የአውሮፓው ህብረት የጤና ሚንስትሮችና ኢቦላ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 16.10.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮፓው ህብረት የጤና ሚንስትሮችና ኢቦላ

የአዉሮፓ ኅብረት የጤና ሚኒስትሮች ኤቦላ ከተስፋፋባቸዉ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የሚመጡ ተጓዦችን በየአዉሮፕላን ማረፊያዉ የሚቆጣጠሩበትን ስልት ባስቸኳይ ዳግም ለመከለስ ተስማሙ።

ብራስልስ ላይ የተሰባሰቡት 21 የኅብረቱ አባል ሃገራት ሚኒስትሮች በተጨማሪም የድንበር ኬላዎቻቸዉ ላይም ለሚደረገዉ ጥንቃቄ ለመተባበር ወስነዋል። የአዉሮጳ ኮሚሽን የኅብረቱ አስፈፃሚ አካል ኤቦላ ካጠቃቸዉ ሃገራት በሚነሱ በረራዎች ላይ የሚካሄደዉን የምርመራ ስልት የመቆጣጠሩን ኃላፊነት ወስዷል።

በዚሁ መሠረትም ላይቤሪያ፣ ጊኒ እና ሴራሊዮን ላይ የሚደረገዉ ምርመራ በዓለም የጤና ድርጅት አስተባባሪነት እንደሚካሄድ የኅብረቱ የጤና ኮሚሽነር ቶኒዮ ቦርግ አመልክተዋል። እንዲያም ሆኖ ስለተናጠል ጥንቃቄዉ እያንዳንዱ አባል ሀገር የየራሱን ርምጃ እንደሚወስድ ተገልጿል።

በያዝነዉ ሳምንት ከምዕራብ አፍሪቃ በኤቦላ ተሐዋሲ ተይዞ የመጣ የተመድ ባልደረባ ህይወቱ ያለፈባት ጀርመን የፍራንክፈርት አዉሮፕላን ማረፊያ የጤና ጉዳይ ተጠሪ አንቶኒ ቫልሶክ፤ ለጊዜዉ የሚያሰጋ ነገር አለመኖሩን ነዉ ያመለከቱት፤

«ፍራንክፈርት በኤቦላ ከተጠቁት የምራብ አፍሪቃ ሃገራት የቀጥታ በረራ ግንኙነት የላትም። በየቀኑ ወደናይጀሪያ ሁለት በረራዎች ናቸዉ ያሉን። ናይጀሪያ ደግሞ በኤቦላ ከተጠቁት ሃገራት ዉስጥ የለችበትም።»

በተያያዘ ዜና ፍሮንትይር የተሰኘዉ አየርመንገድ ስድስት የበረራ ሠራተኞቹን ለጥንቃቄ ለ21 ቀናት ተገልለዉ እንዲቆዩ ማድረጉም ተገልጿል። አየርመንገዱ ይህን ርምጃ የወሰደዉ በያዝነዉ ሳምንት መጀመሪያ አሜሪካ ዉስጥ የኤቦላ ታማሚን ስታክም የነበረች ነርስን ማጓጓዙን ከደረሰበት በኋላ ነዉ። ነርሷ በኤቦላ መያዟ መረጋገጡን ያመለከተዉ የአየርመንገዱ መግለጫ ሁለት አብራሪዎችና አራት የበረራ አስተናጋጆች የጤና ይዞታቸዉ እስኪጣራ ተገልለዉ እንዲቆዩ ማድረጉን ዘርዝሯል።

የዓለም ጤና ጥበቃ ድርጅት (WHO) ከትንንት በስቲያ ባወጣው፣ መግለጫ ላይ እንዳለው፤ ከምዕራብ አፍሪቃ የኢቦላ ሥርጭት፣ ባስቸኳይ ካልተገታ ከታኅሳስ ወር ጀምሮ በየሳምንቱ 10ሺ የሚሆኑ ሰዎች በኢቦላ ተኀዋሲ ሊጠቁ ይችላሉ በማለት ማስጠነቀቁ የሚታወስ ነው።

ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ፤ የኢቦላ ተኀዋሲ ተስፋፍቶባቸዋል ከሚባሉ የምዕራብ አፍሪቃ አገሮች በሚገቡ መንገደኞች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ ጀምረዋል። የአውሮፓ ሕብረት የጤና ሚንስትሮች ዛሬ የመከሩትም፤ ኢቦላ ወደ ክፍለ ዓለሙ እንዳይዛመት የድንበር ቁጥጥርን ለማጠናከርና በተቀናጀ መልኩ በተግባር መተርጎም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ነው።

ገበያው ንጉሤ

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic