የአውሮፓ ሕብረትና በጀቱ | ኤኮኖሚ | DW | 13.02.2013
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአውሮፓ ሕብረትና በጀቱ

የአውሮፓ ሕብረት በተለይም በጋራ ምንዛሪው ዓባል ሃገራት ውስጥ በተፈጠረው የዕዳ ቀውስ የተነሣ ብርቱ ፈተና ተደቅኖበት ነው የሚገኘው።

የአውሮፓ ሕብረት በተለይም በጋራ ምንዛሪው ዓባል ሃገራት ውስጥ በተፈጠረው የዕዳ ቀውስ የተነሣ ብርቱ ፈተና ተደቅኖበት ነው የሚገኘው። ይሄው አጠቃላይ ሁኔታ ደግሞ በሕብረቱ የበጀት ይዞታ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጽዕኖ ማሳደሩ አልቀረም። ሆኖም የአውሮፓ ሕብረት ዓባል መንግሥታት ባለፈው ሣምንት መጨረሻ ባካሄዱት የመሪዎች ጉባዔ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ በሚቀጥሉት ሰባት ዓመታት በጀት ላይ ከስምምነት ለመድረስ በቅተዋል።

አስታራቂ መፍትሄ ሆኖ ስምምነት የተደረገበት ከ 2014 እስከ 2020 የሚዘልቅ በጀት 960 ሚሊያርድ ዶላር የሚደርስ ሲሆን ይህም ቀደም ካለው የረጅም ጊዜ በጀት ሶሥት በመቶ ያነሰ መሆኑ ነው። የሕብረቱ ኮሚሢዮን የጠየቀው የ 1,4 ቢሊዮን ኤውሮ በጀት ነበር። ታዲያ ከዚህ አንጻር ስምምነቱ አግባብ አለው ወይስ እንዲያው ለዕርቅ ሲባል የተደረገ አስታራቂ መፍትሄ ነው? የሚል ጥያቄን ቢያሰነሣ ብዙም አያስደንቅም። ብዙ ታዛቢዎች አዲሱ በጀት የሕብረቱን አስፈላጊ ወጪ ለመሸፈን በቂ እንደማይሆን ነው ከወዲሁ የሚናገሩት።

ስምምነቱ በመንግሥታቱ ዘንድ ሕጋዊ አሳሪነት ቢኖረውም በሌላ በኩል ዓባል ሃገራቱ የሚከፍሉት ገንዘብ ያነሰ መሆኑ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ሁሉ ችግርን የሚፈጥር ወይም እጥረትን የሚያስከትል እንደሚሆን አንድና ሁለት የለውም። መንግሥታቱ እንከፍላለን ያሉት ገንዘብ በተጨባጭ በ 908 ሚሊያርድ ኤውሮ የተወሰነ ሆኖ ይገኛል። ይህን መሰሉ ሁኔታ ደግሞ ባለፉት ጊዜያትም በሕብረቱ የታቀደ ወጪ እንዳይፈስ መሰናክል ነበር። ሁኔታው ወደፊትም የሚቀጥል ነው የሚመስለው። ይህም ሆኖ ግን የሕብረቱ ሸንጎ ፕሬዚደንት ሄርማን-ፋን-ሮምፑይ ውጣ ውረድ የበዛውን ድርድር ውጤት በእርካታ ነው የተቀበሉት።

«መለስ ብዬ ሳስብ በጠቅላላው የድርድር ሂደት በጉዳዩ ያለንን ትኩረት ባለመሳታችን ደስተኛ ነኝ። ሌላው ቀርቶ ከባድ በሆነ የኤኮኖሚ ሁኔታ እንኳ የእርጋታና የዕድገት መሠረታዊ ዓላማችንን ለመጠበቅ ችለናል»

ድርድሩ እርግጥ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ቀላል አልነበረም። በሕብረቱ ውስጥ የሰጭና የተቀባይ ሃገራት ቅራኔ ጥልቅ መሆኑ በተደጋጋሚ ሲታይ ቆይቷል። የበጀቱ ክፍያ ከዚህ ቀደም በተለመደ መልኩ ይቀጥል ወይስ አዲስ መልክ ይያዝ ብዙ ማነጋገሩ አልቀረም። የጀርመኗ ቻንስለር ወሮ/አንጌላ ሜርክል እንደጠቀሱት በመጨረሻ የተገኘው ውጤት ሁለቱን ወገን ያስታረቀ ነበር።

«ስምምነቱ እጅግ አስፈላጊ ነበር። ምክንያቱም ይህ ስምምነት አውሮፓ ውስጥ በሚቀጥሉት ዓመታት ጠቃሚ የሆኑ ፕሮዤዎችን ለማራመድ የውሣኔና የማቀድ ብቃት ስለሚሰጠን ነው»

ይህ እርግጥም የኤኮኖሚ ዕድገትንና የሥራ መስኮችን በመክፈት ረገድ ወሣኝነት አለው። ለመዋዕለ ነዋይ አድራጊዎች የዕቅድ ዋስትና ማረጋገጥም ግድ ነው።

የበጀቱ ስምምነት ምንም እንኳ ገንዘቡ ከበፊቱ ቢቀንስም እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ደከም ላሉት የደቡብና የምሥራቅ አውሮፓ ሃገራት የሚሰጠውን የእርሻ ድጎማና የመዋቅራዊ ግንባታ ዕርዳታ ዓቢይ ማተኮሪያው እንዳደረገ የሚቀጥል ነው። ሰፊ የዕርሻ ልማት ይዞታ ያላቸው ስፓኝ፣ ኢጣሊያና ፈረንሣይ ይህ ጥቅማቸው እንዳይነካ አጥብቀው ሲታገሉ የፈረንሣዩ ፕሬዚደንት ፍራንሱዋስ ኦላንድ እንዲያውም በጉባዔው ላይ ባሰሙት ንግግር ውጤቱን የራሳቸው የትግል ፍሬ አድርገው አቅርበውታል።

«የማሕበረሰቡ የጋራ ፖሊሲ፤ የእርሻ ፖሊሲው፤ የትስስር ፖሊሲው እንዲቀጥል ነው የፈለግሁት። እንደምታውቁት የእርሻው ፖሊሲ ለፈረንሣይ ትልቅ ክብደት አለው»

ኦላንድ ይህን የሚሉት እርግጥ ፈረንሣይ ጥቅም ስላላት ብቻ ሣይሆን የእርሻ ልማት አውሮፓ ውስጥ ወደፊት ጥሩ ዕድል እንዳለው ስለሚያምኑም ነው። ኦላንድ ከስምምነቱ በኋላ ባሰሙት ንግግር ከ 900 ሚሊያርድ ኤውሮ በታች በጀት የጠየቁትን ዋነኛ የሃሣብ ተቀናቃኛቸውን የብሪታኒያውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮንን ወረፍ ሳያደርጉም አላለፉም። አስታራቂው ሃሣብ ከተጨባጩ ሁኔታ አንጻር ጥሩ መፍትሄ መሆኑን ነው ያመለከቱት። ይሁንና ካሜሮንም ቢሆን ራሳቸውን አሸናፊ አድርገው ለማቅረብ ከመሞከር ወደ ኋላ አላሉም።

«የብሪታኒያ ሕዝብ የሰባት ዓመቱን በጀት ለመጀመሪያ ጊዜ ለማስቀነስ በመቻላችን ኩሩ እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ»

በሌላ በኩል የሕብረቱ የበጀት ስምምነት ባለፈው አርብ ገና በይፋ ሳይገለጽ ነው የአውሮፓን ፓርላማ ተቃውሞ ያስከተለው። ስምምነቱ እንዲጸና በቅድሚያ በአውሮፓ ፓርላማ መጽደቅ ሲኖርበት የሽትራስቡርጉ ም/ቤት ግን ስምምነቱን በቬቶው ሊሽር እንደሚችል አስጠንቅቋል። የአውሮፓው ፓርላማ ፕሬዚደንት ጀርመናዊው ሶሻል ዴሞክራት ማርቲን ሹልስ ሕብረቱ የ 960 ሚሊያርድ ኤውሮ ወጪ እንደሚያስፈልገውና ግን አሁን 52 ሚሊያርድ ኤውሮ እንደሚጎል ሲገልጹ ስምምነቱ በፓርላማው ተቀባይነት እንደማያገኝ ነው ያስገነዘቡት። ሹልስ ከጀርመን ቴሌቪዥን ጣቢያ ZDF ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ስምምነቱ እንዴት የብዙሃን ድጋፍ ሊያገኝ እንደሚችል አይገባኝም ብለዋል።

« የ 960 ሚሊያርድ ኤውሮ ስምምነት እንደሚደረግ እኔም አውቃለሁ። ይህ የሰባት ዓመት በጀት ነው። ግን ልክ የአንድ ዓመት ወጪ እንደሆነ መስሎ ይቀርባል። እንግዲህ 960 ሚሊያርዱ ኤውሮ የሰባት ዓመት ወጪ ነው። ሆኖም የሚያሳዝነው በተጨባጭ የሚቀርበው ገንዘብ 908 ሚሊያርድ መሆኑ ላይ ነው። እንግዲህ የ 52 ሚሊያርድ ኤውሮ ጉድለት እንደሚኖር መታወቅ አለበት። እናም እንደ ፓርላማው ፕሬዚደንት ለመናገር የምፈልገው ይህ የም/ቤቱን ድጋፍ ጨርሶ እንደማያገኝ ነው»

ማርቲን ሹልስ ስምምነቱን እንዲያውም እንደማሞኘት አድርገው ተመልክውታል።

«እዚህ እየተካሄደ ያለው አታላይ ድርጊት ነው። የተወሰነው ለ 960 ሚሊያርድ ኤውሮ ወጪ የ 908 ሚሊያርድ ኤውሮ ገቢ ነው። ይህ ደግሞ ኪሣራን የሚያመለክት ሲሆን በብራስልስ የተከለከለ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። ስለዚህም ፓርላማው አይተባበርም። በወቅቱ በዓባል ሃገራቱ በብዙ ጥረት ልንቀንሰው የሚገባ ብዙ ኪሣራ አለብን። የያዝነው 2013 ዓ-ም የሕብረቱ በጀት ራሱ 16 ሚሊያርድ ኤውሮ ኪሣራ የተጫነው ነው። እና ይባስ ብሎ አሁን 52 ሚሊያርድ ከታከለበት ይህን ጤናማ ፖሊሲ አድርጌ አልመለከተውም»

የጀርመኗ ቻንስለር ወሮ/አንጌላ ሜርክል በበኩላቸው ከአውሮፓ ፓርላማ ጋር በሁለት ጠቃሚ ነጥቦችለመቀራረብ እንደሚሹ አመልክተዋል። ከዚሁም አንዱ ጥቅም ላይ ያልዋለን በጀት ወደተከታዩ ዓመት ማሸጋገርና መጠቀም መቻል ነው። ይህ ቀደም ሲል የአውሮፓ ፓርላማ ጥያቄ እንደነበርም ይታወሳል። ጀርመን ለሕብረቱ በሚቀርበው የዓባል ሃገራት መዋጮ ታላቋ ባለድርሻ ስትሆን እስካሁን ስራ ላይ ሳይውል የተረፈው ገንዘብ እንዲታሰብላት ታደርግ ነበር። ስለዚህም ከዚህ አንጻር በፓርላማው አቅጣጫ የተሰነዘረው አስታራቂ ሃሣብ ጠቃሚና ክብደት የሚሰጠው ነው። በነገራችን ላይ ጀርመን ለአውሮፓ ሕብረት የምታቀርበው የበጀት መዋጮ ድርሻ ከሁለት ዓመት በፊት 19 ሚሊያርድ ኤውሮ ገደማ ይጠጋ ነበር።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 13.02.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17cyu
 • ቀን 13.02.2013
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/17cyu