የአውሮጳ ኅብረት መሪዎች ጉባኤ ውሳኔዎች
ዓርብ፣ ጥቅምት 8 2017በዋናነት በዩክሬን፤ በመካከለኛው ምሥራቅ፤ የስደተኞች እና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ትናንት የተወያየው 27 አባላት ያሉት የአውሮጳ ኅብረት በጉባኤው ውሳኔ አሳልፏል ። የጉባኤው ዋነኛ ትኩረት የነበረው የስደተኞች እና ፈላሲያን ጉዳይ ነበር ተብሏል ። ፖላንድ በተለይ በምስራቃዊ ደንበሯ የሚገቡ ስደተኞችን የተገን ጥያቄ ላለማስተናገድ መወሰኗን ዐሳውቃለች ።
ዩክሬን፤ መካከለኛው ምስራቅና የስደተኖች ጉዳይ አይነተኛ አጀንዳዎች የሆኑበት ጉባኤ
ትናንት እዚህ ብራስልስ የሀያ ሰባቱ የአውሮጳ ኅብረት አገሮች መሪዎች ባካሄዱት ስብሰባ፤ በዋናነት ሩሲያ በዩክሬን ላይ እያካሄደች ባለው ጦርነት፣ በመካከለኛ ምስራቅና ፤በፈላስያንና ስደተኖች ጉዳይ በሰፊው ተወያይተው ውሳኔዎችን አሳልፈዋል። የስደተኞች ጉዳይ ከዩኪሬንና መካከለኛው ምስራቅ ይበልጥ የመሪዎቹ ስብሰባየ ትክረት እንድነበርም ተገልጿል።
በዩክሬን ላይ ተላለፉ ውሳኔዎች
በጉባኤው የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ሚስተር ቭላድሚር ዘለንስኪ ተገንተው በቅርቡ ላሜርካው ፕሬዝዳንት ያቀረቡትንና የድል ፕላን ያሉትን ሰነድም ማቅረባቸው ታውቋል። ድል ፕላኑ ጦርነቱን በአንድ አመት ውስጥ በድል ለማጠናቀቅና ሰላም ለመፍጠር ዩክሬንን የኔቶ አባል እንድትሆን መገባዝን፣ የወታደራዊ እርዳታና የኢኮኖሚ ድጋፍን በበቂ ሁኒት ማግኘትን የመሳሰሉትን በቅድመ ሁኒታ የሚያስቀምጥ ነው ተብሏል።
መሪዎቹም በቀረበው የፕሬዝዳንት ዘለንስኪ እቅድና በቀጠለው የሩሲያ ጥቃት ላይ በመወያየት፤ ለዩክሬን የሚሰጡትን እርዳታ አጠናክረው ለመቀጠል የወስኑ መሆኑ የካውንስሉ ፕሬዝዳንትና የስብሰባው መሪ ሚስተር ቻርለስ ሚሸል አስታውቀዋል።"ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ ባስቸኳይ ያስፈልጋቸዋል፤ የፋይንናስ ድጋፍም ባስቸኳይ አያስፈልጋቸዋል፤ ይህንንም ባለፈው በሰባቱ ባለጸጋ አገሮች ባስቀመጡት የእርዳታ ማዕቀፍ መሰረት ተግባራዊ ለማድርግ ተስማምተናል” በማለት መሪዎቹ የቀረበውን የድል ዕቅድ ስለመቀበል አለመቀበላቸው ሳይሆን እርዳታው ግን ለመቀጠል የተስማሙ መሆኑን አስታውቀዋል።
በመካከለኛው ምስራቅ ላይ
መካከለኛ ምስራቅን በሚመለክት ሚስተር ሚሸል በጋዜጣዊ መግለጫቸው፤ የህብረቱ መሪዎች ባለፈው አመት በብዙዎቹ የምራብ አገራት በአሸባሪነት የተፈረጀው ሀማስ በእስራኤል ዘላማዊ ዜጎች ላይ ያደረሰውን ጥቃት በማስታወስና እስራኤል እራሷን የመካላከል መብት ያልት መሆኑንም አጽንኦት ስተው፤ ባሁኑ ወቅት በጋዛና ሊባኖስ የተኩስ ማቆም እንዲደረግ መሪዎቹ ዳግም ጥሪ ማቅረባቸውን ገልጸዋል። "በጋዛና ሊባኖስ የተኩስ ማቆም እንዲደረግ እንፈልጋለን፤ በሊባኖስ የተባበሩት መንግስታት የሰላም አስከባሪ ሀይል የደረሰውን ጥቃት እናወግዛለን፣ የመንግስታቱ ድርጅት ውስኔዎች እንዲከበሩም እንጠይቃለን” በማለት በዚህ በኩል ህብረቱ የሚችለውን የሚያደርግ መሆኑን ግልጽ አድርገዋል ።
በስደተኞች ጉዳይ የተነሱ ሀሳቦችና የተላለፉ ውሳኔዎች
ከዩክሬንና መካከለኛው ምስራቅ አጀንዳዎች ይበልጥ ግን በዚህ የመሪዎች ስብሰባ የስደተኞችና ፈላስያን አጀንዳ ዋናውና የሁሉንም ትኩረት ያገኘ አጀንዳ እንደሆነ ነው በሰፊው ሲነገር የቆየው። በዚህ አጀንዳ ላይ መሪዎቹ ትኩረት ሰተው የተወያዩበትን ፍሬ ነገር የኮሚሺኑ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ቮንዴርሌየን ሲገልጹ፤ "አንዱና ዋናው የመያየ ጉዳይ ተመላሽ ስደተኖችን በሚመለክት የጋራ አሰራር ሊኖር ስለሚችልበት ነው። በአሁኑ ወቅት ጥያቄዎቻቸው ውድቅ ከሆነባቸው ውስጥ ወደ አገሮቻቸው የተመለሱት 20 ከመቶ ብቻ ናቸው” በማለት ያልተፈቀደላቸው ህብረቱን ሊለቁ በሚችሉባቸው የጋራ አሰራሮችና ስልቶች ላይ ውይይት መደርጉን ይፋ አድርገዋል።
ወይዘሮ ቮንዴርሌየን በዚህ አጀንዳ ላይ የተደረጉ ውይይቶችን ሲያብራሩም፤ " ለሶስት የተለያዩ ሁኔታዎች ሶስት ሀስቦች ውይይት ተደርጎባቸዋል። አንዱ ተገን ሊያገኙ ለሚገባቸው ስደተኖች በሌላ ሶስተኛ አገርም ቢሆን ተገን ሊያገኙ የሚችሉበት አሰራር ነው። ምክኒያቱም ተገን ጠያቂዎች ተገን የሚገኙት አውሮፓ ህብረት ብቻ መሆን አይኖርበትም። ሁለተኛው የተመላሽ ስደተኖች ማቆያ ካምፕን የሚመለክት ነው፡ በአውሮፓ እንዲቆዩ ያልተፈቀደላቸው ተገን ጠያቂዎች ሊቆዩ የሚችሉበት ካምፕ ወይም ሃብ ማለት ነው። ሶስተኛ የመንግስታቱ ድርጅት የስደተኖች መርጃና የፍልሰተኖች ድርጅቶች ክህብረቱ ውጭ ያሰፈሯቸውን ስደተኖች ለመመስ የሚያስፈልገው የፋይናንስ ደጋፍ ነው” በማለት በሁሉም መንገድ ግን ስደተኖች እንዳይገቡና ገብተው ተገን የተነፈጋቸው ደግሞ ወደ አገራቸውም ይሁን ወደ ሌላ አገር እንዲላኩ የሚያስችሉ አሰራሮችን መሪዎቹ የተወያዩ.መሆኑን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ፖላንድ በተለይ በምስራቃዊ ደንበሯ የሚገቡ ስደተኞችን የተገን ጥያቄ ላለማስተናገድ የወሰነች መሆኑን መሪዎቹ ድርጊቱ ሩሲያና ቤላሩስ በህብረቱ ላይ የከፈቱት ሁለገብ ጥቃት አካል መሆኑን በማመን የፖላንድን እርምጃ ላለመቃወም የወሰኑ መሆኑ ተገልጿል።
ኅብረቱና መንግስታት በስደተኖች ላይ ጥብቅ እርምጃ እንዲወስዱ ያደረጋቸው ገፊ ምክኒይት
ህብረቱና አባል አገራቱ ባሁኑ ወቅት ስደተኖች ወደ አገሮቻቸው እንዳይገቡ ጥብቅና ልዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ እንደሆነና ለምሳሌ ጣሊያን ደግሞ የገቡ ስደተኖችን ወደ አልባኒያ በማዛወር ጉዳያቸውን እዚያ ለመክታተል መወስኗ አነጋጋሪ ቢሆንም መሪዎቹም ሆኑ ህብረቱ ግን ይህን አሰራር እንዳልተቃወሙት ነው የተስማው። ይህ የሆነበት ምክኒያትም በአሁ ወቅት ከዚህ ቀደም ከታየው በተለየ ሁኔታ ወደ ህብረቱ የሜገቡ ስደተኖች ቁጥር ጨምሮ ሳይሆን፤ ይልቁንም በያገሮቹ አክራሪና ስደተኛ ጠል የፖለቲካ ፓርቲዎች ከፍተኛ ድምጽ በማገኝት በአንዳንድ አባል አገሮች መንግስት እስከመህን በመድረሳቸው እንደሆነ ነው በብዙዎች የሚታመነው።
ገበያው ንጉሤ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ሸዋዬ ለገሰ