የአውሮጳ ኅብረትና የሜድትሬንየን ባህር አካባቢ ሀገሮች ስብሰባ | ኤኮኖሚ | DW | 02.12.2003
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

የአውሮጳ ኅብረትና የሜድትሬንየን ባህር አካባቢ ሀገሮች ስብሰባ

አሣ አምስቱ የአውሮጳ ኅብረት አባል መንግሥታት ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በያመቱ ከሜድትሬንየን ባህር አካባቢ ሀገሮች አቻዎቻቸው፡ እንዲሁም ከራስ ገዙ አስተዳደር ተወካይ ጋር አንዴ በመገናኘት እአአ በ 1995 ዓም የተፈራረሙትን የባርሰሎና መርሐ ግብር የተሰኘውን የጉድኝት ስምምነት ለማነቃቃት ይሞክራሉ። ይኸው ዓመታዊ ጉባያቸው በዛሬው ዕለት በኢጣልያዊትዋ የኔአፕል ከተማ ተጀምሮዋል። በዚሁ ዓመታዊ ጉባዔ ላይ ሊቢያ በታዛቢነት ብቻ ነው የምትካፈለው። የተ መ ድ በዚችው ሰሜን አፍሪቃዊት ሀገር ላይ አሳርፎት የነበረውን ማዕቀብ ካነሣና የሊቢያ መንግሥትም ዜጎቹ ባካሄዱት የሽብርተኝነት ጥቃት ሰበብ ከለባ ለሆኑት ቤተዘመዶች ካሣ ለመክፈል ከተስማማ ወዲህ የአውሮጳ ኅብረት ከሊቢያ ጋር ግንኙነቱን ለማጠናከር ይሻል። ይሁንና፡ አሁንም በሞአመር ጋዳፊ መንግሥት አንፃር ማዕቀቡን ያላነሣችው ዩኤስ አሜሪካ ይህንኑ የመቀራረብ ፍላጎት በጥርጣሬ ነው የምትመለከተው። በአውሮጳ ኅብረት እና በሊቢያ መካከል የኤኮኖሚው ግንኙነት ጥብቅ ነው። ኢጣልያ ከውጭ በንግድ ከምታስገባው ነዳጅ ዘይት መካከል ግማሹን ያህል የምታስገባው ከሊቢያ ነው፤ ጀርመንም ብትሆን ከሚያስፈልጋት ድፍድፉ የነዳጅ ዘይት መጠን አሥራ ሦስት ከመቶውን ከሊቢያ ትገዛለች። በተለይ ኢጣልያ ከሊቢያ ጋር ጠንካራ የፖለቲካ ትብብር ያላት ሀገር ናት። እንደሚታወቀው በሺህ የሚቆጠሩ አፍሪቃውያን ስደተኞች ድንበርዋ ከሞላ ጎደል ክፍት በሆነባት ሊቢያ በኩል አድርገው ወደ ሜድትሬንየን ባህር ዳርቻ ከደረሱ በኋላ፡ በሕገወጡና በአደገኛው የመርከብ ጉዞ አማካይነት ወደ ኢጣልያ የላምፔዱዛ ደሴት፡ ወይም የሲሲሊ ባህር ዳርቻ ወይም ወደ መሀል ሀገር ለመግባት ይሞክራሉ። ይኸኸው ሁኔታ ቅር ያሰኛቸው የኢጣልያ ጠቅላይ ሚንስትር ሲልቪዮ ቤርሉስኮኒ ስደተኞቹ ወደሀገራቸው ሊመለሱ የሚችሉበትን ስምምነት ከአልጀሪያ፡ ከሞሮኮ እና ከቱርክ ጋር ለመድረስ ጥረት ጀምረዋል። ይሁንና የሚመለከተቸው ሀገሮች በዚሁ ረገድ አንዳችም ስምምነት ለመድረስ አልፈለጉም። የአውሮጳ ኅብረት በወቅቱ ከሞሮኮ፡ ከቱኒዝያ፡ ከዮርዳኖስና ከቱርክ ጋር በተለይ በዕቃ ዝውውር ላይ የሚታየውን ከፍተኛውን የግምሩክ መጠን ለመቀነስ የሚያስችል አንድ የትሥሥር ውል ተፈራርሞዋል። ከአልጀሪያና ከግብፅ ጋር ውሉ ቢፈረምም እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም። ራስ ገዙ የፍልሥጤም አስተዳደርና ሊባኖስም ውሉን በጊዚያዊነት ይገለገሉበታል። ከሶርያ ጋር ግን የውሉ ድርድር አሁንም አዳጋች እንደሆን መገኘቱን የኅብረቱ ተጠሪዎች ገልፀዋል። የአውሮጳ ኅብረት የውጭ ግንኙነት ተጠሪ ክሪስ ፓተን እንዳስረዱት የትሥሥሩ ውል ዓላማዎች በሜድትሬንየን ባህር አካባቢ ሀገሮች መካከል አንድ ነፃ የንግድ ዞን ለመፍጠር እና ፀረ ሽር ዘመቻን ለማጠናከር ነው።

ተዛማጅ ዘገባዎች