የአውሮፓና የላቲን አሜሪካ ንግድ | ኤኮኖሚ | DW | 19.05.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአውሮፓና የላቲን አሜሪካ ንግድ

የአውሮፓ ሕብረትና ሜርኮሱር በመባል በሚታወቀው የጋራ ገበያ የተጠቃለሉት የደቡብ አሜሪካ መንግሥታት መሪዎች በነጻ ገበያ ውል ላይ የሚያካሂዱትን ንግግር ትናንት ስፓኝ ላይ እንደገና ጀምረዋል።

default

ውሉ ሰፍኖ አዲሱ የንግድ ክልል ቢፈጠር 800 ሚሊዮን ገደማ የሚጠጋ ሕዝብ ተጠቃሚ የሚሆንበት ነው። ሁለቱም ወገኖች ዓለምአቀፉን የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ለማስወገድ በሚያደርጉት ጥረት ገበዮቻቸውን ለመክፈትና የንግድ ግንኙነታቸውን ለማስፋፋት ይፈልጋሉ። የጋራው መርሆ ብዙ ንግድ፤ ያነሰ የገበያ እገዳ የሚል ሲሆን ጉባዔው በአጠቃላይ ለተሻለ የኤኮኖሚ ትብብር ተሥፋ ሰጭ ሆኖ ነው የታየው።

የአውሮፓ ሕብረትና የደቡብ አሜሪካ የጋራ ገበያ የሜርኮሱር ስብስብ ሃገራት የነጻ ንግድ ውል ለማስፈን እንደገና ለመነጋገር ተስማምተዋል። እርግጥ የአውሮፓ ሕብረት በተሰናከለው ንግግር ለመቀጠል ቢስማማም ገበሬዎቹ የላቲን አሜሪካን ርካሽ ስጋ በገበዮቻቸው ላይ መፍሰስ በመፍራት ለተቃውሞ እየተዘጋጁ ነው። በሌላ በኩል በዓለም ላይ ታላላቅ ከሚባሉት አንዱ በሆነው የንግድ ክልል ከሜርኮሱር ጋር የንግድ ውል ቢሰፍን የአውሮፓን ሕብረት ድርሻ ቁልፍ በሆኑት የላቲን አሜሪካ ገበዮች በብራዚልና በአርጄንቲና የሚያሰፋ ነው።

ሜርኮሱር በዓለም ላይ አምሥተኛ ታላቁን አጠቃላይ ብሄራዊ ምርት የሚይዝ ሲሆን ፓራጉዋይና ኡሩጉዋይን የመሳሰሉትን አገሮችም ይጠቀልላል። ሆኖም ፈረንሣይን ጨምሮ ሌሎች አሥር የሕብረቱ መንግሥታት አዲሱን ንግግር ሲቃወሙ ቆይተዋል። እነዚሁ እንደሚሉት የደቡብ አሜሪካው የጋራ ገበያ የሜርኮሱር የስጋ ንግድ የአውሮፓን አምራቾች ገቢ በያመቱ በ 6,3 ቢሊዮን ዶላር ሊቀንስ ወይም ይህንኑ ያህል ገቢ ሊያሳጣ የሚችል ነው። ይህን መሰሉ ክርክር ደግሞ ስምምነቱን ለአሠርተ-ዓመት ያህል አግዶ ሲቆይ ድርድሩ ከባድ ሆኖ መቀጠሉም የሚቀር አይመስልም።

የ 32 መንግሥታት መሪዎችን ያሰባሰበው አውሮፓ ሕብረትና የላቲን አሜሪካ ጉባዔ ለወትሮው ድብብዝ ገጽታ መለያው ሆኖ ለቆየው የስፓኝ የሕብረቱ የመንፈቅ ርዕስነት ዘመንም ጥቂትም ቢሆን ግርማ-ሞገስ ማላበሱ አልቀረም። ጠቅላይ ሚኒስትር ሆሴ-ሉዊስ-ዛፓቴሮ አገራቸው ከብዙዎቹ የላቲን አሜሪካ አገሮች ጋር አንድ ታሪክ፣ ባሕልና ቋንቋ እንደምትጋራ በመጥቀስ ስፓኝ በትራንስ-አትላንቲኩ ግንኙነት ላይ ያላትን አማካይ ሚና አስረግጠዋል። ዛፓቴሮ ይሄው ግንኙነት በተለይም በዛሬው የፊናንስና የኤኮኖሚ ቀውስ ወቅት ደግሞ ይበልጥ ጠቃሚ ነው ባይ ናቸው።

“ዛሬ ከተደቀነብን ዓለምአቀፍ ፈተና አንጻር ዓለምአቀፍ ተባባሪዎች ነን። አጽናፋዊ እየሆነች በሄደችው ዓለማችን ላይ ብልጽግና የሚገኘው ሃይልን በማስተባበር ብቻ ነው። በምድራችን ላይ ዛሬ ከኤኮኖሚ ዕድገትና ከጥሩ ማሕበራዊ ፖሊሲ ላይ መድረስ የሚቻለው በግልጽነትና በለዘብተኛ መርህ እንጂ ገደብ በማድረግ አይደለም”
ይህም በኤኮኖሚው ዘርፍ ነጻውን ንግድ ማስፋፋትና ገበዮችን የሚዘጉ አግባብ የለሽ መሰናክሎችን ማስወገድ ማለት ነው። በዚሁ የከፈታ ፖሊሲ መርህም ነው የአውሮፓ ሕብረት ከስድሥት የማዕከላዊ አሜሪካ አገሮች ጋር ለነጻ ንግድ ስምምነት የቀረበ የትስስር ውል የፈረመው።

የአውሮፓ ሕብረት ከዓለምአቀፉ የኤኮኖሚ ቀውስ ለማገገም በሚያደርገው ጥረት በላቲን አሜሪካ አዳዲስ ገበዮችን መፈለጉ እየጨመረ ሄዷል። የደቡብ አሜሪካ ክፍለ-ዓለም ድሃ፣ በፖለቲካ ያልተረጋጋና የዩናይትድ ስቴትስ ጓሮ ሆኖ የሚታይበት ጊዜ አልፏል። ቺሌንና ብራዚልን በመሳሰሉት አገሮች የዴሞክራሲ ስር መስደድ ምልክቶች የሚታዩ ሲሆን ላቲን አሜሪካ ዓለምአቀፉን ቀውስ በመቋቋም ረገድም አስደናቂ ጥንካሬ ነው ያሳየችው። የአካባቢው አገሮች ቀውሱን ለማቋቋም ፈጣን ዕርምጃዎችን ሲወስዱ የክፍለ-ዓለሚቱ አጠቃላይ ምርት በያዝነው ዓመት ከአራት በመቶ በላይ እንደሚያድግ የኢንተር-አሜሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚደንት ሉዊስ-አልቤርቶ-ሞሬኖ ይተነብያሉ።

አቅጣጫውም ሆነ ሕልሙ እንግዲህ በአጠቃላይ የዕድገት ነው። የቺሌው ፕሬዚደንት ሴባስቲያን ፒኒየራ ኤል-ፓይስ ለተሰኘው የማድሪድ ዕለታዊ ጋዜጣ እንዳስረዱት ላቲን አሜሪካ ከአስከፊ ድህነት የተላቀቀች፣ ለዕድገት ዕድልን የምትፈጥር፣ የለማች አካባቢ መሆን ያስፈልጋታል። ይህ የሌሎቹ ሜርካሱር አገሮች አመለካከትም ሲሆን የአውሮፓ ሕብረት ሩቡን የዓለም ንግድ ድርሻ በያዘው አካባቢ በቻይናና በዩናይትድ ስቴትስ ፉክክር ዕድሉን እንዳያጣ መፍራቱ አልቀረም። ለነገሩ የአውሮፓ ሕብረት በላቲን አሜሪም ዛሬም ታላቁ መዋዕለ-ነዋይ አቅራቢና ከአሜሪካ ቀጥሎ ሁለተኛው የንግድ ተለዋዋጭ ነው።
የላቲን አሜሪካና የካራይብ አገሮች ባለፈው 2009 ዓ.ም. በአውሮፓ ሕብረት የውጭ ንግድ ላይ የነበራቸው ድርሻ ስድሥት በመቶ ያህል ነበር። እያደገ በሄደው የጋራ ፍላጎት የተነሣም ትናንት ሃያ ሰባት ዓባላትን የጠቀለለው ሕብረትና ስድሥት የማዕከላዊ አሜሪካ አገሮች ንግድን ለማለዘብና ወደ አገር በሚገባ ምርት ላይ የሚጣል ቀረጥን ለመቀነስ ተስማምተዋል። ሕብረቱ ከፔሩና ከኮሎምቢያ ጋርም ተመሳሳይ ውል የሚፈራረም ሲሆን ስምምነቱ የሚሰፍነው የአውሮፓ ሕብረት የአንዴያን ማሕበሰብ ከተሰኘው የደቡብ አሜሪካ ድርጅት ጋር በሚያካሂደው ድርድር ጥላ ስር ነው።
እርግጥ ዓባላቱ ከሕብረቱ ጋር የሚደረግ ንግድ ይጥቀም አይጥቀም በሃሣብ የተከፋፈሉ ናቸው። ኤኩዋዶር ለምሳሌ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሪካርዶ ፓቲኖ እንደሚሉት አገራቸው በነጻ ንግድ ውል ብቻ መወሰን የምትሻ አይደለችም። እንደርሳቸው ከሆነ የልማት ግቧን እንድትጠብቅ የሚያስችል ስምምነትም የውሉ አካል ሊሆን ይገባዋል።

የአውሮፓ ሕብረትና የላቲን አሜሪካ ከመንግሥት ነጻ የሆኑ ድርጅቶች ደግሞ የማድሪዱን የመሪዎች ጉባዔ በሰብዓዊ መብትና በአካባቢ ተፈጥሮ ላይ በማተኮር ፈንታ ንግድን ብቻ የተመለከተ ነው ሲሉ ተችተዋል። ከነዚሁ መካከል የተወሰኑት ባወጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስገነዘቡት ጉባዔው ያለመው ለአውሮፓ ሕብረትና ለታላላቁ የላቲን አሜሪካ አምራቾች ብቻ ገበያን በመክፈቱ ላይ ነው። ለምሳሌ ኮሎምቢያ ከሕብረቱ ጋር ያደረገችው የነጻ ንግድ ስምምነት አንድ የአገሪቱ ግራ አዘንባይ የፖለቲካ ጥምረት እንደገለጸው ወተት ከአውሮፓ የሚገባ በመሆኑ የ 400 ሺህ ከብት አርቢዎች ቤተሰቦችን የሕልውና መሠረት የሚያሳጣ ነው።
ሰብዓዊ መብትና የንግድ ፍትሃዊነት ከተነሣ ጉባዔው በእርግጥ የንግድ ጉዳዮች ብቻ የተንጸባረቁበትም አልነበረም። ተሳትፎው የፖለቲካ ባህርዩን በግልጽ ነው ያሳየው። ለምሳሌ ግራ አዘንባዩ የቬኔዙዌላ ፕቴዚደንት ኡጎ ቻቬዝ አንዳች ምክንያት ሳይሰጡ ከስብሰባው ሲቀሩ የኩባው የሥልጣን አቻቸው ራውል ካስትሮም በጉባዔው ላይ አልተገኙም። ይህም ያለ ምክንያት አይደለም። የአውሮፓ ሕብረት ከኩባ ጋር መልሶ ንግግር ለመጀመር የሰብዓዊ መብት ከበሬታን ቅድመ-ግዴታ እንደሚያደርግ የውጭ ጉዳይ ተጠሪው ካትሪን ኤሽተን በማያሿማ ሁኔታ ነው ያስገነዘቡት።

“ግልጽ ነው ኩባ የሰብዓዊ መብት ጥያቄዎችን በተመለከተ ሁኔታውን እንድታሻሽል እንፈልጋለን። ባለፉት ወራት ስጋት ላይ ጥለውን የቆዩትን ነገሮች ለርሷ ማስታወስ የለብኝም። ግን በማንኛውም በምናደርገው ግንኙነት ላይ ሁሌም ስናገረው የነበረ ነው ግንኙነቱን መልሰን መላልሰን በአዲስ መልክ መመዘን ይኖርብናል”

Lateinamerika Gipfel Madrid EU

የስፓኝ መንግሥት በበኩሉ ከኩባ ጋር የሚደረገው ንግግር ያላንዳች ቅድመ-ግዴታ እንዲካሄድ ግፊት ማድረጉ አልቀረም። ግን ስኬት ሊያገኝ አልቻለም። በሌላ በኩል የዴሞክራሲው ጥያቄ የአውሮፓ ብቻ ሣይሆን የላቲን አሜሪካም ነው። ይህንኑም ከሀለት ዓመት በፊት ያለፈውን የአውሮፓ ሕብረትና የካቲን አሜሪካ የመሪዎች ጉባዔ ያስተናገዱት የፔሩው ፕሬዚደንት አላን-ጋርሢያ-ፔሬዝ ግልጽ አድርገዋል።

“በመሆኑም የዚህ ጉባዔ መልዕክት የዴሞክራሲ ነው። ነጻነትን በዘመኑ አስፈላጊ መሆኑን ያመለክታል። ማለት ዴሞክራሲ በሕዝቦቻችን መካከል፤ ዴሞክራሲ በየአገራችን ውስጥ! ይህም በሁላችንም አገሮች የሥልጣን ክፍፍል፣ ነጻ ፕሬስ፣ ነጻ ፓርቲዎች፣ ነጻ ምርጫ መኖር ማለት ነው። ይህ አንዱ የውይይታችን መስፈርትም ይሄው ሊሆን ይገባዋል”

በጉባዔው ላይ ተናጠል የሁለት አገሮች ችግር መነሣቱም አልቀረም። ለምሳሌ የአርጄንቲናዋ ፕሬዚደንት ክሪስቲና ፌርናንዴዝ-ዴ-ኪርሽነር ለአዲሱ የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለዴቪድ ካሜሮን ከሰላሣ ዓመታት በፊት በፋልክላንድ ወይም ማልቪን በመባልም በሚታወቁት ደሴቶች የተካሄደውን ጦርነት አስታውሰዋል።

“እባክዎን በማልቪን ደሴቶች ሉዓላዊነት ላይ ድርድራችንን እንደገና እንጀምርና በዚሁ የተባበሩት መንግሥታት በጉዳዩ ያስተላለፉትን ገና በሥራ ላይ ያልዋለ የ 1965 ውሣኔ ገቢር እናድርግ። እኛ ሰላም ፈላጊ አገር ነን”

ችግሩ ካሜሮን ማድሪድ ላይ አለመገኘታቸውና መልዕክቱ ወይም ጥሪው አለመድረሱ ላይ ነው። ያም ሆነ ይህ የአውሮፓ ሕብረት ሸንጎ ርዕስ ሄርማን-ፋን-ሮምፑይ እንደገለጹት የሚቀጥለው የነጻ ንግድ ስምምነት ድርድር ተከታይ ዙር ለፊታችን ሐምሌ ወር መጀመሪያ ገደማ ታስቧል።

MM/DW/dpa

Negash Mohammed

ተዛማጅ ዘገባዎች