የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አድማ | ኢትዮጵያ | DW | 17.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች አድማ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ሰራተኞች የሆኑ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ዛሬ ለተወሰኑ ሰዓታት አድማ በመምታታቸው የአውሮፕላን በረራ ተስተጓጉሏል፡፡ ሰራተኞቹ አድማውን የመቱት በተደጋጋሚ ሲጠይቁ የቆዩት የደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጭማሪዎች ጥያቄ ስላልተመለሱላቸው ነው ተብሏል፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 05:55

የሰራተኛ ማህበሩ የአቪዬሽን ባለስልጣንን ተጠያቂ አድርጓል

የአዲስ አበባዉ ቦሌ ዓለም አቀፍ አዉሮፕላን ጣቢያ ዛሬ ረፋዱን በኢትዮጵያ እምብዛም የማይታይ ክስተት አስተናግዷል- የስራ ማቆም አድማ፡፡ አድማው የተደረገው የአውሮፕላኖችን ስምሪት በሚቆጣጠሩ ባለሙያዎች መሆኑ ደግሞ የአየር ማረፊያው አገልግሎቱን ለሰዓታት እንዲያቋርጥ አስገድዶታል፡፡ በአካባቢዉ የነበሩ እንደተናገሩት በረራ የነበረባቸው ስምንት አውሮፕላኖችም በያሉበት መሬት ቆንጥጠው እንደያዙ ቆይተዋል፡፡ በርካታ መንገደኞችም ከጉዟቸው ተስተጓጉለው የመንገደኞች መቆያን አጨናንቀዋል፡፡ 

የሰራተኞቹ አድማ ባልተለመደ መልኩ በመንግስታዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰበር ዜና መልክ ተላልፏል፡፡ በጣቢያው የቀረቡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ኃላፊዎችም አድማው መደረጉን እና ከትርፍ ሰዓት ክፍያ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡ እነዚሁ ኃላፊዎች ዘግየት ብለው የበረራ ተቆጣጣሪዎች ወደ ስራ መመለሳቸውን እና መደበኛ የበረራ አገልግሎት መቀጠሉን በዚያው ጣቢያ ቀርበው አስረድተዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ የአየር ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች የሰራተኛ ማህበር ዛሬዉኑ መግለጫ ቢያወጣም እወክላቸዋለሁ የሚላቸዉ ሠራተኞች ስለመቱት አድማ ምንም አላለም። ሆኖም በመስሪያ ቤቱ ለሚታዩ ችግሮች የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣንን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ 

የሰራተኛ ማህበሩ “በአየር ትራፊክ ቁጥጥር እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች በኢንዱስትሪው ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያመጣ ለሚመለከተው አካል ማስገንዘቡን” አስታውሷል፡፡ ሆኖም ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ “በቂ ትኩረት ባለማግኘቱ ችግሩ ሊባባስ መቻሉን” በማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ፍጹም ጥላሁን ስም የወጣው መግለጫ ያትታል፡፡ 

መስሪያ ቤቱ በስሩ ያሉ “ሙያተኞች ያነሷቸውን ህጋዊ እና ሙያዊ መብቶችን በማገናዘብ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ፤ ከፍተኛ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች ከቦታው ላይ በማንሳት፣ ከፍተኛ የስራ ጫና ባለባቸው ሌሎች የስራ መደቦች እንዲሸፍኑ በማስገደድ፤ ፍጹም የሙያውን ስነ ምግባር የሚጻረር ውሳኔ፣ ኃላፊነት በጎደለው መልኩ አስተላልፏል” ሲል መግለጫው ወንጅሏል፡፡ ይህ ውሳኔም “ችግሩን በማባባስ፣ ሙያተኛውን አላስፈላጊ ጫና ውስጥ በማስገባት ኢንዱስትሪውን ለከፍተኛ አደጋ ሊያጋልጥ ይችላል” ሲል አስጠንቅቋል፡፡   

በአየር ተቆጣጣሪነት ለአራት ዓመት ያገለገሉ የቀድሞ የመስሪያ ቤቱ ባልደረባም ሙያው “በከፍተኛ ጫና ውስጥ የሚሰራ እንደሆነ” ጠቅሰው ይህም ለበርካታ ችግሮች እንደሚያጋልጣቸው ይናገራሉ፡፡ ባለሙያዎቹ ያሉባቸውን ችግሮችም ይዘረዝራሉ።  

ዛሬውን ስለተስተጓጎሉ በራራዎች የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለሥልጣናትን በስልክ ለማነጋገር በተደጋጋሚ ደዉለን ጥያቄያችንን በኢሜይል እንድንልክ ጠይቀዉን ልከንላቸዉ ነበር። መልስ ግን አልሰጡንም። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለሥልጣናት በመስሪያ ቤታቸዉ ለሚነሱ ጉዳዮች መልስ እና አስተያየት ሲጠየቁ ሰበብ አስባብ እየፈጠሩ ሲጠፉ የዛሬዉ የመጀመሪያቸዉ አይደለም። የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ኃላፊዎችንም በስልክ ማግኘት አልቻልንም። 

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ተስፋለም ወልደየስ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic