የአውቶሞቢሉ ኢንዱስትሪ ዘርፍና ቀውሱ | ኤኮኖሚ | DW | 25.02.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአውቶሞቢሉ ኢንዱስትሪ ዘርፍና ቀውሱ

ዓለምአቀፉ የፊናንስ ቀውስ ብርቱ የኤኮኖሚ ችግር ደቅኖባቸው ከሚገኙት የበለጸገው ዓለም ኢንዱስትሪዎች መካከል አንዱና ምናልባትም ዋነኛው የአውቶሞቢሉ ዘርፍ ነው።

የኦፔል ፋብሪካ በጀርመን-ቦሁም

የኦፔል ፋብሪካ በጀርመን-ቦሁም

የአውቶሞቢሉ ኢንዱስትሪ ዘርፍ በወቅቱ ጥልቅ በሆነ ቀውስ ውስጥ ወድቆ ነው የሚገኘው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ገበዮቹ ሲመነምኑ አምራቾቹ ፋብሪካዎች ሥራቸውን መቀነስ ወይም ከናካቴው ጨርሶ ማቆም እስከመገደድ መድረሳቸው አልቀረም። በአውቶሞቢሉ ኢንዱስትሪ ውስጥ የተፈጠረው ቀውስ ደግሞ በራሱ ብቻ ተወስኖ አልቀረም። መዘዙ ብዙዎች መገጣጠሚያ ዕቃዎች የሚያቀርቡ አምራች ፋብሪካዎችን ጭምር ከሕልውና ፈተና ላይ ሲጥል ለሥራ አጦች መበራከትም ምክንያት እየሆነ ነው። ለዚህም ነው የምዕራቡ ዓለም መንግሥታት ዘርፉን በድጎማ ከውድቀት ለማዳን ሲጣደፉ የሚታዩት። የአውቶሞቢሉ ኢንዱስትሪ በመቶ ዓመት ገደማ ሕልውናው የዛሬውን ያህል ከባድ ፈተና ላይ የወደቀበት ጊዜ አይታወስም። አዝማሚያው ወዴት ነው?

የአውቶሞቢሉ ኢንዱስትሪ መላውን ሃያኛ ምዕተ-ዓመት በበለጸጉት አገሮች የከበርቴው ስርዓት ምሶሶ ሆኖ ነበር ያሳለፈው። ዛሬም ቢሆን አንዱ ታላቅ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ነው። በዓለም ዙሪያ በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞች በያመቱ 60 ሚሊዮን ገደማ የሚጠጉ አውቶሞቢሎችን ያመርታሉ። ግንዛቤ ለመስጠት ያህል ይህም ከሃብታሞቹ የበለጸጉ መንግሥታት አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት አንጻር አሥር በመቶውን ያህል ድርሻ የሚይዝ መሆኑ ነው። ለዚሁ ምርት በያመቱ ከዓለም የብረታ-ብረት ምርት 15 በመቶው፤ 25 በመቶው መስታወትና 50 በመቶው የጎማ ወይም የፕላስቲክ ምርት በስራ ላይ ይውላል።
የምርቱን ወጪ 60 ከመቶ ድርሻ የሚይዙት ደግሞ አወቶሞቢሉን ለመገጣጠም በሥራ ላይ የሚውሉት አሥር ሺህ ያህል ዕቃዎች ናቸው። በሌላ በኩል አውቶሞቢሎች በያመቱ ከዓለምአቀፉ የነዳጅ ዘይት ምርት ግማሹን መፍጀታቸውም ሌላው ሃቅ ነው። የዚህ ዘርፍ መዳከም መዘዝ እንግዲህ ከመለዋወጫ ምርት አቅራቢዎች ባሻገር ሌሎች መስኮችንም የሚጎዳ ነው የሚሆነው። በዓለም ላይ ታላላቆቹ አምራቾችና ከሰባ በመቶ የሚበልጠውን አውቶሞቢል የሚሸጡት ስድሥት ግዙፍ ኩባንያዎች ጀነራል ሞተርስ፣ ቶዮታ፣ ሬኖ-ኒሣን፣ ፎልክስ ዋገንና ዳይምለር ክራይስለር ናቸው። በዓለምአቀፍ ደረጃ ከሚመረቱት አውቶሞቢሎች 80 በመቶው የሚሸጠው ደግሞ በአሜሪካና በአውሮፓ ሲሆን የገበያው ማቆልቆል ጎልቶ የሚታየውም በነዚሁ በበለጸጉት የዓለም ክፍላት ነው።

ከዚሁ ሌላ በቻይናና በመሳሰሉ ሃገራት ገበዮች ደርቶ የቆየው ንግድ ጋብ ማለትም ሁኔታውን ማባባሱ አልቀረም። የተለያዩ ኩባንያዎች ሁኔታውን በማጤን ቀደም ሲል የተነበዩትን የሽያጭ ተመን ዝቅ አድርገው ሲያርሙ ክራይስለርና ፎርድን የመሳሰሉት የአሜሪካ ታላላቅ አውቶሞቢል አምራቾች በመኖር-አለመኖር ትግል ላይ ነው የሚገኙት። በዘርፉ ከተፈጠረው ከወቅቱ ቀውስ ሰባ ዓመታት ሙሉ ከስኬት ታሪክ ሌላ የማያውቀው የጃፓን ኩባንያ ቶዮታ እንኳ ከዚህ ችግር አላመለጠም። ቶዮታ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ የአሜሪካ ተፎካካሪውን ጀነራል ሞተርስን በማለፍ በዓለም ላይ ቀደምቱ ለመሆን በቅቶ ነበር። ግን ከዚያን ወዲህ በዘርፉ የነበረውን ግርማ-ሞገስ በማጣት እንደሌሎቹ ሁሉ እየተንገዳገደ ነው።

የዓለም ኤኮኖሚ ቀውስ ክፉኛ የተጫነው ይሄው ኩባንያ ከኢሢያ ውጭ ታላቅ በሆነው የአሜሪካ ገበያው የሸጣቸው አውቶሞቢሎች 16 ከመቶ ገደማ ዝቅ ብለዋል። ቶዮታ ገበያውን ይበልጥ ለማስፋት ውጥን በነበረው በዚህ በጀርመንም 27 በመቶ ነው ያቆለቆለው። እርግጥ ቶዮታ የአሜሪካን ኩባንያዎች ያህል አይሁን እንጂ ከባድ ቀውስ ላይ ነው የሚገኘው። በመሆኑም የምርት ተግባሩን በከፊል ሲያቆም ጃፓን ውስጥ በሚገኙት 12 ኩባንያዎቹ ውስጥ ምርትን ለመቀነስ ሠራተኞቹ በዚህ በያዝነው የካቲትና በመጪው መጋቢት ወራት የ 11 ቀናት ልዩ እረፍት እንዲወስዱ እስከማድረግ ደርሷል።
ኩባንያው በሌሎች አገሮችም የምርቱን ሂደት ጋብ ሲያደረግ በአሜሪካና በሕንድ አዳዲስ ፋብሪካዎችን ለማቆም የነበረው ዕቅድ መሸጋሸጉም ግድ ነው የሆነው። በዚህ በጀርመንም የሰሞኑ ታላቅ ኤኮኖሚ-ነክ ውይይት ያተኮረው ብርቱ ችግር የገጠመውን የኦፔልን ኩባንያ በመንግሥት ድጋፍ ከውድቀት ማዳን አለማዳኑ ነው። ቀውስ ላይ በሚገኘው በአሜሪካ ጀነራል ሞተርስ ኩባንያ ሥር የሚገኘው ኦፔል ከውድቀት አፋፍ ላይ ሲደርስ ጀርመን ውስጥ በሚገኙ አራት ኩባንያዎቹ ውስጥ የሚሰሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ተቀጣሪዎቹ የሥራ ዋስትና አደጋ ተደቅኖበታል። የኢንዱስትሪው ቀውስ ብርቱ ማሕበራዊ ቀውስን እንዳያስከትል እያሰጋ ነው።
ኩባንያው ከወደቀበት መልሶ እንዲነሣ የ 3,3 ሚሊያርድ ዶላር የመንግሥት ዋስትና እንደሚያስፈልገው ሲነገር መንግሥት ለምንና እንዴት መርዳት አለበት የሚሉ ጥያቄዎች እያከራከረ ነው። የክርስቲያን ዴሞክራቱ ሕብረት የምጣኔ-ሐብት ክንፍና የም/ቤት ዓባል ሚሻኤል ፉክስ ለምሳሌ ገንዘቡ ቢቀርብ በቀጥታ ወደ አሜሪካ ወደ ኦፔል እናት ኩባንያ ወደ ጀነራል ሞተርስ ነው የሚፈሰው፤ ይህን መቀበል አይቻልም ይላሉ። የመንግሥትን ተሳትፎ አጠያያቂ አድርገው ከሚመለከቱት ባለሙያዎች መካከል የፌደራሉ የጀርመን ኢንዱስትሪ የቀድሞ ፕሬዚደንት ሃንስ-ኦላፍ-ሄንክልም ይገኙበታል።

“እዚህ በአውቶሞቢሉ ኢንዱስትሪ ችግር ላይ መጣሩ ተገቢ መስሎ አይታየኝም። ለመሆኑ መጨረሻው የት ላይ ነው? ኦፔል ከተረዳ በሚቀጥለው ቀን BMW-ን፤ ከዚያም ዳይምለርን፤ እንዲያም ሲል መላውን መለዋወጫ አቅራቢ ኩባንያዎች መደገፍ ግድ ይሆናል። እንግዲህ ሳናስበው በአንድ ሌሊት ጀርመን ዴሞክራቲክ ሬፑብሊክን እንደገና መልሰን ገሃድ ልናደርግ ነው”

በሄንክል አስተሳሰብ መንግሥት ባንኮችን እንጂ ኢንዱስትሪዎችን ሊረዳ አይገባውም። ይሁንና ብዙዎቹ ፖለቲከኞች አስተያየቱን አይቀበሉትም። ኤኮኖሚዋ በተለይ በውጭ ንግድ ላይ ጥገኛ ለሆነው ለጀርመን የንግድ ምሶሶ ሆኖ የቆየው የአውቶሞቢሉ ኢንዱስትሪ ሕልውና ትልቅ ትርጉም አለው። ለዚህም ነው ኩባንያውን ከውድቀት ለማዳን፤ የሥራ ቦታዎችንም ለማቆየት የሚደረገው ጥረት ማመዘኑ። ቀውሱ ምናልባት ከሚቀጥለው 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለዘብ እያለ ሊሄድ እንደሚችል ዕምነት መጣሉም አልቀረም። መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆን አይቻል እንጂ!

ሆኖም ግን የመስኩ አዋቂዎች በአማካይና በረጅም ጊዜ በአውቶሞቢሉ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ተሃድሶ መደረጉ ወሣኝነት እንዳለው ነው የሚናገሩት። ከፋብሪካ የሚወጣው የወደፊቱ አውቶሞቢል ምናልባት በውጭ ገጽታው ከእስካሁኑ አይለይ ይሆናል። ሆኖም በጉዳዩ ጥናት የሚያካሂዱት የዶቼ ባንክ የምርምር ዘርፍ ባልደረባ ኤሪክ ሄይማን እንደሚሉት ውስጣዊ ይዘቱና የሞተሩ ድምጽ ሌላ ነው የሚሆነው።

“በወቅቱ በአውቶሞቢሉ ኢንዱስትሪ ውስጥ ጊዜው መለወጥ እየያዘ ነው። ከመቶ ዓመት በሚበልጥ ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጥንቱ ነዳጅ አቃጣይ ሞተር ጎን ሌላ ማንቀሳቀሻ ዘዴ ለመገልገል ዕድሉ አለ። በሚቀጥሉት ዓመታትና አሠርተ-ዓመታት የአውቶሞቢሉ ሞተር ይበልጥ በኤሌክትሪክ ሃይል የሚንቀሳቀስ እየሆነ እንደሚሄድ ነው የምንጠብቀው። እና አሁንና በሚቀጥለው ጊዜ ትክክለኛውን ምርት የሚያራምዱት ኩባንያዎች ከቀውሱ ተጠናክሮ ለመውጣት የተሻለ ዕድል እንደሚኖራቸው እርግጠኛ ነው”

አዝማሚያው በተለያዩ ምክንያቶች ወደዚያው መሆኑ ብዙም አያጠያይቅም። እርግጥ በኤኮኖሚ ቀውስ ሳቢያ በወቅቱ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ወደታች ማቆልቆሉ ሊያስቸግር ይችላል። ሆኖም ሃብቱ ውሱን በመሆኑ የኤኮኖሚው ችግር ካለፈ በኋላ የቤንዚንና የናፍጣ ዋጋ ተመልሶ መናሩ ደግሞ የማይቀር ነገር ነው። ይህም የነዳጅ ፍጆትን ለመቀነስ የሚደረገውን የተሃድሶ ጥረት ግድና ቀጣይም ያደርገዋል። ሂደቱ ለነገሩ ኤሪሽ ሄይማን እንደጠቀሱት ባለፉት ጥቂት ዓመታትም መታየት የያዘ ጉዳይ ነው።

“ባለፉት ዓመታት ብዙ ነዳጅ የማይፈጁ ትናንሽ መኪናዎች በሰፊው ከገበያ ሲነሱ ታዝበናል። እኔ የማምነው ተጠቃሚውም የአሁኑ የቤንዚን ዋጋ መውደቅ ጊዜያዊ መሆኑን እንደተረዳ ነው። የወቅቱ ዓለምአቀፍ የኤኮኖሚ ቀውስ መልሶ ሲለዝብ፤ እንደሚያልፍም አልጠራጥርም፤ ያኔ የነዳጅ ዘይት ዋጋ መልሶ ነው የሚጨምረው። እና በአማካይና በረጅም ጊዜ የተሽከርካሪው ፍጆት ምንነት ለገዢው ዋና የግዢ ውሣኔው መለኪያ ይሆናል”

የጀርመን ቀደምት የአውቶሞቢል ኩባንያዎች በዚህ ለተፈጥሮ ጥበቃም በሚበጅ ቴክኖሎጂ ምርምር ቀደምት ናቸው። ሆኖም አውቶሞቢልን በኤሌክትሪክ ባትሪ የማንቀሳቀሱ ጥበብ ገና ውድ መሆኑ ነው ችግሩ። በሌላ በኩልም ለተሃድሶው የሚያስፈልገው መዋቅራዊ ለውጥ ከዛሬ ወደነገ በአንዴ ሊከናወን አይችልም። ስለዚህም ከአሥር ከአሥራ አምሥት ዓመታት በኋላም ተገልጋዩ በአብዛኛው ነዳጅ በሚፈጁት ሞተሮች መዘወሩን ይቀጥላል። አቅጣጫው ግን ወደ ኤሌክትሪኩ ሞተር ለመሆኑ አንድና ሁለት የለውም።

ለማንኛውም የአውቶሞቢሉ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ቀውስ በወቅቱ ውጣ-ውረድ ማሰኘቱን ይቀጥላል። መንግሥታቱም ኤኮኖሚያቸውን መልሶ ለማነቃቃትና ሥራ አጥነት እንዳይስፋፋ ለማድረግ በያዙት ትግል በሚሊያርድ የሚቆጠር የድጎማ ገንዘብ ማፍሰሳቸው አይቀርም። ችግሩ የክስረቱ ሂደት ወሰኑ አለመታወቁ ላይ ነው።

MM