የአውሮጳ ኅብረት፡ የአፍሪቃ፡ የካሪቢክና የፓሲፊክ ሀገሮች ውይይት | ኤኮኖሚ | DW | 06.02.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአውሮጳ ኅብረት፡ የአፍሪቃ፡ የካሪቢክና የፓሲፊክ ሀገሮች ውይይት

የአውሮጳ ኅብረት በነገው ዕለት በሞሪሸስ ደሴት ውስጥ ከአሥራ ስድስት የደቡባዊ እና የምሥራቃዊ አፍሪቃ ሀገሮች ጋር ሁለተኛውን ዙር ድርድር ይጀምራል። በኅብረቱ የንግድ ተጠሪ ፓስካል ላሚ የሚመራው የነገው ድርድር የኅብረቱ አባል ሀገሮች ገበያዎችን ለአዳጊዎቹ ሀገሮች ምርት በተቻለ መጠን ክፍት የማድረጉንና የደቡብ ደቡቡን የልማት ትብብር የማጠናከሩን ዓላማ ይዞ ተነሥቶዋል።

የአውሮጳ ኅብረት እአአ በ 2000 ዓም በአህፅሮት ኤ ሲ ፒ በሚል መጠሪያ ከሚታወቁት ሰባ ዘጠኝ የአፍሪቃ፡ የካሪቢክ እና የፓሲፊክ አካባቢ ሀገሮች ጋር በተፈራረመው የኮቶኑ ውል መሠረት ከነዚሁ አዳጊ ሀገሮች ጋር በየተራ በሚያካሂዳው ድርድር የኤኮኖሚ ጉድኝት ውል የመፈረም ዓላማ አለው። ኅብረቱ ከምዕራባውያኑና ከማዕከላውያኑ የአፍሪቃ መንግሥታት ጋር ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ ድርድር ማካሄዱን ቀጥሎዋል። አውሮጳውያኑ ተደራዳሪዎች የኅብረቱን አባል ሀገሮች ገበያዎች ለአዳጊዎቹ ሀገሮች ምርቶች ነፃ ለማድረግ ከጀመሩት ጥረታቸው ጎንም፡ በራሳቸው በአፍሪቃውያኑ መንግሥታት መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ተነሣሥተዋል። በአፍሪቃ እና በአውሮጳ መካከል የሰሜን ደቡቡ ትብብር ድርድር ከመጀመሩ በፊት፡ በእሪቃውያቱ ሀገሮች መካከል ያካባቢው ኅብረቶች የሚቋቋሙበት ሂደት አዎንታዊ ውጤት እንደሚያስገኝ መታመኑን የገለፁት የኅብረቱ ተጠሪ ማርቲን ዲም ሲያስረዱ እንዲህ ይላሉ። « ትልቁ ትኩረት የተሰጠው ርዕስ ያካባቢ ትብብር ነው። ለልማቱ መስክ የወደፊቱን ዕጣ ለማሳመር ወሳኙ ቃል ውኅደት ነው። የአካባቢ ውኅደትን በማነቃቃትየመዋቅር ታማኝነትንና የመንግሥታት መልካም አመራርን ለማጠናከር ይቻላል። ይህም በበኩሉ ለብዕላን አማላዩን ሁኔታ ይፈጥራል። የልማት እና የኤኮኖሚ ዕድገትንም ለማስገኘት ወሳኙ ድርጊት ውኅደት ነው።»
የአውሮጳ ኅብረት እና የአፍሪቃ፡ የካሪቢክ እንዲሁም የፓሲፊክ አካባቢ ሀገሮች እአአ እስከ 2008 ዓም ድረስ የኤኮኖሚ ጉድኝቱ ውል ይፈረማል ብለው ተስፋ አድርገዋል። እስከዚያም ድረስ በተለያዩት የአፍሪቃ አካባቢዎች መካከል ነጻዎቹ የንግድ ዞኖች ቢቋቋሙ መልካም እንደሚሆን የኅብረቱ ተጠሪ አስረድተዋል። ነገ በሞሪሸስ በሚጀመረው ድርድር ላይ ባለፈው መስከረም ወር በካንኩን ሜክሲኮ ካላንዳች ውጤት ለተበተነውና ወደፊት አዲስ ድርድር ለሚያደርገው የዓለም ንግድ ድርጅት ስብሰባ ጠቃሚ ሀሳቦችን ሊያፈልቅ ይችላል ተብሎ ተገምቶዋል።
ሁለት መቶ ሰማንያ ሚልዮን ሕዝብ የሚኖርባቸው አሥራ ስድስቱ የምሥራቃዊውና ደቡባዊው የጋራ ገበያ አባል ሀገሮች፡ ማለትም፡ ቡሩንዲ፡ ኮሞሮ ደሴቶች፡ ጅቡቲ፡ ኤርትራ፡ ኢትዮጵያ፡ ኬንያ፡ ማዳጋስካር፡ ሞሪሸስ፡ ርዋንዳ፡ ሴይሼልስ፡ ሱዳን፡ ዩጋንዳ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ እአአ እስከ 2004 መጨረሻ ድረስ ከአውሮጳ ኅብረት ጋር የጉድኝቱን ውል ለመፈራረም ነው የሚሹት። ኅብረቱ ከደቡብ አፍሪቃ ጋር ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ የንግድ ውል ተፈራርሞዋል። ሌሎቹ የደቡባዊ አፍሪቃውያት ሀገሮችም የበኩላቸውን የንግድ ውል የመፈራረም ፍላጎት አጉልተዋል። የአውሮጳ ኅብረት የንግድ ተጠሪ ፓስካል ላሚና የልማት ተጠሪ ፖል ኒልሰን ከሁለት ሣምንታት በፊት በአዲስ አበባ ከአፍሪቃውያን መንግሥታት ንግድ ሚንስትሮች ጋር በሚያካሂዱት ዓቢይ ጉባዔ የጉድኝቱ ውል ፍረማ በሚፋጠንበት ጉዳይ ላይ ይመክራሉ።