የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ የስኬት ዕርምጃ | ኤኮኖሚ | DW | 28.05.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ የስኬት ዕርምጃ

ለአውሮፓውያኑ የጋራ ምንዛሪ ኤውሮ መከሰት መሠረት የሆነው የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ከተቋቋመ በፊታችን ዕሑድ አሥር ዓመት ይሆነዋል።

default

በዚህ በጀርመን ፍንክፉርት ከተማ ላይ ተቀማጭ የሆነው ባንክ ተልዕኮውን ልመወጣት መቻሉን በጅምሩ አጠያያቂ ያደረጉት ጥቂቶች አልነበሩም። ግን ማዕከላዊው የገንዘብ ተቋም ዛሬ ተጠራጣሪዎቹን ሁሉ ዝም ለማሰኘት በቅቶ ነው የሚገኘው። ታሪኩ የስኬት ታሪክ ነው። የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ እ.ጎ.አ. ሰኔ 1 ቀን. 1998 ዓ.ም. የጀርመንን የፊናንስ ከተማ ፍራንክፉርን ማዕከሉ በማድረግ ተቋቋመ። ባንኩ ከተቋቋመ በፊታችን ሰንበት አሥር ዓመቱን ሊይዝ ቢሆንም የምንዛሪው ትስስር ጽንደ-ሃሣብ ከአምሥት አሠርተ-ዓመታት በላይ የቆየ ታሪክ አለው።
የፈረንሣዩ የኤኮኖሚና የፊናንስ ጠቢብ ዣክ ሩፍ በ 50ኛዎቹ ዓመታት መጀመሪያ ላይ የአውሮፓ አንድነት ከሆነ በምንዛሪው ሕብረት ብቻ ሊሰምር እንደሚችል ይተነብያሉ። አመለካከታቸው ትክክለኛ ለመሆኑ እስከዛሬ የተደረገው ዕርምጃ ምስክር ነው። የአውሮፓን የምንዛሪ ሕብረት ለማስፈን ለመጀመሪያ ጊዜ ሃሣብና ዕቅድ መንሸራሸር የያዘው በትክክል በ 60ና በ 70ኛዎቹ ዓመታት ነበር። ይሁንና የቀድሞው የጀርመን ቻንስለር ሄልሙት ሽሚት እንደሚያስረዱት ግፊቱ የመጣው ከውጭ ነበር።

“የግፊቱ ምንጭ የቪየትናሙ ጦርነትና ወጪው ያስከተለው ነበር። በአሜሪካ የጊዜው የኒክሰን መስተዳድር ዶላርን በወርቅ የመመንዘሩን ግዴታ ብቻ ሣይሆን ከዚያም ባሻገር በ 1972 ና በ 1973 በምንዛሪዎች መካከል ያለውን ቋሚ የምንዛሪ ገበያ ዋጋ ደምብም ያነሣል። እርግጥ የጊዜው የፈረንሣይና የጀርመን የገንዘብ ሚኒስትሮች ከ 1945 የብሬተን-ዉድስ ስምምነት አንስቶ ይሰራበት የነበረው የምንዛሪ መለዋወጫ ደምብ ያላንዳች ተተኪ አማራጭ መወገዱን ተቃውመውታል። ግን ሃያል የኤኮኖሚ ክብደት ያላትን አሜሪካን ገፍተን ጥረታችንን ዕውን ለማድረግ አልቻልንም”

የአንዴው የጀርመን ቻንስለር በጊዜው የአገሪቱ የፊናንስ ሚኒስትር ነበሩ። እንግዲህ በ 1972 ዓ.ም. በመጀመሪያ ስድሥት፤ ከዚያም ዘግየት ብሎ ዘጠኝ የአውሮፓ መንግሥታት በአንድ ላይ በመሆን የጊዜውን የአውሮፓ ማሕበረ-ሕዝብ በለውጥ ምንዛሪ ማሕበር ማስተሳሰራቸው ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ዕርምጃ መውሰድ ስላለባቸው ነበር። እነዚሁ አገሮች የምንዛሪዎቻቸውን ግንኑነት በጠበበ ውጣ-ውረድ መጠን እንዲገደብ ለማድረግ ግዴታ ያሰፍናሉ። ይህ የምንዛሪ ልውውጥ ደምብ በአውሮፓው ማሕበረ-ሕዝብ ዓባል ሃገራት መካከል የአገልግሎት ሰጪውን ዘርፍና የመዋዕለ-ነወዩን እንቅስቃሴ ይዞታ እንዲያቃልልና እንዲራምድ የተወጠነ ነበር።
የተሳታፊዎቹ ሃገራት ማዕከላዊ ባንኮች ጣልቃ የመግባት ግዴታ ለስምምነቱ ገቢርነት ቁልፍ ይሆናል። የሚተሳሰቡትም Europian Currency Unit በአሕጽሮት ECU በተሰኘ የምንዛሪ መስፈርት ነበር። አሁንም የቀድሞው የጀርመን ቻንስለር ሄልሙት ሽሚት፤
“በጊዜው ያኔ በግልጽ ሳይነሣ የቀረ፤ ECU-ን ወደ አንድ የጋራ ምንዛሪ የማሳደግ የግብ ራዕይ ነበረን። ግን ብችኛው አማራጭ የመሆኑ ጉዳይ ገና ግልጽ አልነበረም። ምናልባት ከያገሩ ብሄራዊ ምንዛሪ ጎን ለጎን የሚራመድ ገንዘብ ይሆናል ተብሎ ነበር የታሰበው። ታዲያ ጉዳዩን አንስቶ ወደፊት ያራመደው ዣክ ዴሎር ነበር”

ዣክ ዴሎር እንደጊዜው የአውሮፓ ኮሚሢዮን ፕሬዚደንትነታቸው ለአውሮፓው የምጣኔ-ሐብትና የምንዛሪ ሕብረት የመሠረት ድንጋይ ይጥላሉ። ይህም ከአሥር ዓመታት በፊት ለአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ መመሥረትና ከዚሁ አንድ ዓመት በኋላም ለኤውሮ የጋራ ምንዛሪነት መንገድ ማመቻቸቱ ይታወሣል። እንደ ጊዜው የጀርመን ፌደራል ባንክ ፕሬዚደንት እንደ ካርል-ኦቶ-ፖል ከሆነ ለኤውሮና ለማዕከላዊው ባንክ መከሰት ቀደም ካለው የተለየ ሌላም ምክንያት ነበር። ይህም የጀርመኑ ብሄራዊ ምንዛሪ የ ዴ-ማርክ ጥንካሬና የስኬት ታሪክ ነው።
ካርል ኦቶ-ፖል መለስ ብለው እንደሚያስታውሱት የጀርመኑ ምንዛሪ እጅግ የተረጋጋ በመሆኑ አንዳንድ አናሣ አገሮች የቆየ የፊናንስ ,ፖሊሲያችውን ሙሉ በሙሉ በመተው ምንዛሪያቸውን ከርሱው ማስተሳሰሩን መርጠው ነበር።

“ሆላንድን ወይም ዴንማርክን ለመሳሰሉት አገሮች ተስማሚ ነበር። አዎን ትንሽ ነንና ጀርመኖች አግባብ ያለው የፊናንስ ፖሊሲ ከተከተሉ እኛም ልንከተላቸው እንችላለን ይላሉ። ለፈረንሣይ ደግሞ የጋራ ምንዛሪው የክብር ጉዳይ ነበር። እንደኔ ትዝብት ፈረንሣይን በመሳሰሉት ተሳታፊ አገሮች የአውሮፓውን ምንዛሪ ለማስፈን ለመቻላችን ይህ አንዱ ምክንያት ነበር። ዛሬ በአውሮፓው ማዕከላዊ ባንክ ውስጥ መላው ገንዘብ አታሚ ባንኮች ይወከላሉ። ይህም የአውሮፓ የፊናንስ ፖሊሲ እንደ ቀድሞው በፌደራሉ ባንክ ሣይሆን መላው ዓባል ሃገራት በሚሳተፉበት አንድ አካል ይራመዳል ማለት ነው”

የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ከአሥር ዓመታት በፊት በሩን ሲከፍት የመጀመሪያ ፕሬዚደንቱ “ሚስተር ኤውሮ” የሚል ቅጽል ስያሜ ያተረፉት የኔዘርላንዱ ተወላጅ ቪም ዱሰንበርግ ነበሩ። ስያሜው በዕውነትም የተጋነነ አልነበረም። ማዕከላዊው ባንክ በርሳቸው አመራር ኤውሮን ያላንዳች ችግር በ 12 ሃገራት ውስጥ ጥሬ ገንዘብ ለማድረግ ይበቃል፤ ገንዘቡን የተረጋጋ ለማድረግም ብዙ ጊዜ አይወስድም። ዛሬ የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ ከተቋቋመ ከአሥር ዓመታት በኋላ የጋራው ምንዛሪ ኤውሮ በዓለም ላይ ሁለተኛው ታላቅ ምንዛሪ ለመሆን በቅቶ ነው የሚገኘው።
ይህ የጀርመን ባንኮች ፌደራል ማሕበር መሪ ማንፍሬድ ቬበር እንደሚሉት በታሪክ ውስጥ ተመሳሳይ የማይገኝለት ነው። የጀርመን አስተዋጽኦም በቀላሉ የሚገመት አይሆንም። ጀርመን የአውሮፓው ማዕከላዊ ባንክ በፌደራል ባንኳ አርአያ እንዲዋቀር የተሣካ ግፊት አድርጋለች። ይህም ማዕከላዊው ባንክ ለብቻው የምንዛሪ ዋጋን የማረጋጋት ግዴታ ያለበት ሙሉ በሙሉ ነጻ የሆነ አካል ነው ማለት ነው። በውሣኔዎቹ ላይ ማንም ጣልቃ ሊገባ አይችልም። እርግጥ በአጠቃላይ የአውሮፓን አንድነት ለማጠቃለል ገና ብዙ ሥራ ይቀራል።
ሆኖም ኤውሮ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በዓለም ላይ ታላቁ ምንዛሪ እንደሚሆን የቀድሞው የጀርመን ቻንስለር የሄልሙት ሽሚትም ዕምነት ነው። “በኔ አመለካከት የአውሮፓን አንድነት ለማጠናቀቅ እንደገና ግማሽ ምዕተ-ዓመት ልንፈጅ እንችላለን። ኤውሮ ግን ከአንድ አሠርተ-ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የዓለም ምንዛሪነቱን እንደሚያስመሰክር አያጠያይቅም”

የአፍሪቃ ልማት ጉባዔ በጃፓን

ጃፓን-ዮኮሃማ ላይ በዛሬው ዕለት ሶሥት ቀናት የሚፈጅ ዓለምአቀፍ የአፍሪቃ ልማት ጉባዔ ተከፍቷል። የጃፓን መንግሥት ይህን በየአምሥት ዓመቱ የሚያዘጋጀውን ጉባዔ ስያካሂድ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ መሆኑ ነው። በስብሰባው ላይ ከሃምሣ የሚበልጡ የአፍሪቃ መንግሥታት ከፍተኛ ተጠሪዎች ይሳተፋሉ። የጃፓኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማሣሂኮ ኮሙራ ትናንት በዋዜማው እንደገለጹት የምግብ ዋጋ ንረት ዓቢይ ክብደት የሚሰጠው የአጀንዳ ርዕስ ነው። “የምግብ ዋጋ ንረት ባስከተለው የአፍሪቃን ሃገራት ከሕልውና አደጋ ላይ በጣለው ችግር ላይ እንደምናተኩርና ችግሩን ለመፍታት እንደምንጥር ተሥፋ አደርጋለሁ። ይህ በጋራ መግለጫችን ላይም ጠቃሚ ቦታ የሚኖረው ርዕስ ነው”

ጃፓን ለአፍሪቃ የምትሰጠውን ዕርዳታ እስከ 2012 ዓ.ም. ወደ 12,2 ሚሊያርድ ኤውሮ ከፍ በማድረግ በእጥፍ እንደምታሳድግ ጠቅላይ ሚኒስትር ያሲኦ ፉኩዳ ከወዲሁ ቃል ገብተዋል። የዘንድሮው ጉባዔ ዓላማ የአፍሪቃን ኤኮኖሚ ለማራመድ የሚያስፈልጉ ልዩ ዕርምጃዎችን በመውሰዱ ላይም የሚያልም ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ፉኩዳ ዘንድሮ በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉት ቀደምት መንግሥታት የተሰባበቡበት የቡድን 8 ሊቀ-መንበር መሆናችውም ስብሰባውን ተጨማሪ ክብደት ይሰጠዋል።

እርግጥ የጃፓን በአፍሪቃ ላይ ማተኮር ያለምክንያት አይደለም። እንደ ቻይና ወይም ሕንድ በክፍለ-ዓለሚቱ ጥሬ ሃብት ላይ ያተኮረ ነው። የልማት ዕርዳታ በተፈጥሮ ሃብት ልዋጭ ለማለት ይቻላል። ግዙፎቹ የእሢያ አገሮች ለራሳችው ጥቅም ሲሉ በአፍሪቃ ላይ በሰፊው ማተኮራቸው በመሠረቱ ወደ ኋላ ለቀረችው ክፍለ-ዓለም የሚበጅ ነው። እርግጥ ከታወቀበት! አፍሪቃውያኑ መንግሥታት የተፈጥሮ ሃብታችውን መዋቅራዊ ግንባታን ለማፋጠን፣ ጤና ጥበቃና ትምሕርትን ወደፊት ለማራመድ፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ለዘላቂ ልማት አስፈላጊ የሆነውን ዕውቀትን ለማስገባትም መጠቀም አለባቸው።
ይህ ካልሆነ የልማት ዕርዳታው መጨመር የረባ ትርጉም አይኖረውም። የታንዛኒያው ፕሬዚደንት ጃካያ ኪክዌቴ ትናንት በጃፓን የንግድ ሰዎች ፊት ባሰሙት ንግግር ችግሩን ጠቅሰውታል። “የምንማራችው ሁለት መሠረታዊ ነገሮች አሉ። አንደኛው ትክክለኛ የመንግሥት ፖሊሲ፣ የልማት ስልትና ዕርምጃዎችን ማስፈን ነው። እስካሁን የወሰድናቸው ዕርምጃዎች ከዕድገት ይልቅ ኋላ ቀርነትን ነው ያስከተሉት። ሁለተኛው ዕድገትን፣ የኢንዱስትሪ መስፋፋትን በማራመዱና የግሉን ዘርፍ በማዳበሩ ረገድ ተግባራዊ የመንግሥት ሚና ማስፈለጉ ነው። ሶሥተኛ ለኢንዱስትሪ ልማት በጎ ፖሊሲዎች መኖር አለባቸው” ችግሩ በብዙዎቹ የአፍሪቃ አገሮች ሃቁ ከዚህ የራቀ መሆኑ ላይ ነው።


ተዛማጅ ዘገባዎች