የአውሮፓ ሕብረት ዕድገትና የፈርሆይገን ራዕይ | ኤኮኖሚ | DW | 23.03.2006
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአውሮፓ ሕብረት ዕድገትና የፈርሆይገን ራዕይ

በመሠረቱ አውሮፓ ሁሉም ድርሻቸውን የሚወጡበት፤ ሁሉም ደግሞ እንዲሁ በዚያው መጠን ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት ብትሆን ይመረጣል። ይህ ቢቀር የአውሮፓው ኮሚሢዮን ምክትል ርዕስና የሕብረቱ የኢንዱስትሪ ኮሜሣር የጉንተር ፈርሆይገን ራዕይ ነው።

ጀርመናዊው ኮሜሣር ጉንተር ፈርሆይገን 25ቱ የአውሮፓ ሕብረት ዓባል መንግሥታት ጠንከር ባለ ሁኔታ የኤኮኖሚ ዕድገት ካላደረጉና በሥራ ገበያ ፖሊሲ አኳያም እመርታ ካላሣዩ በዓለምአቀፍ ደረጃ ካለው ዕርምጃ ወደኋላ እንዳይቀሩ በጣሙን መስጋታቸው አልቀረም። በመሆኑም አውሮፓን እስከፊታችን 2010 ዓ.ም. በዕድገትና በፉክክር ብቃት በዓለም ላይ ጠንካራ የኤኮኖሚ ወይም የንግድ አካባቢ ለማድረግ ስልታዊ ጥረት ማራመዱ ተገቢ ነው ባይ ናቸው።

ይህ እርግጥ ለአውሮፓው ሕብረት አዲስ ነገር አይደለም። ሕብረት የኋላ ኋላ ይተወው እንጂ በ 2000 ዓ.ም. “የሊዝበን ስትራቴጂ” በሚል ተመሳሳይ ፕሮዤ ይዞ መነሣቱ የሚዘነጋ አይደለም። ጉንተር ፈርሆይገን አሁንም ተመሳሳይ ሁኔታ እንዳይፈጠር ያስጠነቅቃሉ። “እስከ 2010 ቢቀር በሂደት እንኳ ለውጥ እንዲታይና የዕድገቱን ልዩነት ማጥበብ የሚቻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር ብዙ መጣር ይኖርብናል” ብለዋል የኢንዱስሪው ኮሜሣር!

አውሮፓ የአመራረት ቅልጥፍናን፣ የኤኮኖሚ ዕድገትንና የሥራ ገበያ መስፋፋትን በተመለከተ በዓለምአቀፉ ገበያ ላይ ከኋላ ስትጎተት ነው የምትታየው። በወቅቱ አሜሪካና ጃፓን ከኤኮኖሚ ቀውሳቸው በመላቀቅ መልሰው እየተንሰራሩ ሲሆን አውሮፓ ግን ገና ያቆለቆለውን ዕድገት እንደገና ለማንቀሳቀስ በመታገል ላይ ትገኛለች። የቅርቡ የኤውሮ-ዞን ዕድገት በዝቅተኛ 1.3 በመቶ መጠን ውሱን ሆኖ ታይቷል። በጉንተር ፈርሆይገን ዕምነት ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ በሕብረቱ ውስጥ የዕቅድና የመርህ መብዛት፤ እንዲሁም ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ቁልጭ ብሎ አለመቀመጡ ነው። ዛሬም ቢሆን በርካታ በብሄራዊ ደረጃ የተገጠገጡ ደምቦች ሌላው ቀርቶ በራሱ በሕብረቱ ውስጥ የምርቶችን ነጻ እንቅስቃሴ ሲያሰናክል፤ እንዲያም ሲል የዕድገት አቅምን ሲያዳክም ነው የሚታየው።

የነጻ ገበያውን ለውጥ ለማራመድ የተወጠነው ጉባዔ በሕብረቱ ውስጥ መልሶ ባገረሸው ብሄራዊ ጥቅምን የማስቀደም አሠራር ሳቢያ አወዛጋቢ እንዳይሆን ትናንት በጣም ነበር ያሰጋው። ሆኖም ይህንኑ አዝማሚያ በጋራ መግለጫ ለመኮነን ኢጣሊያ የጸነሰችውን ዕቅድ በወቅቱ የሕብረቱ ሊቀ-መንበር በአውስትሪያ የዲፕሎማሲ ጥረት ወይም ግፊት መልሳ ስባዋለች። ብሄራዊ ጥቅምን በማስቀደም በተለይ የምትወቀሰው ፈረንሣይ ናት። በተለይ በሕብረቱ መስፋፋት የተነሣ የመጤዎቹ አገሮች ሠራተኛ ገበያዋን እንዳይወረው በጣም ነው የምትሰጋው።
መንግሥታዊ ኩባንያዎቿ በውጭ ተፎካካሪዎች እንዳይገፉ ትከላከላለች። የኢጣሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤርሉስኮኒ የትናንቱን የጋራ መግለጫ ለማንቀሳቀስ መሞከራቸውም ያለ ምክንያት አልነበረም። የኢጣሊያው ኩባንያ ኤኔል የፈረንሣዩን ስዌዝ ለመጠቅለል የነበረውን ፍላጎት ፓሪስ መግታቷ ሳያስቆታቸው እንዳልቀረና ለዕርምጃው እንዳነሳሳቸው አንድና ሁለት የለውም። አንዳንድ ዲፕሎማቶች እንደጠቆሙት ደግሞ ዕርምጃው ቤርሉስኮኒ በመጪው ወር መጀመሪያ ላይ በሚካሄደው የኢጣሊያ ምርጫ ድጋፍ ለማጠናከር ያደረጉት፤ የፖለቲካ ዕርምጃም ጭምር መሆኑ ነው።
ይሁንና ለምሳሌ ስፓኝም ባለፉት ሣምንታት አንድ የጀርመን ግዙፍ የኤነርጂ ኩባንያ በዚሁ መስክ ኢንዱስትሪዋ ሰርጎ ለመግባት ያደረገውን ሙከራ ለመከላከል ስትጥር ታይታለች። በመሆኑም ጉዳዩ ውሎ አድሮ መነሣቱ የማይቀር ጉዳይ ነው። ፈረንሣይ የአውሮፓውን ሕብረት የአገልግሎት ዘርፍ ነጻ ለማድረግ የተያዘውን ጥረትም በቀደምትነት የምትቃወመው አገር ናት። ግን ሁለት ቀናት የሚፈጀው የመሪዎች ጉባዔ ለዘብ ባለ መልክ ከማለፍ ባሻገር በብሄራዊ ጥቅም ላይ ያተኮረ ፖሊሲ በሚያጠናክሩት አገሮች ላይ እጣት መቀሰሩ ያጠራጥራል።

በኩባንያዎች ላይ ተጭነው የሚገኙት ደምቦች ውስብስብ ከመሆናቸው ባሻገር ለአምራቾቹ ውድም ናቸው። የኢንዱስትሪው ኮሜሣር ጉንተር ፈርሆይገን ይህን መሰናክል ለመቋቋም ቀደም ብለው ባለፈው ዓመት ጥረት ያንቀሳቀሱትም ለዚህ ነበር። የብራስልስን የሰነድ ክምር ፈታትሾ መንገዱን ለመጠራረግ መቻሉ እርግጥ ብዙ ጊዜ መጨረሱ የማይቀር ቢሆንም ፈርሆይገን የመጀመሪያ ስኬት ላይ መድረሳቸውን ነው የሚናገሩት።

“ለምሳሌ የኤኮኖሚ ጥቅሙና ቢሮክራሲያዊ አለመሆኑ ሙለ በሙሉ ስይጣራ አንድም የአውሮፓ ሕብረት ሕግ ይሁን አዲስ ሃሣብ የሚቀርብበት ጊዜ አልፏል። ይህም ማለት አንድ ሃሣብ ከኮሚሢዮኑ ጠረጴዛ ከመቅረቡ በፊት ከወጪ አንጻር በኩባንያዎች ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ በትክክል እስከምን ነው፤ ተጨማሪ ቢሮክራሲን ሊያስከትልስ ይችላል ወይ፤ እነዚህን ሁለት ፈተናዎች በቅድሚያ ማለፍ ይኖርበታል።”

በሌላ በኩል በአንጻሩ ከኩባንያዎች የሚጠበቀው ደግሞ የአውሮፓውን የፉክክር ደምብ ማክበራቸው ነው። ጉንተር ፈርሆይገን አንዳንድ ብሄራዊ መንግሥታት ባለፉት ሣምንታት በኩባንያዎች ውሕደት ጉዳይ የወሰዱትን የመከላከል ዕርምጃ ይነቅፋሉ። “አውሮፓ ውስጥ ብሄራዊ ጥቅምን በማስቀደም የሚደረግ የመከላከል ዘመቻ፤ በተጨማሪም ከንቱ ሕዝባዊነት ለማለት ይቻላል የተቀሰቀሰ ሲሆን ይህም እጅግ የሚያሰጋ ነው። ይህ ለማንኛውም ተጽዕኖው በፖለቲካው ወገን ሣይሆን በገበዮች ሁኔታ የሚወሰን አንድ ታላቅ የአውሮፓ ውስጣዊ ገበያን የመፍጠሩን ሃሣብና ግቡንም የሚጻረር ነው።”

ታላቅ የአውሮፓ ውስጣዊ ገበያን ገሃድ በማድረጉ በኩል አስፈላጊውን ነጻነት በሥራ በመተርጎሙ ሕብረቱ በሚገባ የረካ ሆኖ አይገኝም። በተለይ በአገልግሎት ሰጪው ዘርፍ ይህ ነጻነት ፈር ሲይዝ ጨርሶ አይታይም። ታዲያ ሁኔታው በኩባንያዎችና በሠራተኞች ዘንድ ብርቱ ስጋትን መስከተሉ ብዙም አያስደንቅም። የኑሮ ሁኔታው ከፍተኛ የሆነ ሠራተኛ ለምሳሌ በዚህ በጀርመን ርካሽ የሥራ ጉልበት በሚያቀርቡ የውጭ ሙያተኞች ፉክክር ማሕበራዊ ደረጃው እንዳይወድቅ መስጋቱ አስገራሚ ሊሆን አይችልም።
ችግሩ አፋጣኝ መፍትሄን የሚጠይቅ ሲሆን እርግጥ የአውሮፓ ፓርላማ የአልግሎት ዘርፉን የቆየ መርህ ጥንካሬ ማላላቱ አልቀረም። የብራስልሱ ኮሚሢዮንም አንድ አዲስ ደምብ ለማስፈን እንደሚሻ እየገለጸ ነው። ፈርሆይገን እንደሚሉት “ደምቡ ለአውሮፓ አገልግሎት ሰጪዎች በመላው አውሮፓ ወገን የማይለይ የገበያ ተሳትፎን ለማረጋገጥ የሚያበቃ መሆን ይኖርበታል። ግን በዓባል አገራቱ ውስጥ የሚሰጠው አገልግሎት እንዴትና በምን መንገድ፤ በስምምነቶችና በደምቦቹ፤ በተለይም አገልግሎቱ በሚሰጥበት አገር የደሞዝና የማሕበራዊ ኑሮ ደረጃ ላይ ጥገኛ ሆኖ መካሄዱ ግድ ነው።”

በሕብረቱ ውስጥ የሠራተኞችን ነጻ እንቅስቃሴ የሚመለከተው መርህ በማንኛውም መንገድ በ 2011 ዓ.ም. እንደሚጸና ይጠበቃል። ቢዘገይ ያኔ ነው፤ ከአዳዲሶቹ የሕብረቱ ዓባል ሃገራት ጋር የተደረገው ስምምነት የጊዜ ገደብ ሲያከትም መላው የአውሮፓ ገበያ ሙሉ በሙሉ ለሠረተኞችና ለአገልግሎት ሰጪ ዘርፎች ክፍት የሚሆነው። ስለዚህም ዓባል መንግሥታቱ ደምቡን ከመጠን በላይ መጋፋቱን ከአሁኑ እንዲተዉ መመከሩም አልቀረም።

ችግሩ ብዙ ቢሆንም ለገበያ ፉክክር በቂ ሆኖ ለመገኘት ዓባል ሃገራትና ኩባንያዎች ይበልጥ በምርምርና በልማት ላይ ገንዘብ በሥራ ላይ እንዲያውሉ ነው የሚያሳስቡት። ጥናቶች እንደሚያሳዩት በነዚህ ዘርፎች ይበልጥ ገንዘብ በሥራ ላይ በሚውልባቸው አገሮች የኤኮኖሚው ዕድገት ውጤት የተሻለ ሆኖ ነው የሚገኘው።
የአውሮፓ ሕብረት በወቅቱ ቻይናንና ሕንድን የመሳሰሉ ብርቱ ተፎካካሪዎች ውድድሩን ይበልጥ ባከበዱበት ጊዜ ዕድገቱን ለማጠናከር በፍጥነት ተሃድሶ ማድረጉ ግድ ነው።