የአውሮፓ ብሔረተኛ ፓርቲዎች ያሳደሩት ስጋት  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 24.01.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮፓ ብሔረተኛ ፓርቲዎች ያሳደሩት ስጋት 

በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ የቀኝ ፅንፈኛ ፓርቲዎች ቡድን አባላት እና ደጋፊዎቻቸው በምዕራብ ጀርመንዋ በኮብሌንዝ ከተማ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ባካሄዱት ስብሰባ የየሀገሮቻቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበር በጋራ እንደሚታገሉ አስታውቀዋል ። ጀርመንን ጨምሮ በአንዳንድ የአውሮጳ ሀገራት የተጠናከሩት የእነዚህ ብሔረተኛ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ስጋት አሳድሯል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:46

የአውሮፓ ብሔረተኛ ፓርቲዎች ቡድን

 ከስጋቶቹ አንዱ በያዝነው በጎርጎሮሳዊው 2017 አውሮፓ ውስጥ በሚካሄዱ አገር አቀፍ ምርጫዎች ላይ ሊያሳድሩ ይችላሉ የተባለው ተጽእኖ ነው ። ከዚህ ሌላ ፓርቲዎቹ ለአውሮጳ ህብረት ህልውናም አሳሳቢ ሆኗል ። 
ባለፈው ቅዳሜ ኮብሌንዝ ውስጥ በአውሮጳ ህብረት ፓርላማ የብሔረተኛ ፓርቲዎች ቡድን አባላት እና ደጋፊዎቻቸው ስብሰባ በተካሄደበት አዳራሽ ፣ የ28 ቱም የህብረቱ አባል ሀገራት ባንዲራ ነበር። የአውሮጳ ህብረት መለያ የሆነው በጥቁር ሰማያዊ መደብ ላይ የወርቅ ኮከቦች ያሉበት አርማ ግን የለም ።በዚህ ስብሰባ ላይ ከተገኙት  ፀረ የአውሮጳ ህብረት አቋም ያለው የዚህ  ቡድን አባላት ዋና ዋና መሪዎች መካከል ፣ አማራጭ ለጀርመን የተባለው ፀረ ፍልሰት ፓርቲ መሪ ፍራውከ ፔትሪ ፣ፍሮ ናስዮናል  የተባለው የፈረንሳይ ብሔረተኛ ፓርቲ መሪ እና በቅርቡ በሀገሪቱ በሚካሄደው ምርጫ ፓርቲያቸውን ወክለው ለፕሬዝዳንትነት የሚወዳደሩት ማሪ ለፐን ፣ፀረ እስልምና አቋም ያለው የኔዘርላንድሱ የነፃነት ፓርቲ የተባለው ቡድን መሪ ጌርት ዊልደርስ ፣ የኦስትሪያው የነፃነት ፓርቲ ዋና ፀሐፊ ሃራልድ ቪሊምስኪ እና ፀረ የአውሮጳ ህብረት አቋም ያለው የኢጣልያው ኖርዘርን ሊግ ፓርቲው ማቴዮ ሳልባኒ ይገኙበታል ። የስብሰባው እድምተኞች የአባል ሀገራትን ዜጎች መብት ይጋፋል የሚሉትን የአውሮጳ ህብረትን ፣ ለቆ የመውጣት ፍላጎታቸውን በንግግሮቻቸው ሲያንጸባርቁ ነበር ። በብሄረተኞቹ ፓርቲዎች እምነት ዓለም ዓቀፉ

የምጣኔ ሀበት ትስስር ዜጎችን እየጎዳ ነው ። ከፍተኛ ትምህርታቸውን እዚህ ጀርመን የተከታተሉት የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር እና የህግ ባለሞያ ዶክተር ለማ ይፍራሸዋ እንደሚያስረዱት ደግሞ ፣ ፀረ ስደተኛ አቋም ያላቸው እነዚህ ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎች በሁሉም ጉዳይ ለዜጎች ቅድሚያ ትኩረት ይሰጥ የሚል ተመሳሳይ ጥያቄም ያነሳሉ  ። 
በኮብሌንዙ ስብሰባ ላይ እንደተገለፀው የብሔረተኞቹ ቡድኖች ፍላጎት የወደፊቷ አውሮጳ ፤ ውሳኔዎች በብሔራዊ ደረጃ የሚተላለፉባት ፣ ፍልሰት በቁጥጥር የሚካሄድባት በጋራው ገንዘብ ዩሮ የማትገበያይ እና ድንበርም ክፍት የማይሆንባት እንድትሆን ነው ። በነዚህ አስተሳሰቦች ላይ አንድ አቋም ካላቸው ከአውሮፓ ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎች  መካከል የፈረንሳዩ ብሔረተኛ ፓርቲ ፍሮ ናስዮናል ፣ የኔዘርላንድሱ የነጻነት ፓርቲ እንዲሁም የጀርመኑ «አማራጭ ለጀርመን» በ2017 ምርጫ ይጠብቃቸዋል ። በሦስቱ ሀገራት በሚካሄዱት ምርጫዎች ላይ የነዚህ ፓርቲዎቹ ተጽእኖ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ነው የሚገመተው ። 
«አማራጭ ለጀርመን» የተባለው ፓርቲ ፣በህዝብ አስተያየት መመዘኛ ከ11 እስከ 15 በመቶ ድጋፍ አለው ። ይህም ፓርቲም በመስከረም በሚካሄደው ምርጫ በጀርመን ምክር ቤት መቀመጫ ሊያገኝ እንደሚችል ጠቋሚ ምልክት ነው ተብሏል ። ግምቱ ከያዘ ፓርቲው ከ1945 ወዲህ ጀርመን ምክር ቤት  በመግባት የመጀመሪያው የቀኝ ክንፍ ፓርቲ ይሆናል ። በፈረንሳይ በኔዘርላንድስ እና በጀርመን በተረጋጉት ፖለቲከኞች እና በተለመዱት ፓርቲዎች ቅር የተሰኘው ህዝብ ተቃውሞውን ለመግለፅ ለቀኝ ጽንፈኖች ድምፅ ሊሰጥ ይችላል ተብሎ በሰፊው ተገምቷል ። ታዲያ ቀኝ ፅንፈኞች የሚቃወሟቸውን አሠራሮች እናስተካክላለን የሚሉባቸው መንገዶች ፣ ምን ያህል ተቀባይነት አላቸው ? 
በዚህ ዓመት በፈረንሳይ በኔዘርላንድስ እና በጀርመን በሚካሄዱ ምርጫዎች በብሔራዊ ምክር ቤቶች ውስጥ መቀመጫዎች ሊያገኙ ይችላሉ የሚባሉት ብሔረተኛ ፓርቲዎች ለአውሮፓ ህብረትም ፈተና መሆናቸው አይቀርም ። ቀኝ ፅንፈኞች አጥብቀው የሚቃወሙት የህብረቱ የስደተኞች ፖለቲካ እና በየሀገሩ የሚወሰደው እርምጃ በዶክተር ለማ አስተያየት በአውሮፓ ህብረት

የሸንገን ስምምነት ነጻ እንቅስቃሴ ላይ ችግር ሊያስከትል እንደሚችል ይገመታል ። ምናልባት ከህብረቱ የወጣችውን  የብሪታንያን ፈለግ ለመከተል የሚያስቡ ከዩሮ ተጠቃሚ አባል ሀገራት ማህበር ወይም ደግሞ ከሌሎች ስምምነቶች የሚያፈነግጡ ሀገራት ሊኖሩ ይችላሉ የሚሉ ስጋቶች እንዳሉ ነው  ። ዶክተር ለማ ።
ብሪታንያ ባለፈው ዓመት ከአውሮጳ ህብረት አባልነት ለመውጣት መወሰኗ እና በዚህ ዓመት የዶናልድ ትራምፕ በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንትነት መመረጥ ለአውሮጳ ቀኝ ጽንፈኞች የልብ ልብ ሰጥቷል ። ትራምፕ የብሪታንያ ህዝብ ከአውሮጳ ህብረት ለመውጣት ያሳለፈው ውሳኔ አድናቂ ናቸው ። ሀገራቸው ለሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት በምህጻሩ NATO የምታወጣው ገንዘብ መብዛቱንም ተቃውመዋል ። የቀኝ ፅንፈኞች የልብ ልብ ማግኘት እና የትራምፕ አቋሞች ለአውሮጳ ህብረት የሚመቹ አይመስሉም ።በዶክተር ለማ አስተያየት ግን ይህ አውሮጳ እንዲጠናከር እና ራሱን ችሎም እንዲቆም ያደርጋል ። ህዝቡ ለቀኝ ጽንፈኞች ድምፅ እንዳይሰጥም ከወዲሁ የማስተካከያ እርምጃዎች ከተወሰዱ ውጤቱ እንደሚያሰጋው ላይሆን ይችላል ። ኮብሌንዝ ባለፈው ቅዳሜ ያስተናገደችው የብሔረተኛ ፓርቲዎቹን ስብሰባ ብቻ አልነበረም ። እነርሱም በመቃወም የተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍም ጭምር እንጂ ። በዚሁ ሰልፍ ላይ የጀርመን ምክትል መራሄ መንግሥትን ጨምሮ በርካታ የጀርመን ፖለቲከኞች ተገኝተው ነበር ። 

 ማብራሪያ በመስጠት የተባበሩንን ዶክተር ለማ ይፍራ ሸዋን እናመሰግናለን ። ለአውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅት አስተያየት ጥያቄ ወይም ጥቆማ ካላችሁ በፌስቡክ በSMS በኢሜል እንዲሁም በዋትስ አፕ አድራሻዎቻችን ላኩልን እናስተናግዳለን ።  

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ 
 

Audios and videos on the topic