የአውሮጳ የኃይል አቅርቦት ቀውስና መዘዙ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 26.07.2022
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮጳ የኃይል አቅርቦት ቀውስና መዘዙ

ሩስያ ወደ አውሮጳ የምታስተላልፈውን ጋዝ መጠን እንደምትቀንስ ማሳሰቧ በሩስያ ዩክሬን ጦርነት ሰበብ የጋዝ አቅርቦት ቀውስ ለገጠማቸው የአውሮጳ ሀገራት በተለይም ለጀርመን ተጨማሪ ስጋት ሆኗል።ሩስያ ወደ አውሮጳ የምልከውን ጋዝ ከነገ ጀምሮ እቀንሳለሁ ማለቷ ሌሎች በርካታ ኪሳራዎችና ተጽእኖዎችም ማድረሱ አይቀርም። ይበልጥ ተጎጂዋ ደግሞ ጀርመን ናት።

የአውሮጳ የኃይል አቅርቦት ቀውስና መዘዙ

በሩስያ ዩክሬን ጦርነት ሰበብ በአውሮጳ የተከሰተው የኃይል አቅርቦት ቀውስ በዚህ ሳምንት ተባብሶ ቀጥሏል። ግዙፉ የሩስያ የነዳጅ አምራችና ሻጭ ኩባንያ ጋዝፕሮም እስካሁን ወደ አውሮጳ ሲያስተላልፍ የነበረውን ጋዝ መጠን ከነገ ጀምሮ እንደሚቀንስ አስታውቋል። ጋዝፕሮም እንዳለው ኖርድ ስትሪም አንድ በተባለው የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር እስካሁን ወደ አውሮጳ ሲያከፋፍል  የቆየውን ጋዝ ከነገ ረቡዕ ጀምሮ በፊት ይልክ ከነበረው መጠን ወደ 20 በመቶ ዝቅ ያደርጋል። አውሮጳ ለመጪው ክረምት ጋዝ ለማከማቸት ጥረት በሚያደረግበት በዚህ ወቅት ላይ ሩስያ አስቀድማ ጋዙ ይቀነሳል ማለቷ፣ለአውሮጳ በተለይ ለጀርመን ዱብ እዳ  ሆኗል። በእስካሁኑ ስጋት ላይ ይህ ሲጨመር መስመሩን ከነአካቴው እንዳትዘጋውም እየተፈራ ነው። የሩስያው መንግሥት የሚያስተዳድረው የጋዝፕሮም ኩባንያ  ትናንት በትዊተር እንዳስታወቀው እርምጃው ተግባራዊ ሲሆን  በጋዝ ማስተላለፊያ መስመሩ በቀን ወደ አውሮጳ የሚላከው ጋዝ 33 ሚሊዮን ኩቢክ ሜትር ብቻ ነው የሚሆነው።ይህም ከዚህ ቀደም ሩስያ በዚሁ መስመር ትልከው ከነበረው ጋዝ አንድ አምስተኛው ብቻ ነው። 

ኩባንያው  ጥገና ያስፈልገዋል ያለው  አንድ ተርባይን ስራ ስለሚያቆም የሚላከው ጋዝ ይቀንሳል ። ይህም የነዳጅ ዋጋ ከእስካሁኑ በጣም እንዲንር  አድርጓል።ጀርመን የተማሩት የመርሰዲስ ቤንዝ ኩባንያ ባልደረባ የምጣኔ ሀብት ምሁር ዶክተር ጸጋዬ ደግነህ ለዶቼቬለ እንደተናገሩት ሩስያ ወደ አውሮጳ የምልከውን ጋዝ መጠን ከነገ ጀምሮ እቀንሳለሁ ማለቷ ሌሎች በርካታ ኪሳራዎችና ተጽእኖዎችም ማድረሱ አይቀርም። ዶክተር ፀጋዬ ለእረፍት ከሄዱባት ከስዊድን ለዶቼቬለ በስልክ እንደተናገሩት ከሁሉም ይበልጥ ተጎጂዋ ደግሞ ጀርመን ናት።
እንደ ዶክተር ጸጋዬ ይህ ደግሞ ተያያዥ ምጣኔ ሀብታዊ አንድምታዎች ይኖሩታል። ከዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ዩሮ ተዳክሟል። ከዩክሬኑ ጦርነት በኋላ የዩሮ የመግዛት አቅም መዳከም «የአንዱ ቤት ሲቃጠል ሌላው መብራቱ ነው እንደሚባለው ለዶላር ጠቅሟል። ሩስያ የምትልከው ጋዝ የሚቀንስበት ምክንያት  ወደ አውሮጳ ጋዝ የምትልክበት  ኖርድ ስትሪም አንድ የተባለው ጋዝ ማስተላለፊያ መስመር አንድ ተርባይን ለጥገና ከሄደበት ካናዳ እስካሁን አለምመምጣቱ መሆኑን ተናግራለች። ሌላ ሁለተኛ ተርባይንም ችግሮች እየታዩበት ነው ብላለች ሩስያ ።የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በሩስያ ላይ የተጣሉት ማዕቀቦች የኖርድ ስትሪም አንድን ስራ አስቸጋሪ አድርገውታል ሲሉም ችግሩን በማዕቀብ ጣዮቹ አላከዋል። ይህን ግን ኅብረቱም ሆነች ጀርመን  አይቀበልም። ሩስያ የጋዝ አቅርቦትን እንደ መያዣ እየተጠቀመች እያታለለችንም ነው እያሉ ነው። 
በሩስያ ጋዝ ቅነሳ ላይ ዛሬ የመከሩት የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት መንግሥታት ወደፊት ከሩስያ በኩል ሊያጋጥም የሚችል ተጨማሪ የጋዝ አቅርቦት ቅነሳን ለመቋቋም፤ በክረምቱ ወራት ጋዝ በቁነና ለማከፋፈል ዛሬ ተስማምተዋል።የህብረቱ አባል ሀገራት የኃይል ሚኒስትሮች ከመጪው ነሐሴ እስከ መጋቢት ድረስ የጋዝ ፍላጎታቸውን መጠን በ15 በመቶ ለመቀነስ ያለመ ረቂቅ ሕግ አጽድቀዋል። ይህ ለችግሩ የታቀደ ጊዜያዊ መፍትሄ ነው ግን ችግሩ የሚቀጥል ከሆነ ሌሎች መዘዞችንም ማስከተሉ አይቀርም ይላሉ ዶክተር ፀጋዬ።

ሩስያ ወደ ተቀረው አውሮጳ  የምትልከውን ጋዝ መጠን የምትቀንሰው መስመሩ ለጥገና ተብሎ እስካለፈው ሐሙስ ድረስ ለ10 ቀናት ተዘግቶ በተከፈተ በአምስት ቀኑ መሆኑ ነው። በ«ኖርድ ስትሪም አንድ» መስመር የሚመጣው ጋዝ ለ10 ቀናት ተቋርጦ እንደገና ስራውን  ከጀመረ በኋላ ጀርመን የምታገኘው ጋዝ ወደ 40 በመቶ ዝቅ ብሎ ነበር። የአሁኑ ቅነሳ ሲታከልበት ደግሞ  የጋዝ አቅርቦቱ በግማሽ ይቀንሳል ተብሏል። ጋዝ ለኢንዱስትሪዎች ማንቀሳቀሻ ለኤሌክትሪክ ማመንጫ እና በክረምት ደግሞ ለቤቶች ማቆምያ ጥቅም ላይ ይውላል።በተለይ በጥቅምት ገደማ ለሚጀምረው የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ከባድ ክረምት በቂ ጋዝ ካልተከማቸ  ክፍለ ዓለሙ ለኤኮኖሚ ዝግመት ይዳረጋል የሚሉ ስጋቶች እየተሰሙ ነው። በዚህ የተነሳም በክረምቱ ወራት ጋዝን በራሽን  ማከፋፈል ግድ ሆኗል።እንደ ቼክ ሪፐብሊክ ያሉ የአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት የሩስያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን  ፣የጋዝ አቅርቦትን እንደ ማስፈራሪያ በመጠቀም  «ቆሻሻ» ሲሉ የጠሩትን ጨዋታቸውን መቀጠላቸው እንደማይቀር እያስጠነቀቁ ነው። 

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ
 

Audios and videos on the topic