የአውሮፓ ህብረት የስደተኞች ፖሊሲና ጀርመን | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 15.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮፓ ህብረት የስደተኞች ፖሊሲና ጀርመን

በ2015 ብዙ ስደተኛ ወደ አውሮፓ ከገባ ወዲህ በአንዳንድ ሃገራት የደረሰውን ጫና ለማቃለል የአውሮፓ ህብረት በጀመረው ጥረት ቀጥሏል።ይሁንና የህብረቱ አባል ሃገራት ችግሩን ለመፍታት በሚታቀዱትና በሚሰነዘሩት ሃሳቦች ላይ ተመሳሳይ አቋም አለመያዛቸው መፍትሄውን አጓታል ። ጀርመን ደግሞ ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ይረዳል ያሉችውን እርምጃ ወስዳለች ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:25
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:25 ደቂቃ

የአውሮፓ ህብረትና የጀርመን የስደተኞች ፖሊሲ

በተገባደደው በጎርጎሮሳውያኑ 2015 ከ2ተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ በብዛት ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የተባለ ስደተኛ ወደ አውሮፓ መጥቷል ። በዚህ ጊዜ ውስጥም ከ900 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ ክፍለ ዓለሙ መግባታቸው ተነግሯል። ከመካከላቸው ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ጥገኝነት የጠየቁት በጀርመንና በሃንጋሪ ነው ። በስዊድን በኢጣልያና በኦስትሪያም በርካታ ስደተኞች ተገን ጠይቀዋል ። አንዳንድ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ወደ ሃገራቸው የመጣው ስደተኛ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ሌሎች ሃገራት እንዲወስዱላቸው መጠየቃቸውን ቀጥለዋል ። ህብረቱ ከዚህ ቀደም ግሪክ ኢጣልያና ማልታን በመሳሰሉ ስደተኞች በብዛት በሚገቡባቸው ሃገራት ያሉ ስደተኞችን አባል ሃገራት እንዲከፋፈሉ ቢያቅድና ቢወስንም ሂደቱ እንደተጓተተ ነው ። በሌላ በኩል ህብረቱ ሰዎች በብዛት በሚሰደዱባቸው ሃገራት የልማት እርዳታዎችን አጠናክሮ በመስጠት ለስደት መንስኤ የሆኑ ችግሮችን የመከላከል እቅድም አለው ። ይሁንና እነዚህን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ስብሰባዎች ና ንግግሮች ቢካሄዱም ፈጣን እርምጃዎች ሲወሰዱ ግን አልታየም ። ይህን የመሳሰለው ቸልተኝነት በእጅጉ እየተተቸ ነው። አባል ሃገራት የሚቀርቡላቸውን የተለያዩ የትብብር ጥሪዎች ጆሮ ዳባ ልበስ ማለታቸውና ና የሚወስዷቸው እርምጃዎችም መዘግየታቸው የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ጌርድ ምዩለር እንዳሉት አሳፋሪ ሆኗል ።በርሳቸው አስተያየት ከአሁን በኋላ ችግሩን ለመግታት ተጨማሪ ጊዜ መባከን የለበትም ።
« ከአሁን በኋላ ተጨማሪ ጉባኤዎች ንግግሮችና ውይይቶች አያስፈልጉንም ።ተግባራዊ እርምጃ መውሰድ ነው ያለብን

Gerd Müller Bundesminister für wirtschaftliche Zusammenarbeit und Entwicklung

ጌርድ ምዩለር

።የላምፔዱዛው አሳዛኝ እልቂት ከደረሰ ከሁለት ዓመት በኋላ አውሮፓውያን ለሰደተኞችም ሆነ ቀውስ ውስጥ ለሚገኙ ሃገራት የተጨበጠ ነገር አለማድረጋችን አሳፋሪ ነው ። ለምሳሌ ሊባኖስ ና ዮርዳኖስ የሚገኙ የስደተኞች መጠለያዎችን ስንመለከት እጅግ አስደንጋጭ ነው ። በዚህ የተነሳም ሰዎችን በህይወት ለማቆየት እንዲቻል በመጀመሪያ ደረጃ ለዓለም ዓቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ እርዳታ መስጠት ይገባል ። ጀርመን ብሪታንያና ኖርዌይ በየካቲት ወር ለንደን ውስጥ አንድ ጉባኤ ያካሂዳሉ ።ከአውሮፓ የበለጠ ትብብር እንፈልጋለን ።»
አውሮፓውያን ይህን የጋራ ችግራቸውን በጋራ ለመፍታት ተባብረው የመሥራታቸው አስፈላጊነት ተደጋግሞ የሚወሳ ጉዳይ ነው ። ባለፈው ሳምንት የ28 ቱ የህብረቱ አባል ሃገራት የልማትና ተራድኦ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ከተነሱት ጉዳዮች ውስጥ ከዚህ ቀደም የተላለፉት ውሳኔዎች ወደ ተግባር የሚተረጎሙበት መንገድ ይገኝበታል ። ይህም ለስደተኞች ቀውስ መፍትሄ ተብለው የቀረቡትና በማልታ የተካሄደው የአውሮፓ ና የአፍሪቃ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተደረሱባቸውን ውሳኔዎች ያካትታል ።የቀድሞ የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ የህዝብ እንደራሴ ምዩለር በብራሰልስና በሌሎች የአውሮፓ ህብረት ተቋማት ለሚካሄዱ ረዥም ጊዜ የሚወስዱ ውይይቶች አዲስ እንዳይደሉ ይናገራሉ ። ሆኖም ይላሉ ምዩለር አውሮፓውያን ሰዎችን ከሞት ለማትረፍ ሊወሰዱ በሚገባቸው እርምጃዎች ላይ ፈጥኖ ከመንቀሳቀስ ይልቅ የገንዘብ ተቋማትን ለማዳን ሲረባረቡ ነው የሚታዩት ።
«አንድ በጣም ግልጽ እንዲሆን የምፈልገው ነገር ።ይህ ከሰብዓዊ እልቂት ጋር አብሮ የሚሄድ መዋቅር አይደለም ።ጉዳዩ ስለ ባንኮች አይደለም ፤ ለባንኮች ጉዳይ ቢሆን መጠነ ሰፊ እና እጅግ ፈጣን እርምጃ እንወስድ ነበር ።የሰው ልጆችን ህይወት ለሚመለከት ጉዳይ ተመሳሳዩ እርምጃ እንዲወሰድ መመኘት ብቻ ነው የምንችለው ።»
ለዚህም ሶሪያውያን በተጠለሉባቸው የስደተኞች ካምፖች የሚታየውን አሳዛኝ ሁኔታ በምሳሌነት የሚያነሱት ምዩለር መፍትሄ ያሉትንም ጠቁመዋል ።
«ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ሶሪያውያን በሚገኙባቸው የስደተኞች መጠለያዎች ውስጥ 100 ሺህ የሚሆኑ ህፃናት በቆሻሻ ፕላስቲኮች ላይ ተወልደዋል ።ይህ የሰዎች በህይወት የመኖር ጥያቄ ነው ።ስለዚህ አሁን በመጨረሻ ውጤት ላይ መድረስ አለብን ። በበኩሌ ከዛሬ 2 ዓመት አንስቶ እንደምለው 28 ቱን የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የሚያስተባብር ብቃት ያለው

የአውሮፓ ህብረት የስደተኞች ጉዳይ ኮሚሽነር እንዲወከል ጥሪ አቀርባለሁ ። ከአውሮፓ በኩል ደግሞ ለችግሩ ማቃለያ ለመሠረተ ልማትና ለስደተኞች እርዳታ የሚውል ገንዘብ መወረት ይገባናል ። ከዚህ በተጨማሪም እያንዳንዱ ሃገር የራሱን የቤት ሥራ መወጣት ይኖርበታል ። »
ምዩለር ከዚህ ሌላ ዓለም ዓቀፉን የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን UNHCR ን አብነት ያደረገ የአውሮፓ ህብረት የስደተኞች ጉዳይ ድርጅት እንዲቋቋምም ሃሳብ አቅርበዋል ። ይህ እንዲሆን የሚጠይቁት የጀርመን ክርስቲያን ሶሻል ህብረት በጀርመንኛው ምህፃር CSU ፓርቲ ፖለቲከኛ ምዩለር የአውሮፓ ህብረት ሊያስብባቸውና ሊዘጋጅባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች ውስጥ በዚህን መሰሉ እርዳታ የተሻለ ቦታ እንዲኖረው ማድረግ መሆኑን ያይጠቁማሉ ። ከዚህ ሌላ ውሳኔዎች ተግባራዊ መሆን አለመቻላቸውም ሊጤን ይገባል ይላሉ ።
« የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን በምህፃሩ UNHCR የተባበሩት መንግሥታት የህፃናት መርጃ ድርጅት UNICEF እንዲሁም የዓለም የምግብ ድርጅት በምህፃሩ WFP ሥራቸውን በጥሩ ሁኔታና በአግባቡ ያከናውናሉ ። ሆኖም ከዚሁ ጋር መታሰብ ያለበት ለምንድነው በተለያዩ ጊዜያት ቀውሶች ሲከሰቱ አውሮፓ በራሱ ተቋማት ፈጣንና ወሳኝ እርምጃ የማይወስደው ?።በተለያዩ ጊዜያት ከባድ የተፈጥሮ አደጋዎች ፣ኤቦላን የመሳሰሉ ወረርሽኞች ሊከሰቱ ይችላሉ ።አሁን ደግሞ ትልቁ ፈተናችን የሆነውና ለሚቀጥሉት አሥርት ዓመታት፣ ወይም ቢያንስ ቢያንስ በመጪዎቹ ጥቂት ዓመታትም የሚዘልቀው የስደተኞች ቀውስ ገጥሞናል ።እናም የአውሮፓ ህብረት እንዴት ነው የተሻለ ቦታ የሚይዘው የመሪዎቹስ ውሳኔዎች ጥቅም ምንድነው? የሚሉትንን ጥያቄዎች ማንሳት አለብን ። »
ምዩለር በምሳሌነት ያነሱት በተወሰኑ አውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ውስጥ የሚገኙ 160 ሺህ ስደተኞችን ለመከፋፈል የተደረሰበትን ውሳኔ ነው ።ከሶስት ወራት በፊት በይፋ ውሳኔ የተሰጠበት ይህ ጉዳይ እስካሁን ድረስ ተግባራዊ አልሆነም ።ከ4 ሳምንት በፊት የአውሮፓ መሪዎች ከአፍሪቃ መሪዎች ጋር ወደ አውሮፓ የሚደረግ ስደትን ማስቆም በሚቻልበት መንገድ ላይ ተነጋግረው ውሳኔዎችንም አሳልፈዋል ። በዚሁ መሠረት የጀርመን መንግሥትም የስደትን መንስኤ ከምንጩ ለማድረቅ ፣ሰዎች በብዛት ከሚሰደዱባቸውና የስደተኞች መተላለፊያ ከሆኑ ሃገራት መንግሥታት ጋር ተባብሮ የመሥራት ጥረት ጀምሯል ። የስደት መንስኤ የሆኑ መሠረታዊ ችግሮችን መከላከል የሚያስችል መላ ለመፈልገ ሚኒስትር ምዩለር ወደ ኤርትራ ሄደዋል ።በአሁኑ ጊዜ ወደ አውሮፓ በብዛት ከሚሰደዱት ህዝቦች መካከል ኤርትራውያን ከሶሪያ ቀጥሎ ሁለተኛውን ደረጃ ይይዛሉ ። ምዩለር ትናንት ካይሮ ግብፅ ሆነው እንደተናገሩት የጀርመን መንግሥት የኤርትራውያንን ስደት ለማስቆም ፣ በኤርትራ የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል

ስደተኞችም ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ይፈልጋል ። ይህም አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ከመሳሰሉ ዓለም ዓቀፍ የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ከባድ ትችቶች ተሰንዝሮበታል ። ዜጎችን ለሚጨቁን ሰብዓዊ መብቶችን ለማያከብር ና ለስደትም ለሚዳርገው ለኤርትራ መንግሥት እገዛ ማድረግ ፍፁም ተቀባይነት አይኖረውም ሲሉም የኤርትራውያን የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ይከራከራሉ ። ሚኒስትር ምዩለር በበኩላቸው የእገዛው ዓላማ መንግሥትን ሳይሆን ሰዎችን መርዳት ነው ይላሉ።
« ትብብር ማለት በነዚህ ሃገራት ያሉትን ሁኔታዎች ተቀብያለሁ ማለት አይደለም ። ከዓለማችን ሃገራት በሁለት ሶስተኛው ሃሳብን በነፃ የመግለፅ መብት አይከበርም ። ይሁንና ሰዎችን መርዳት ይገባናል ። ለዚህም ነው ወደ ኤርትራ ሄጄ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ለምን ሃገሪቱን ለቀው ወደ አውሮፓ እንደሚሰደዱ ከሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ጋር የምወያየው ።ርግጥ ነው ስለ ሃገሪቱ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ማንሳታችን አይቀርም ። ከአውሮፓ ህብረት ጋር ደግሞ በሃገሪቱ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉና ወደፊትም ለወጣቱ ምን ማድረግ እንደሚቻል እንወያያለን ።
ምዩለር እንደሚሉት መሥሪያ ቤታቸው ህዝቡን ለመርዳት ያሰበው ከሙስና በፀዱ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች አማካይነት ነው ።
«አፍሪቃ 54 ሃገሮች ያሉት ክፍለ ዓለም ነው ። ስለ ችግሩ መሪዎቹ የሚነግሩንን ብቻ ሰምተን ጉዳዩ ን እዚያ አንተወውም ። ሥልጣኑን በሙሉ ጠቅለው የያዙና ጭካኔ በተሞላበት መንገድና አለአግባብም የሚጠቀሙበት መሪዎች አሉ ። የኛን መሥፈርት የማያሟሉ መሪዎች አሉ ። ያም ሆኖ ህዝቡን ለመርዳት ቆረጠናል ። ስለዚህ የጀርመን የልማት ተራድኦ መሥሪያ ቤት ሁኔታዎችን ለማሻሻል በተለይ ከሃገር በቀል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር ይሠራል ። እዚህ ላይ የኔ መመሪያ ሙስና ባለበት አሠራር ውስጥ ገንዘብ አይሰጥም የሚል ነው ። »
በምዩለር አባባል ወደፊት ከፍተና ዋጋ የሚያስከፍሉ ችግሮች ውስጥ ላለመግባት ከአሁኑ ወሳኝ እርምጃዎችን መውሰድ ይጠቅማል ።እንደ ምዩለር ከአፍሪቃ ጋር የሚደረግ ትብብር እንዲሁም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ የሚወሰዱ የጋራ እርምጃዎች የጋራ ጥቅምን ያስገኛሉ ። ይህ ካልሆነ ግን ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ማግኘቱ አስቸጋሪ ይሆናል ።
«ይህ የመጀመሪያ እርምጃ ነው ።መሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልገናል ።ለወደፊቱ የልማት ትብብር ትኩረት ካልሰጠን ና ራሳችንን ለማታለል ትንሽ ነገር እየወረወርን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በዚህ መልኩ እንዲሰራ ከፈለግን ለተግዳሮቶቻችን መፍትሄ አናገኝም ። »

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic