የአውሮፓ ሕብረትና የ ACP ድርድር | ኤኮኖሚ | DW | 19.11.2008
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአውሮፓ ሕብረትና የ ACP ድርድር

የአውሮፓ ሕብረት ከአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሢፊክ አካባቢ መንግሥታት ስብስብ ጋር አዲስ የኤኮኖሚ ሽርክና ውል ለማስፈን ያካሄደው ድርድር በተጣለለት የጊዜ ገደብ፤ ባለፈው 2007 ዓ.ም. መጨረሻ ዕውን ሣይሆን መቅረቱ ይታወሣል።

የአውሮፓ ሕብረት መለያ

የአውሮፓ ሕብረት መለያ

ድርድሩን በመደበኛ ጊዜው ለማጠናቀቅ ከአውሮፓ ኮሚሢዮን በኩል ወደ መጨረሻው አንዳንድ የማግባባት ጥረት መደረጉ አልቀረም። ኮሚሢዮኑ ድርድሩን ለማቅለል በሚል በአገልግሎት ሰጪው ዘርፍ አኳያ ያስቀመጠውን ቅድመ-ግዴታ ለማለዘብ ዝግጁ መሆኑ ለምሳሌ አንዱ ነበር። ይሁን እንጂ የአውሮፓ ሕብረትና የአፍሪቃ መንግሥታት መሪዎች የሊዝበን ጉባዔ ከከሸፈ ከአንድ ዓመት ገደማ ወዲህ ውሉን በተመለከተ አንዳች ዕርምጃ አልተደረገም። ለምን?
እንደሚታወቀው 78 በአብዛኛው የቀድሞ የአውሮፓ ቅኝ ግዛቶች የነበሩ ሃገራትን የሚጠቀልለው የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሢፊክ ስብስብ የሁለት ወገን ገበያ ከፈታን ግድ የሚያደርገውን አዲስ የኤኮኖሚ ሽርክና ውል እንዲፈርም የአውሮፓ ኮሚሢዮን ግፊት ሲያደርግ ነው የቆየው። ከታዳጊው ዓለም ስብስብ በርከት ያሉት የድሃ ድሃ የሚባሉ ሃገራት በፊናቸው ውሉ እስካሁን ወደ አውሮፓ ገበያ ለመዝለቅ ተሰጥቷቸው የቆየውን ልዩ የንግድ አስተያየት ከንቱ የሚያደርግ ከሆነ ለመፈረም ዝግጁ አለመሆናቸውን በየጊዜው ማስገንዘባቸው አልቀረም። እነዚሁ አውሮፓውያን መንግሥታት ለስጋታችን ተገቢውን ትክረት ሊሰጡ ይገባል ባዮች ናቸው።

እርግጥ ብራስልስ ባለፈው ዓመት ውሉን ለማስፈን የተጣለው የጊዜ ገደብ ሊያከትም መቃረቡን ምክንያት በማድረግ ታዳጊዎቹ አገሮች ለአውሮፓውያኑ አገልግሎት ሰጭ ዘርፍ ገበዮቻቸውን እንዲከፍቱ ታደርግ የነበረውን የድርድር ግፊት በመቀነስ በምርት-ነክ ስምምነት ላይ ወሰን እስከማለት ደርሳ ነበር። የአውሮፓው ሕብረት ከስኳርና ከሩዝ በስተቀር በመላው የ ACP ምርቶች ላይ ጥሎ ያቆየውን ኮታና ቀረጥ ጨርሶ እንደሚያስወግድ ቃል በመግባት ድርድሩን ለማፋጠንም ሞክሯል። ሆኖም የአውሮፓው ኮሚሢዮን ግፊት ለዝቦ ለአስታራቂ መፍትሄ የሚያበቃ ዕርምጃ አልታየም፤ ዉሉ በታሰበው ጊዜ ሊሰፍን ሳይችል ነው የቀረው።

ከመንግሥታት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች በበኩላቸው የአውሮፓ ሕብረት ለማስፈን የሚፈልገው ውል ታዳጊዎቹ አገሮች በቀላሉ ሊቀበሉት የሚከብድ ነው፤ ድህነትን ለመታገልም አይበጅም ሲሉ ቆይተዋል። ውሉ ታዳጊዎቹ አገሮች ኤኮኖሚያቸውን ብዙ-ወጥ በማድረግ እንዲለሙ የሚረዳ ሆኖ የታሰበ ነው ይባል እንጂ በዓለም ንግድ ድርጅት ውሣኔ መሠረት ገበዮቻቸውን ለአውሮፓ ምርቶችና አልግሎቶች እንዲከፍቱ የሚያደርግ መሆኑ እነዚህን ወገኖች አልተዋጠላቸውም። እስከዚያው፤ ማለት እስካለፈው ዓመት መጨረሻ ሲሰራበት የቆየው የኮቶኑ ውል ታዳጊዎቹ አገሮች ገበዮቻቸውን እንዲከፍቱ የሚጠይቅ አልነበረም። በአንጻሩ የተወሰኑት ድሆች አገሮች በልዩ የንግድ አስተያየት ምርቶቻቸውን ለአውሮፓ ገበዮች እንዲያቀርቡ ተፈቅዶላቸው ቆይቷል።

ውሉ ለታዳጊዎቹ አገሮች ልማት ከመበጀቱ ይልቅ የእስካሁኑን ስምምነት ሕገ-ወጥ
ያደረገውን የዓለም ንግድ ድርጅትን የጊዜ ገደብ ለማክበር ተብሎ ከተፈረመ ከመንግሥት ነጻ የሆኑት ድርጅቶች እንደሚሉት ፈሩን የሣተ ነው የሚሆነው። ታዳጊዎቹ አገሮች በተለይ ለአውሮፓ የአልግሎት ዘርፍና የመዋዕለ-ነዋይ ኩባንያዎች ገበዮቻቸውን በመክፈታቸው በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ድሃ ሕዝባቸው የኑሮ መሠረቱን ሊያጣ ይችላል። እ.ጎ.አ. ከ 1975 ዓ.ም. የሎሜ ውል ጀምሮ የነበረው ለታዳጊ አገሮች የአውሮፓን ገበዮች ከፍቶ የቆየው ልዩ የንግድ አስተያየት በአንድ መንገድ ቀጣይነት ካላገኘ ስጋቱ፤ ችግሩ በቀላሉ ወደጎን መገፋቱ የሚያጠራጥር ነው።
ACP በዓለም ላይ ድሃ የሆኑትን በርካታ አገሮች የሚጠቀልል ስብስብ ነው። በተለይም የድሃ ድሃ ከሚባሉት መካከል አፍሪቃውያን ያመዝናሉ። በመሆኑም እስካለፈው ዓመት ድረስ ሲሰራበት በቆየው የልዩ አስተያየት ውል ማክተም በተለይ ተጎጂ የሆኑት እነዚህ ሃገራት ናቸው። ችግሩን በተጨባጭ ምሳሌ ለማሣየት ያህል በአውሮፓው ሕብረት ውስጥ የሚረባው አሣማና ዶሮ ሕዝቡ ከሚፈጀው በላይ ነው። እና ሕብረቱ በዚሁ ሳቢያ የዋጋ ውድቀት እንዳይፈጠር ይህን የተትረፈረፈ ምርቱን በመደጎም ለውጭ ንግድ ያውላል። ይህ ደግሞ ለአፍሪቃው ከብት አርቢ ብርቱ ጠንቅ ነው።

አውሮፓውያኑ አንዱን ኪሎ የአሣማ ስጋ በ 44 የኤውሮ-ሣንቲም ወደ ውጭ ይሸጣሉ። የአፍሪቃ ገበሬ ታዲያ በዚህ ዋጋ ለመፎካከር አቅም የለውም። አንድ ኪሎ ስጋ ለማምረት አራት ዕጅ ወጪ ማፍሰስ ግድ ይሆንበታል። የዶሮውና የሌላውም የዕርሻ ምርት ወተት ይሁን ስንዴ ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። ከዚሁ ሌላ የአውሮፓ ሕብረት አማካሪ ኦሊቨር-ዴ-ሹተር እንደሚሉት አፍሪቃዊው ገበሬ በቀላሉ አንዱን ምርት ትቶ በሌላ የማተኮር አቅም የለውም። ከብት አርቢው ድንገት ተነስቶ ዕሕል አምራች ለመሆን አይችልም።

“ለዚህም ምክንያቱ የእርሻ ልማት ከአፈሩ የተለያ ባህርይና በአንድ ሌሊት ሊቀየር ከማይችል ከተለየ የአስተራረስ ጥበብ ዕውቀት ጋር የተሳሰረ ነገር መሆኑ ነው። ስለዚህም ለእርሻው ለውጥ የሚያስፈልገው ጊዜ እንበል ምርትን ከጫማ ወደ ቲ-ሸርት ከመለወጡ ይልቅ ጠቃሚ ይሆናል”

ይህ የኤኮኖሚ ሽርክናውን ውል በተመለከተ ዛሬም ታላቁ የታዳጊዎቹ ሃገራት ስጋት ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው። ውሉ ሕብረቱንና 80 ገደማ የሚደርሱ የአፍሪቃ፣ የካራይብና የሰላማዊ ውቂያኖስ አካባቢ ሃገራትን የሚመለከት ሲሆን የድሃ ድሃ የሚባሉ ሃምሣ መንግሥታትን 750 ሚሊዮን ሕዝብ ዕጣም ይመለከታል። ይህ በዚህ እንዳለ የአውሮፓ ሕብረት ሊገባደድ በተቃረበው 2008 ዓ.ም. ሂደት ተናጠል የአካባቢ ስምምነቶችን ሲዋዋል ነው የቆየው። ከ 16 የካራይብ አገሮች ጋር ስምምነቱ ሰፍኗል።
ኬንያን፣ ኡጋንዳንና ሩዋንዳን የመሳሰሉትን የምሥራቅ አፍሪቃ መንግሥታት ጨምሮ ከ 22 ሌሎች የ ACP አገሮች ጋር ጊዜያዊ ውል መፈረሙም አልቀረም። እንደሚባለው እነዚህ ስምምነቶች ለጊዜው የምርት ንግድን ብቻ የሚመለከቱ ናቸው። አጠቃላዩ ውል ገሃድ ከሆነ አልግሎት ሰጪውን ዘርፍና መዋዕለ-ነዋይን መጠቅለል ይኖርበታል። የካሜሩን ዓለምአቀፍ የትምሕርትና የተፈጥሮ ጥበቃ አራማጅ ድርጅት ባልደረባ ቲልደር ኩሚቺኢ ሽርክናውን በጥርጣሬ ዓይን መመልከት ከቀጠሉት ወገኖች አንዱ ናቸው።

“የኤኮኖሚ ሽርክናው ውል አሁን ባለው መልክ ከተፈረመ የ ACP-ን አገሮች የሚጠቅም አይሆንም። ግን መልሶ ቢጤንና ይበልጥ በልማት ላይ ቢያተኩር፤ ቀድሞ በዓለምአቀፉ ንግድ ላይ ከመተኮሩ በፊት ብሄራዊና የአካባቢ ንግድን ለማበረታታት ቢጣር የሚበጅ ነው የሚሆነው”

በወቅቱ የዓለም ንግድ ድርጅት እንደሚጠይቀው በአውሮፓ ሕብረት ምርቶች ላይ የተጣለው ቀረጥ ቢነሣ የአፍሪቃ አገሮች 230 ሚሊዮን ኤውሮ ገደማ የቀረጥ ገቢ ሊያጡ ይችላሉ። ይህ የብሪታኒያው ግብረ-ሰናይ ድርጅት የኦክስፋም ግምት ሲሆን በዚህ በጀርመን የኤኮኖሚ ተራድኦ ሚኒስቴር ባልደረባ ኤቪታ ሽሚግ በበኩላቸው ለሁኔታው መሻሻል ቁልፍ የሚያደርጉት በታዳጊው ሃገራት የውስጥና የአካባቢ የንግድ ልውውጥ መሻሻል ላይ ነው።

“በታዳጊዎቹ አገሮች አንዱ ወደ ሌላው ጎረቤት አገር የሚያደርገው የውጭ ንግድ አብዛኛውን ጊዜ በጣም ውስብስብ የበዛበት ነው። ሰው ወይም ነጋዴው ለደጅ ጥናት፣ ቅጾችን ለመሙላትና ባለሥልጣናትን በጉቦ ለመደለል በድንበር ላይ ብዙ ቀናት ይንገላታል። እና ግልጽነት ለማስፈንና ይህን የወረቀት ጣጣ ለማስወገድ ቢቻል ውስጣዊና የአካባቢውን ንግድ ለማሻሻል እንደሚረዳ አያጠራጥርም”

ስለዚህም የተለያዩ አማራጮችን አጣምሮ መመልከቱ የሚጠቅም ጉዳይ ይሆናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ድርድሩ ለ ACP ሃገራት ወደ አውሮፓ ገበዮች የመዝለቅ አስተማማኝ ሁኔታ ኖሮ መጠናቀቁ የግድ አስፈላጊ ነው። እርግጥ በዚህ ረገድ እስካሁን ብዙም ጭብጥ ዕርምጃ ታይቷል ለማለት አይቻልም። ስምምነቱ እንደታሰበው በቅርብ ዕውን ይሆናል ብሎ መጠበቁን አዳጋች የሚያደርገውም ይሄው ሃቅ ነው።

ከአርባ ከሚበልጡት ልዩ የንግድ አስተያየት ሲደረግላቸው ከቆዩት የ ACP ሃገራት አብዛኞቹ የሚገኙት አፍሪቃ ውስጥ ነው። የአፍሪቃ ድህነትና የልማት ዕጣ ደግሞ በዚህ በጀርመን ባለፈው ዓመት በኢንዱስትሪ ልማት የበለጸጉ ቀደምት መንግሥታት የቡድን 8 መሪዎች ጉባዔ መነጋገሪያ ጉዳይ ነበር። ጀርመን ያስተናገደችው የቡድን 8 ጉባዔ ከዓለም ኤኮኖሚ ሁኔታና ከተፈጥሮ ጥበቃ ቀጥሎ የአፍሪቃን ልማት ዓቢይ ርዕሱ ሲያደርግ አፍሪቃ ከድህነት አዙሪት እንድትወጣ መደረግ ያለበትና የሚገባው ሁሉ በተለያየ ደረጃ ተደርድሯል። ግን ፍሬ አለመስጠቱ ነው ችግሩ!

ወቅቱ ለአሥርተ-ዓመታት ያልታየ የፊናንስ ቀውስ በተለይ የበለጸጉትን መንግሥታት ከኤኮኖሚ ውድቀት አፋፍ ላይ የጣለበት ነው። ይህ ደግሞ የልማት ዕርዳታንም ሆነ የመዋዕለ-ነዋይን ፍሰት ሊገድብ የሚችል በመሆኑ በተለይ የድሃ-ድሃ የተባሉት አገሮች ለሽርክናው ውል ተጠቃሚነት በሚያበቃ ሁኔታ መዋቅራዊ ዕርምጃ ማድረጋቸውን አጠያያቂ ይደርገዋል። ጉዳዩ ከዚህ ባሻገር አጠቃላይ የዓለም ንግድ ፍትሃዊነት መስፈኑንም የሚጠይቅ ነው። ይሁንና በዚሁ ፍትሃዊነት ላይ ያለመው የዶሃው ድርድር ግብዓተ-መሬቱ አይፈጸም እንጂ ሞቷል ቢባል ብዙም ማጋነን አይሆንም።

በአውሮፓ ሕብረትና በ ACP ሃገራት መካከል አጠቃላይ የኤኮኖሚ ሽርክና ውል ለማስፈን ተይዞ የነበረው ድርድርም ፍትሃዊ አቅጣጫን መያዝ ካልቻለ እንደ ዶሃው ሆኖ ነው የሚቀረው። በሌላ በኩል ሕብረቱ በተናጠል ከታዳጊው ዓለም መንግሥታት ወይም የአካባቢ ስብስብ ጋር ስምምነቶችን ለማስፈን የሚያራምደው ፖሊሲ ለድሆቹ አገሮች ጨርሶ የሚጥቅም አይሆንም። በተረፈ እስካሁን ሊረሳ የቃጣውን ድርድር መልሶ ለማንቀሳቀስ ለጊዜው የተያዘ ቀነ-ቀጥሮ የለም። መቼና እንዴት፤ በምን ግብ ይቀጥላል፤ ጠብቆ መታዘቡ ነው የሚመረጠው።


ተዛማጅ ዘገባዎች