የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እጩ ፕሬዝዳንት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 01.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን እጩ ፕሬዝዳንት

የአውሮፓ ሕብረት መሪዎች የቀድሞውን የላክሰምበርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዦን ክሎድ ዩንከርን ለሕብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንትነት አጭተዋል ። የዩንከር መታጨት ከብሪታኒያ በኩል ተቃውሞ ገጥሞት ነበር ።

የአውሮፓ ሕብረት ዋነኛ ተቋም የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን፣ በማናቸውም ቦታ የህብረቱን ጥቅሞች ማስጠበቅ ዐብይ ተግባሩ ነው ።የኮሚሽኑ የበላይ ፕሬዝዳንቱ ሲሆን ፣ የህብረቱን አዳዲስ ህጎች ማርቀቅ የህብረቱን መርሆች በሥራ ማስፈጸም እና ህብረቱ የሚሰጣቸውን እርዳታዎች መቆጣጠር ከተግባራቱ ይደመራሉ ።ፕሬዝዳንቱ የሚመረጠውም በ28ቱ የህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች ነው ። የፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመን 5 ዓመት ነው ። የመሪዎቹ እጩ ፕሬዝዳንት ሥራውን የሚረከበው የህብረቱ ፓርላማ አባላት ሹመቱን ሲያፀድቁ ብቻ ነው ።የአሁኑ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሆሴ ማኑዌል ባሮሶ የሥልጣን ዘመን እጎአ በህዳር 2014 ያበቃል ። ባለፈው አርብ ብራሰልስ ቤልጂግ ውስጥ የተሰበሰቡት የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት መሪዎች ባሮሶ ሲወርዱ የሚተኩዋቸውን ፕሬዝዳንት አጭተዋል ። መሪዎቹ የቀድሞውን የላክሰምበርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዦን ክሎድ ዩንከርን በ26 የድጋፍና በ2 የተቃውሞ ድምፅ ለዚህ ሃላፊነት አጭተዋል ። የዩንከርን እጩነት የተቃወሙት የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ኬምረን እንዲሁም የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን ነበሩ ። ዩንከር መታጨታቸውን በየአጋጣሚው ሲቃወሙ የቆዩት ኬምረን ዩንከር ከተመረጡ በኋላ እንኳን ደስ አለዎ ቢሏቸውም የተቃውሞአቸውን ምክንያትም ዘርዝረው ተናግረዋል ።

«ውጤቱን መቀበል አለብን ። ብሪታኒያ ሁሌም እንደምናደርገው ብሔራዊ ጥቅሞቿን ለማስጠበቅ አሁን ከአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ጋር መሥራት አለባት ።ሆኖም ፍፁም ግልፅ ላደርግላችሁ ዕለቱ ለአውሮፓ መጥፎ ቀን ነው ። የብሔራዊ መንግሥታትን አቋም ፣የብሔራዊ ፓርላማዎችን ስልጣን ዝቅ የማድረግ አደጋ ላይ ይጥላል ። በተጨማሪም ለአውሮፓ ፓርላማ አዲስ ሥልጣን ያስረክባል ።»

ብሪታንያ የምትቃወመው የብሔራዊ መንግሥታትን ሥልጣን ቀምቶ ለማጠቃለል የሚሻው የአውሮፓ ፓርላማና የዚሁ ፖለቲካ አራማጅ የሆኑት ዩንከር ያራምዱታል የምትለውን ጊዜ ያለፈበትን ዓይነት የፌደራል አወቃቀርን እንዲሁም ዩንከር የሥልጣን ጥም ያላቸው ስው ናቸው ስትል ነው ። ጠቅላይ ሚኒስትር ኬምረን ዩንከር የአውሮፓ ህብረትን በተሃድሶ ለውጥ ለማሻሻል በጎ ፈቃዱም ሆነ ጥበቡ የላቸውም ሲሉም ያጣጥሏቸዋል ። ይህ ደግሞ የሚያስከትለው መዘዝ ይኖራል ሲሉም አስጠንቅቀዋል ።የህብረቱን አባል ሃገራት ይበልጥ ለማቀራረብ እየተባለ የሚከናወነው ብሔራዊ ሥልጣናችንን እየተጋፋ ነው የሚሉት ኬምረን እንደገና ከተመረጡ ሃገራቸው በህብረቱ አባልነት መቀጠል ያለመቀጠሏን ህዝባቸው እጎአ በ2017 ድምፅ በመስጠት እንዲወስንበት እንደሚያደርጉ ካስታወቁ ቆይተዋል። የብሪታኒያ ወግ አጥባቂ ፓርቲ ፖለቲከኛ ማርቲን ካላን ለፕሬዝዳንትነት የታጩት ዩንከር አንዳችም ለውጥ የማያደርጉ ከሆነ ብሪታኒያውያን አሉታዊ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ ይላሉ ።

« እንደሚመስለኝ አሁንም እንደገና የብሪታንያውያን አመለካከቶች ፣ የብሪታኒያውያን ጥቅሞች ፣የብሪታኒያ ድምፅ ሰጭዎች ከግምት ውስጥ አልገቡም የሚል ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ ። ብዙውን ነገር የሚወሰነው እርሳቸው የሚያከናውኑት ነው ። በአውሮፓ ተሃድሶ ለማድረግ ፣ ህዝቡ በአውሮፓ የሚይፈልገውን ለማስቆም ተዘጋጅተዋል ?ተሃድሶን ትኩረቱ ያደረገ አስተማማኝ የኤኮኖሚውም አቅጣጫ ለመከተልስ አስበዋል ? ያን ካደረጉ በህዝበ ውሳኔው ህዝቡ የአውሮፓ ህብረትን ሊደግፍ ይችላል ። ያን ካላደረጉ ግን ተቃራኒው ነው የሚሆነው »

ዩንከር የታጩበት ምክንያትና ከአሁን በኋላም ማከናወን የሚገባቸው የብሪታንያ ፖለቲከኞችን ሲያነጋገር ። ከፈረንሳይ በኩል ደግሞ የርሳቸው መመረጥ አዎንታዊ አስተያየት ነው የተሰጠው ።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ዩንከር የታጩት በህብረቱ የምርጫ መስፈርት መሰረት መሆኑን ያስረዳሉ ።

«ፈረንሳይ እንደምታየው ከሆነ ጉዳዩ የአንድን ሰው መምረጥ የሚመለከት አይደለም የፖለቲካዊ ሂደቶች አመክኖአዊ ውጤት ነው ።ጉዳዩ የሚመለከተው ለአሁኑ ሥልጣን የታጩትን ሰው የመደገፍ ያለመደገፍ አይደለም ። ከዚህ አመክንዮ ያደረሰው የአውሮፓ ፓርላማ የምርጫ ዝግጅት ነበር ። እዚህም ላይ በምርጫ ውጤት የመሪቱን ቦታ የሚይዝ ፓርቲ ለአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንትነት እጩ ማቅረብ እንደሚችል በግልፅ የሚጠቁም ነበር ። ብልጫ ካገኘው የአውሮፓ ህዝባዊ ፓርቲ ከዣን ክሎድ ዩንከር የተሻለ ሰው አልተገኘም ።»

ኦሎንድ ለማስረዳት እንደሚሞከሩት የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት የሚሆነውን ሰው የሚወስነው የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ምርጫ ውጤት ነው ። ዦን ክሎድ ዩንከር ባለፈው ወር በተካሄደው የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ምርጫ አብልጫ ድምፅ ያገኘው የመሃል ቀኙ « የአውሮፓ ህዝቦች ፓርቲ » ግንባር ቀደም እጩ ነበሩ ። ይህም ለኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ሃላፊነት ለመታጨታቸው ዐቢዩ ምክንያት ነው ።በምርጫው ሂደት ከብሪታኒያ በኩል የተሰነዘረውን ስጋት የኔዘርላንድና የስዊድን መሪዎችም ተጋርተው ነበር ። በመጨረሻ ላይ ግን እንደ ጀርመንዋ መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ሁሉ እነርሱም ለዩንከር ድምፃቸውን ሰጥተዋል ። ሜርክል የህብረቱን አባል ሃገራት ይበልጥ ለማቀራረብ በሚከናወነው ተግባር ከሃገራት የሚጠበቀው በአቅማቸው መጠን እንጂ ከኣቅማቸው በላይ መራመድ እንዳይደለ አስረድተዋል ።

« እዚህ ላይ ግልፅ ሆኖ የታየው በአውሮፓ ህብረት ውል መሠረት ይበልጥ የተቀራረበ ህብረት ቢባልም ይህን ለማሟላት ሁሉም ሃገሮች በእኩል ፍጥነት መራመድ አለባቸው ማለት አይደለም »

ለአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንትነት የታጩት ዦን ክሎድ ዩንከር እጎአ እስከ 2013 ድረስ የትንሽቷ ሃገር የላክሰምበርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ ። በዚሁ ሃላፊነት ለ18 ዓመታት አገልግለዋል ።ከአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት በዚህ ሃላፊነት ላይ ለረዥም ጊዜ በመቆየት ዩንከር ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛሉ ። ከጠቅላይ ሚኒስትረነታቸውም በፊት ለ20 ዓመታት የገንዘብ ሚኒስትር ነበሩ ። ዩንከር የአውሮፓ የጋራ መገበያያ ገንዘብ ዩሮ ስራ ላይ እንዲውል ባበረከቱት አስተዋፅኦም ስማቸው ይነሳል ።በዩሮ የሚገበያዩ አባል ሃገራትን ያቀፈውን ማህበር ለ8 ዓመታት በቋሚ ፕሬዝዳንትነት መርተዋል ።

ሉክስምበርግ ከሰራተኛ ማህበር መሪ የተወለዱት ዩንከር የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ቤልጂግና ሃገራቸው ሉክስምበርግ ነው ። ከዚያም ከሽትራስቡርግ ፈረንሳይ በህግ የማስተርስ ዲግሪ አግኝተዋል የህይወት ታሪካቸው እንደሚያትተው ግን በዚህ ሙያ አልሰሩም ። ዩንከር እጎአ በ1975 የህግ ትምህርት ከመጀመራቸው ከ5 ዓመት በፊት ነበር የክርስቲያን ሶሻል ህዝባዊ ፓርቲ አባል የሆኑት ። ከተመረቁ በኋላም የፓርላማ ፀሃፊ ሆኑ ።በመንግሥት አስተዳደር ውስጥ በከፍተኛ ሃላፊነት መስራት የጀመሩት በ1982 በሚኒስትር ዴታነት ሲሆን በ1984 በጠቅላይ ሚኒስትር ዣክ ሳንተር ካቢኔ የሰራ ሚኒስትር ነበሩ ። እንዲህ እንዲህ እያሉ የሃገራቸውጠቅላይ ሚኒስትር እስከመሆን የደረሱት ዩንከር አሁን ደግሞ ለትልቁ የአውሮፓ ህብረት ሥልጣን ለአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንትነት ታጭተዋል ። ሹመታቸው የሚፀድቀው ግን የዛሬ 15 ቀን የአውሮፓ ፓርላማ ድምፅ ከሰጠበት በኋላ ነው ። ዩንከር ሃላፊነቱን ሲረከቡ በህብረቱ አባል ሃገራት የበጀት አያያዝ ህግና ስርዓት እንዲሰፍን ማድረግን እንዲሁም እድገትና ለወጣቶች ስራ መፍጠር አብይ ትኩረታቸው እንደሚሆን ተናግረዋል ። ከሁሉም በላይ ግን ዓላማቸው አውሮፓንና አውሮፓውያንን ማቀራረብ መሆኑን ከተመረጡ በኋላ በሰጡት አስተያየት ተናግረዋል ።

« አገናኝ ድልድይ መገንባት እፈልጋለሁ ። ተባብሮ መምራትና በአውሮፓ በመግባባት ስምምነት ላይ የሚደረስበት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው የምጥረው ።»

በሌላ ዜና የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት ዛሬ ሽትራስቡርግ ፈረንሳይ ውስጥ በሰጡት ድምፅ ሶሻል ዲሞክራቱን ማርቲን ሹልዝን ዛሬ ዳግም ፕሬዝዳንታቸው አድርጎ መርጠዋቸዋል ። 409 የምክር ቤቱ አባላትኙ ሹልዝ ለሚቀጥለው ሁለት ዓመት ተኩል በሃላፊነታቸው እንዲቀጥሉ ድምፃቸውን ሰጥተዋል ። አልተሳካላቸውም እንጂ ሹልዝ ለአውሮፓ ህብረት ፕሬዝዳንትነት ተወዳድረው ነበር ።

ሂሩት መለሰ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic