የአውሮፓና የአፍሪቃ የንግድ ግንኙነት | ኤኮኖሚ | DW | 03.11.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአውሮፓና የአፍሪቃ የንግድ ግንኙነት

የዓለምን ንግድ ፍትሃዊ በማድረግ የታዳጊ ሃገራትን ልማት ለማፋጠን እ.ጎ.አ. በ 2001 ዓ.ም. ተጀምሮ የነበረው የዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ ድርድር መክሽፉና እስካሁን መልሶ ለማንሰራራት አለመቻሉ ይታወቃል።

default

ድርድሩን ያከሽፈው በተለይም የበለጸጉት መንግሥታት የእርሻ ምርቶቻቸውን በመደጎም የታዳጊውን ዓለም ገበሬ የፉክክር አቅም ከሚያዳክም የአሠራር ዘይቤያቸው አልላቀቅ ማለታቸውና ገበዮቻቸውንም በሚገባ ለመክፈት ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነበር። የበለጸጉት መንግሥታት በሌላ በኩል ከአካባቢ ቡድኖች ወይም ተናጠል ሃገራት ጋር የንግድ ሽርክና ማስፈኑን እንደ አማራጭ አድርገው ሲያራምዱ ቆይተዋል።
የዓለም ንግድ ድርጅት የዶሃ ድርድር ዙር መክሽፍ በተለይም የታዳጊ ሃገራት አምራቾች በበለጸገው ዓለም ገበዮች ላይ የተሻለ ድርሻ እንዲኖራቸው ያደርጋል ሲል ቀደም ሲል ተጥሎ የነበረውን ተሥፋ ከንቱ ነው ያደረገው። ምዕራባውያኑ መንግሥታት ለዚሁ ምትክ በመሻት ከዓለም ንግድ ድርጅት ውጭ ከአካባቢ ቡድኖች ወይም ተናጠል ሃገራት መዋዋሉን አማራጭ ካደረጉ ቆይተዋል።

ዋሺንግተን በማዕከላዊና ላቲን አሜሪካ አካባቢ የነጻ ገበያ ስምምነቶችን ለማስፈን የአውሮፓ ሕብረትም በብዛት የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቹ ከሆኑት ከአፍሪቃ፣ ከካራይብና ከሰላማዊው ውቂያኖስ አገሮች ጋር የኤኮኖሚ ሽርክና ውል ለመፈራረም መጣሩ አልቀረም። እርግጥ ለታዳጊዎቹ አገሮች በዓለም ንግድ ድርጅት ጥላ ስር የሚደረግ ስምምነት በበጀ ነበር። ተነጥሎ ሊጎዳ የሚችል አይኖርምና! የወቅቱ አዝማሚያ ግን የድርድር አቅማቸውን እንዳያሳንስ ለስጋት መንስዔ ሆኖ የቆየ ጉዳይ ነው።

የአውሮፓ ሕብረት ከ 78 የአፍሪቃ፣ ካራይብና ፓሲፊክ አገራት ጋር ለማስፈን የሚጥረው የኤኮኖሚ ሽርክና ስምምነት በሁለቱ ወገን መካከል የነጻ ንግድ ክልል ገሃድ መሆኑን ግቡ ያደረገ ነው። የውሉ መሠረት ከአሥር ዓመታት በፊት በሁለቱ ወገኖች መካከል ተፈርሞ የነበረው የኮቶኑ ውል መሆኑም ይታወቃል። የኤኮኖሚ ሽርክናው ውል ታዳጊዎቹ አገሮችም ገበዮቻቸውን ለአውሮፓ እንዲከፍቱ የሚጠይቅ ነው። ይህ ደግሞ ብዙዎቹን ታዳጊ አገሮች የምዕራቡ ምርት ማራገፊያ እንዳይሆኑ ስጋት ላይ መጣሉ አልቀረም። ለዚህም ነው ሕብረቱ ለምሳሌ ከምሥራቅ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ ጋር የሚያካሂደው ድርድር እንደሚያሳየው ከባድ ሆኖ የሚገኘው።

ኬንያን፣ ኡጋንዳን፣ ታንዛኒያን፣ ሩዋንዳንና ቡሩንዲን የመሰሉትን አምሥት ዓባል ሃገራት ያቀፈው የምሥራቅ አፍሪቃ የኤኮኖሚ ማሕበረሰብና የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሢዮን ባለፈው ሰኔ ወር ታንዛኒያ ርዕሰ-ከተማ አሩሻ ላይ ተሰብስበው ሶሥተኛ ድርድራቸውን አካሂደው ነበር። ሁለቱ ወገኖች በዚሁ ድርድር ስምምነቱን ለማጠናቀቅ ከሚያቀርብ ዕርምጃ መድረሳቸው በጊዜው ቢነገርም በተለይ የልማት ዕርዳታ ጉዳይ ገና ማሰሪያ ያላገኘ ነጥብ ነው። ስለዚህም የምሥራቅ አፍሪቃው የኤኮኖሚ ማሕበረሰብ ጠቅላይ ጸሐፊ ጁማ ምዋፓቹ ሰሞኑን እንደገለጹት የአውሮፓ ሕብረት ውሉ እንዲፈረም እስከመጪው ሕዳር ወር ያስቀመጠው የጊዜ ገደብ መጠበቁ የሚያጠራጥር ሆኗል።

ባለሥልጣኑ እንዳሉት እርግጥ ስምምነቱ መስፈኑ አይቀርም። በሌላ በኩል ግን በወቅቱ መሰናክል የሆኑት የንግድና የልማት ጉዳዮች እንዴት ማሰሪያ እንደሚያገኙ አይታወቅም። የበለጸገው ዓለም ነጻ የንግድ ክልሎችን ለማስፈን በሚጥርበት ጊዜ ታዲያ በመልማት ላይ የሚገኙት አገሮችም እርስበርሳቸው የሚያደርጉትን የአካባቢ ንግድ ማጠናከራቸው የሚበጅ እንደሚሆን ብዙዎች የኤኮኖሚ ጠበብት የሚሰነዝሩት አስተያየት ሆኖ ቆይቷል። እንደተባለውም ቀስ በቀስ ዕርምጃ መታየቱ አልቀረም።
ለምሳሌ በአፍሪቃና በሌሎች አዳጊ የዓለም አካባቢዎች መካከል የሚካሄደው የደቡብ ደቡቡ ንግድ ባለፈው አሠርተ-ዓመት ስኬታማ እየሆነ ነው የሚጣው። የምርቱ ንግድ በያመቱ በአማካይ ከ 12 በመቶ የበለጠ ዕድገት ይታይበታል። በበለጸገው ሰሜንና በደቡቡ ዓለም መካከል የሚካሄደው ንግድ ዕድገት በአንጻሩ ከዚሁ ግማሽ ያህል ቢሆን ነው። የደቡብ ደቡቡ ንግድ በሌላ ስሌትም የዓለም ንግድን ሰድሥት በመቶ ድርሻ ይይዛል። ዛሬ በተፋጠነ ዕድገት ላይ የሚገኙት ቻይናን የመሳሰሉት ሃገራት ተጽዕኖ እንግዲህ ዓለምአቀፉን የኤኮኖሚ ቀውስ ለማሽነፍም ወሣኝነት እንዳለው በግልጽ የሚታይ ነገር ነው።

ታዳጊ አገሮች የደቡብ ደቡቡን ንግድ በማስፋፋት ዕርምጃቸውን ለማጠናከር ቆርጠው እንደተነሱ ባለፉት ዓመታት በያጋጣሚው ታይቷል። ከዚህ ቀደም የተካሄዱት የአፍሪቃና የእሢያ፣ የደቡብ አሜሪካና የአረቡ ዓለም፤ እንዲሁም የአፍሪቃና የደቡብ አሜሪካ መሪዎች ጉባዔ ይሄው ፍላጎት የተንጸባረቀባቸው ነበሩ። በተለይ በአፍሪቃና በአሕጽሮት ብሪክ በመባል በሚጠሩት ራመድ ያሉ አገሮች ብራዚል፣ ሩሢያ፣ ሕንድና ቻይና መካከል የሚደረገው የንግድ ልውውጥ እ.ጎ.አ. ከ 1985 ዓ.ም. ወዲህ ከአሥር ዕጅ በላይ ነው የጨመረው።

በ 2007 ይሄው ንግድ ከ 256 ሚሊያርድ ዶላር በልጦ ነበር። ከጠቅላላው የአፍሪቃ ንግድ ቢነጻጸር 33 ከመቶውን ያህል ድርሻ የሚይዝ መሆኑ ነው። እርግጥ የአፍሪቃ ውስጣዊ ንግድ ዕድገት በጥቅሉ ከደቡብ ደቡቡ ሲነጻጸር ዝግታ የሚታይበት መሆኑ አልቀረም። በተመሳሳይ ጊዜ ሰባት በመቶ ገደማ ብቻ ነው ያደገው። በሌላ በኩል በምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ እሢያ የአካባቢው ውስጣዊ ንግድ ከጠቅላላው ከአርባ በመቶ የበለጠውን ድርሻ ይይዛል። እናም የተጣጣመ ሚዛን ለጊዜው ጎልቶ አይታይም። ይህም የአፍሪቃን ተጠቃሚነት ለጊዜውም ቢሆን ውሱን ወይም አጠያያቂ የሚያደርግ ነው።

በላቲን አሜሪካ ለደቡብ ደቡቡ የአካባቢ ንግድ መስፋፋት በተቀዳሚነት ግፊት ስታደርግ የቆየችው ብራዚል ናት። ብራዚልን ከሌሎች ታዳጊና ራመድ ካሉ አገሮች ጋር በተሻለ የንግድ መረብ ማስተሳሰሩ የተሰናባቹ ፕሬዚደንት የሉዊስ-ኢናሢዮ-ዳ-ሢልቫ ግብ ሆኖ ነው የቆየው። የቀድሞው የሙያ ማሕበር መሪ ቀደም ሲል በ 2004 የሣኦ-ፓውሎ የተባበሩት መንግሥታት የንግድ ጉባዔ የደቡቡ ዓለም ብሄራዊ ኤኮኖሚዎች በተሻለ ሁኔታ ሊጣጣሙ የሚችሉባቸውን አዳዲስ ጥርጊያዎች ለመክፈትና ትብብርን ለማራመድ እንደሚፈልጉ ነበር የተናገሩት።

የብራዚል ውጥን ከጊዜ በኋላ የታሰበውን ፍሬ መስጠቱም አልቀረም። ብራዚል አሁን ከሰሜኑ ዓለም ይልቅ ለታዲዎቹና በመራመድ ላይ ላሉት አገሮች የበለጠ ምርት ትሸጣለች። ከዩ.ኤስ.አሜሪካና ከጎረቤቲቱ አርጄንቲና ቀጥላ ሶሥተኛዋ ዋነኛ የንግድ ሽሪኳ ቻይና ናት። የብራዚል ኩባንያዎች ከቻይና ቀጥሎም በተለይ በአፍሪቃ ላይ አተኩረዋል። ፕሬዚደንት ሉዊስ-ኢናሢዮ-ዳ-ሢልቫ በሥልጣን ጊዜያቸው አፍሪቃን ከአሥር ጊዜ በላይ መጎብኘታቸው ፍላጎቱ ምን ያህል የጠነከረ እንደሆነ የሚያመለክት ነው። የአገሪቱ የውጭ ንግድና የመዋዕለ-ነዋይ አቅርቦት አራማጅ ተቋም አፔክስም ንግዱን ለማስፋፋት የሚያደርገውን ጥረት ሲያጠናክር ነው የቆየው።
ብራዚል ከሣሃራ በስተደቡብ ወደሚገኙት የአፍሪቃ አገሮች የምታስገባው ምርት ባለፉት አሥር ዓመታት በስምንት ዕጅ ገደማ ከፍ ብሏል። በወቅቱ መጠኑ ከአሥር ሚሊያርድ ዶላር ሲበልጥ ይህም ከብራዚል አጠቃላይ የውጭ ንግድ አምሥት በመቶው መሆኑ ነበር። እርግጥ ከአምሥት ሚሊያርድ የሚበልጠው የውጭ ንግድ የተካሄደው ከሶሥት አገሮች ከአንጎላ፣ ከደቡብ አፍሪቃና ከናይጄሪያ ጋር ነው። ሆኖም ሂደቱ በዚሁ ተወስኖ የሚቀር አይመስልም። ለብራዚል በተለይም በዓለምአቀፉ የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ የተነሣ በአፍሪቃና በእሢያ አዳዲስ ገበዮች መገኘታቸው የሚማርክ ሆኖ መገኘቱ አልቀረም።

ቻይና ለምሳሌ ሁለት ሶሥተኛውን ጥሬ ዕቃ ባቄላና ጥሬ ብረትን የመሳሰለውን ከብራዚል ስትገዛ ተሰርተው ያለቁ ምርቶችን ግን አትወስድም። በአንጻሩ ብራዚል ለአፍሪቃ የምትሸጠው ምርት በዓይነቱ ብዙ ነው። ሲሦው ብቻ ነው በጥሬ መልክ የሚላከው። ሁለት-ሶሥተኛው በአንጻሩ ተሠርቶ ያለቀ ምርት ነው። ይህም ከጨርቃ-ጨርቅ እስከ ቤት ዕቃና እስከ እርሻ ልማት መኪናዎች ብዙ ዓይነት ምርቶችን ይጠቀልላል። ለዚህም ምክንያት አልጠፋም።

አፍሪቃን ብንወስድ አህጉሪቱ ገና የራሷን ኢንዱስትሪ በሚገባ ማሳደግ አልቻለችም። ስለዚህም አፍሪቃውያን ከብራዚል የኢንዱስትሪ ምርቶችን በብዛት ይገዛሉ። ብራዚል ከመልክ-ምድራዊ ስሌት አንጻርም ለአፍሪቃ ቀረብ ያለችዋ አገር ናት። ከዚሁ በተጨማሪ አንጎላንና ሞዛምቢክን ከመሰሉት ፖርቱጋልኛ ተናጋሪ አገሮች ጋር ደግሞ ቋንቋውም አንድ ዓይነት ነው። ይህም ቀድሞ በተለይ ከሰሜኑ የኢንዱስትሪ አገሮች ይገዙ የነበሩ ምርቶችን በገበያ ላይ አቅርቦ መሸጡን ማቃለሉ አልቀረም። የወደፊቱ ሂደትም ተሥፋ ሰጭ ነው።

በአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም የብራዚል ዋነኛ የንግድ ሸሪክ አንጎላ ስትሆን ከዓለምአቀፉ ቀውስ በፊት በነበሩት ዓመታት ከፍተኛ የኤኮኖሚ ዕድገት ይጠበቅባት በነበረችው በነዳጅ ዘይት ሃብት የታደለች አገር ብዙ የብራዚል ኩባንያዎችም መዋዕለ-ነዋይ ያደርጋሉ። በከፊል በመንግሥት ዕጅ የሆነው ነዳጅ ዘይት አውጭ ኩባንያ ፔትሮብራስ ለምሳሌ በአንጎላ ጠረፍ ላይ በዘይት ፍለጋ ተግባር የተሰማራ ነው። ሌሎች ግዙፍ ፕሮዤዎችም አሉ። ብራዚል በሚቀጥሉት ዓመታት ከሞዛምቢክ ጋር ያላትን የንግድ ግንኙነትም በሰፊው እንደምታጠናክር ነው የሚጠበቀው። ከወዲሁ አንድ የብራዚል የማዕድን ኩባንያ በማዕከላዊው ሞዛምቢክ የሚገኝ የማዕድን ከሰል ለማውጣት 1,3 ሚሊያርድ ዶላር መድቦ እየሰራ ነው።

ለማንኛውም የደቡብ ደቡቡ ንግድ አሁንም ዓለምአቀፉ ቀውስ ባስከተለው ተጽዕኖ ሳቢያ ጫና እንደገጠመው ይቀጥላል። ለአካባቢው ንግድ አንዱ ድክመት እስከቅርቡ በተመሳሳይ ጥሬ ዕቃዎች ላይ ማተኮርና እንዲያም ሲል የፉክክሩ መጠናከር ሆኖ ቆይቷል። በነዚህ ሃገራት መካከል ያለው የንግድ ግንኙነት ትልቅ እመርታ ያደረገው በሕንድና በቻይና የተፋጠነ የኢንዱስትሪ ዕድገትና ይሄው ባስከተለው የፍጆት ፍላጎት መጨመር ነው። በሌላ በኩል በደቡቡም ዓለም ቢሆን እስካሁን የተገኘው ዕርምጃ ቀጣይነት እንዲያገኝ የቀውሱን ግፊት ጨርሶ ማሸነፉ ግድ ነው የሚሆነው።

መሥፍን መኮንን

ነጋሽ መሐመድ