የአውሮፓ ሕብረት የኮሚሽኑ የአመራር አባላት ድልድል ጥያቄ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 17.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮፓ ሕብረት የኮሚሽኑ የአመራር አባላት ድልድል ጥያቄ

የአውሮፓው ሕብረት አባል ሃገራት ፣ በብራሰልስ ያካሄዱት ጉባዔ እስከዛሬ ጧት ድረስ ቢጓተትም የ 28 ቱን ሃገራት ኮሚሽን ፤ በሚመጡት 5 ዓመታት እነማን እንደሚመሩት በመወሰን ረገድ ስምምነት ላይ ሳይደርስ መቅረቱ ተነገረ ። ጎርጎሪዮሳዊው 2014

ዓም ከማክተሙ በፊት ሥልጣናቸውን የሚያስረክቡት የሕብረቱ የሚንስትሮች ም/ቤት ፕሬዚዳንት ቤልጂጋዊው ሄርማን ፋን ራምፖይ፣ እልባት ባለመደረጉ ያሳዝናል ይሁንና ከባድ የሚሰኝ ችግር አይደለም ብለዋል። አያይዘውም ፣ በሁሉም ነጥቦች ላይ ፣ እንዲሁ በመግባባት ውሳኔ ማሳለፍ ከማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን በመጠቆም፤ የሆነው ሆኖ፣ ነሐሴ 24 2006 በሚካሄደው ሌላ የመሪዎች ጉባዔ ግን ፣ መጨረሻ ውሳኔ ላይ መደረሱ አይቀሬ ይሆናል ነው ያሉት።

በአውሮፓው ሕብረት ኮሚሽን ፣ ዋና ዋና ቦታዎችን እነማን ይያዙ? መራኅያነ-መንግሥትና ርእሳነ ብሔር ፣ ለጊዜው እልባት ሊያደርጉለት ያልተቻለ ጉዳይ ሆኗል።የአውሮፓው ሕብረት የሚንስትሮች ም/ቤት ፕሬዚዳንት ፋን ራምፖይ፣ ፈተናውን ቀለል አድርገው ለማየት ነው የሚከሩት።

« በመጠኑም ቢሆን ደስ የማያሰኝ ሂደት ነው ፤ ነገር ግን የገዘፈ ችግር የሚባል አይደለም። እንደተገነዘብኩት ከሆነ፤ ለተመደቡት የኃላፊነት ቦታዎች ትክክለኛ ሰዎችን ለመምረጥ እምብዛም ያን ያህል አልተዘጋጀንም።»

በመጀመሪያ ሳንክ ያጋጠመው ብሪታንያዊቷን የሕብረቱ የውጭ ፖለቲካ ዋና መሪ ካትሪን ኤሽተንን ወደፊት የሚተካቸውን በመሠየም ረገድ ነው። በዛሬው ዕለት 60 ዓመት የልደት በዓላቸውን በስብሰባ ላይ ያከበሩት ፣ የጀርመን መራኂተ መንግሥት ወ/ሮ አንጌላ ሜርክል፣ አሠያየም ላይ የሴቶችና የወንዶች ምደባ ተፈላጊ ሆኖ መቅረቡ ውሳኔውን ምናልባት ሳያከብደው እንዳልቀረ ሳይጠቁሙ አላለፉም። ይሁንና መሆን ስለሚገባው ጉዳይ እንዲህ ብለዋል።

«መታየት ያለበት፤ ይህ የእኔ ጥልቅ እምነት ነው፤ የሚንስትሮች ም/ቤቱ ፕሬዚዳንት ፣ እኛን የ 28 አባል ሃገራቱን መራኅያነ መንግሥት ፣ የማስተባበር ችሎታ ያለው መሆን አለበት። እዚህ ላይ ለሆነ የፖለቲካ ፓርቲ አባል አይደለም ትኩረት የምሰጠው፤ ሁሉን አስተባብሮ የመያዝ ችሎታ ካለው እጩ ላይ ነው ዋናው ጉዳይ! እነዚህ ጥያቄዎች ሁሉ ዛሬ ማታ በሚገባ ሊመከርባቸው ይገባል። ታዲያ ከጥሩ ውጤት ላይ መደረስ ይኖርበታል።»

የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ፍርንሷ ዖላንድ፣ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ «ቀጣይዋም የአውሮፓው ሕብረት ዲፕሎማት ሴት ትሆናለች ፤ ይህንም ስናሰላስል፤ የአውሮፓን ገጽ በሚገባ የምታንፀባርቀውን በማሰብ ነው» ማለታቸው ተጠቅሷል። አያይዘውም የአውሮፓ ሶሺያሊስቶች፣ ግራ ዘመም አመለካከት ያላት የውጭ ፖለቲካ ጉዳይ ኀላፊ ይሻሉ ነው ያሉት። የሊቱዋንያ ፕሬዚዳንት ዳሊያ ግሪባውስካይት ፣ ከጉባዔው ሲወጡ ባሰሙት ንግግር ፣ «በቀረቡት እጩዎች ላይ ገና አጠቃላይ መግባባት ላይ ባለመደረሱ ፣ ውሳኔ ላይ አለመደረሱ ማለፊያ ነው» ከማለታቸውም በማያያዝ አገራቸውና ሌሎቹም የቦልቲክ ባህር አዋሳኝ አገሮች ፤ ፖላንድ ጭምር የኢጣልያን ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ፌደሪቻ ሞጌሪኒን እጩነት ፈጽሞ እንደማይቀበሉት ነው የተናገሩት።

እንደነርሱ አመለካከት ኢጣልያዊቷ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሞጌሪኒ ተመክሮ የሚያንሳቸው ሲሆን፤ የኢጣልያ መንግሥትም በአጠቃልይ፤ ከሞስኮ ጋር ያለውን ጠቃሚ የኤኮኖሚ ትሥሥር ለመጠበቅ አጥብቆ ስለሚሻ፤ ዩክሬይንን በተመለከተ በሩሲያ ላይ ያለው አቋም የተለሳለሰ ነው ።

አንዳንድ ዲፕሎማቶች እንደሚሉት ከሆነ፤ አቋማቸው ወደ ማዕከል -ቀኝ የአውሮፓ ህዝባዊ ፓርቲ የሚጠጋው የአሁኑ የሕብረቱ የሰብአዊ ርዳታ ኮሚሽነር ቡልጋሪያዊቷ ክሪስታሊና ጊዖርጊቫ ማለፊያ አማራጭ ናቸው። የሞገሪኒ ዕድል መደብዘዙን የተገነዘቡት የኢጣልያ ጠ/ሚንስትር ማቴዎ ሬንዚ፤ ኢጣልያ የምትሻው ፣ ይህ ወይም ያኛው የሥልጣን ቦታ እንዲሰጣት ሳይሆን ፣ ጨዋነት ፣ አክብሮት ነው ማለታቸው ተጠቅሷል።

የአውሮፓው ሕብረት የሚንስትሮች ም/ቤት ፕሬዚዳንት ለመሆን፤ የደንማርክ ጠ/ሚንስትር፤ ሶሺያል ዴሞክራቲቱ ፣ ሄለ ቶርኒንግ-ሽሚት ፣ ከብሪታንይ ጭምር ሰፊ ድጋፍ አላቸው ነው የተባለው። ደንማርክ ከዩውሮ አባል ሃገራት መካከል ስለሌለችበት ለፈረንሳይ አልዋጥላት ብሏል።

ዖላንድ በበኩላቸው ይበልጥ ተፈላጊው ሰው ሳይሆን የአመራር ዘይቤው ነውም ብለዋል። የአየርላንድ ወግ አጥባቂ ጠ/ሚንስትር ኤንዳ ኬኒ፣ የላትቪያ ቫልዲስ ዶምብሮቭስኪስ፤ የኢስቶኒያ አንድሩስ አንሲፕ ወይም የኔደርላንድ ጠ/ሚንስትር ማርክ ሩተ ፣ ሁሉም ለዘብተኛ ማዕከላውያን አማራጮች እንደሚሆኑ ተመልክቷል።

ተክሌ የኋላ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic