የአውሮፓ ማሕበረ-ሕዝብና የፖርቱጋል ኤኮኖሚ | ኤኮኖሚ | DW | 26.01.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአውሮፓ ማሕበረ-ሕዝብና የፖርቱጋል ኤኮኖሚ

የፖርቱጋል የምጣኔ-ሐብት ይዞታ አገሪቱ የአውሮፓን የኤኮኖሚ ማሕበረ-ሕዝብ፤ የዛሬውን የአውሮፓ ሕብረት ከተቀላቀለች ከሁለት አሠርተ-ዓመታት በኋላም ቀድሞ የታለመውን ያህል ለብልጽግና የሚያበቃ ዕርምጃን ለማሣየት አልቻለም። በተለይ ባለፉት አምሥት ዓመታት ባለበት ቀጥ ብሎ ነው የሚገኘው። በመሆኑም ፖርቱጋል መሰል ዓባል መንግሥታትን ተከትላ ለመራመድ፤ ልዩነቱንም ለማጥበብ ሳትችል ቆይታለች። ዛሬ ፖርቱጋል ከሕብረቱ ዓባል መንግሥታት አማካይ የዕድገት መስፈርት በታች ማቆልቆል የቀጠለች መሆኑ ነው ጎልቶ የሚታየው።

በአንጻሩ እ.ጎ.አ. በ 1986 ዓ.ም. ማሕበረ-ሕዝቡን አብራት የተቀላቀለችው ጎረቤቷ ስፓኝ ተገቢውን ዕርምጃ በማድረግ ዛሬ ካናዳን ቀድማ በዓለም ላይ ሥምንተኛዋ የኤኮኖሚ ሃይል ለመሆን በቅታለች። ፖርቱጋልን ሌላው ቀርቶ ከአንድ ዓመት ተኩል ገደማ በፊት ሕብረቱን የተቀላቀሉት አዳዲሶቹ ዓባል መንግሥታት የቀድሞይቱ የዩጎዝላቭ ሬፑብሊክ ስሎቬኒያና ትንሿ ደሴት ማልታ እንኳ አልፈው እንደተራመዱ ነው የኤኮኖሚ ዕድገት መረጃዎች የሚጠቁሙት። ፖርቱጋልን ባለፉት ሰባት ዓመታትም በአጀማመራቸው ደከም ካለ ሁኔታ የተነሱት አየርላድና ግሪክም እንዲሁ ጥለዋት አልፈዋል።

ለመሆኑ በተመሳሳይ ሁኔታና ጊዜ ማሕበረ-ሕዝቡን የተቀላቀሉት የፖርቱጋልና የስፓኝ የኤኮኖሚ ሂደት ለምን የተለያየ መልክ ሊይዝ ቻለ? ዋናው ምክንያት እርግጥ በአውሮፓው ማሕበረ-ሕዝብ ዓባልነት የተገኘውን ገንዘብና አጋጣሚ በትክክለኛ ፖሊሲ የመጠቀሙ፤ ለዕድገት አመቺ የሆኑትን ለውጦችም በጊዜው የማካሄዱ ጉዳይ ነው። በፖርቱጋል ይህ በተለያዩ ምክንያቶች የሚገባውን ያህል ገቢር አልሆነም።

የስፓኝ ኤኮኖሚ በሌላ በኩል የዓለም ባንክ በቅርቡ አውጥቶት የነበረ መረጃ እንደሚያመለክተው G-8 በመባል የሚጠሩት ቀደምት የበለጸጉ መንግሥታት አካል ከሆነችው ከካናዳ በልጦ ተገኝቷል። በነገራችን ላይ ይህ ስፓኝ የሃያላኑ መንግሥታት ስብስብ በዓባልነት እንዲቀበላት ለመጠየቅ እንድትችል መብት የሚሰጣት ነው። ለማስታወስ ያህል የወቅቱ የ G-8 ዓባል መንግሥታት በኤኮኖሚ ሃያልነታቸው ቀደምት የተባሉት አሜሪካ፣ ጃፓን፣ ጀርመን፣ ብሪታኒያ፣ ፈረንሣይ፣ ኢጣሊያና ካናዳ፤ እንዲሁም በፖለቲካ ምክንያት የስብስቡ አካል የሆነችው ሩሢያ ናቸው።
ቻይና ምንም እንኳ በኤኮኖሚ ጥንካሬዋ በዓለም ላይ ስድሥተኛውን ቦታ የያዘች ቢሆንም የስብስቡ ዓባል አልሆነችም። የእስካሁኑ መመዘኛ መስፈርት ካልተቀየረ ምናልባት ግዙፏ የሩቅ-ምሥራቅ እሢያ አገርም ዓባል የምትሆንበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም። ወደ አውሮፓው ሕብረት መለስ እንበልና ስፓኝ ኤውሮ-ዞን እየተባለ በሚጠራው የጋራ ምንዛሪውን ኤውሮን በተቀበሉት 12 አገሮች ውስጥም 3,.5 በመቶ ዕድገት በማሣየት ጠንካራዋ ሆና ተገኝታለች። የተቀሩት የኤውሮ-ዞን 11 አገሮች፤ አውስትሪያ፣ ቤልጂግ፣ ፊንላንድ፣ ፈረንሣይ፣ ጀርመን፣ ግሪክ፣ አየርላንድ፣ ኢጣሊያ፣ ሉክሰምቡርግ፣ ኔዘርላንድና ፖርቱጋል እድገታቸው ከስፓኝ ሲወዳደር በሲሦው የተወሰነ ነበር።

የፖርቱጋል እንዲያውም ባለፈው ዓመት ከአውሮፓው ሕብረት አማካይ የ 1.5 በመቶ ዕድገት ወደ 0.3 ያቆለቆለ ሆኖ ነው የታየው። የፖርቱጋል የኤኮኖሚ ዕድገት በያዝነው ዓመት በ 0.8 በመቶ ብቻ የተወሰነ፤ በተከታዩ ዓመትም ግፋ ቢል 1.2 በመቶ ቢደርስ ነው የአገሪቱ ማዕከላዊ ባንክ አስተዳዳሪ ቪቶር ኮንስታንሢዮ የሚገምቱት። ለወደፊት ብዙ የሚያበረታታ አይደለም።

የተጠበቀው የማይቀር ከሆነ ፖርቱጋል ከአውሮፓው ሕብረት አማካይ የኤኮኖሚ ዕድገት መጠን ወደታች እያቆለቆለች መሄዷ ይቀጥላል ማለት ነው። ከዚህም ባሻገር ውስጣዊ የልማት ደረጃዋ ሲታይ ሕብረቱ ወደ 25 ዓባል መንግሥታት ከመስፋፋቱ በፊት ከነበሩት ከተቀሩት 14 አገሮች ተስተካክሎ ለመራመድ አሠርተ-ዓመታት ሊፈጅባት ይችላል። በወቅቱ የሚቀርቡት የአገሪቱን የኤኮኖሚ ይዞታ የሚያመለክቱ መረጃዎች እውነትም ያን ያህል ተሥፋን የሚያዳብሩ አይደሉም።
እርግጥ ለኤኮኖሚ ዕድገት መንኮራኩር የሆነው የግል ፍጆት ማደጉን የቀጠለ ቢሆንም ዕርምጃው ካለፉት ዓመታት አንጻር ይበልጥ አዝጋሚ እንደሚሆን ነው የሚጠበቀው። ፍጆታው በ 2004 2.3 በመቶ፤ በተከታዩ ዓመትም ጥቂት ዝቅ ብሎ 2.1 በመቶ ሲያድግ በዚህ በያዝነውና በመጪው 2007 ደግሞ በ 1.1 በመቶ ብቻ የተወሰነ እንደሚሆን ግምት አለ። የፖርቱጋል የውጭ ንግድም ከሁለት ዓመታት በፊት ከነበረው 5.4 በመቶ መጠን ወደ 1.2 በመቶ አቆልቁሏል። የመዋዕለ-ነዋይ ተግባራዊነትም እንዲሁ!

አጠቃላዩ ሁኔታ የሚያሣየው የፖርቱጋል ኤኮኖሚ ብርቱ ቀውስ የተጠናወተው መሆኑን ነው። ፖርቱጋል እርግጥ ብቻዋን አትሁን እንጂ የአውሮፓውን ሕብረት ሶሥት በመቶ የበጀት ኪሣራ መስፈርት ማሟላት ተስኗት መታየቷም አልቀረም። የኤኮኖሚ ሁኔታዋ ይበልጥ የጨለመ የሚሆነው ደግሞ ከጎረቤቲቱ ስፓኝ ሲነጻጸር ነው። ሁለቱ የቀድሞ ሃያላን ቅኝ ገዢዎች ከሃያ ዓመታት በፊት የአውሮፓውን የኤኮኖሚ ማሕበረ-ሕዝብ በተቀላቀሉበት ጊዜ ሁለቱም በተመሳሳይ የዕድገት ደረጃ ላይ ነበሩ። ሁለቱም በምጣኔ-ሐብት ይዞታቸው ከሌሎቹ የጊዜው ዓባል መንግሥታት የሚስተካከሉ አልነበሩም።

ሆኖም ባለፉት ሁለት አሠርተ-ዓመታት ስፓኝ በተከታታይ ዘላቂ ውጤትን የሚያስከትሉ ስኬታማ ለውጦችን ለማካሄድ ትችላለች። ይህም ዛሬ በኤኮኖሚ ቀደምት ከሆኑት መንግሥታት አቻ ሊያድጋት በቅቷል። የአውሮፓ ሕብረት ዓባልነት 44 ሚሊዮን ለሚሆነው የስፓኝ ሕዝብ በአጠቃላይ ጠቃሚ የኑሮ ሁኔታ መሻሻልን አስከትሏል። በፖርቱጋል በአንጻሩ ዛሬም ከአገሪቱ 10.5 ሚሊዮን ሕዝብ ከአምሥት-አንዱ በድህነት ነው የሚኖረው።

ስፓኝና ፖርቱጋል ማሕበረ-ሕዝቡን ሲቀላቀሉ የዜጎቻቸው ዓመታዊ ነፍስ-ወከፍ ገቢ እኩል ነበር። ከጊዜው ዓባል መንግሥታት አማካይ ገቢ ሲነጻጸር 60 በመቶውን ድርሻ ነበር የያዘው። ሆኖም በ 1995 ዓ.ም. የስፓኝ ነፍስ ወከፍ ገቢ ከአውሮፓው አማካይ መጠን አንጻር ወደ 98 በመቶ ከፍ ሲልና ልዩነቱ እየጠበበ ሲሄድ ፖርቱጋል በ 75 በመቶ በመወሰን የኋላ ተከታይ ሆና ትጎተታለች። ጥናቶች የሚያመለክቱት የወደፊቱም ሂደቷ አቆልቋይ እንደሚሆን ነው።

ለዚህ ደግሞ ብዙ ዓለምአቀፍና ውስጣዊ መነሾ ያላቸው ምክንያቶች አሉ። በአውሮፓው ሕብረት ውስጥ ፖርቱጋል በተለይ ርካሽ የሥራ ጉልበትና ምርት በዝቅተኛ ዋጋ የሚያቀርቡት የምሥራቅ አውሮፓ አዳዲስ ዓባል አገሮች ብርቱ ፉክክር ገጥሟታል። በዓለምአቀፍ ደረጃም አያበበ የመጣው የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪዋ ከቻይናና ከሕንድ በዝቅተኛ ዋጋ በገፍ በሚራገፍ የአልባሣት ምርት ጨርሶ ሕልውናውን እንዳያጣ እያሰጋ ነው።

የፖርቱጋልን የወደፊት የኤኮኖሚ ዕድገት ተሥፋ በሶሻሊስቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በሆሤ ሶክራቴስ የሚመራው መንግሥት የበጀት ኪሣራውን ለማለዘብ የሚከተለው የቁጠባ ፖሊሲም የደበዘዘ አድርጎታል። የግብር መጨመር የሕዝቡ የፍጆት አቅም እንዲቀንስ ሲያደርግ በመንግሥቱ የቁጠባ ፖሊሲ ሳቢያ መዋዕለ ነዋይ ማቆልቆሉም ዕድገትን መግታቱ አልቀረም።

በርካታ የኤኮኖሚ አዋቂዎች እንደሚሉት ባለፉት ሃያ ዓመታት ከአውሮፓ የኤኮኖሚ ማሕበረ-ሕዝብና በኋላም ከአውሮፓው ሕብረት ወደ ፖርቱጋል በገፍ የፈሰሰው ገንዘብ አገሪቱን ዘመናዊ ለማድረግ ግልጋሎት ላይ መዋሉ ባይቀርም ሁለት ሚሊዮን ሕዝብን ከድህነት ለማላቀቅ አልቻለም። ፖርቱጋል ዛሬ በአውሮፓ ሕብረት ውስጥ በከፍተኛ የማሕበራዊ ፍትህ ጉድለት፣ በዝቅተኛ የሠራተኛ ክፍያና በሌላ በኩልም በመንግሥት ኩባንያ አስተዳዳሪዎች ታላቅ ደሞዝ ከፋይነት ሥም የወጣላት አገር ናት።

የፖርቱጋል ዜጎች ከሃያ ዓመታት በፊት ከአውሮፓው ማሕበረ-ሕዝብ መቀላቀሉን አገሪቱ ዘመናዊ ዕድገት ታደርጋለች በሚል በታላቅ ተሥፋ ነበር የተቀበሉት። ይሁንና አንድ “ዲያሪዮ-ዴ-ኖቲሢያስ” የተሰኘ የሊዝበን ዕለታዊ ጋዜጣ በቅርቡ እንዳለው በፍላጎትና በሃቅ መካከል ያለው ልዩነት እያንዳንዷ ቀን ባለፈች ቁጥር ይበልጥ እየሰፋ በመሄድ ላይ ነው። ለግሉ የኤኮኖሚ ዘርፍ የአውሮፓው ማሕበረ-ሕዝብ ዓባልነት እርግጥ ሰፊ ገበዮችን ከፍቷል። ለሠራተኞችና ለድሃው ነዋሪ ግን በአውሮፓ ደረጃ ከፍ ያለ ደሞዝና የተሻለ የኑሮ ደረጃ ማግኘቱ ዕውን እስኪሆን ብዙ ጊዜ የሚያልፍ ነው የሚመስለው። ማለቂያ ያጣ ተሥፋ!

እርግጥ የአውሮፓው ማሕበረ-ሕዝብ፤ በኋላም የአውሮፓ ሕብረት ዓባልነት ለፖርቱጋል በአጠቃላይ አልበጀም ማለት አይደለም። ችግሩ በሁለት አሠርተ-ዓመታት ውስጥ የተካሄደው መዋቅራዊ ግንቢያና የጥቂቶች የፍጆት አቅም መዳበር የብዙሃኑን የአገሪቱን ሕዝብ የኑሮ ሁኔታ ከማሻሻሉ ጥረት ጋር ተጣጥሞ አለመራመዱ ላይ ነው።

የአገሪቱ ፕሬስ ባለፉት ሣምንታት በጉዳዩ በሰፊው በማተኮር ችግሩን ግልጽ አድርጎ ለማሣየት ሞክሯል። አጠቃላዩ ግንዛቤም ጎረቤቲቱ ስፓኝ የአውሮፓን ሕብረት ገንዘብ በመጠቀም በኤኮኖሚ ቀደምት ከሆኑት የዓለም መንግሥታት መስተካከል ስትበቃ ያለፉት ሃያ ዓመታት የፖርቱጋል መንግሥታትና ባለሥልጣናት ግን ጥቂቶች የታደሉበትን የሃብታም መደብ ከመፍጠር አልፈው ዕድሉን ለልማት ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል የሚል ነው።

ከገጠር ወደ ጠረፍ ከተሞች የሚጎርፉትን ዜጎች መግታት፣ የአገሪቱን የኢንዱስትሪ መሠረት ለማጠናከርም ሆነ አንዴ ታላቅ የነበረውን የአሣ አጥማጅ ዘርፍም ከውድቀት ለማዳን አልተቻለም። በዘመነ-ግሎባላይዜሺን ይበልጥ በአንድ በተሳሰረው የዓለም ገበያ ላይ እኩል ለመፎካከር አስፈላጊ የሆነው የትምሕርትና የሙያ ተሃንጾም እንዲሁ ተጓድሏል ነው የተባለው። በአጭሩ ፖርቱጋል ስፓኝ ከተቀሩት የበለጸጉ የአውሮፓ መንግሥታት ጋር የነበራትን የዕድገት ልዩነት ለማጥበብ ያደረገችውን መሰል የተሣካ ጥረትና የተፋጠነ የኤኮኖሚ ዕርምጃ ዕውን ማድረግ አልቻለችም።

ስፓኝ ባለፉት ሃያ ዓመታት ስድሥት ሺህ ኪሎሜትር ርዝመት ያለው ፈጣን አውራ ጎዳናና ዘመናዊ የፈጣን ባቡር መረብ ለዜጎቿ ዘርግታለች። ኩባንያዎቿን በአውሮፓ ደረጃ ለተፎካካሪነት ስታበቃ የእርሻ ኢንዱስትሪዋን ዘመናዊ በማድረግም በዓለም ላይ ፍቱን ከሆኑት አንዱ እንዲሆን አብቅታለች። ለነገሩ ፖርቱጋልም ብዙ አድርጋለች። እክሉ ግን ለወደፊቱ ዕድገት ወሣኝ የሆነው ዕርምጃ አለመቅደሙ ነው፤ ጋዜጣው “ዲያሪዮ” እንዳጠቃለለው።