የአውሮጳ ኅብረትና የቤላሩስ ውዝግብ  | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 16.11.2021
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮጳ ኅብረትና የቤላሩስ ውዝግብ 

በሀገራቸው የሚካሄዱ ጦርነቶችን ሸሽተው ተገን ፍለጋ አውሮጳ ለደረሱ ሰዎች ኅብረቱ ፊቱን ማዞሩ ከእሴቶቹ አንዱ ተደርጎ የሚወሰደውን ሰብዓዊ መብቶችን ማክበርን በመጣስ እያስተቸው ነው። ሉካሼንኮን ስደተኞችን የፖለቲካ መሳሪያ አድርገዋል ሲል የሚከሰው ኅብረቱ ለችግሩ በሚሰጠው ፖለቲካዊ መልሰ መተቸቱ ቀጥሏል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 11:01

የአውሮጳ ኅብረትና የቤላሩስ ውዝግብ 

የአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ስደተኞችን በፖለቲካ መሳሪያነት እየተጠቀመች ነው ባሏት በቤላሩስ  ላይ ጫናውን አጠናክረዋል። በሌላ በኩል ቤላሩስና ፖላንድ ድንበር ላይ የሚገኙ ስደተኞች ወደ ኅብረቱ አባል ሀገራት እንዳይገቡ የሚከላከለው የአውሮጳ ኅብረት፣ ችግር ላይ የሚገኙ ስደተኞችን መብት በመጣስ መወቀሱ ቀጥሏል። 
ከቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ግዛቶች አንዷ የነበረችው ቤላሩስ ፣ምሥራቅ አውሮጳ የምትገኝና ከአምስት ሃገራት ጋር የምትዋሰን የባህር በር የሌላት ሀገር ናት። በጎርጎሮሳዊው 1990 ከሶቭየት ኅብረት ተነጥላ ራስዋን የቻለች ሀገር የሆነችው ቤላሩስ  በስተምሥራቅና ሰሜን ምሥራቅ ከሩስያ፣ በስተደቡብ ከዩክሬን፣ በስተምዕራብ ከፖላንድ በስተሰሜን ምዕራብ ደግሞ ከሊትዌንያና ከላትቪያ ጋር ትዋሰናለች። ከሶስት የአውሮጳ ኅብረት አባል ሃገራት ጋር የምትዋሰነው ቤላሩስ የኅብረቱ አባል የመሆን ፍላጎት የላትም። ይህች ሃገር ካለፉት ጥቂት ወራት አንስቶ ከአውሮጳ ኅብረት ጋር ከፍተኛ ውዝግብ ላይ ናት።ውዝግብ  ተካሮ በቀጠለበት በዚህ ወቅት ላይ  የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት በቤላሩስ ላይ  ለአምስተኛ ጊዜ ማዕቀብ ለመጣል መወሰናቸውን የኅብረቱ የውጭ ጉዳዮች ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬል አስታውቀዋል።ቦሬል እንዳሉት ማዕቀቡ ኅብረቱ በተደረጀ መንገድ ስደተኞችን ወደ አውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት የማስገባት ጥረት ታደርጋለች ሲል በሚከሳት በቤላሩስ ባለሥልጣናትና በተለይም ከመንግሥቱ ጋር ይተባበራሉ በተባሉ አየር መንገዶች ላይ ጭምርም ነው የሚጣለው።  

«በዚህ ማዕቀብ ከተለያዩ ሀገራት ሰዎችን ወደ ቤላሩስ የሚያመጡና ከዚያም ወደ አውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት ድንበሮች የሚያሸጋግሩ በረራዎችን በማመቻቸት የሚሳተፉ ተጨማሪ ሰዎች ላይ እገዳ መጣል እንችላለን። ከዚሁ ጋር ለአምስተኛ ጊዜ በሚጣለው አዲስ የማዕቀብ ማዕቀፍ ላይ ተስማምተናል።ይህ ማዕቀብም በሚቀጥሉት ቀናት ይጠናቀቃል።»
ቦሬል በትናንቱ መግለጫቸው እንዳስረዱት ማዕቀቡ ቁጥራቸውን በውል ባልጠቀሷቸው ብዙ ባሏቸው ላይ ተጽእኖ ያደርጋል። የአውሮጳ ኅብረት፣የቤላሩስ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ ባለፈው ዓመቱ  የቤላሩስ ምርጫ ሰበብ የአውሮጳ ኅብረት በሀገራቸው ላይ ማዕቀብ መጣሉን ለመበቀል  ስደተኞችን ወደ አውሮጳ ኅብረት በማስገባት ኅብረቱን ለማናጋት እየሞከሩ ሲል ይከሳል። ሉካሼንኮ በበኩላቸው ኅብረቱ እወስዳለሁ ያላቸውን የማዕቀብ ዛቻዎች አጣጥለው ሀገራቸው በተደራጀ መንገድ ስደተኖችን ወደ ኅብረቱ አባል ሃገራት ለማስገባት ትጥራለች መባሉን አስተባብለዋል። ይልቁንም ሉካሼንኮ  ሀገራቸው በአንጻሩ ስደተኞቹ ወደ የመጡበት እንዲመለሱ እየጣረች መሆኑን አስረድተዋል።
«በተደራጀ መንገድ ስደተኞችን ማምጣት ያስገኛል ተብሎ ከሚታሰበው፣ችግሩ ነው የሚብሰው።እኛ ይህን አድርገን አናውቅም፤ አላቀድንምም።በማዕቀብ ያስፈራሩናል። እሺ ደህና እናያለን። እነርሱ ይቀልዳል ብለው ነው የሚያስቡት። እንደዛ አላደርግም ፤ የትም ልንሄድ አንችልም። ይህ የስደተኞች መጠለያ ሰፈር እንዲዘጋ የታቸለንን ሁሉ እያደረግን ነው። ወደ አውሮጳ ኅብረት ለመሄድ የሚፈልጉት እንዲሄዱ፣የማይፈልጉትን ደግሞ በአውሮፕላን ለመመለስ ዝግጁ ነን። ሆኖም ከእነዚህ ሰዎች ማናቸውም ለመሄድ እንደማይፈለጉ ልናገር እወዳለሁ። ተመልሰው የሚሄዱበት

እንደሌላቸውም መረዳት ይገባል። »
በአሁኑ ጊዜ ከሶሪያ ከኢራቅ ከአፍጋኒስታንና ከሌሎች ጦርነት ከሚካሄድባቸው የእስያ ሀገራት ቤላሩስ የመጡ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ቤላሩስና ፖላንድ ድንበር ላይ ይገኛሉ። ስደተኞቹ የሰሜኑ ንፍቀ ክበብ ክረምት እየበረታ በሄደበት በዚህ ወቅት ላይ በብርድ በምግብና ውኃ እንዲሁም በመጠለያ እጦት እየተሰቃዩ ነው። ከመካከላቸው የ9 ሰዎች ሕይወት አልፏል።ካለፈው ነሐሴ አንስቶ ድንበር ላይ የፈሰሱትን እነዚህን ስደተኞች ቤላሩስ በአጸፋ እርምጃ የፖለቲካ መሳሪያ አድርጋ እየተጠቀመችባቸው ነው ሲል የአውሮጳ ኅብረት ይከሳል። የዶቼቬለ የብራሰልስ ዘጋቢ ገበያው ንጉሴ እንደሚለው የስደተኞቹ ቁጥር ከ10 ሺህ በላይ ይገመታል። ለተፈጠረው የስደተኞች ቀውስ ቤላሩስን ተጠያቂ ያደረገው የአውሮጳ ኅብረት ለ5ተኛ ጊዜ በሚጥለው ማዕቀብም አየር መንገዶችንና ተያያዥ የጉዞ ድርጅቶችን የመንግሥት ባለሥልጣናትንም ዒላማ አድርጓል።
27ቱ የኅብረቱ አባል ሀገራት ከአሁኑ ማዕቀብ አስቀድሞ በጎርጎሮሳዊው ነሐሴ 2020 በተካሄደው በአወዛጋቢው የቤላሩስ ምርጫ ሰበብ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀቦችን ጥሏል። ከቤላሩስ ጋር የምታዋሰነው የኅብረቱ አባል ሀገር ፖላንድ ስደተኞች ድንበሯን አልፈው እንዳይገቡ 15ሺህ ወታደሮችን በተጠንቀቅ አሰማርታለች።ይህ አሀዝ የድንበር ጠባቂዎችንና የፖሊሶችን

ቁጥር አይጨምርም።የፖላንድ እርምጃ አንዳንድ ኅብረቱ ደግፏል። ኅብረቱ በቤላሩስ ላይ ማዕቀቡን ማጠናከሩ ፖላንድን አስደስቷል። የሉካሼንኮ አገዛዝ ተቃዋሚ ፖላንድ፣የቤላሩስን ተቃዋሚዎች አስጠግታለች።ይህም በሁለቱ አገራት መካከል አለመግባባቱን አባብሷል።
በድንበሩ መዘጋት በስደተኞች ላይ የሚደርሰው እንግልት የአውሮጳ ኅብረትን ትዝብት ላይ ጥሏል።በሀገራቸው የሚካሄዱ ጦርነቶችን ሸሽተው ተገን ፍለጋ አውሮጳ ለደረሱ ሰዎች ኅብረቱ ፊቱን ማዞሩ ከእሴቶቹ አንዱ ተደርጎ የሚወሰደውን ሰብዓዊ መብቶችን ማክበርን በመጣስ እያስተቸው ነው።በዚህም ከተመ ድርጅት ሳይቀር ስሞታ ቀርቦበታል። ሉካሼንኮን ስደተኞችን የፖለቲካ መሳሪያ አድርገዋል ሲል የሚከሰው ኅብረቱ ራሱ፣ የስደተኞቹ ይዞታ ግምት ውስጥ ባለመስገባት ለችግሩ በሚሰጠው ፖለቲካዊ መልሰ መተቸቱ መቀጠሉን ነው ገበያው ያስረዳል።

 
በዚህ የተነሳም የአውሮጳ ኅብረት ድንበሩ ላይ የሰብዓዊ ጥሰት በመፈጸም በመብት ተሟጋቾች መከሰሱ ቀጥሏል። የኅበረቱ አባል ሀገራት በራቸው ላይ ለደረሰው ለዚህ ችግር የበኩላቸውን መፍትሄ ለመሻት መጣራቸው ግን አልቀረም።የጀርመን መራኂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል  ችግሩን ለማቃለል በሚቻልበት መንገድ ላይ ከሉካሼንኮ ጋር ተነጋግረዋል። የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዌል ማክሮም ከሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር መክረዋል።ስደተኞቹ ፈቃደኛ ከሆኑም ወደመጡበት ሀገር ለመመለስም እየተሞከረ ነው።በዚህ ረገድ የኢራቅ መንግሥት ጥረቱን ለመሳካት እንደሚተባበር አስታውቋል።ሆኖም ገበያው እንደሚለው ይህ ብቻውን መፍትሄ ሊሆን አይችልም።
 

ኂሩት መለሰ

አዜብታደሰ 

Audios and videos on the topic