የአውሮፓ ሕብረት የልማት ዕርዳታ ፖሊሲ | ኤኮኖሚ | DW | 09.03.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአውሮፓ ሕብረት የልማት ዕርዳታ ፖሊሲ

የሕብረቱ የልማት ዕርዳታ ጉዳይ ኮሜሣር ሉዊስ ሚሼል ለአውሮፓ የልማት ዕርዳታ የተሻሉና በውል የተቀናበሩ ደንቦችን ዕውን ለማድረግ ባለፉት ሣምንታት ከለጋሽና ተቀባይ መንግሥታት፤ እንዲሁም ከመንግሥት ነጻ ከሆኑ ድርጅቶች ተጠሪዎች ጋር አውደ-ጥናቶችን አካሂደው ነበር። ከዚሁ ጥረት የተገኘው ጽንሰ-ሃሣብም ባለፈው ሐሙስ በቤልጂግ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አማካይነት ብራስልስ ላይ ቀርቧል።

የአውሮፓ ሕብረት ከዚህ ቀደም ይከተል በነበረ ፖሊሲው ብዙ ገንዘብ በከንቱ መባከኑን በማመልከት የልማት ዕርዳታውን ፍቱን ለማድረግ ሊወሰዱ የሚገባቸውን ጭብጥ ዕርምጃዎች አስተዋውቋል። የሕብረቱ ኮሚሢዮን ባለፈው ሣምንት ያቀረበው ሃሣብ 25ቱ ዓባል መንግሥታት ለጉዳዩ የጋራ አመለካከት እንዲኖራቸው የሚጠይቅና የጋራ ፖሊሲውን ፍቱን በማድረግ፣ እንዲሁም በመጣጣሙ ተግባር ላይ ያለመ ነው። የሕብረቱ ዓባል መንግሥታት የልማት ፕሮዤዎችን በማራመዱ በኩል የሚፈጠሩትን መሰናክሎች በጋራ እንዲያስወግዱም ይጠይቃል።

ኮሚሢዮኑ ባወጣው ዕቅድ መሠረት ለጋሽ ወይም አበዳሪዎቹ አገሮች በመካከላቸው ያለውን የአሠራር ሂደት ማጣጣም፣ ፖሊሲዎቻቸውን ማቀናጀትና ከተቀባይ መንግሥታት ዓመታዊ ዕቅዶች ጋር ማዛመድ ይጠበቅባቸዋል። ዓባል መንግሥታቱና ኮሚሢዮኑ ዓመታዊ የዕቅድ አወጣጥ ተግባራቸውን አንድ-ወጥ ሂደት ማስያዛቸውም ሌላው ተፈላጊ ጉዳይ ነው። ተግባሩን ፍሬያማ ለማድረግ በተወሰነ የዕርዳታ ተግባር ዓይነት የበለጠ ልምድ ያለው የሕብረቱ ዓባል ሃገር የአውሮፓውያኑን መንግሥታት ዕቅድ እንዲያቀናጅም ይበረታታል።

በኮሚሢዮኑ የቀረበው ሃሣብ ወይም በተግባር እንዲተረጎም የሚጠበቅ መርህ ዕርዳታ አቅራቢዎቹ የሕብረቱ መንግሥታት ማን ምን ያህል ለማን እንደሚሰጥ፣ ማለት የተዘነጋ አገር ካለ ለመለየትና ተደራራቢ የዕርዳታ ፕሮግራሞች እንዳይኖሩ ለማድረግ የሚያስችል አንድ የለጋሾች ዝርዝር አትላስ መፈጠሩንም የሚጠቀልል ነው። የልማት ኮሜሣሩ ሉዊስ ሚሼል ከሶሥት ዓመታት የጥንቅር ሥራ በኋላ የተሰባሰበ የለጋሾች-አትላስ የተሰኘ መረጃ አቅርበዋል። መረጃው ሰነድ ለመጀመሪያ ጊዜ ማን ምን ያህል ለየተኛው አገር እንዳቀረበ ጭብጥ ሆኖ ሰፍሮበታል።
በዚሁ መሠረት አብዛኛው የአውሮፓ ዕርዳታ ወደ ኮንጎ፣ ታንዛኒያ፣ ሞዛምቢክና አፍጋሃኒስታን ነው የፈሰሰው። ለማነጻጸር ያህል የአሜሪካ ዕርዳታ ደግሞ በዋነኛነት በኢራቅ፣ ዮርዳኖስና ኮሎምቢያ ላይ ያተኮረ ሆኖ ነው የሚገኘው። ጃፓንም በቻይናና በማሌይዚያ ላይ አተኩራለች። የድሃ-ድሃ የሚባሉት የአፍሪቃ አገሮች የሚገባውን ያህል የዓይን ማረፊያ አለመሆናቸውን ከዚሁ መገንዘቡ ብዙም አያዳግትም።

እርግጥ ይህ ለመሆኑ ከትኩረት ማነስ ባሻገር ሌላም ምክንያት አለው። የአውሮፓው ኮሚሢዮን እንደሚለው በወቅቱ ተቀባይ አገሮች አበዳሪዎች በሚከተሉት የተለያየ የአሠራር ዘይቤና ቅድመ-ግዴታ ችግር ገጥሟቸው ነው የሚገኙት። በመሆኑም ይሄው የደምቦች ብዛት በልማት በጣሙን ወደ ኋላ ከቀሩት አገሮች የአስተዳደር መዋቅር ድክመት ጋር ተጣምሮ እንደተቀባይ የሚያስፈልግ አቅማቸውን ማዳከሙ አልቀረም።

የአውሮፓው ሕብረት የልማት ኮሜሣር ሉዊስ ሚሼል እንዳስረዱት የብራስልሱ ኮሚሢዮንና ዓባል መንግሥታቱ በያመቱ የሚያወጡት የልማት ዕርዳታ 36 ሚሊያርድ ኤውሮ ገደማ ይጠጋል። ይህ ሕብረቱ በዓለምአቀፍ ደረጃ ከሚያወጣው ከጠቅላላ ዕርዳታው ግማሹ መሆኑ ነው። ግን በሌላ በኩል ሕብረቱ በዓለም ላይ በተናጠል ሲታይ ታላቁ ለጋሽ ይሁን እንጂ በዓለም አቀፍ ድርጅቶችና በተቀባይ አገሮች ዘንድ ያለው ተጽዕኖ ወይም ክብደት በአንጻሩ አነስተኛ ሆኖ ነው የሚገኘው። ሉዊስ ሚሼል ከዚሁ የተነሣ በዓለምአቀፉ መድረክ የሕብረቱን የፖለቲካ ገጽታ ለማጉላት የቅርብ ትብብርና የልማት ተግባር የጋራ ቅንጅት መስፈኑን ይሻሉ።

እስካሁን በብዙ ቢሮክራሲ የተነሣና እያንዳንዱ አገር ብሄራዊ ፍላጎቱን በማስቀደሙም ምክንያት ሥራው ተገቢው ትብብር የጎደለው ሆኖ ነው የቆየው። “ለበለጠ ትብብርና ተግባርን በጋራ ለማራመድ ለመብቃት ስንወያይ አርባ ዓመታት አልፈዋል። አሁን ሁኔታውን ለመለወጥ ዕርምጃ መውሰድ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ የገባነውን ቃል ማክበር አለብን ብዬ ነው የማምነው።” ብለዋል የልማት ኮሜሣሩ ሉዊስ ሚሼል!

የአውሮፓ ኮሚሢዮን ወደፊት በልማት ዕርዳታ አኳያ የዓባል መንግሥታቱን የአካባቢ ተግባር በሚገባ እርስበርስ ማጣጣም ይፈልጋል። ፕሮዤዎቻቸው አንዱ የሌላውን የሚያሟሉ እንጂ እርስበርስ የሚፎካከሩ መሆን የለባቸውም። በዕርዳታ ተቀባዮቹ አገሮች የራሳቸው ተጠሪዎች የሌሏቸው የዓባል መንግሥታት የኤምባሢ ሠራተኞችን እንዲገለገሉ ነው የሚመከረው። ተጠሪዎችን በጋራ ማሰልጠን ማስፈለጉም ተነግሯል። በወቅቱ በታዳጊው ዓለም በርካታና የተለያዩ ረዳቶች በገፍ መገኘታቸው የፈጠረው ውስብስብ ለድሆች አገሮች መስተዳድሮች ከአቅም በላይ ሣይሆን አልቀረም።

የአውሮፓ ሕብረት አስተዳደር ዘርፍ ለልማት ዕርዳታ የሚወስደውን ዕርምጃ ለተቀባዮቹ አገሮች እንዲቀል አንድ-ወጥ ማድረግ ይኖርበታል። ሉዊስ ሚሼል የልማት ዕርዳታ ፕሮዤዎችን ለማራመድ 800 ገደማ በሚጠጉ የተለያዩ የአሠራር ሂደቶች ተጨናንቆ ስለሚገኝ አንድ ተቀባይ አገር በማሣወቅ የሁኔታውን ምስቅልቅል እንደሚከተለው አስረድተዋል።

“የተለያዩት ደምቦች ተደቅነውበት ለሚገኝ አንድ ተቀባይ አገር ሁኔታው ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ምናልባት ልታስቡት ትችላላችሁ። በተመሳሳይ ጊዜ ላጋሽ አገሮች ታዳጊዎቹ አገሮች የተቀባይነት ብቃት የሚፈለገውን ያህል ትልቅ ሆኖ አይገኝም ሲሉ ነው የሚያማርሩት። ሆኖም በቅድሚያ የራሳችንን ደጃፍ በማጽዳት አሠራራችንን አንድ-ወጥ ማድረግ የመጀመሪያው ዕርዳታ ነው።”

“Action Aid International” የተሰኘው ዓለምአቀፍ የግብረ-ሰናይ ድርጅት ለጋሽ አገሮች እስካሁን ከሚያቀርቡት የልማት ዕርዳታ ሰፊውን ድርሻ ለቢሮክራሲ፣ ከመጠን በላይ ደሞዝ ለሚከፈላቸው ሠራተኛቻቸውና የራሳቸውን ኩባንያዎች ለመደገፍ ሲያባክኑ ቆይተዋል ሲል ይነቅፋል።

ሉዊስ ሚሼል በበኩላቸው የሕብረተሰብ ግፊትን በመቀስቀስ የአውሮፓ ሕብረት መንግሥታት ባለፈው ዓመት ገብተውት የነበረውን ቃል እንዲያከብሩ ለማድረግ ተነሳስተዋል። በዚሁ ቃል መሠረት መንግሥታቱ በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ ሕብረቱ ከአጠቃላዩ ብሄራዊ ምርት 0.7 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ ለልማት ዕርዳታ ማውጣት ይኖርበታል። ይህም በዓመት 66 ሚሊያርድ ኤውሮ ገደማ የሚጠጋ ሲሆን ከአሁኑ አንጻር እጥፉን ያህል መሆኑ ነው።

የልማት ዕርዳታው ቅልጥፍና ጉዳይ በብራስልስ በወቅቱ ዓቢይ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ እየሆነ እንደሄደ የተሰወረ ነገር አይደለም። የሕብረቱ የውጭ ግንኙነት ኮሜሣር ቤኒታ-ፌሬሮ-ቫልድነር እንዳስረዱት የውጭ ዕርዳታ ቅልጥፍና ጉዳይ ዛሬ በኮሚሢዮኑ አጀንዳ ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው ነው። ኮሚሢዮኑ በዓለምአቀፍ ደረጃ ለአውሮፓውያኑ ዕርዳታ ቅንጅት መሻሻል ጥርጊያ እየከፈተ ሲሆን የተፋጠነና ያልተወሳሰበ ዕርዳታ የተለመደ መደበኛ ነገር እንዲሆን ነው የሚፈለገው። “የመጪዎቹ ዓመታት ዓላማዬ ይህ ነው” ብለዋል ፌሬሮ ቫልድነር!

ዴንማርክ፣ ሉክሰምቡርግ፣ ስዊድንና ኔዘርላንድ ኮታውን ከአሁኑ ያሟላሉ። ጀርመንና ሌሎች መሰል የሕብረቱ ዓባል መንግሥታት ደግሞ ከዚህ ግብ ለመድረስ ከብዷቸው ነው የሚገኘው። የበርሊን መንግሥት ደግሞ-ደጋግሞ እንዳለው የተገባውን ቃል ዕውን ለማድረግ አዲስ የገንዘብ ምንጭ መገኘት ይኖርበታል። ለማንኛውም ወደፊት ከሚሰፋው የሕብረቱ ዕርዳታ አብዛኛውን ከሣሃራ በስተደቡብ ለሚገኙት የአፍሪቃ አገሮች ለመስጠት ነው የሚታሰበው።

የኮሚሢዮኑ ሃሣብ ለጊዜው በሁሉም የሕብረቱ መንግሥታት ዘንድ በጎ አመለካከት የተሰጠው መስሎ አይታይም። አንዳንዶች እንደሚያምኑት ብሄራዊ ፍላጎትን የሚጫን መስሎ መታየቱ አልቀረም። ይሁንና የልማቱ ኮሜሣር ሉዊስ ሚሼል በሌላ በኩል በልማት ዕርዳታው ጉዳይ የሕብረቱን ዓባል መንግሥታት ብሄራዊ ሉዓላዊነት ለማጥበብና ሁሉንም ብራስልስ ውስጥ ለመወሰን ይፈልጋሉ ሲል የሚሰነዘርባቸውን ወቀሣ አጥብቀው ነው ያስተባበሉት።

“ይህ ትክክል አይደለም። ተጨማሪ ሥልጣን እንዲኖረኝ ጨርሶ አልፈልግም። ዓባል መንግሥታት የራሳቸው የሆነ ሚናና ሥልጣናቸውን እንዲያጡም አልሻም። የልማት ዕርዳታው ፖሊሲ ሃላፊነት በጋራ በዓባል መንግሥታትና በኮሚሢዮኑ መካከል የሚውል ይሆናል።”

ለማንኛውም የሉዊስ ሚሼል የልማት ዕርዳታ ጽንሰ-ሃሣብ ገቢር እንዲሆን ገና በአውሮፓ ፓርላማና በሕብረቱ የሚኒስትሮች ሸንጎ መጽደቅ ይኖርበታል። እስከያዝነው 2006 ዓ.ም. መጨረሻ ለመጀመሪያዎቹ ታዳጊ አገሮች ዕርዳታ የጋራ ዕቅድ እንደሚቀርብ ነው የሚጠበቀው።

ሃሣቡ በወቅቱ እንደሚታየው ተቀባይነት ሊያገኝ የሚችል ነው የሚመስለው። ጥያቄው በተግባር በዕውነት መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል ወይ ነው። ቢራክራሲን ለማስወገድ ወይም ቢቀር ለመቀነስ፣ ተግባርን ለማጣጣምና ቅድሚያ ሊሰጠው በሚገባ የልማት ዕርዳታ ተግባር ላይ ለማተኮር ማሰቡ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ጨርሶ አያጠራጥርም። ይሁንና የዕርዳታ አሰጣጡ መንገድ ከተቀባዩን ወገን ሙስናን አጥብቆ የመታገልና የበጎ አስተዳደር ብቃት ፍላጎትን በቅድመ-ግዴታነት ካላስቀመጠ ሕዝብን ተጠቃሚ ለማድረግ ማብቃቱ ያጠያይቃል።