የአውሮፓ ህብረትና የጀልባ ስደተኞች | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 21.04.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮፓ ህብረትና የጀልባ ስደተኞች

የአውሮፓ ህብረት በሜዲቴራንያን ባህር ላይ ተደጋግሞ የሚደርሰውን የስደተኞች እልቂት ማስቆም ያስችላል ያለውን እቅድ ትናንት አቅርቧል ። የእቅዱ ተግባራዊነት ግን እያነጋገረ ነው ።

ባለፈው ቅዳሜ ከሊቢያ ተነስተው በሜዲቴራንያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ ጉዞ ከጀመሩ ስደተኞች ወደ አንድ ሺህ የተገመቱት የባህር ሲሳይ መሆናቸው ከተሰማ በኋላ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል ያለውን እቅድ ለአባል ሃገራት ሚኒስትሮች አቅርቦ እቅዱ ተቀባይነት አግኝቷል ። የህብረቱ አባል ሃገራት የውጭ ና የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት ሉክስመበርግ ውስጥ በጉዳዩ ላይ ከመከሩ በኋላ ለችግሩ አጣዳፊ መልስ ይሰጣል የተባለውን ባለ 10 ነጥብ የድርጊት መርሃ ግብር ነው የተቀበሉት ። ይኽው የድርጊት መርሃ ግብርም ከነገ በስተያ የህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች በሚያካሂዱት ጉባኤ ላይ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል ። የድርጊት መርሃ ግብሩ ትኩረት ከሰጣቸው ጉዳዮች ውስጥ በሜዲቴራንያን ባህር ላይ የሚካሄደው የነፍስ አድን ተልዕኮ ዋነኛው ነው ። የሚኒስትሮቹን ስብሰባ ውጤት የተከታተለው የብራሰልሱ ዘጋቢያችን ገበያው ንጉሴ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ከደረሰው ከላምፔዱዛው የስደተኞች እልቂት በኋላ የኢጣልያ ባህር ኃይል ለአንድ ዓመት ያህል ያካሄደው የማሬ ኖስትሮም ተልዕኮ ሲቋረጥ በቀጠለው የጀልባ ስደተኞች ሞት ምክንያት ተደጋጋሚ ወቀሳ የሚቀርብበት የአውሮፓ ህብረት በዚህ የድርጊት መርሃ ግብር ይህን ክፍተት መድፈን ዋነኛው ትኩረቱ አድርጎታል ይላል። ከዚህ ሌላ ገበያው

እንደሚለው በድርጊት መርሃ ግብሩ ከዚህ ቀደም ያልተሞከሩ አዳዲስ እርምጃዎችንም ለመውሰድ ታቅዷል ።በድርጊት መርሃ ግብሩ ውስጥ የተካተተው የነፍስ አድኑ መርሃ ግብር ብቻ ሳይሆን ስደተኞቹን ወደ መጡበት የመመለስ እርምጃም ጭምር ነው ።የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን በሜዲቴራንያን ባህር ላይ ተደጋግሞ የደረሰውን የስደተኞች እልቂት ለማስቆም ይረዳል ሲል ትናንት ይፋ ያደረገው ይህ ድርጊት መርሃግብር የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰነዘሩበት ነው ። ብዙዎች ህብረቱ ይህን መሰሉ እቅድ ለማውጣት ቁጥራቸው ወደ ሺህ የተጠጋ ስደተኞች እስኪያልቁ መጠበቅ ነበረበት ወይ ሲሉ ወቅሰዋል ። አንዳንዶች ደግሞ የድርጊት መርሃ ግብሩን ተግባራዊ ይሆናል ብለው አያምኑም ።በተለያዩ የአፍሪቃ ሃገራት የሚገኙ ስደተኞችን የሚረዳው ጋንዲ የተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ሃላፊ ዶር አልጋነሽ ፍስሃ ትናንት ለአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት የውጭ ጉዳይና የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች የቀረበውን ይህ እቅድ ተግባራዊ መሆኑን ይጠራጠራሉ ። ዶክተር አልጋነሽ ይህን የሚሉት የከዚህ ቀደሙን ልምድ በምሳሌነት በማንሳት ነው ።

«አስታውሳለሁ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ከላምፔዱዛ እልቂት በኋላ ብዙ ነገሮችን ለማድረግ ቃል ገብተው ነበር ። ግን ቃል ከገቡት ውስጥ አንዱንም ተግባራዊ አላደረጉም ። ይህ የአውሮፓ ህብረት ኢጣልያን ለብቻዋ በመተው የፈፀመው የመጀመሪያ ስህተት ነው ። በ2ተኛ ደረጃ በርግጥ ትልቁ ስህተት ያለው ደላሎቹ ጋ ነው ። በትንሽም ይሁን በትልቅ ጀልባ ማዕበሉ ኃይለኛ መሆኑንም እያወቁ ለገንዘብ ሲሉ ጀልባዎቹ ከሚችሏቸው ሰዎች በላይ እየጫኑ ብዙ ሰዎች በሜዲቴራንያን ባህር ውስጥ ህይወታቸውን አጥተዋል ። የአውሮፓ ፓርላማም ሃላፊነት አለበት እላለሁ ።ኢጣልያም እንዲሁ ለስደተኞቹ ጎርፍ ራሷን አላዘጋጀችም ።»

ገበያው በበኩሉ የድርጊት መርሃ ግብር በራሱ በቂ አይደለም የሚል ትችትም ቀርቦበታል ይላል ።ከዚህ ሌላ ከዚህ ቀደም ተግባራዊ ሊሆኑ ያልቻሉ እቅዶች በድርጊት መርሃግብሩ እንደገና መካተታቸውም ተነቅፏል ።

ከዚህ ሌላ ገበያው እንደሚለው ህብረቱ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎች አባል ሃገራት በሙሉ በተለያዩ ምክንያቶች በተናጠል ተግባራዊ ማድረጉ ሁሌም ላይሳካላቸው ይችላል ።

እስካሁን በሊቢያ ድንበር ላይ ስደተኞችን የሚጠባበቁና ወደ ትናንሽ ጀልባዎች የሚያሻግሩ 18 ትላልቅ ጀልባዎች እንዳሉ ዶክተር አልጋነሽ ያስረዳሉ ።ደላሎቹ ትላልቆቹን ጀልባዎች ይከራዩና ስደተኞቹን ከተወሰነ ጉዞ በኋላ ወደ ትናንሽ ጀልባዎች ያሻግሯቸዋል ። እነዚህን ስደተኞችን የሚጭኑ ጀልባዎችን ለመያዝና ለማጥፋት ህብረቱ ያወጣው እቅድ መልካም ቢሆንም ዶክተር አልጋነሽ እንደሚሉት እንዲህ በቀላሉ የሚሳካ አይመስላቸውም ።

«በሊቢያ የሚካሄደው እጅግ ከባድ ጦርነት ነው ።እዚያ ሶስት ቡድኖች ናቸው ያሉት። አንደኛው ዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ የተቀበለው የሊቢያ መንግሥት ሲሆን ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ቡድንም እዚያ ይገኛል የሙስሊም ወንድማማቾችም ሊቢያ አሉ ።እና ከማን ጋር ነው የሚነጋገሩት ። ምክንያቱም ሊቢያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች በተለያዩ ቡድኖች እጅ ስር ነው ያሉት ።»

ያም ሆኖ የአሁኑ የህብረቱ እንቅስቃሴ እንደ ጥሩ ጅምር ተደርጎ እንደሚወሰድ ነው ገበያው የሚናገረው ።

የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት መሪዎች ከነገ ወዲያ በሚያካሄዱት ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀው የድርጊት መርሃ ግብር የስደተኞችን እልቂት መግታት መቻል አለመቻሉ በሂደት የሚታይ ይሆናል

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic