የአውሮጳ ኅብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ዘገባ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 09.07.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮጳ ኅብረት የኢትዮጵያ ልዑክ ዘገባ

የአውሮጳ ኅብረት በኢትዮጵያ ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት ባደረገው ቅኝት መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ የግዳጅ ሰፈራ አለመኖሩን አመለከተ። ዶቼቬለ ያነጋገራቸዉ የአውሮጳ ኅብረት የኢትዮጵያ ልዑክ መሪ አምባሳደር ዣቪየር ማርሻል ፤ ኅብረቱ ከኢትዮጵያ ጋር ባለ ሶስት አምዶች የልማት ትብብር እንዳለውም ገልፀዋል።

ለሰብዓዊ መብቶች የሚሟገቱ ተቋማት በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ለልማት በሚል ነዋሪዎችን ከቦታቸው በማንሳት የግዳጅ ሰፈራ ይፈፅማል ሲሉ መግለፃቸው የሚታወቅ ነው።

የአውሮጳ ኅብረት በኢትዮጵያ ባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት ባደረገው ዳሰሳ መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ የግዳጅ ሰፈራ አለመኖሩን በዘገባው አስታወቀ። እንደ ሂውማን ራይትስ ዎች ያሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ግን የኢትዮጵያ መንግስት ለልማት በሚል የግዳጅ ሰፈራ እያካሄደ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ። የአውሮጳ ኅብረት በኢትዮጵያ የግዳጅ ሰፈራ አለመኖሩን የገለፀው «ሠብዓዊ መብቶች እና ዲሞክራሲ በዓለማችን 2011» በተሰኘው ዘገባዉ ነው። የአውሮጳ ኅብረት የኢትዮጵያ ልዑክ መሪ አምባሳደር ዣቪየር ማርሻል ከነባልደረቦቻቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ይህን ለማጣራት ቅኝት እንዳደረጉ ገልፀዋል፥

«እንግዲህ ባደረግኩት ማጣራት የሰፈራ መርሃ-ግብር አለ። እዚህ ጋ ማለት የምፈልገው፤ ለእኔ የኢትዮጵያ መንግስት ሰዎዝን ከአንዶ ስፍራ ሌላ ቦታ ማስፈር ፍፁም ሕጋዊ ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ሰዎችን በግዳጅ እንደማያሰፍር ይገልፃል። እናም ያን ተከትሎ የተባለው እውነት ነው ወይንስ ሐሰት የሚለውን ለማጣራት የተለያዩ ውይይቶች ይኖራሉ። ሂውማን ራይትስ ዎች አንድ ነገር ሊል ይችላል፤ የእኛ የለጋሾች ማጣራት ደግሞ ትንሽ ለየት ያለ ነው።»

አምባሳደሩ የአውሮጳ ኅብረት የልዑካን ቡድን ሁኔታዉን በጋምቤላ እና ቤንሻንጉል አካባቢዎች እንዳጣራም አመልክተዋል። በማጣራቱ ሂደት ራሳቸው ጭምር ከአንድ ዓመት በፊት በቦታው እንደተገኙም አክለዋል። መቀመጫውን ኒውዮርክ ያደረገው የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች ግን አሁንም ድረስ የግዳጅ ሰፈራ በኢትዮጵያ እንደሚከናወን  ዘግቧል። የኢትዮጵያ መንግስት በታችኛው የኦሞ ሸለቆ የሚገኙ ከ5000 እስከ 10 000 የሚጠጉ ነዋሪዎችን ከመኖሪያቸው በግዳጅ እንዳስነሳ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪው ድርጅት በቅርቡ አስታውቋል። መንግስት ሰዎቹን ከቦታቸው ያስነሳቸው  100 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ  መሬትን ለሰፋፊ እርሻ ልማት ለመጠቀም በሚል እንደሆነም ድርጅቱ ገልጿል። የአውሮጳ ኅብረት የኢትዮጵያ ልዑክ አምባሳደር ዣቪየር በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት አያያዝ ላይ ከመንግስት ጋር ተነጋግረው እንደሆን ተጠይቀው ሲመልሱ በእርግጥም ጉዳዩን አንስተው እንደተነጋገሩበት እና እንደሚነጋገሩበትም አብራርተዋል። ከመንግስት ጋር በሚደረጉ ዉይይቶች ደግሞ በዋናነት የንግግራችን ማዕቀፍ የኮቶኑ ስምምነት ነው ሲሉም አክለውበታል፣

Karte Äthiopien englisch«ከኢትዮጵያ መንግስት ጋ በመሰረቱ 3 አምዶች ያሉት ሰፊ ግንኙነት ነው ያለን።  የመጀመሪያው የልማት ትብብር ነው። ሁለተኛው ፖለቲካዊ ግንኙነት ሲሆን፤ ሶስተኛው የንግድ ግንኙነት ነው። ያ በኮቶኑ ስምምነት ላይ ተቀምጧል። ስለዚህ የእኔ እና የአውሮጳ ኅብረት ባልደረቦቼ ተግባር መሰረታዊ ማዕቀፍ በሆነው በኮቶኑ ስምምነት መሠረት፤ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋ ያለንን የትብብር ማዕቀፍ፤ በተቻለ መጠን ጥሩ በሆነ መልኩ እንዲሁም በሀቅ ተግባራዊ ማድረግ ነው።»

የኮቶኑ ስምምነት በአፍሪቃ፣ ካሪቢያን፣ ፓሲፊቅ ሀገራት እና በአውሮጳ ኅብረት ማኅበረሰብ እና  አባል የተፈረመ የትብብር ስምምነት ነው።  የስምምነቱ አንቀፅ ስምንት የትብብር ስምምነት በፈፀሙት ወገኖች መካከል የሚገኘውን የፖለቲካ ጉዳዮች ይመለከታል። አንቀፁ በተባባሪ ሀገራት መካከል የሚገኝ የሰብአዊ መብት አያያዝ፣ የዲሞክራሲ መርሆች እና የመልካም አስተዳደር መሻሻልን አንስቶ መደበኛ ንግግር ያደርጋል ይላል። በዚህ መሰረት ታዲያ ልዑኩ በፀረ ሽብር ህግ ተከሰዉ ጥፋተኛ በተባሉት በእነ አቶ አንዱአለም አራጌ እና ጋዜጠኞች ጉዳይ ላይ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ጋር ተነጋግሮ እንደሆን ተጠይቀው ሲመልሱ፥

«በዚያ ጉዳይ ከመንግስት ጋር እየተነጋገርን ነው። በእነ አንዷለም ላይ ባለፈው በአቃቤ ህግ የቀረበውን የፍርድ ውሳኔ ሀሳብ ከሆነ ያ በሂደት ላይ ያለ፣ ያልተጠናቀቀ ነገር ነው። ምክንያቱም ገና ፍርድ አልተሰጠም። ስለዚህ ፍርዱ ስላልተጠናቀቀ ቢያንስ በይፋ ይህ ነው ብዬ አልናገርም።»

«ሠብዓዊ መብቶች እና ዲሞክራሲ በዓለማችን 2011» የተሰኘው የአዉሮጳ ኅብረት ዘገባ የኢትዮጵያ መንግስት የጀመረው የ5 ዓመቱ የልማት መርሀ ግብር አቅምን ለመገንባት እና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ያለመ እንደሆነ ይገልፃል። ይህ፤ መንግስት ሲቪል ማኅበረሰባት እንዲጠናከሩ እና መልካም አስተዳደር እንዲጎለብት መቁረጡን እንደሚያመለክትም ዘገባው አመልክቷል። ይሁንና የአውሮጳ ኅብረት በኢትዮጵያ የሠብዓዊ መብት አያያዝ እና የሲቪል ማኅበረሰባትን እንቅስቃሴ በሚመለከት የወጣው ህግ ሳያሳስበው እንዳልቀረ አስታውቋል። ያም በመሆኑ ኅብረቱ፤ የኢትዮጵያ መንግስት፣ ለጋሾች እና ሲቪል ማኅበረሰባትን ያሳተፈ የሶስትዮሽ ንግግር መጀመሩንም ገልጿል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 09.07.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15UFg
 • ቀን 09.07.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/15UFg