የአውሮፓ ሕብረትና የዕርዳታ ፖሊሲው ማከራከር | ኤኮኖሚ | DW | 29.08.2007
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአውሮፓ ሕብረትና የዕርዳታ ፖሊሲው ማከራከር

የአውሮፓ ሕብረት የሰብዓዊ ዕርዳታ ፖሊሲ የአስቸኳይና የረጅም ጊዜ የልማት ዕርዳታ አሰጣጥ ተግባሩን በሚገባ ለያይቶ ያስቀመጠ አለመሆኑን የአውሮፓ ፓርላማ ሰሞኑን በጉዳዩ ያወጣው አንድ ዘገባ አመልክቷል።

የኮሚሢዮኑ ፕሬዚደንት ባሮሶ

የኮሚሢዮኑ ፕሬዚደንት ባሮሶ

የአውሮፓ ሕብረት ምንም እንኳ በዓለም ላይ ታላቁ የልማት ዕርዳታ አቅራቢ ቢሆንም በፖሊሲው አተረጓጎም ረገድ ሲተች እርግጥ አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ለመሆኑ ታዳጊ አገሮች በምዕራቡ ዓለም የልማት ዕርዳታ እስካሁን ምን ያህል ተጠቅመዋል፤ ዕርዳታው የዕድገት መንኮራኩር ለመሆንስ በቅቷል ወይ? ይህ ዛሬ ብዙ የሚያከራክር ጉዳይ ነው። እንዲያውም በተለይ ኋላ ቀርታ ለምትገኘው ክፍለ-ዓለም ለአፍሪቃ የልማት ዕርዳታ አይበጅም የሚለው አስተያየት ባለፉት ጊዜያት በተደጋጋሚ የሚሰማ ነገር ሆኗል።

የአውሮፓ ሕብረት ባለፈው 2006 ዓ.ም. በ 2,7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ሰብዓዊ ዕርዳታ በመስጠት በዓለም ላይ ታላቁ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ለጋሽ ነበር። ሆኖም ዕርዳታው በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብን ችግር ማስታገሱ ይነገርለት እንጂ የአውሮፓ ፓርላማ በጉዳዩ ባወጣው አዲስ ዘገባ እንዳመለከተው የሰብዓዊው ዕርዳታ ዓላማ ከነበረው የበለጠ በትክክል ሊዘረዘር የሚገባው ነው። ዘገባውን ያረቀቁት ፈረንሣዊው የአውሮፓ ፓርላማ ዓባል ቲየሪ ኮርኒሌት እንዳሉት ሰብዓዊው ዕርዳታ የሚቀርብበት ጊዜና ቦታ በማያሻማ ሁኔታ ተቀምጧል ለማለት አይቻልም።
ኮርኒሌት ከሰብዓዊ ዕርዳታው ጋር በተሳሰሩ ቁልፍ መሠረተ-ዓላማዎች ላይ የሕብረቱ የበላይ አካል የአውሮፓው ኮሚሢዮን ባለፈው ሰኔ ወር አቅርቦት ለነበረው ጽንሰ-ሃሣብ የተወሰነ አመኔታ ቢሰጡትም ዘገባቸው በሕብረቱ የሰብዓዊ ዕርዳታ አያያዝ ላይ መዋቅራዊ ድክመት መኖሩን ቁልጭ አድርጎ ያስቀመጠ ነው። እንደምሳሌ በኮሚሢዮኑ የሰብዓዊ ዕርዳታ ቢሮና በሥሩ በሚገኘው የተፈጥሮ ጥበቃ ዘርፍ መካከል ተገቢው ትብብር እንደሌለ ይናገራሉ። ፈረንሣዊው እንደራሴ እንደጠቀሱት በአካባቢ አየር ለውጥ ሳቢያ የተፈጥሮ ቁጣ የሚያስከትለው ጉዳት እያደገ በመሄድ ላይ በመሆኑ የቀውስ አደጋን መቀነስ ለሚደግፉ ዕርምጃዎች በአውሮፓው ሕብረት ሰብዓዊና የልማት ዕርዳታ ተግባር በሁለቱም ዘርፎች በጀት ሊጨመር ይገባዋል።

የዕርዳታ ድርጅቶችም ቅርጽ ያለው ፖሊሲ ይሻሉ

ይህ የአውሮፓ ዋና ዋና የድንገተኛ ዕርዳታ ቡድኖች ፍላጎትም ነው። ከመንግሥት ነጻ የሆኑት አበር ቡድኖች ወደፊት ከሚቀርበው ሰብዓዊ ዕርዳታ 10 በመቶው ቀውስን ቀድሞ ለማለዘብ ወይም ለመከላከል በሚካሄዱ ተግባራት ላይ እንዲውል ይጠይቃሉ። በአካባቢ ይዞታ ሳቢያ የሚፈጠሩ ቀውሶች የሚያስከትሉትን ጥፋት ከወዲሁ የመቀነሱ ዕርምጃ አስፈላጊነት በዓለምአቀፍ ደረጃ ጎልቶ የመጣው በተለይ ከታሕሣስ 2004 የትሱናሚ መዓት በኋላ ነው። ማዕበሉ በደቡባዊው እሢያ አያሌ ሰዎችን ሲገድል እስከዛሬ አሻራው ያልተሰወረ እጅግ ከባድ የሆነ የንብረት ጥፋት አድርሶ ማለፉም የቅርብ ትውስት ነው።
ችግሩ ገና የመጪዎቹ አሠርተ-ዓመታት ፈተናም ሆኖ እንደሚቀጥል አንድና ሁለት የለውም። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ግምት አደጋውን ለመቀነስ ወጥቶ ገቢር መሆን የሚኖርበት የድንገተኛ ተግባር ስልታዊ ዕቅድ ከ 2050 በኋላ በያመቱ ወደ 300 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ያለ ነው የሚሆነው። ከአራት ዓመታት በፊት በእሢያው አካባቢ ቀድሞ አደጋን ለመለየት የሚያስችል ፍቱን የማስጠንቀቂያ ዘዴ ቢኖርና ሕዝብ ያላንዳች ዝግጅት እንዳይጠመድ ቢደረግ ኖሮ ሩብ ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ በከንቱ ባላለቀም ነበር። ይህ ትልቅ ትምሕርታዊነት አለው። ማለት በተግባር ተቀባይነትን ካገኘ!

የአውሮፓ ኮሚሢዮንም ችግሩን ተረድቶታል

እርግጥ የድንገተኛ ጊዜ ትብብር ወዶ ገብ ድርጅቶች፤ በአሕጽሮት VOICE በመባል የሚጠራው ስብስብ ተጠሪ ካትሪን ሺክ እንደሚሉት አደጋን ቀድሞ ለመከላከል የሚወጣው ገንዘብ የሰብዓዊ ዕርዳታውን በጀት የሚሻማ መሆን የለበትም። ሕይወት ለማትረፍ የተመደበ ገንዘብ ለዚያው ተግባር ሊውል ይገባዋል። ካትሪን ሺክ በሌላ በኩል እንደሚያስረዱት ይሁንና ቀውስ መከላከሉ የትምሕርት ፕሮግራሞችን ከመሳሰሉ ሌሎች የዕርዳታ ዘርፎች ሊተሳሰር የሚችል ነው። ለምሳሌ የመሬት ነውጽ በሚያዘወትርባችው አገሮች የሚኖሩ ሕጻናት ችግሩ ሲከሰት እንዴት ራሳችውን ለማዳን እንደሚሞክሩ ማስተማር ጠቃሜታ ይኖረዋል።

የአውሮፓ ኮሚሢዮን ባለሥልጣናትም የሕብረቱ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፖሊሲ መሻሻል የሚያሻው ለመሆኑ ዕውቅና መስጠት ይዘዋል። ለዚህም በቅርቡ በደቡባዊው ፔሩ ደርሶ በነበረው የመሬት ነውጽ ዓለምአቀፍ ለጋሾች ተግባራቸውን ለማቀናበር የገጠማቸው ችግር አነሳሽ ሣይሆን አልቀረም። በሰብዓዊውና በዘላቂው የልማት ዕርዳታ መካከል ልዩነት በማስቀመጡም ሆነ ከአንዱ ወደ ሌላው በመሸጋገሩ ረገድ የሕብረቱ ቢሮክራሲ ጉዳዩን እንዳከበደውም ግልጽ እየሆነ መምጣቱ አልተሰወረም። ሰብዓዊው ዕርዳታ የአጭር ጊዜ ተግባር ሊሆን ሲገባው እየተራዘመ መሄዱ በተግባር ሲታይ የቆየው ጭብጥ ሁኔታ ነው።

የብሪታኒያ ወግ-አጥባቂ የአውሮፓ ፓርላማ ዓባል ኒርጅ ዴቫ ኮሚሢዮኑን በቀውሶች ወቅት ፈጣን ዕርምጃ በመውሰድ ተግባሩ ያወድሳሉ። ሆኖም በሰብዓዊው ተግባርና በዓለምአቀፉ ልማት ረገድ ፍቱን ቅንጅት ይጎለዋል ባይ ናቸው። ዴቫ በተፈጥሮ ቁጣና ለምሳሌ ያህል የዳርፉርን በመሰለው ሰውሰራሽ ጥፋት መካከል ትልቅ ልዩነት ያደርጋሉ። በመሆኑም የአውሮፓ ሕብረት አንዱ ሊወስደው የሚችል ጠቃሚ ዕርምጃ ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ሕግጋት በሚረገጡበት ጊዜ የሆነ ማዕቀብ ለመጣል መብቃት ነው። ማመንታትም የለበትም። እርግጥ በሌላው እንደራሴ በስዊድኑ አንደርስ ቪይክማን አስተሳሰብ በየቦታው የሚደርሱ ቀውሶችን ነጣትሎ ማስቀመጡ ቀላል ነገር ላይሆን ይችላል።

ቪይካንም ቢሆን በዓለም ላይ የሚከሰተው የተፈጥሮ ቁጣ በአብዛኛው የሰውልጅ የቀሰቀሰው መሆኑን አጠያያቂ አያደርጉም። ይሁንና በአካባቢ አየር ለውጥና በዚሁ ምን ሊከተል እንደሚችል ከማጤን ይልቅ ይበልጡን ሰብዓዊ ድርጅቶች በሚቀጥሉት አሠርተ-ዓመታት ሊያጋጥማቸው በሚችለው ሁኔታ ላይ ቢተኮር ይበጃል ባይ ናችው። ለማንኛውም የአውሮፓ ሕብረት በሰብዓዊ ዕርዳታና በልማት ተግባር መካከል ቁልጭ ያለ መስመር ማስቀመጥ ይጠበቅበታል። የምግብ ዕርዳታ በሰብዓዊው ዕርዳታ ፖሊሲ ውስጥ የድንገተኛ ጊዜ ዕርምጃ ብቻ ሆኖ ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው። እንደ ዩ-ኤስ-አሜሪካ የምግብ ዕርዳታን ለረጅም ጊዜ ማቅረቡ በአንጻሩ በድሆች አገሮች ኤኮኖሚ ላይ ጎጂ ተጽዕኖ እንደሚኖረውና በተለይም ደሃውን ገበሬ እንደሚጎዳ በግልጽ የሚታይ ሆኗል።

የልማት ዕርዳታ ከናካቴው ይበጃል ወይ?

የአውሮፓ ሕብረት የዕርዳታ ፖሊሲ ፍቱን ቅርጽ መያዝ ይኖርበታል በሚባልበት በአሁኑ ጊዜ የልማት ዕርዳታ ከናካቴው ለታዳጊው ዓለም ሰፊ ሕዝብ አልበጀም፤ ሌላ መፍትሄ መገኘት ይኖርበታል የሚለው አስተሳሰብም ባለፉት ጊዜያት ከያቅጣጫው ሲሰማ ቆይቷል። ሃብታም ሃገራት የታዳጊውን ዓለም ዕድገት ለማፋጠን ከአጠቃላይ ብሄራዊ ምርታችው 0,7 ከመቶ የሚሆነውን ድርሻ ለማቅረብ ቃል ከገቡ አሠርተ-ዓመታት አልፈዋል። ግን ይህን እስከዛሬ ዕውን ያደረጉት በእጣት የሚቆጠሩ አገሮች ብቻ ናቸው። ቃልና ተግባር ተጠጥመው አልተራመዱም።

ይህም ሆኖ በሌላ በኩል የበለጸጉት መንግሥታት የልማት ዕርዳታ በአሃዝ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም። እርግጥ ይዘቱም ሆነ ተግባራዊነቱ ብዙ የተወሳሰበና የተምታታ መሆኑም ሌላው ሃቅ ነው። አንድ ነገር ግን ጨርሶ አያሻማም። ከልማት ዕርዳታው ብዙ ገንዘብ ለአቅራቢዎቹ ሃገራት ባለሙያዎች የተጋነነ ደሞዝና ለቁሳቁሳዊ ግዢ ሲባክን የተረፈው ጥቂቱ ደግሞ እፍኝ ወደማይሞሉ ወደ ተቀባዩ ሃገራት ባለሥልጣናት ኪስ ሲፈስ ነው የኖረው። የዕዳ ምሕረት አዲስ የልማት ዕርዳታ ሆኖ የታሰበበትም ጊዜ አጋጥሟል።

እንግዲህ ሰፊው የታዳጊው ዓለም ሕዝብ የሚገባውን ያህል ተጠቃሚ አልሆነም ማለት ነው። ከዚህ እንጻር የልማት ዕርዳታው አቅርቦት አልበጀም የሚለው አስተሳሰብ አዘውትሮ መሰማት መያዙ ብዙም ሊያስደንቅ አይችልም። እርግጥ ጥያቄው በዛሬው ዓለም ከመቼውም በላይ በድሃና በሃብታም በተከፈለበት ሁኔታ ታዳጊዎቹ ሃገራት ያለ ሰብዓዊና የልማት ዕርዳታ እንዴት ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ ነው። ብራስልስ ላይ ተቀማጭ የሆነው Europian Enterprise Institute የተሰኘ ተቋም ፕሬዚደንት ፔተር ዩንገን እንደሚሉት ከሆነ ሌላ አማራጭ መንገድ አይታጣም።

የልማት ዕርዳታን አጥብቀው የሚቃወሙት ጀርመናዊው ፔተር ዩንገን በቅርቡ በአክራ ዩኒቨርሲቲ ለአፍሪቃ በሚበጀው የዕድገት ለውጥ ላይ በተካሄደ ጉባዔ ክፍለ-ዓለሚቱ የሚያስፈልጋት ካፒታሊዝም ነው ብለዋል። በርሳቸው ዕምነት የልማት ዕርዳታን መቃወም ድሆች ወደተሻለ ኑሮ እንዳይሸጋገሩ መግታት አይደለም። ይልቁንም የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን ውልድ የሆነው የልማት ዕርዳታ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል ባይ ናቸው። በእርግጥም የልማት ዕርዳታ የሚሰጥበት ሁኔታና መስፈርት ከተረጂው ሕዝብ ይልቅ በራሱ በለጋሹ ጥቅም ላይ የተመሠረተ መሆኑ ዛሬ ብዙም አያጠያይቅም።
ተጠቃሚዎቹ ጥቂቶች ናቸው

ከአቅራቢዎቹ መንግሥታት አግባብ ያላችው ወይም የሚጣጣሙ የታዳጊ ሃገራት ገዢዎች ውለታቸው በዕርዳታው ይጣጣል። ዛሬ ሌላው ቀርቶ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንኳ የለጋሾቹን አቋም መደገፍና አብሮ መቆም የሚያስሽልም ነው። ይህም ዕርዳታው ሕዝቡ በሚኖረው የኤኮኖሚ ዕድገት ላይ ብዙም ትኩረት እንደማይሰጥ ያመለክታል። ከዕርዳታው ተጠቃሚው እንግዲህ በእጣት የሚቆጠሩ የከፍተኛው የሕብረተሰብ መደብ ዓባላት ሲሆኑ እንዲያውም የበለጠውን የልማት ዕርዳታ የሚያገኙት አገሮች በአብዛኛው የተዳከመ ዕድገት የሚታይባቸው ናቸው። ድህነትን በሚገባ ለመቀነስ፤ የረባ ዕድገት ለማሣየት አልቻሉም ማለት ነው።

ፔተር ዩንገን እርግጥ እንበል በድርቅ አካባቢዎች የውሃ ምንጭ መክፈትን የመሳሰሉ ጭብጥ ፕሮዤዎች በልማት ዕርዳታ መካሄዳችውን አይቃወሙም። በሌላ በኩል ግን ሕዝብን የምግብ ዕርዳታ ጥገኛ ማድረግ የነገዎቹን ድሆች የሚወልድ የማይበጅ መንገድ ነው ባይ ናቸው። ከውጭ የሚገባ የምግብ ዕርዳታ የተቀባዩን አገር የእርሻ ልማት ያዳክማል። ድሃውን ገበሬ ይበልጥ ድሃ ነው የሚያደርገው። በድጎማ የሚመረተው የአውሮፓ ሕብረት የእርሻ ውጤት በአፍሪቃ በዝቅተኛ ዋጋ ቢራገፍ አገሬው የፉክክር ብቃት እንደማይኖረው ግልጽ ነው። ታዲያ አማራጩ ምን ሊሆን ይችላል?

ጀርመናዊው የኢንዱስትሪ ተጠሪ አፍሪቃ መካከለኛ የሕብረተሰብ መደብ በማሳደግ ለረባ ዕርምጃ እንድትበቃ የካፒታሊዝም መስፋፋት የሚበጀው መፍትሄ እንደሚሆን አይጠራጠሩም። ለዚህም እንደ ምሳሌ የሩቅ ምሥራቅ እሢያ ሃገራትን ይጠቅሳሉ። ለለውጡ ወሣኙም የመሬት ስሪት ተካሂዶ የርስት ባለቤትነት ከጥቂቶች ዕጅ መውጣቱና የእርሻ ኤኮኖሚ ትምሕርት በሰፊው መዳረስ መቻሉ ነው። አፍሪቃ ከዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ትስስር፤ ከግሎባይዜሺን ሂደት መገለል የለባትም። አንድ አካሉ መሆን እንጂ! ፔተር ዩርገን ከጠቅላላው የልማት ዕርዳታ ይልቅ በዚህ መንገድ በማምራት የእሢያ ልምድ እንደሚያሳየው ድህነትን የበለጠ ለመታገል እንደሚቻል ነው የሚያምኑት። ሃሳቡ ባልከፋም ነበር። ጥያቄው ገቢር መሆን መቻሉ ላይ ነው።