የአውሮፓ ዋንጫ 2012 ሩብ ፍጻሜ | ስፖርት | DW | 25.06.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ስፖርት

የአውሮፓ ዋንጫ 2012 ሩብ ፍጻሜ

በፖላንድና በኡክራኒያ የጋራ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ሩብ ፍጻሜው ዙር ባለፈው ምሽት በእንግሊዝና በኢጣሊያ ግጥሚያ ተጠናቋል።

በፖላንድና በኡክራኒያ የጋራ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ሩብ ፍጻሜው ዙር ባለፈው ምሽት በእንግሊዝና በኢጣሊያ ግጥሚያ ተጠናቋል። ሁለቱ ቡድኖች አንድም ጎል ባለታየበት በመደበኛውና በተጨማሪው ሰዓት ሊሸናነፉ ባለመቻላቸው ጨዋታው የለየለት በፍጹም ቅጣት ምት ነበር። በዚሁ መሠረትም ኢጣሊያ 4-2 ለመርታት በቅታለች። ለኢጣሊያ የመጨረሻዋንና ወሣኟን የፍጹም ቅጣት ጎል ያስቆጠረው አሌሣንድሮ ዲያማንቲ ነበር።

በመሠረቱ በጠቅላላው የጨዋታው ሂደት ጥንካሬ ያሳየውም የኢጣሊያ ብሄራዊ ቡድን ነው። ቡድኑ በመደበኛው ጊዜ ብዙ የጎል ዕድል ሲያመልጠው ጥቂት ቢሳካለት ኖሮ በሁለትና ሶሥት ጎሎች ልዩነት ለማሸነፍ በበቃም ነበር። ከተጫዋቾቹ አንዱ ሪካርዶ ሞንቶሊቮ እንደተናገረው ቡድኑ የተሻለው እንደነበርም ጨርሶ አያጠራጥርም።

«ዛሬ ጥሩ ስንጫወት በሚገባም ነው ያሸነፍነው። ሐሙስ ከጀርመን ጋር እንጋጠማለን። የጀርመን ቡድን ደግሞ ብዙ ጠንካራ ተጫዋቾች ያሉት ሃያል ቡድን ነው። ግን በዚህ የተነሣ አክብሮት እንጂ ፍርሃቻ የለንም»

በአጠቃላይ የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድን በአንጻሩ በመከላከል ጨዋታ ሲወሰን በፍጹም ቅጣት ምት ገደ ቢስ መሆኑን ትናንትም እንደገና ደግሞታል። እንግሊዝ በጎርጎሮሳውያኑ 1990 ኢጣሊያ ውስጥ ተካሂዶ በነበረው የዓለም ዋንጫ ውድድር ከግማሽ ፍጻሜው በፍጹም ቅጣት ምት ከተሰናበተች ወዲህ የትናንቱን ጨምሮ ከታላላቅ ውድድሮች ለስድሥተኛ ጊዜ በተመሳሳይ ሁኔታ መውጣቷ ነው። መርገምት ብለውታል ብዙ ታዛቢዎች!

ለማንኛውም የኢጣሊያ ብሄራዊ ቡድን በፊታችን ሐሙስ ዋርሶው ላይ በሚካሄደው ሁለተኛ ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ከጀርመን የሚገናኝ ሲሆን ይህም ከባድ ግጥሚያ እንደሚሆን ከወዲሁ በማያጠራጥር ሁኔታ የሚጠበቅ ነው። ጀርመን ለግማሽ ፍጻሜው ያለፈችው ባለፈው አርብ ግሪክን 4-2 በመርታት ነበር። ታዲያ ቡድኑ ምንም እንኳ እስካሁን ባደረጋቸው ግጥሚያዎች ሁሉ ብርቱ ጥንካሬን ቢያሳይም ከኢጣሊያ ጋር የሚያካሂደው ጨዋታ ግን ጨርሶ ቀላል የሚሆን አይመስልም።

ብዙዎቹ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች በግማሽ ፍጻሜው ከኢጣሊያ ሣይሆን ቀለል ብላ ከታየችው ከእንግሊዝ ለመገናኘት የጣሉት ተስፋ ዕውን አልሆነላቸውም። «ስኩዋድራ-አዙራ» እየተባለ የሚጠራው የኢጣሊያ ቡድን ለጀርመን እጅግ የሚፈራ ተጋጣሚ ሆኖ ነው የኖረው። በነገራችን ላይ ጀርመን በአንድ የአውሮፓ ወይም የዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ኢጣሊያን አሸንፋ አታውቅም። ይህ ደግሞ በተጫዋቾቹ ላይ ብርቱ የመንፈስ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ፍጹም አያጠራጥርም።

የቀድሞው የኢጣሊያ ብሄራዊ ቡድን በረኛ ዲኖ ዞፍ ለምሳሌ የቡድኑን ጠንካራነት በማመልከት ጀርመን ቀላል ግጥሚያ እንደማይጠብቃት ነው ያስገነዘበው። በተለይም ከስድሥት ዓመታት በፊት ጀርመን እዚህ ባዘጋጀችው የዓለም ዋንጫ ውድድር በግማሽ ፍጻሜው በኢጣሊያ 2-0 ተሸንፋ የዋንጫ ዕድሏን ማጣቷ ገና አልተረሳም። እናም የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ተጫዋቾች አሁን በአንድ በኩል ይህን እንበቀላለን እያሉ ነው። በትክክል የሚሆነውን ለማወቅ እርግጥ እስከፊታችን ሐሙስ ምሽት መጠበቁ ግድ ይሆናል።

በወቅቱ አሰልጣኙን የአኺም ሉቭን ምናልባትም ብዙ የሚያሳስበው በአካል ጉዳት እስካሁን ሙሉ አቅሙን ሊጠቀም ያልቻለው የመሃል ሜዳ ኮከብ የባስቲያን ሽባይንሽታይገር ጉዳይ ነው። እርግጥ እንደ ቡድኑ አምበል እንደ ፊሊፕ ላም ከሆነ የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ብዙ ጠንካራ ተቀያሪ ተጫዋቾች ስላሉት የደከመውን መተካቱ የሚከብድ አይሆንም።

«አሁን ለአውሮፓ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ደርሰን ነው የምንገኘው። እናም እዚህ የሁለት፣የሶሥት ወይም የአራት በመቶ ጉድለት መኖር የለበትም። ሰፊ ቡድን፤ ጥሩ ተጫዋቾች አሉን። ሆኖም ባስቲያን ሽባይንሽታይገር ቢጫወት ጠቃሚ ነው»

በዚህም በዚያም ከጀርመንና ከኢጣሊያ አንዱ ወደ ፍጻሜው የሚዘልቅ ሲሆን ሌላው የፍጻሜ ተሳታፊ የሚወጣው ደግሞ በፊታችን ረቡዕ በስፓኝና በፖርቱጋል መካከል ከሚካሄደው ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያ ነው። ውድድሩን በሽንፈት የጀመረችው ፖርቱጋል እየጠነከረች በመምጣት በሩብ ፍጻሜው ቼክ ሬፑብሊክን 1-0 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍጻሚው ስትሻገር ስፓን ደግሞ ለዚሁ የበቃችው ፈረንሣይን በፍጹም ልዕልና ከውድድሩ በማስወጣት ነው።

ለፖርቱጋል ብሄራዊ ቡድን አሁን ግማሽ ፍጻሜ ግጥሚያው ሁለት ቀናት ቀርተውት ሳለ በተለይም በሻቪና በኢኒየስታ የሚመራው የስፓኝ መሃል ሜዳ ተጫዋቾች ልዕልና ራስ ምታት መሆኑ አልቀረም። እነዚህ ተጫዋቾች መሃል ሜዳውን ከመቆጣጠር ባሻገር ለአጥቂዎቻቸው ወሣኝ ኳስ የማሳለፍ ትልቅ ብቃት ስላላቸው የፖርቱጋል ተከላካዮች አንዳች ስህተት መስራት የለባቸውም። ይህ ደግሞ ከባድ ነገር ነው የሚሆነው። የፖርቱጋል ለፍጻሜ የመድረስና ብሎም ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ዋንጫ ባለቤት የመሆን ዕድል ምናልባት በተለይም የኮከብ ተጫዋቹ የክሪስቲያኖ ሮናልዶ በዕለቱ በጣሙን አይሎ መገኘት ሊሆን ይችላል።

ፖርቱጋል ከስምንት ዓመታት በፊት እንደ አዘጋጅ አገር ከፍጻሜ ደርሳ በመጨረሻ በግሪክ በመሸነፍ ትልቅ የዋንጫ ዕድል እንዳመለጣት የሚዘነጋ አይደለም። ለማንኛውም በወቅቱ «ዋንጫዋን አሁን» የሚለው ድምጽ በአገሪቱ እንደገና መጉላት ይዟል። የሆነው ሆኖ ሁሉንም በጊዜው እንደርስበታልን። ዓለምአቀፍ ጋዜጦች በበኩላቸው ዛሬ ሰፊ ትኩረት የሰጡት ለኢጣሊያ ድልና ለእንግሊዝ አሳዛኝ ስንብት ነው።

የኢጣሊያው ጋዜጣ «ኮሪዬሬ-ዴሎ-ስፖርት» የኢጣሊያን ብሄራዊ ቡድን ከሌላ ፕላኔት የመጣ ግሩም ቡድን በማለት ሲያወድስ «ቱቶ-ስፖርት» ደግሞ በጀርመኑ አሠልጣኝ በየአኺም ሉቭ አቅጣጫ አንበሶቹ እኛ ነን ሲል ለቡድኑ ያለውን ታላቅ አድናቆት ገልጿል። የእንግሊዝ ጋዜጦች በአንጻሩ በአገሪቱ ብሄራዊ ቡድን የከፋ ዕጣ ላይ ሲያተኩሩ «ዴይሊይ-ሚረር» የተሰኘው ጋዜጣ በፍጹም ቅጣት ምት መሰናበቱን የተለመደው ነገር እንደገና ተደገመ ሲል መርገምት ብሎታል።

«ኢንዲፔንደንት» የተሰኘው ጋዜጣ በበኩሉ የወቅቱ ብሄራዊ ቡድን ከደቡብ አፍሪቃ የዓለም ዋንጫ በድክመቱ ቀድሞ ከተሰናበተው የእንግሊዝ ቡድን ጨርሶ የተለየ መሆኑን በመጥቀስ ከኤውሮ 2012 የተሰናበተው በክብርና ተሥፋ በሚሰጥ ሁኔታ መሆኑን አትቷል። የስፓኙ ጋዜጣ «ስፖርት» በአውሮፓው ዋንጫ ውድድር የመጀመሪያው የፍጹም ቅጣት ምት ውሣኔ ጣሊያኖችን በግሩም የማጥቃት አጨዋወታቸው በአግባብ መካሱን ሲያትት «ኤል-ፓይስ» ደግሞ ድንቁን ተጫዋች አንድሬያ ፒርሎን ማወደሱን ነው የመረጠው። «አዙሪዎች ለድል የበቁት ፒርሎን የመሰለ ግሩም፣ የተለየና ወሣኝ ተጫዋች ስላላቸው ነው» ሲል ጽፏል።

የፖርቱግል ጋዜጣ «ፑብሊኮ» ፍጹም ቅጣቱ ለእንግሊዝ እንደገና የቅዠት ሆነ ሲል «አ-ቦላ» ደግሞ ኢጣሊያ ድሉ እንደሚገባት በመጥቀስ ጀርመን ቀላል ተጋጣሚ እንደማይጠብቃት አስጠንቅቋል። የስዊድኑ «ስቬንስካ ዳግብላደት ደግሞ አራት የሚገባቸው ቡድኖች ለግማሽ ፍጻሜው ማለፋቸውን በማተት ስፓኝና ጀርመን ለፍጻሜ እንደሚደርሱ ተንብይዋል።

እንደገና ለማስታወስ ያህል በግማሽ ፍጻሜው ዙር በፊታችን ረቡዕ ፖርቱግል ከስፓኝ ኡክራኒያ-ዶኔትስክ ውስጥ የምትጋጠም ሲሆን በማግሥቱ ሐሙስ ደግሞ ጀርመንና ኢጣሊያ ፖላንድ ርዕሰ-ከተማ ዋርሶው ላይ ይገናኛሉ። ፍጻሜው ግጥሚያ የሚደረገው በፊታችን ዕሑድ ኪየቭ ውስጥ ነው።

ፎርሙላ-አንድ

ስፓን-ቫሌንሢያ ላይ ትናንት ተካሂዶ የነበረው የፎርሙላ-አንድ አውቶሞቢል እሽቅድድም አሸናፊ አገሬው ፌርናንዶ አሎንሶ ሆኗል። አሎንሶ ለዚያውም ከ 11ኛ ቦታ ተነስቶ ቀዳሚ ለመሆን መብቃቱ ብዙዎችን ነው ያስደነቀው። በውድድሩ የፊንላንዱ ተወላጅ ኪሚ ራይኮነን ሁለተኛ ሲወጣ ጀርመናዊው የሰባት ጊዜ የዓለም ሻምፒዮን ሚሻኤል ሹማኸር ደግሞ ሶሥተኛ ሆኗል።

አውስትራሊያዊው ማርክ ዌበር አራተኛ ሲሆን የብሪታኒያው ጄሰን ባተን በስምንተኝነት ተወስኗል። ያለፉት ሁለት ዓመታት ሻምፒዮን ጀርመናዊው ዜባስቲያን ፌትል እንዲያውም ወደ 21ኛው ቦታ ነው ያቆለቆለው። ከፎርሙላ-አንዱ ሃያ እሽቅድድሞች 8ቱ ተጠናቀው አሁን በአጠቃላይ 111 ነጥቦች ፌርናንዶ አሎንሶ የሚመራ ሲሆን ማርክ ዌበር በ 91 ሁለተኛ፤ የብሪታኒያው ሉዊስ ሃሚልተን በ 88 ሶሥተኛ፤ እንዲሁም ዜባስቲያን ፌትል በ 85 አራተኛ በመሆን ይከተላል።

ቴኒስ

በዓለም ላይ ታላላቅ ከሆኑት የቴኒስ ውድድሮች አንዱ የዓመቱ የዊምብልደን ውድድር በዛሬው ዕለት ሲከፈት እስካሁን የሚከተሉት ወጤቶች ተመዝግበዋል። በወንዶች የአሜሪካዊው የራያን ስዊቲንግና የኢጣሊያ ተጋጣሚው የፖሊቶ ስታራቼ ጨዋታ 6-2,2-0 እንደሆነ ሲቋረጥ በሴቶች የጆርጂያዋ አና ታቲሽቢሊ የታይላንዷን ታማሪን ታናሱጋርን 6-4,6-2 አሸንፋለች።

ኢጣሊያዊቱ ካሚላ ጆርጂ የአገሯን ልጅ ፍላቪያ ፓኔታን 6-4,6-3፤ ቻይናዊቱ ሊ-ና ካዛኳን ክሤኒያ ፔርቫክን 6-3,6-1፤ እንዲሁም የአውስትራሊያዋ ሣማንታ ስቶሱር የስፓኟን ካርላ ሱዋሬስን 6-1,6-3 አሸንፈዋል። በዛሬው ዕለት ከሚካሄዱት መክፈቻ ግጥሚያዎች መካከል የዓለም አንደኛው ስርቢያዊ ኖቫክ ጆኮቪች ከስፓኙ ሁዋን-ካርሎስ-ፌሬሮ ጋር የሚያደርገውና በዓለም አንደናዋ በሩሲያዊቱ በማሪያ ሻራፖቫና በአውስትራሊያ ተጋጣሚዋ በአናስታዚያ ሮዲዮኖቫ መካከል የሚካሄደው ጨዋታ በጉጉት የሚጠበቁት ናቸው።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 25.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15L9i
 • ቀን 25.06.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15L9i