የአውሮፓ ህብረትና የምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ትብብር | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 26.05.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮፓ ህብረትና የምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ትብብር

የአውሮፓ ህብረት ፣የህብረቱ አባል ያልሆኑ 6 የምሥራቅ አውሮፓ ሃገራትን ይበልጥ ለማቅረብ እየጣረ ነው ።በህብረቱና በ6ቱ የምሥራቅ አውሮፓ ሃገራት ትብብር ጉባኤ ላይ እንደተገለፀው ህብረቱ ለሃገራቱ የሚሰጠውን ድጋፍ ለማጠናከር ቃል ገብቷል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:25
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
08:25 ደቂቃ

የአውሮፓ ህብረትና የምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ትብብር

የአውሮፓ ህብረትና የህብረቱ አባል ያልሆኑ 6 የምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ትብብር ከተመሠረተ 6 ዓመታት አስቆጥሯል ። በትብብሩ ውስጥ የተካተቱት ከአውሮፓ ህብረት ጋር የሚጎራበቱት 6 የቀድሞዎቹ የሶቭየት ህብረት ሪፐብሊኮች አርመን አዘርባጃን ቤላሩስ ጆርጅያ ሞልዶቫ እና ዩክሬን ናቸው።የትብብሩ ዓላማም በህብረቱ ና በ6ቱ ሃገራት መካከል በንግድና በኤኮኖሚ እንዲሁም የሰዎች ዝውውርን በሚመለከቱና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የመወያያ መድረክ መፍጠር ነው ። ከዚህ ሌላ ህብረቱ በሃገራቱ የሚካሄዱ ተሃድሶ እርምጃዎችንም ያበረታታል ። የሃሳቡ ጠንሳሽ ፖላንድ ስትሆን ከስዊድን ጋር በጋራ ነበር ሃሳቡን አዘጋጅተው ያቀረቡት ።የሁለቱ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በጎርጎሮሳዊው ግንቦት 2008 ሃሳቡን ብራሰልስ ውስጥ ለአውሮፓ ህብረት የአጠቃላይ ጉዳዮችና የውጭ ግንኙነቶች ምክር ቤት አቀረቡ ። በዓመቱ ግንቦት 2009 ፕራግ ቼክ ሪፐብሊክ ውስጥ የህብረቱና የስድስቱ የቀድሞዎቹ የሶቭየት ህብረት ሪፐብሊኮች ትብብር እንቅስቃሴ ተጀመረ ። የሁለቱ ወገኖች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በትብብሩ ማዕቀፍ ላይ ያተኮረ የመጀመሪያ ስብሰባቸውን ብራሰልስ ቤልጂግ ውስጥ ታህሳስ 2009 ዓም አካሄዱ ። ከዚያን ጊዜ አንስቶም የትብብሩ አባል ሃገራት መሪዎች በየሁለት ዓመቱ ጉባኤ ያካሂዳሉ ። የትብብሩ አራተኛ

ጉባኤ በወቅቱ የአውሮፓ ህብረት ሊቀ መንበር በላትቪያ ዋና ከተማ ሪጋ ውስጥ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ተካሂዷል ። በዚሁ ጉባኤ ላይ የአውሮፓ ህብረት ለ6ቱ የቀድሞዎቹ የሶቭየት ህብረት ሪፐብሊኮች የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ከፍ ለማድረግና በህብረቱ አባል ሃገራት የዜጎችን ነፃ ዝውውር ለመፍቀድ ቃል ገብቷል ። የአውሮፓ ህብረት ከ6ቱ የምስራቅ አውሮፓ ሃገራት ጋር በመሰረተው ትብብር ሩስያ ደስተኛ አይደለችም ። ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን በተለያዩ አጋጣሚዎች ቅሬታዋን ከመግለፅ ወደ ኋላ ብላ አታውቅም ። ትብብሩ እንደተመሰረተ የያኔው የሩስያ ፕሬዝዳንት ዲሚትሪ ሜድቬዴቬ ፋይዳ ቢስ ሲሉ አጣጥለውት ነበር ። ሩስያ ህብረቱ ትብብሩን በሃገራቱ ላይ የተፅእኖውን አድማስ ለማስፋት የሚጠቀምበት መሣሪያ ነው ስትል ስጋትዋን ታሰማለች ። በሩስያ አባባል ህብረቱ ትብብሩን ለነዳጅ ዘይት ማፈላለጊያ እየተጠቀመበት ነው ። ከዚህ በተጨማሪም ሩስያ ህብረቱ በተለይ በቤላሩስ ላይ ከመጠን ያለፈ ጫና እያደረገባት ነው ስትልም ትከሳለች ። ሩስያ እንደምትለው ቤላሩስ እንደ ሩስያ ከጆርጅያ ለተገነጠሉት ለአብካዝያና ለደቡብ ኦሴትያ ግዛቶች እውቅና ከሰጠች ምናልባት ልትገለል ትችላለች የሚል ስጋት እንዳላትም ትናገራለች ። ሃገራቱ እንደ ሉዓላዊ ግዛት ፣መውሰድ መያዝ በሚፈልጉት አቋም

ላይ ህብረቱ ይጫናቸዋል ስትል በደጋጋሚ ጊዜያት ትወቅሳለች ። ሆኖም የትብብሩ ሃሳብ አመንጪ ፖላንድ አስተያየቱ ተቀባይነት የለውም ስትል ታጣጥላለች ። የፖላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶናልድ ቱስክ በሪጋው ጉባኤ ላይ የሁለቱ ወገኖች ግንኙነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ነው የሚናገሩት ።
«የአውሮፓ ህብረት የረዥም ጊዜ አጋር ነው ። ትብብራችንም ሆነ የሪጋው ጉባኤ ተለዋዋጭ ውሳኔዎችን የማሳለፍ ዓላማ የላቸውም ወይም ደግሞ ግዙፍ እርምጃዎችንም ለመውሰድ ያለሙ አይደሉም ። ግንኙነታችን በነፃነት በፈቃደኝነት በመከባበር እና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ነው »
በሪጋው የትብብሩ አባል ሃገራት መሪዎች ጉባኤ ላይ የጀርመን መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በሰጡት አስተያየትም ከምሥራቅ አውሮፓዎቹ ሃገራት ጋር የተመሰረተው ትብብር ሃገራቱ አንድ አቅጣጫ ብቻ እንዲከተሉ የሚያስገድድ አለመሆኑን በግልጽ ተናግረዋል ። ህብረቱ ሃገራቱ እንከተላለን የሚሉትን መንገድም እንደሚቀበልም አስታውቀዋል ።
« የምሥራቅ አውሮፓ ሃገራት የአውሮፓ ህብረት እሴቶችን የመቀበል ፍላጎት ካሳዩ የራሳቸው ሉዓላዊ ውሳኔ ነው የሚሆነው ። ማንም ቢሆን ይህን ራሳቸውን የሚመርጡትን መንገድ የማመቻቸት መብት የለውም ።»
የትብብሩ ዓላማ ሜርክል እንዳሉት የአውሮፓ ህብረት አባል ካልሆኑት የምሥራቅ አውሮፓ ሃገራት ጋር ተቀራርቦ መስራት እንጂ

ወደ ህብረቱ እንዲቀላቀሉ መገፋፋት አይደለም ።
«ከምሥራቅ አውሮፓ ሃገራት ጋር ጉድኝት መፍጠሩ የአውሮፓ ህብረት የማስፋፋፍያ መሣሪያ አይደለም ። ሆኖም ከአውሮፓ ህብረት ጋር የማቀራረቢያ መሣሪያ መሆኑ አያጠራጥርም »
ባለፈው ሀሙስ እና አርብ በተካሄደው የሪጋው ጉባኤ ህብረቱ ከዩክሬን ጋር የ1.8 ሚሊዮን ዩሮ ወይም የ2 ቢሊዮን ዩሮ የብድ ስምምነት ተፈራርሟል ።ይህም ህብረቱ የአውሮፓ ህብረት ላልሆነ ሃገር እስከዛሬ ከሰጠው ብድር ከፍተኛው ነው ። ህብረቱ ከዚህ ቀደምም ለዩክሬን 1.61 ዩሮ የሚጠጋ ገንዘብ አበድሯል ።ከትብብሩ አባላት መካከል በተለይ ዩክሬን ጆርጅያና ሞልዶቫ ከህብረቱ ጋር ቅርብ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ግንኙነት መፍጠር የሚያስችሉ ስምምነቶች ፈርመዋል ። ለነዚህ ሃገራትም በሚቀጥሉት ዓመታት እስከ 2 ቢሊዮን ዩሮ የሚደርስ ውረታን ለመሳብ የሚያስችላቸው 200 ሚሊዮን ዩሮ ለመስጠት ቃል ገብቶላቸዋል ።አነዚህ ሃገራት የአውሮፓ ህብረት አባል የመሆን ፍላጎት አላቸው ይሁንና በሪጋው ጉባኤ ይህን ምኞታቸውን ቢያንስ በአጭር ጊዜ እውን ሊያደርግ የሚችል ተስፋ አላገኙም ። ከዚያ ይልቅ ህብረቱ በተለይ የዩክሬንና የጆርጅያ ዜጎች በአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ያለ ቪዛ መግባት እንዲችሉ ሃገራቱ የሚጠበቅባቸውን የህብረቱን መስፈርቶች ማሟላት አለማሟላታቸውን እስከሚቀጥለው ዓመት ታህሳስ አጋማሽ ድረስ እንደሚገመግም ቃል ገብቷል ። የህብረቱ ባለሥልጣናት እንደሚሉት የግምገማው ውጤት በጎ ከሆነ የሁለቱ ሃገራት ዜጎች ብዙም ሳይቆይ በአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ያለ ቪዛ የመዘዋወር ፈቃድ ሊያገኙ ይችላሉ ። በዚህ ረገድ ጆርጅያ አስፈላጊ ዝግጅቶችን ማድረጓን ተናግራለች ።
ጠቅላይ ሚኒስትሯ ኢራኪል ጋሪባሽዊሊ ዜጎቻቸው በህብረቱ አባል ሃገራት በነፃ እንዲዘዋወሩ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል ።
«በብዙ ዘርፎች ጎላ ያሉ ለውጦች አድርገናል ብዬ አስባለሁ ። እንደሚመስለኝ የጆርጅያ ዜጎች ቪዛ የማያስፈልገው ዝውውር ሊፈቀድላቸው ይገባል ። »

ከ6ቱ የምስራቅ አውሮፓ ሃገራት አርመንያና ቤላሩስ የሩስያው የዩሮ ኤዥያ የኤኮኖሚ ህብረት አባል ናቸው ።በአንፃሩ ዩክሬን ጆርጅያና ሞልዶቫ ከህብረቱ ጋር ጥብቅ ግንኙነት መመሥረት ይፈልጋሉ ። ባለፈው ሳምንቱ የሪጋ ጉባኤ የአውሮፓ ህብረት ለዩክሬንና ለሌሎች የትብብሩ አባላት የሰጠው ብድርና ና ቃል የገባው ገንዘብ እንዲሁም ያለ ቪዛ ዝውውርን እፈቅዳለሁ ሲል የሰጠው ተስፋ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ይፈፀም የነበረውን ሁኔታ የሚያስታውስ ተደርጎ ነው የተወሰደው ። አንዳንድ የህብረቱ አባል ሃገራት መሪዎች መፍቅሬ አውሮፓ የሆኑትን የትብብሩን አባላት ይበልጥ ለማቅረብ ቢስማሙም ውሳኔያቸው የሩስያውን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲንን የሚተነኩስ እንዳይሆን መስጋታቸው አልቀረም ። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፍራንሷ ኦሎንድ ትብብሩ ከሩስያ ጋር ሌላ ግጭት የሚፈጥር እንዳይሆን መጠንቀቅ እንደሚገባ አሳስበው ነበር ።ህብረቱ ከአጎራባቾቹ ከቀድሞዎቹን የሶቭየት ህብረት ሪፐብሊኮች ጋር የፈጠረው ትብብር ሩስያን ለመቃወም ታስቦ የተደረገ አለመሆኑን ደጋግሞ ቢናገርም የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ የአውሮፓ ህብረት ለሃገራቱ ከምዕራባውያን ጋር ናችሁ ወይስ ከሩስያ ጋር የሚል የተሳሳተ ምርጫ እያቀረበላቸው ነው ሲሉ የሪጋው ጉባኤ በተጠናቀቀበት አርብ ወቅሰዋል ።
ኂሩት መለሰ
ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic