የአውሮፓ ሕብረትና የኤ.ሢ.ፒ.አገሮች ድርድር | ኤኮኖሚ | DW | 24.06.2005
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአውሮፓ ሕብረትና የኤ.ሢ.ፒ.አገሮች ድርድር

የአውሮፓው ሕብረት በወቅቱ በዚሁ ስምምነት ላይ በመመሥረት ነጻ የንግድ ውል በሚሰፍንበት ሁኔታ ከያንዳንዱ የአካባቢው ቡድኖች ጋር እየተደራደረ ነው። እርግጥ ድርድሩ ተገቢውን ሚዛን የጠበቀ በመሆኑ የሚጠራጠሩት ብዙዎች ናቸው። የነጻው ንግድ ውል ከሰፈነ እስካሁን ከአውሮፓው ሕብረት አኳያ የታዳጊዎቹን አገሮች ምርቶች ወደገበዮቹ በማስገባቱ ረገድ የሚሰጠውን የአንድ ወገን የንግድ ማቃላያ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ የሚተካ ይሆናል። ይህ የዓለም ንግድ ድርጅት የጠየቀውም ለውጥ ነው።
በሌላ በኩል ከመንግሥት ቁጥጥር ነጻ የሆኑ ድርጅቶች፣ ጠበብትና አንዳንድ የአፍሪቃ፣ ካራይብ፣ ፓሲፊክ ስብስብ አገሮች የአውሮፓው ሕብረት በድርድሩ ላይ የያዘውን አቋም ይነቅፋሉ። በወቅቱ ድርድር የሚደረግበት አዲስ ውል “Economic Partnership Agreement” ”የኤኮኖሚ ሽርክና ውል” የተሰኘ ነው። የለውጡ ደጋፊዎችና አራማጆች የአንድ ወገኑ የንግድ ማቃለያ መርህ ባለፉት ሰላሣ ዓመታት እጅግ ድሃ የሆኑትን የ ACP ሃገራት ኤኮኖሚ አላዳበረም ይላሉ።
በመሆኑም የአፍሪቃ፣ የካራይብና የፓሲፊክ አገሮች ወደፊት ገበዮቻቸውን በጠነከረ ሁኔታ ለአውሮፓ ሕብረት ምርቶች መክፈት ይኖርባቸዋል። የአውሮፓ ሕብረት ውሉን ድሆቹን አገሮች ለዓለም ገበያ ተፎካካሪነት የሚያበቃ ሁነኛ መሣሪያ አድርጎ ነው የሚመለከተው። የኋላ ኋላ ሁለቱም ወገኖች የአዲሱ ሽርክና ተጠቃሚዎች ይሆናሉ የሚል ዕምነት አለው።
ይሁንና በሌላ በኩል ሃሣቡን አጠያያቂ አድርገው የሚመለከቱም አልታጡም። በሰሜናዊው ጀርመን የብሬመን ከተማ ዩኒቨርሲቲ የዓለም ኤኮኖሚ ጥናት ማዕከል ባልደረባ ወሮ/ማራይከ ሜይን ለምሳሌ የበለጸጉት መንግሥታት ድሆች አገሮች በጅምላ ገበዮቻቸውን እንዲከፍቱ ከመጫን እንዲቆጠቡ ያስጠነቅቃሉ።

ማራይከ “ይህ የአውሮፓው ሕብረትና የኤ.ሢ.ፒ. ሃገራት የንግድ አወቃቀር የተለያየ በመሆኑ በአንድ በኩል አስቸጋሪ ነው። ማለት የሕብረቱ የበላይነት ባዳጊዎቹ አገሮች የኢንዱስትሪን መውደም የሚያስከትል ችግር ሊፈጥር ይችላል። ሌላው ችግር የነዚሁ አገራት ኋላ ቀር መዋቅራዊ ይዘትና የምርት ብቃት ውሱንነት ነው። ይህ በአዲሱ የሽርክና ውሎች ውስጥ እንዴት እንደሚቀመጥ እስካሁን ግልጽ አይደለም።” ነው ያሉት።

ማራይከ ሜይን ብራስልስ ከኤ.ሢ..ፒ. አገሮች ጋር በአንድ ጊዜ በብዙዎች ጉዳዮች የያዘውን መደራደርም ትክክል አይደለም ሲሉ ተችተዋል። በነገራችን ላይ ይህ በወቅቱ ለታዳጊ አገሮች ሙሉ የዕዳ ምሕረት እንዲደረግና የልማት ዕርዳታው በእጥፍ እንዲጨምር የሚገፋፋው የብሪታኒያው የአፍሪቃ ኮሚሢዮንም አመለካከት ነው።

ይህን አስተያየት ከመንግሥት ቁጥጥር ነጻ የሆኑ የተለያዩ የአውሮፓና የአፍሪቃ ድርጅቶችም ይጋራሉ። የአውሮፓው ሕብረት የአፍሪቃ፣ ካራይብ ፣ፓሲፊኩን, ስብስብ አገሮች ነጻ ዕድገት እየገታ ነው ባዮች ናቸው። ከድርጅቶቹ መካከል በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል የፈረንሣዩ አጂር ኢሢ፣ ኦክስፋም ኢንተርናሺናል፣ “Third World Network” የተሰኘው የጋና ቡድንና ዓለምአቀፉን ኤኮኖሚ ሥርዓት የሚተቸው የጀርመን ድርጅት በአሕጽሮት ዊድ ይገኙበታል።

በጀርመኑ ድርጅት ዕምነት የሽርክናው ውል በመጀመሪያ ደረጃ የድሆቹን አገሮች ዕድገት ማስቀደሙ ግድ ነው። እነዚህ አገሮች ገበዮቻቸውን በፍጥነት እንዲከፍቱ መገደድ የለባቸውም። የድርጅቱ ባልደረባ ክላውስ ሺልደር እንደሚሉት በድርድሩ ላይ ንግግሩ በዕውነት ልማትን የማይጋፋ መሆኑን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ቅድመ-ግዴታዎች መካተት ይኖርባቸዋል። የገበዮቹ መከፈት ከልማት ዕርምጃ ጋር ተያይዞ መራመድ የሚኖርበት ጉዳይ እንጂ በጊዜ የሚገደብ መሆንም የለበትም።