመታት ዉስጥ ታይቶ የማይታወቀዉ ዓይነት ድርቅ ሊያመጣ ፣ ከዚያም አልፎ ከባድ የሰባዊ ቀዉስ ሊያስከትል እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አስተባባሪ መስሪያ ቤት፣ በምህፃሩ «ኦቻ» በዚህ ወር አጋማሽ ባወጣዉ ዘገባው ጠቅሶዋል። ሌላው የተመ መስሪያ ቤት፣ የዓለም የምግብ ድርጅትም ፣ በወቅቱ በታየው የአየር ንብረት ለዉጥ የተነሳ በአፍሪቃ ቀንድ በሚገኙት ሶማሊያ፣ ኢትዮጵን፣ ዩጋንዳ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ ብዙ ሰው የምግብ እርዳታ ጠባቂ መሆኑን አመልክቶዋል። ከሶስት ዓመት በፊት የ«ኢጋድ» አባል የሆኑት የአፍሪቃ ቀንድ አገሮች መሪዎች ድርቅ መቼም ቢሆን ወደ ረሃብ እንደማይለወጥ የሚቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ቃል መግባታቸው የሚታወስ ነው፥ ይኸው ቃላቸው ምን ያህል ተግባራዊ ስለመሆኑ በዶይቼ ቬሌ ስቱዲዮ በመገኘት ቃለ ምልልስ የሰጡት የ«ኢጋድ» ዋና ጸሐፊ፣ አምባሳደር ኢንጂነር ማህቡብ ማሊም ስያስረዱ፣

«ያ ማለት እኛ የአየር ንብረት ለዉጥ ክስተትን እናስቆማለን ማለት አይደለም፣ ያ ሁሌም ይቀጥላል። ግን እኛ የምንጥረው ሕዝባችን ድርቅ የሚያስከትለውን መዘዝ መቋቋም የሚችልበትን መንገድ መሻት ነው። ድርቅ ወደ ረሃብ እንዳይለወጡ ማቋቋም እና ማጠናከር ነበር። ላረጋግጥልህ የምችለው ያ ቃል ከተገባ ዛሬ ከሶስት ዓመት በኋላ ስራችንን ማቀናበር የምንችልበት የተሻለ መዋቅር እንዳለን፣ ሕዝቦችም በተሻለ መንገድ ተቀራርበው በመስራት ላይ እንደሚገኙ ነው። ካስፈለገም የሚገባውን ርዳታ በአስቸኳይ ወደሚያስፈልገው ቦታ ከበፊቱ በተሻለ መንገድ ማድረስ እንችላለን። ለችግሮቹ ቶሎ መፍትሔ በማፈላለጉ ላይ ከሶስት ዓመት በፊት ከነበርንበት ጋር ሲታይ ዛሬ በተሻለ እና በተጠናከረ አቋም ላይ ያስቀምጠናል።»


በአየር ንብረት ለዉጥ በሚፈጠረው ድርቅ እና መዘዙ አንፃር በአስቸኳይ እርምጃ መዉሰድ ላይ ከአካባቢው አገሮች መሪዎች አኳያ የፖለቲካ ፊቃደኝነት መጓደሉ ችግሩን እንደሚያባብሰው «አዲስ ስታንዳርድ» የተሰኘው ወርሀዊ መፅሄት ኢትዮጵያን በምሳሌነት በመጥቀስ ዘግቦዋል። የ«ኢጋድ ዋና ጸሐፊ አምባሳደር ማሊም ግን አባባሉ በቦታው ያለውን ሁኔታ እንደማይገልጽ ነው ያመለከቱት። አምባሳዳሩ ስያብራሩ፣ <<እዉነቱን ለመናገር የተባለዉ ጉዳይ መሬት ጋር ካለዉ እዉነታ ጋር ሲታይ ትክክል ነዉ ብዬ አላስብም። ባለፈዉ ጊዜ በተከሰተዉ ድርቅ ሁሉም አገሮች ቢጠቁም፣ ኢትዮጵያንም ጨምሮ ማለት ነዉ፣ ኢትዮጵያ ካሉት አገሮች ሁሉ ችግሩን የተቋቋመች አንዱዋ ናት። የዓለም አቀፍ ጣልቃ ገብነት ሳይመጣ በፊት ነበር በኢትዮጵያ ያለዉ ስርዓት ችግሩን የተቋቋመው። እኔም እንደማየዉ፣ ችግሩ ሳይከሰት በፊት የአስቸኳይ ጊዜ እንዲታወጅ ጥያቄዎች ይመጣሉ፣ የአስቸኳይ ጊዜ የእርዳታ ጥሪ ማድረግ ግን ለርዳታ ሰጪ ድርጅቶች ለችግሩ መንገዶች ይክፍታል፣ ግን እኛ ማድረግ የምንፈልገዉ እዉነት እና ታማኝ በመሆን ችግሩን በራሳችን አቅም የቅድመ ማሰጠንቀቂያ ስርዓትን እና መርሀግብር መዘርጋት ነው የምንፈልገው። »


አሁን በተያዘው ጎርጎሪዮሳዊው ህዳር 2015 መጨረሻ ከ200 አገሮች የተውጣጡ ልዑካን በፓሪስ ለ21ኛዉ የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ተመልካች ጉባዔ ላይ ተገናኝተው ለመወያየት ዝግጅት ላይ ይገኛሉ። ዋናዉ የስብባዉ ነጥብ የአየር ንብረት ለዉጥ የሚያደርሰውን ድንገተኛ አደጋ መጠን መገደብ ላይ እርምጃ መዉሰድ እንደሚሆን የመገናኛ ብዙኃን ያመለክታሉ። የአየር ንብረት ለውጥ መዘዝም ችግሩ በሚከሰትባቸው አገሮች ውስጥ አለመረጋጋት ሊያስከትል እንደሚችል ስጋት መኖሩን የዜና አውታሮች ዘገባዎች ገልጸዋል። የአፍሪቃ ቀንድ አገሮች ራሳቸውን ከዚህ ዓይነቱ ችግር ለመከላከል አስፈላጊ የሆነውን የቅድመ ማሰጠንቀቅያ ስርዓትን እና የመረጃ መለዋወጥ ዘዴዎች ለማጠናከር እና ለማዳበር እየሰሩ መሆናቸውን አምባሳደር ማህቡብ ማሊም ገልጸዋል።

መርጋ ዮናስ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic