የአውሮጳ ኅብረት እና የአረብ ሊግ ጉባኤ  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 26.02.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮጳ ኅብረት እና የአረብ ሊግ ጉባኤ 

ይህ ጉባኤ ከመተዋወቂያ መቀራረቢያና ከሐሳብ መለዋወጫ መድረክነት ባለፈ የፈየደው ይኽ ነው የሚባል ነገር የለም የሚል ትችት ቀርቦበታል። አስቀድሞም ቢሆን የሁለቱ ወገኖች የመጀመሪያ ጉባኤ ተጨባጭ በሆኑ ፖለቲካዊ ርምጃዎች ላይ ስምምነት ላይ ይደረሳል ተብሎ አልተጠበቀም። ይህ ባይሆንም ቢያንስ ሁለቱን ወገኖች በሚጎዱ ቀውሶች ላይ መነጋገር ግን ችሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:50

የአውሮጳ ኅብረት እና የአረብ ሊግ ጉባኤ 


የአውሮጳ ኅብረት እና የአረብ ሊግ መሪዎች በአንድ ላይ ጉባኤ ሲቀመጡ የሻርምኤል ሼክ ግብጽ የመጀመሪያቸው ነው። 40 የሚሆኑ የአውሮጳ ኅብረት እና የአረብ ሊግ አባል ሃገራት መሪዎች በተገኙበት በዚህ ጉባኤ ሁለቱ ወገኖች የጋራ ተግዳሮቶቻቸውን በጋራ ጥረት መፍታት እንደሚገባ ተስማምተዋል። በዚሁ የመጀመሪያው ጉባኤያቸው ማብቂያ  ባወጡት የጋራ መግለጫም በተለያዩ መስኮች አዲስ የትብብር ምዕራፍ ለመጀመር ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል። ከትናንት በስተያ አንድ ብለው የጀመሩትን ጉባኤም በቋሚነት ለማካሄድም ተስማምተዋል። ትናንት ሲለያዩ ይፋ እንደተደረገውም ቀጣዩን ጉባኤ የዛሬ 3 ዓመት ብራሰልስ ቤልጅየም ለማካሄድ ቀጠሮ ይዘዋል። የሁለት ቀናቱ የሁለቱ ማህበራት ጉባኤ ከተነጋገረባቸው ጉዳዮች መካከል ፍልሰት ሽብር እና ንግድ ይገኙበታል። የጉባኤው አስተናጋጅ የግብጹ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ጉባኤውን የከፈቱት ግን በአሸባሪነት ላይ በጋራ ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ጥያቄ አዘል ጥሪ በማቅረብ ነበር። 
«አሸባሪነትን ለመዋጋት ሁሉን ያካተተ የትግል ስልት ላይ የመስማሚያው ጊዜ አልደረሰምን? አሸባሪ ቡድኖችን በፀጥታ ጥበቃ ፊት ለፊት  መጋፈጥ አሸባሪነትን መዋጊያ ዋነኛው መንገድ ነው። ይህ ውጊያ ታዲያ ርዕዮተ ዓለማቸውን በሐሳብ መዋጋትንም ይጨምራል። ከዚህ ሌላ ለነርሱ የሚሰጥ የገንዘብ እና ሌሎች ድጋፎችን ማስቆምም አስፈላጊ ነው።»
አልሲሲ በመላው ዓለም እንደ ወረርሽኝ ተዛምቷል ያሉትን አሸባሪነት ለመዋጋት በህብረት ከመቆም ውጭ ሌላ አማራጭ እንደማይኖር ለጉባኤተኞቹ ተናግረዋል። ከቅርብ ወራት ወዲህ በኢራቅ እና በሶሪያ ከባድ ሽንፈት የገጠመው ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው ቡድን ርዝራዦች  በአውሮጳ እና በመካከለኛው ምሥራቅ የአጸፋ ጥቃት ሊፈጽሙ ይችላሉ የሚል ስጋት አለ።

ይህም በፀረ ሽብሩ ትግልም ሆነ በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሁለቱንም ወገኖች የጋራ ትብብር አስፈላጊነትን የሚያጎላ ሆኖ ተገኝቷል። የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ቱስክ እንዳሉት ደግሞ አሸባሪነትን ጨምሮ ሁለቱ ወገኖች በጋራ ሊቋቋሟቸው የሚገቡ ሌሎች በርካታ ተግዳሮቶች አሉ። 
«የአረቡ ዓለም እና የአውሮጳ አጋርነት እውን መሆን ያለበት ወቅት አሁን ነው። እኛ ተመሳሳይ የሆኑ በርካታ ተግዳሮቶችን እየተጋፈጥን ነው። ከመልክዐ ምድራዊ ፖለቲካ አንጻር ሲታይ እንዲያውም ይበልጥ አደገኛ እና  አለመረጋጋትም የሚታይበት ነው። ከመካከላቸው ዓለም አቀፍ የጸጥታ ቀውሶችን እና አሸባሪነትን፣ የአየር ንብረት ለውጥ እና የበርካታ ሰዎች መፈናቀልን መዋጋት እንዲሁም አስተማማኝ ባለሆነው የዓለም  ምጣኔ ሀብት ለዘላቂ እድገት እና ለኢንቬስትመንትን ዋስትና መፍጠር ከጋራ ተግዳሮቶቻችን መካከል ይጠቀሳሉ።»
የሁለቱ ወገኖች የጋራ ተግዳሮት ከሆኑት ውስጥ ፍልሰት አንዱ ነው። በጎርጎሮሳዊው 2015 አውሮጳ ከገቡት ስደተኞች አብዛኛዎቹ ሶሪያውያን ናቸው። ጦርነት ከሚካሄድባት ከሶሪያም ሆነ ከሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ እና የአፍሪቃ ሃገራት ወደ አውሮጳ የተሰደዱ እና የመሰደድ ሙከራም የሚያደርጉ ብዙዎች ናቸው። የአውሮጳ ህብረት በሊቢያ እና በቱርክ በኩል ወደ አውሮጳ የሚካሄድ ፍልሰትን ለመግታት ከቱርክ እንዲሁም የተመድ ድጋፍ ካለው የሊቢያ መንግሥት ጋር የትብብር ስምምነቶች አድርጓል። በሻርም ኤልሼኩ ጉባኤ ፍልሰት ትኩረት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱ  ነበር። የሉክስምበርጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዣቭየ ቤትል በተለይ ፍልሰት እና ከፍልሰት ጋር የተያያዙ ችግሮች የአውሮጳ ህብረትም ሆነ የአረብ አገራት በሃላፊነት መፍትሄ ሊፈልጉለት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አሳስበው ነበር።

«እዚህ የመጣሁት ምን እንደሚሰሩ ልናገር አይደለም። እነርሱም ምን መስራት እንዳለብኝ መንገር የለባቸውም። ሆኖም ለሶሪያ የጋራ መፍትሄዎችን መፈለግ አለብን። ሁሌም ግጭት አለ። ብዙ ወጣቶች ሀገራቸውን ለቀው ይሸሻሉ። ለጉዳዩ ትኩረት ካልሰጠነው የሜዴትራንያን ባህር ወደ መቃብርነት እየተቀየረ ነው። እናም ከባድ ኃላፊነት አለብን።»  
የጀርመን መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል በበኩላቸው የጋራ ባሉት በፍልሰት እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ትብብሮችን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።   
«እነዚህ ሃገራት ለብዙ ጉዳዮች ቅርብ የሆኑ ጎረቤቶቻችን ናቸው። የአውሮጳ ህልውና በከፊል ቢሆን ከአረብ ሊግ አባል ሀገራት ህልውና ላይ የተመሰረተ ነው። ይህን በፍልሰት አይተናል። ስለዚህ ምንም እንኳን የተለያዩ አመለካከቶች ቢኖሩም ተልዕኮአችን ዘርፈ ብዙ የርስ በርስ  ትብብሮችን ማጠናከር ነው።»
ሜርክል በጥቅሉ ዘርፈ ብዙ ትብብሮች ከማለት ውጭ ትብብር የሚደረጉባቸውን መስኮች አልገለጹም ። የግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ግን የፍልሰትን አሉታዊ ሳይሆን አዎንታዊ ገጽታ ነበር ያነሱት።  ፍልሰት ተግዳሮት ሆኖ እንደማይታያቸው ይልቁንም ደህንነቱ የተጠበቀ ያሉት ፍልሰት ላይ በትብብር ከተሰራ  ሁለቱንም ወገን የሚጠቅም እንደሚሆን አልሲሲአስገንዝበዋል። 
«ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ስናነጻጽረው እኛ ፍልሰትን እንደ ተግዳሮት አናየውም። ከዚያ ይልቅ ብዙ የሠራተኛ ኃይል ባለው የአረቡ ዓለም እና ኤኮኖሚያቸው የተለያየ የሰው ኃይል በሚያስፈልገው በአውሮጳ ሀገራት መካከል የመተባበር እድል የሚፈጥር አጋጣሚ አድርገን ነው የምንወስደው ። ስለዚህ እኛ ከናንተ ጋር ደህንነቱ ለተጠበቀ እና ለተደራጀ ፍልሰት የምናደርገው ትብብር የጋራ

ጥቅሞቻችን ገቢራዊ ለማድረግ ይረዳናል።»
ጉባኤው አስቀድሞም እንደተገመተው በሁሉም ጉዳዮች መግባባት ላይ አልደረሰም። ልዩነቶች ከተከሰቱባቸው መካከል የኢራን ጉዳይ አንዱ ነው። በሱኒዎች የሚመሩት የአረብ ሃገራት፣ ሺአቶች በሚያመዝኑበት በቴህራን መንግሥት ላይ ጠንከር ያለ አቋም እንዲወሰድ ጠይቀው ነበር። ይሁን እና በጉባኤው ማጠቃለያ በወጣው የጋራ መግለጫ አውሮጳውያን ይህን መቃወማቸው ነው የተገለጸው። በየመን በሶሪያ በሊቢያ እንዲሁም በእስራኤል እና ፍልስጤም ሰላም ለማውረድ የሚደረጉ ጥረቶችም ጉባኤው ከተነጋገረባቸው ጉዳዮች ውስጥ ይገኛሉ። ጉባኤው እነዚህን ጉዳዮች ማንሳቱ በተለይ ሊቢያን ማረጋጋት በሚቻልበት መንገድ ላይ ሐሳብ መለዋወጡ ቢያንስ እንደ ጥሩ ነገር ታይቷል። ሆኖም  የአውሮጳ ህብረትም ሆነ የአረብ ሃገራት ብቻቸውን በዚያች ሀገር ሰላም ማውረድ የሚያስችል ርምጃ ወውሰድ አለመቻላቸው ነው ችግሩ። በሊቢያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሊቢያ ከሚገኙ የተለያዩ ፈልጭ ቆራጭ ኃይሎች አንስቶ የአረቡ ዓለም ነገሥታት እና አሚሮች ፍላጎት መለያየት ችግሩን ለመፍታት ያስችላሉ የተባሉ መፍትኄዎችን ገቢራዊነት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው ነው የዲ ደብሊው ቤርነት ሬግይርት የዘገበው። በመካከለኛው ምሥራቅ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ደግሞ ሶሪያ ሩስያ ኢራን ዩናይትድ ስቴትስ እና ቱርክ  ወሳኝ ናቸው። ሆኖም የሻርምኤልሼኩ ጉባኤ እነዚህን ኃይሎች አላሳተፈም። እናም ይህ የመጀመሪያ ጉባኤ ከመተዋወቂያ መቀራረቢያ እና ከሐሳብ መለዋወጫ መድረክነት ባለፈ የፈየደው ይኽ ነው የሚባል ነገር የለም የሚል ትችት ቀርቦበታል። አስቀድሞም ቢሆን የሁለቱ ወገኖች የመጀመሪያ ጉባኤ ተጨባጭ በሆኑ ፖለቲካዊ ርምጃዎች ላይ ስምምነት ላይ ይደረሳል ተብሎ አልተጠበቀም። ይህ ባይሆንም ቢያንስ ሁለቱን ወገኖች በሚጎዱ ቀውሶች ላይ መነጋገር ችለዋል። ቤርንድ ሪገርት

እንደዘገበው ጉባኤው ሲያበቃ በወጣው የጋራ መግለጫ ላይ ይህ ነው የሚባል ውሳኔ አልተገለጸም።  የሉክስምበርጉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዣቭየ ቤትል እንዳሉት በዚህ ጉባኤ ለሁሉም ችግሮች ሁነኛ እና የጋራ መፍትኄ ላይ ይደረሳል ብሎ መጠበቁ የዋህነት ነው። 
«ሻርም ኤል ሼክ ውስጥ 24 ሰዓት ተያይቶ በዓለም ሰላም ማስፈን እና ሁሉም ነገር እንዲያበቃ ማድረግ ይቻላል ብሎ ማሰብ በገና አባት እንደማመን ነው ። ሆኖም የጉባኤው ግብ ለጋራ ችግራችን የጋራ መፍትኄ ለመፈለግ የሚረዳ ማዕቀፍ ስለምናገኝበት ኹኔታ ለማጤን ለመነጋገር እና ሀሳብ ለመለዋወጥ ነው።»
በከፍተኛ የጸጥታ ጥበቃ የተካሄደውን የሻርም ኤልሼኩን ጉባኤ በዩናይትድ ስቴትስ የተፈጠሩ ክፍተቶችን ለመሙላት ቻይና እና ሩስያ ሲንቀሳቀሱ የአውሮጳ ሀገራት ባህላዊ፤ ዲፕሎማሲያዊ፤ ኤኮኖሚያዊ እና የየደህንነት ጥቅሞቻቸውን ማስጠበቂያ መንገድ አድርገው ነው የወሰዱት። ጉባኤው ሁለቱ ወገኖች ወደፊት ለሚያካሄዷቸው ንግግሮች መሠረት የጣለ እና እንደመገናኛም ያገለገለ መድረክ ተብሏል። በርካታ የአረብ ሃገራት መሪዎች በተገኙበት በዚህ ጉባኤ ላይ ከአረብ ሊግ በኩል ሁለት አወዛጋቢ መሪዎች አልተካፈሉም፦ የሳዑዲው አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሳልማን እንዲሁም የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦመር አልበሽር፤ ከአውሮፓውያኑ መሪዎች ደግሞ፦ የፈረንሳይ፣ የስፓኝ፣ የላቲቪያ እን የሊትዌንያ መሪዎች አልተገኙም።

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

Audios and videos on the topic