የአውሮፓና የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ሽርክና | ኤኮኖሚ | DW | 08.05.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአውሮፓና የአፍሪቃ የኤኮኖሚ ሽርክና

የአውሮፓ ሕብረት ከአፍሪቃ መንግሥታት ጋር የኤኮኖሚ ሽርክና ውል ለማስፈን ሲጥር የተወሰኑ ዓመታት አልፈዋል።

default

የውሉ ዓላማ ነጻ ንግድን ማስፈን ነው። ለነገሩ በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ገና ከአሁኑ ቀረጥ ሳይከፍሉ ምርቶቻቸውን ወደ አውሮፓ ሕብረት ገበዮች ማስገባት ይችላሉ። የታቀደው ውል ደግሞ እነዚሁ ሃገራት በፊናቸው ለአውሮፓ ንግድ ገበዮቻቸውን እንዲከፍቱ የሚያደርግ ነው።

አንዳንድ የአፍሪቃ ሃገራት ይሁንና ወሉ በሚፈጥረው ፉክክር የራሳቸው ምርቶች ከገበዮች እንዳይገፉ በጣሙን ይሰጋሉ። ስለዚህም የነጻውን ንግድ ውል ለመፈራረም ዝግጁ ሆነው አይገኙም። የአውሮፓ ሕብረት አሁን ለነዚህ መንግሥታት የመደራደሪያ ጊዜ ገደቡን ቢያራዝምም በሌላ በኩል ግፊቱንም አጠናክሯል።

እሰከፊታችን የጎርጎሮሳውናኑ 2014 ዓ-ም መጀመሪያ ውሉን በፊርማ ያላጸደቀ የአፍሪቃ አገር ያላ ቀረጥ ወደ አውሮፓ ሕብረት ገበዮች ምርት ማስገባት የሚችል አይሆንም። ይህ ደግሞ በሚመለከታቸው ሃገራት ውስጥ የሚገኙ ኩባንያዎችን ወይም ነጋዴዎችን ብርቱ ፈተና ላይ ሊጥል የሚችል ነው። ፈተናው ሊሚገጥማቸው ከሚችሉት ኩባንያዎች ባለቤቶች መካከል የካሜሩኑን ዣን-ፒየር-ኢሜሌን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

የኢሜሌ ኩባንያ በምዕራባዊቱ የአፍሪቃ አገር ፍራፍሬ የሚያመርት ሲሆን ከዚሁ 90 በመቶውን ወደ አውሮፓ ሕብረት የሚልክም ነው። ስለዚህም በካሜሩን መንግሥትና በአውሮፓ ኮሚሢዮን መካከል ነጻ የንግድ ውል ለማስፈን በብራስልስ የሚካሄደውን ድርድር በስጋት መመልከቱ አልቀረም።

ዣን-ፒየር-ኢሜሌ እስካሁን በካሜሩንና በአውሮፓ ሕብረት መካከል በተደረገ ጊዜያዊ ስምምነት ተጠቃሚ ሆኖ ቆይተዋል። ይህም ኢሜሌ ከቀረጥ ነጻ ምርቱን ወደ አውሮፓ ሕብረት ገበዮች እንዲያስገባ የሚፈቅድ ነው። ግን ካሜሩንና ሕብረቱ እስከ 2014 መጀመሪያ ከአንድነት ካልደረሱ ቀረጥ መክፈል የሚገደድ ይሆናል።

«ይህ ከሆነ ችግር ላይ መውደቃችን ነው። የምናመርታቸው ፍራፍሬዎች ከደቡብ አሜሪካና ከሕንድ ፍራፍሬ ምርቶች መፎካከር ይኖርባቸዋል። ይህን ደግሞ ብዙ የእርሻ ልማት ችግር ስላለን ልንቋቋመው አንችልም። መንግሥታችንም አይደግፈንም። እና አሁን ደግሞ አውሮፓ ውስጥ ቀረጥ መክፈል ካለብን ከገበያው ተፈንቅለን መውጣታችን ነው»

የቀድሞዎቹ የአውሮፓ ቅኝ ግዛቶች በልዩ አስተያየት ለአሠርተ-ዓመታት ወደ አውሮፓ ገበዮች መዝለቅ ችለው ቆይተዋል። በአንጻሩ የራሳቸውን ገበዮች ለአውሮፓ ሕብረት ምርቶች መክፈት አልተገደዱም። እነዚሁ ACP በሚል አሕጽሮት የሚጠሩት የአፍሪቃ፣ የካራይብና የሰላማዊው ውቂያኖስ የፓሲፊክ አካባቢ ሃገራት ናቸው።

ቡድኑ 79 ዓባል ሃገራት ሲኖሩት የሚበዙትም የአንዴ የፈረንሣይና የብሪታኒያ ቅኝ ግዛቶች ሆነው ይገኛሉ። ለአፍሪቃ ፣ካራይብና ፓሢፊክ ሃገራት ወደ አውሮፓ ገበዮች የመዝለቁን ሁኔታ ለማቃለል የተወሰነው በጎርጎሮሳውያኑ 1975 ዓ-ም በሰፈነው የሎሜ ውል ነበር። ሆኖም ወደ በኋላ በ 2000 ዓ-ም የዓለም ንግድ ድርጅት ለአንድ ወገን ያደላውን ስምምነት ሕጋዊ አይደለም ሲል እንዲቀየር ይወስናል።

የኮቶኑ ውል በሚል ስያሜ የሚታወቀው ተከታይ ስምምነት ገሃድ የሆነው እንግዲህ ከዚህ በኋላ ነበር። እናም ከዚያን ወዲህ የ ACP ሃገራትና የአውሮፓ ሕብረት በአውሮፓ የኤኮኖሚ ውል ላይ በመደራደር ላይ መሆናቸው ይታወቃል። ውሉ በአሕጽሮት EPA – Economic Partnership Agreement ወይም የኤኮኖሚ ሽርክና ውል በመባል የሚጠራ ነው። ታዳጊዎቹ የስብስቡ ዓባል ሃገራት እንደነበረው ምርቶቻቸውን ያለ ቀረጥ ወደ አውሮፓ መላክ ይችላሉ። ግን በአንጻሩ ለአውሮፓ ምርቶች ገበዮቻቸውን መክፈትም ይጠበቅባቸዋል። የሚፈለገው ነጻና የጋራ ጥቅም የሰመረበት ንግድ ነው የዓለም ንግድ ድርጅት እንደሚለው። የአውሮፓው ኮሚሢዮን አፈ ቀላጤ ጆን ክላንሢይም ይህንኑ አቋም ይደግፋሉ።

«ለዓለምአቀፉ ንግድ ደምቦችን የፈጠረው የአውሮፓ ሕብረት አይደለም። ይልቁንም የዓለም ንግድ ድርጅት እንጂ። እኛ ለ ኤሢፒ ሃገራት የተለየ ደምብ ልናሰፍን አንችልም። ይህ ቢሆን የሌላው ዓለም ክፍል ለምሳሌ የላቲን አሜሪካ ተጠሪዎች መጥተው ለምን ለነርሱ ከኛ የተለዩ ደምቦች ፈጠራችሁ ሊሉን ይችላሉ»

እርግጥ የዓለም ንግድ ድርጅት ልዩ አስተያየት መደረጉንም ይፈቅዳል። ለምሳሌ ያህል የድሃ ድሃ ተብለው የሚመደቡት በልማት ኋላ የቀሩ ሃገራት ገበዮቻቸውን ለአውሮፓ ሕብረት እንደዘጉ በመቀጠል በፊናቸው ግን ነጻ ሆነው ወደ አውሮፓ ገበዮች መዝለቅ ይችላሉ። ከነዚሁ ሃገራት 34 የሚሆኑት የሚገኙትም አፍሪቃ ውስጥ ነው። ታዲያ እነዚህን መሰሉ የአፍሪቃ ሃገራት ከአውሮፓ ሕብረት ጋር የነጻ ንግዱን ውል አንፈራረምም ቢሉም የሚከተል ጉዳት አይኖርባቸውም።

ነገር ግን በአንጻሩ እንደ ኬንያ፣ ጋና፣ካሜሩን ወይም ቦትሱዋና በልማት ሻል ያሉት ሃገራት ይህን አስተያየት ሊያጡት ይችላሉ። ስጋት ላይ የሚጥላቸውም ይሄው ነው። የኤኮኖሚው ባለሙያ ፓውል ኮሊየር እንደሚሉት የአውሮፓ ሕብረት የዓለም ንግድ ድርጅትን ደምቦች ገቢር ለማድረግ የያዘው ግፊት እጅግ የጠነከረ ነው።

ለንጽጽር አሜሪካ ከ 2000 ዓ-ም ወዲህ የአፍሪቃ ሃገራት ያላንዳች ቅድመ-ግዴታ በርካታ ምርቶች ወደ ገበዮቿ እንዲያስገቡ ፈቅዳ ቆይታለች። በአሕጽሮት AGOA – African Growth and Opportunity Act የተሰኘ የዕድገት ውል ባህርይ ይህን የመሰለ ነው። ስለዚህም አጎዋ በአውሮፓና በአፍሪቃ መካከል ለሚካሄደ ንግድም አርአያ እንዲሆን ነው ኮሊየር የሚያሳስቡት። ምክንያቱም ድርድሩ በእስካሁን መልኩ የትም አላደረሰም።

«አፍሪቃ የአውሮፓውያኑን ሃሣብ ባለመቀበሏ ዕርምጃ ማድረግ አልተቻለም። ለነገሩ ለአውሮፓ ገበዮቹን መክፈቱ ለአፍሪቃ ሃገራት ብልህ ዕርምጃ ባልሆነም ነበር። በዘመነ-ግሎባላይዜሺን በመሠረቱ ተገቢው ዕርምጃ ለሁሉም ሃገራት የንግድ መሰናክሎችን ማስወገዱ ነው። የአውሮፓ ሕብረት የጊዜ ገደብ በመጣል ግፊት ሲያደርግ ቆይቷል። አሁን ግን የከሸፈውን ድርድር በማስፈራራት ለመቀጠል መፈለግ የተሳሳተው መንገድ ሊሆን ይችላል። ጉዳዩ ምናልባትም ቢታሰብበት የሚሻል ነው»

ኮሊየር የሚያሳስቡት በአውሮፓ አርአያ አንድ ዓይነት የአፍሪቃ የቀረጥ ሕብረት እንዲፈጠር ነው። በተጨባጭ አውሮፓ ለአፍሪቃ ገበዮቿን ትከፍታለች። የአፍሪቃ ሃገራት ደግሞ በአንጻሩ በመካከላቸው ገበዮቻቸውን ይከፍታሉ። ለግንዛቤ እንዲረዳ ለጊዜው በ 54ቱ የአፍሪቃ ሃገራት መካከል የንግድ መሰናክል ሰፍኖ ነው የሚገኘው።

ግን አፍሪቃ በመላው አንድ ነጻ የንግድ ክልል ለመሆን ብትችል ይህ ለአውሮፓም ጠቀሜታ እንደሚኖረው የኤኮኖሚው ባለሙያ ዕምነት ነው። ይህ ቢሣካ አፍሪቃ የበለጸገችና ለአውሮፓም የሚበጅ ሰፊ ገበያ ያላት ልትሆን ትችላለች። በነገራችን ላይ ይህን አመለካከት አንዳንድ የአፍሪቃ መንግሥታትም ይጋሩታል። ለነገሩ የኤኮኖሚ ሽርክናው ውል በአውሮፓ ሕብረት ውስጥም አከራካሪ መሆኑ አልቀረም። የጀርመኗ ቻንስለር የአፍሪቃ ጉዳይ ተጠሪ ጉንተር ኑክ ለምሳሌ በታሰበው ውል ተገቢነት ከሚጠራጠሩት አንዱ ናቸው።

«አፍሪቃውያኑ መንግሥታት እኛ ስለፈለግን ወይም ደግሞ በጠባቡ የተቀመጠው የዓለም ንግድ ድርጅት ውሣኔ ስለጠየቀ ውሉን መፈረም አለባቸው ማለት አንችልም። በእኔ ዕምነት ወደ ኋላ ተመልሰን አዲስ ጅማሮ ማድረግ የሚኖርብን ይመስለኛል»

ግን የአውሮፓ ኮሚሢዮን በወቅቱ ይህ አመለካከት ያለው አይመስልም። ይህን በአዳጊዎቹ የኤሲፒ ሃገራት ያሉት ኩባንያዎችም ሲገነዘቡ መንግሥታቱ የኤኮኖሚ ሽርክናውን ውል ከሕብረቱ እንዲፈራረሙ የተቻላቸውን ሁሉ ስጥሩ ነው የሚታዩት። ነጋዴዎቹ አለበለዚያ ያለምንም ባዶ ዕጃቸውን እንዳይቀሩ ይሰጋሉ። ከቀረጥ ነጻ ወደ አውሮፓ ገበዮች የመዝለቅ ዕድላቸውን ማጣት አይፈልጉም።

እናም የካሜሩኑን የፍራፍሬ ምርት ኩባንያ ባለቤት ዣን-ፒየር-ኤሚሌን የመሰለው ነጋዴ የሚፈልገው የአገሩ መንግሥት የብራስልስን ግፊት ተቀብሎ ውሉን እንዲፈርም ብቻ ነው። አለበለዚያ ከራሱ ክስረት ባሻገር መቶ ገደማ የሚጠጉት ሠራተኞቹና ከሺህ የሚበልጡት ምርት አቅራቢ ገበሬዎች ሥራቸውን ከማጣት ሊያመልጡ አይችሉም።

መሥፍን መኮንን

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic