1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮፓ ኅብረት የደን ጭፍጨፋ መከላከያ ሕግ የኢትዮጵያ ቡና ገበሬዎች እና ላኪዎችን አስግቷል

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ጥር 8 2016

የአውሮፓ ኅብረት ደን ተጨፍጭፎ የተመረቱ ሸቀጦች እንዳይገቡ ለመከልከል ያወጣው ሕግ የኢትዮጵያ ቡና ገበሬዎች እና ላኪዎችን አስግቷል። ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ የሸመቱት ቡና ወደ አውሮፓ ሲገባ ደን ተመንጥሮ እንዳልተመረተ ማረጋገጫ ማቅረብ አለባቸው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ገበሬዎችን ማሳ መዝግቦ ማረጋገጫ የሚያቀርብ ሥርዓት ማበጀት ግን ፈታኝ ነው።

https://p.dw.com/p/4bNpl
Kafeeernte in Äthiopien
ምስል Reuters/M. Haileselassie

የአውሮፓ ኅብረት የደን ጭፍጨፋ መከላከያ ሕግ የኢትዮጵያ ቡና ገበሬዎች እና ላኪዎችን አስግቷል

የአውሮፓ ኅብረት ደን ተጨፍጭፎ የሚመረቱ ሸቀጦች ወደ ገበያው እንዳይገቡ ለመከልከል ያወጣው ሕግ ለኢትዮጵያ ቡና ገበሬዎች፣ ላኪዎች እና ለሀገሪቱ ኤኮኖሚ ኃይለኛ ፈተና ደቅኗል። የአውሮፓ ኩባንያዎች ኢትዮጵያን ከመሰሉ ሀገሮች የሚገዟቸው ሸቀጦች ከጎርጎሮሳዊው 2020 ወዲህ ባሉ ዓመታት ደን ተጨፍጭፎ የተመረቱ አለመሆናቸውን የሚገልጽ የጽሁፍ መግለጫ እና ሊረጋገጥ የሚችል መረጃ ማቅረብ አለባቸው።

ይኸ ኃላፊነት ትከሻቸው ላይ የወደቀ የአውሮፓ ኩባንያዎች ማመንታት እንደጀመሩ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ ታዝበዋል። “የአውሮፓ ቡና ገዢዎች ላይ የሚጣለው ቅጣት ነው የከበደው” የሚሉት አቶ ግዛት “የአውሮፓ ኅብረት ያወጣውን ሕግ የጣሱ ካሉ ከዓመታዊ ገቢያቸው 4 በመቶ ይቀጣሉ። ይኸ ማለት በጣም ብዙ ገንዘብ ነው። ስለዚህ ቡና ገዢዎች ፈርተው ነው የቆሙት” ሲሉ ተጽዕኖውን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

ከቡና በተጨማሪ ደን ተመንጥሮ የተመረቱ የበሬ ሥጋ፣ አኩሪ አተር፣ ዕንጨት እና የዘምባባ ዘይትን የመሳሰሉ ሸቀጦች ወደ ኅብረቱ ገበያ እንዳይገቡ የሚከለክል ሕግ በአውሮፓ ምክር ቤት ጸድቆ ሥራ ላይ የዋለው ካለፈው ሰኔ 2015 ጀምሮ ነው። ሕጉ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ የሚውለው በጎርጎሮሳዊው 2024 መገባደጃ ቢሆንም የአውሮፓ ኩባንያዎች የግዢ ትዕዛዝ ገና ካሁኑ መቀዛቀዝ ጀምሯል።

“አሁን የታዘዘ ቡና ከአንድ ዓመት በኋላ ሊሆን ይችላል [በአውሮፓ] ሱፐር ማርኬት ውስጥ ሊገኝ የሚችለው። ስለዚህ የሚፈለገውን ካላሟላ ቅጣት ውስጥ ይገባሉ። ስለዚህ ከደን ጭፍጨፋ ነጻ መሆኑን አሁን ማረጋገጥ እና የተወሰነ ማስረጃ ይፈልጋሉ። በዚህ ምክንያት ፈርተው ነው የቆሙት” የሚሉት አቶ ግዛት ከኢትዮጵያ ቡና የሚገዙ የአውሮፓ ኩባንያዎች “በፊት እንደልባቸው እንደሚያዙት አሁን እያዘዙ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።

የቡና ፍሬ በኢትዮጵያ ሲለቀም
የአውሮፓ ኅብረት ያወጣው ሕግ ከቡና በተጨማሪ ደን ተመንጥሮ የተመረቱ የበሬ ሥጋ፣ አኩሪ አተር፣ ዕንጨት እና የዘምባባ ዘይትን የመሳሰሉ ሸቀጦች ጭምር ወደ ገበያው እንዳይገቡ የሚከለክል ነውምስል Reuters/M. Haileselassie

በዓለም ገበያ ከሚቀርበው ቡና አንድ በመቶ ገደማ የሚገዛው የጀርመኑ ዳልማየር ኩባንያ በአውሮፓ ኅብረት ሕግ ምክንያት ከኢትዮጵያ የሚሸምተውን ሊቀንስ እንደሚችል አስታውቋል። ከዳልማየር ሥራ አስፈጻሚዎች አንዱ የሆኑት ዮሐንስ ዴንግለር “ከፍተኛ መጠን ያለው የኢትዮጵያ ቡና መግዛት የሚቻልበት መንገድ አይታየኝም” ሲሉ ለሬውተርስ ተናግረዋል።

ጄዲኢ ፒትስን የመሳሰሉ ኩባንያዎች በአንጻሩ አነስተኛ የቡና ማሳ ያላቸው ገበሬዎች ከሚበዙባቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገሮች ፊታቸውን የማዞር አዝማሚያ አሳይተዋል። ይኸ በአውሮፓ የቡና ገዢ ኩባንያዎች ዘንድ የታየ ሽሽት የኦሮሚያ የቡና ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ዋና ሥራ አስኪያጅ ለሆኑት አቶ ደጀኔ ዳዲ ትልቅ ሥጋት ነው።

ከኢትዮጵያ የቡና ምርት 30 በመቶውን የሚገዙት የአውሮፓ ኩባንያዎች መሆናቸው የጠቀሱት አቶ ደጀኔ ዳዲ “አውሮፓ ጥሩ ከፋይ ናቸው። ገበሬውን የሚያበረታቱ የተለያዩ የሰርተፍኬት አሰራሮችን [ተግባራዊ በማድረግ] በእሱም እየገዙ ሕይወታቸውን ሊያሻሽል የሚችል አስተዋጽዖ እያደረጉ ነበር” ሲሉ ይናገራሉ።

የአውሮፓ ኅብረት ያወጣው ሕግ በሚያሳድረው ተጽዕኖ “ገበሬው ቀጥታ ተጎጂ ነው” የሚሉት አቶ ደጀኔ “30 በመቶ ቡና የሚሸጥበትን ገበያ አጣ ማለት ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያመጣ መገመት አይከብድም” ሲሉ ሥጋታቸውን ለዶይቼ ቬለ አጋርተዋል።

የአውሮፓ ምክር ቤት ያጸደቀው ሕግ ለከባቢ አየር ለውጥ እና ለሥነ-ምኅዳር ውድመት ምክንያት የሆነውን የደን ጭፍጨፋ እና መመናመን ለመግታት ያለመ ቢሆንም መዘዙ ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገሮች ለሚገኙ ገበሬዎች ተርፏል። አቶ ግዛት እንደሚሉት “ኢትዮጵያ ውስጥ ጫካ እየተመነጠረ ቡና አይዘራም።”

“ጫካ ተመንጥሮ፣ ቡና ተዘርቶ፣ ያ ቡና አውሮፓ ገበያ ላይ ገብቶ ሕጉን አላሟላችሁም ተብለን የምንወድቅበት መንገድ የለም። ወይም ብዙም አይደለም” የሚሉት አቶ ግዛት “ችግሩ ግን ይኸን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ” ሲሉ ገልጸዋል።

ቡና በኢትዮጵያ ሲታጠብ
በኢትዮጵያ ደን ተመንጥሮ ቡና ባይተከልም የአውሮፓ ኅብረት ባወጣው ሕግ መሠረት ማረጋገጫ ማቅረብ ግዴታ ነውምስል Reuters/M. Haileselassie

ይኸን ማረጋገጫ ለማቅረብ “እያንዳንዱ ቡና ያለበትን ቦታ በሳተላይት ለማየት የሚያስችል” ሥርዓት እንዲዘረጋ መጠየቁን የኦሮሚያ ቡና ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ከ25 ዓመታት በፊት የተመሠረተው እና ከ557 ሺሕ በላይ አባላት ያሉት የኦሮሚያ የቡና ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ሥርዓቶች በማበጀት የምርቱን የት መጣነት የሚያስረዳ መረጃ ሲያቀርብ ቆይቷል።

የኦሮሚያ የቡና ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ለደንበኞቹ የሚያቀርበውን ቡና የትመጣነት የሚያረጋግጥ ሶፍትዌር በአውስትራሊያ ኩባንያ አሰርቶ መረጃውን ሲያቀርብ እንደቆየ የገለጹት አቶ ደጀኔ የአውሮፓ ምክር ቤት ባጸደቀው ሕግ መሠረት ደን ተመንጥሮ እንዳልተመረተ የሚያረጋግጥ ሥርዓት ለመዘርጋት ፈታኝ እንደሚሆን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

“እኛ እስከ 5,000 እንሞክር ብለን በእኛ ወጪ አስሞክረናል። ይኸ ወጪ ለእያንዳንዱ ገበሬ እስከ 5 ዶላር ይሆናል” የሚሉት አቶ ደጀኔ ለየኦሮሚያ የቡና ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን 557 ሺሕ  አባላት ማሳ ተመሳሳይ ሥራ ለማከናወን የሚያስፈልገውን “ወጪ ማን ይቻል?” የሚል ጥያቄ እንዳለ ያነሳሉ።

ለዓለም ገበያ የሚቀርበው ቡና ደን ተጨፍጭፎ እንዳልተመረተ ማረጋገጫ የሚያቀርብ ሥርዓት የመዘርጋቱ ፈተና ግን ገበሬዎችን ብቻ ሳይሆን ላኪዎችን ጭምር የሚመለከት ነው። ከ5 እስከ 6 ሚሊዮን የሚደርሱ የኢትዮጵያ የቡና ገበሬዎችን፣ የማሳቸውን ስፋት መዝግቦ የሚገኝበትን ቦታ ለማረጋገጫ በሚመች መንገድ መሰነድ ፈታኝ እንደሚሆን አቶ ግዛት ይስማማሉ።

“አንድ ኮንቴነር ለመሙላት ምን አልባት የ200 እና የ300 ገበሬ ቡና ሊሆን ይችላል የሚገባው” የሚሉት አቶ ግዛት “ይኸንን የሚመዘግብ ሶፍትዌር ተሰርቶ፣ እያንዳንዱ ገበሬ እንዲመዘገብ ተደርጎ፤ ቡናውን ሲሸጥ ያቺን ማመሳከሪያ ጠቅሶ እንዲሸጥ” ማድረግ “ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅ ከባድ ሥራ” መሆኑን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።

በኢትዮጵያ የተመረተ ቡና ሲለቀም
የአውሮፓ ኅብረት ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ከምትሸጠው ቡና 30 በመቶ ገደማው ገዢ የአውሮፓ ኅብረት ነው። ምስል Reuters/M. Haileselassie

ፈተናው ግን ሥርዓቱን ማበጀት ብቻ አይደለም። የቡና እርሻ በሚገኝባቸው አካባቢዎች የሚገኝ ዛፍ ቢቆረጥ በእርግጥ ደን ጭፍጨፋ ነው? “ዛፍ አትቁረጡ” ከተባለ “ገበሬው እንዴት ይኑር? እንዴት ነው ምግቡን የሚያበስለው?” ሲሉ የኦሮሚያ የቡና ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደጀኔ ይጠይቃሉ። አቶ ግዛት ወርቁም ቢሆኑ እንዲህ አይነቶቹ ጉዳዮች ውስብስብ እንደሆኑ ይስማማሉ።

በሲዳማ የቡና አምራች አካባቢዎች “ባሕር ዛፍ [የእርሻ ማሳ] ድንበሮች ላይ ይተከላል። እሱ ባሕር ዛፍ ተቆርጦ ገቢ ማግኛ ነው። ነገር ግን ከቡናው ጋር ግንኙነት የለውም። ወይም ደግሞ ቡና ለመትከል የማይመቹ መሬቶች አካባቢ ላይ ተተክሎ እሱ እየተቆረጠ ገቢ ማግኛ ነው” የሚሉት አቶ ግዛት የኢትዮጵያ ቡና ወደ አውሮፓ ሲላክ የደን ጭፍጨፋ አለመከናወኑን ለማረጋገጥ በሳተላይት የሚደረግ ማጣራት ጥያቄ ሊያስነሳ እንደሚችል ሥጋት አላቸው።

“ከዚህ ቦታ የመጣው ቡና ይኸ ነው ካላችሁ ባለፈው ዓመት ጫካ ነበረው አሁን ደግሞ ይኸው ተመንጥሯል ሊሉ ይችላሉ። ይኸንን ነው ማረጋገጥ የሚያስፈልገው” ሲሉ የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል።

አቶ ግዛት ወርቁ እና አቶ ደጀኔ ዳዲን ጨምሮ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የቡናው ዘርፍ ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ከሚገኘው የአውሮፓ ኅብረት ጽህፈት ቤት፣ ከቤልጅየም ወደ ኢትዮጵያ ከተጓዙ አማካሪዎች እና የጀርመን ኤምባሲን ከመሳሰሉ ተቋማት ጋር ውይይት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ሕጉ የጸደቀው በአውሮፓ ምክር ቤት በመሆኑ ግን ጉዳዩ እንዲህ በቀላሉ መፍትሔ እንደማያገኝ አቶ ግዛት ያምናሉ። “ብዙ ነገር የምንጠብቀው ከአውሮፓ በኩል ነው” የሚሉት አቶ ግዛት ኢትዮጵያ ከዳፋው ለመዳን ልትከተል ይገባል የሚሏቸው እርምጃዎች አሉ።

ቡና ለቃሚ እናት ሠራተኛ
ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ከምታገኘው ገቢ ቡና ከ30 እስከ 35 በመቶ ድርሻ ቢኖረውም አምራቹ ገበሬ የልፋቱን ያክል ተጠቃሚ አይደለምምስል Reuters/M. Haileselassie

የአውሮፓ ኅብረት ባጸደቀው ሕግ መሠረት “ከእነሱም እርዳታ ጠይቀን ወይም ራሳችንን ችለን በምንችለው ሁሉ ለመመዝገብ መሞከር” አንደኛው የመፍትሔ እርምጃ እንደሆነ አቶ ግዛት ተናግረዋል። “አማራጭ ገበያዎችን በደንብ ማሳደድ” እንደሚገባ የሚመክሩት አቶ ግዛት “የአውሮፓ ኅብረት ያስቀመጠውን የጊዜ ገደብ እንዲያራዝም መጠየቅ” እንደሚገባ መክረዋል።

“የኢትዮጵያ ጉዳይ ከየትኛውም ቡና አምራች ሀገራት የተለየ ነው። የአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያን ቡና አምራቾች በተለየ መነጽር ማየት አለበት” የሚሉት  የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ “የአውሮፓ ኅብረት ጊዜውን ማራዘም አለበት። እንዴት እንደሚፈጸም ደግሞ አብሮ አቅዶ መስራት ነው” ሲሉ ይሞግታሉ።

ኢትዮጵያ በወጪ ንግድ ከምታገኘው ገቢ ቡና ከ30 እስከ 35 በመቶ ድርሻ አለው። ሀገሪቱ በ2014 በጀት ዓመት ለዓለም ገበያ ካቀረበችው 300 ሺህ ቶን ቡና ያገኘችው 1.4 ቢሊዮን ዶላር እጅግ ከፍተኛ የሚባለው ነው። የቡና ንግድ ለሀገሪቱ ከፍ ያለ ጠቀሜታ ቢኖረውም ገበሬዎች ግን እንደልፋታቸው ጥቅም አላገኙበትም።

“በአሁኑ ወቅት ቡና ከሚያመርተው ገበሬ ከ60 በመቶ በላይ ከድሕነት ወለል በታች ነው” የሚሉት የኦሮሚያ የቡና ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ደጀኔ ዳዲ የአውሮፓ ኅብረት ሕግ የሚያስከትለው ዳፋ የቡና ገበሬዎች ጫትን ወደ መሰሉ አዋጪ ሰብሎች ፊታቸውን እንዲያዞሩ ሊገፋፋ እንደሚችል ይሰጋሉ።

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ