የአውሮጳ ቡድኖች የዋንጫ ፍልሚያዎች | ስፖርት | DW | 19.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

የአውሮጳ ቡድኖች የዋንጫ ፍልሚያዎች

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የሩጫ ውድድሮች ድል ተቀዳጅተዋል። አትሌቲኮ ማድሪድ ከ18 ዓመታት በኋላ የስፔን ላሊጋ አሸናፊ ሆኗል። የጀርመኑ ባየር ሙንሽን ተቀናቃኙ ቦሩስያ ዶርትሙንድን ድል ነስቶ ዋንጫውን በእጁ አስገብቷል። የጣሊያን ሴሪኣ ዋንጫን ጁቬንቱስ ጨብጧል። የእንግሊዝ «FA-Cup» ዋንጫን መድፈኞቹ ለንደን ይዘው ገብተዋል።

በማንቼስተሩ ታላቁ የሩጫ ውድድር አትሌት ቀነኒሣ በቀለና ጥሩነሽ ዲባባ አሸናፊ ሆነዋል። ቀነኒሳ በ10.000 ሜትር ሩጫ ኬንያዊው ዊልሰን ኪፕሳንግን ጥሎ ነው ድል የተቀዳጀው። የ5000 እና የ10.000 ሜትር የዓለም ክብር ወሰን ባለቤት እንዲሁም የፓሪሱ ማራቶን ክብር ወሰንን ያሻሻለው አትሌት ቀነኒሣ በቀለ የትናንትናውን የሩጫ ፉክክር በአሸናፊነት ያጠናቀቀው በ28 ደቂቃ ከ23 ሠከንድ በመግባት ነው። በሴቶች የ10.000ሜትር የሩጫ ውድድርም እዛው ማንቼስተር ውስጥ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ በ31 ደቂቃ ከ09 ሰከንድ በማሸነፍ የቀድሞ ድሏን አስጠብቃለች። የብሪታኒያዋ ጌማ ስቲል ጥሩነሽን ተከትላ ሁለተኛ ወጥታለች።

ሻንጋይ ውስጥ በተከናወነው ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማኅበር የጎልደን ሊግ የሩጫ ውድድር በ5000 ሜትር የኔው አላምረው በ13 ደቂቃ ከ04.83 ሠከንድ በመግባት በአንደኛነት ድል ተቀዳጅቷል። ኬንያዊው ቶማስ ፕኬሚ ሎንጎሲዋ ለጥቂት ተቀድሞ ሁለተኛ ሆኗል። ሐጎስ ገብረሕይወት ኬኒያዊውን ተናንቆ በሦስተኛነት አጠናቋል። ብርሐኑ ለገሠ 6ኛ ወጥቷል።

በ3000ሜትር የመሰናክል ሩጫ የሴቶች ፉክክር አሜሪካዊቷ ኤማ ኮቡርን በ9:19:80 አንደኛ ስትወጣ፤ ሶፊያ አሠፋ በ9:25:76 ሁለተኛ እንዲሁም ሕይወት አያሌው በ9:27:25 ሦስተኛ በመውጣት ኢትዮጵያን አስጠርተዋል። በእዚሁ ውድድር ብርትኳን አዳሙ እና እቴነሽ ዲሮም 6ኛ እና 7ኛ ሆነው አጠናቀዋል።

በሴቶች 1500 ሜትር የሩጫ ውድድር ለስዊድን የምትሮጠው አበባ አረጋዊ አንደኛ፤ ባህሬንን ወክላ የምትወዳደረው ሚሚ በለጠ 5ኛ ወጥተዋል። ከኢትዮጵያ ጉዳፍ ፀጋዬ 6ኛ በመሆን አጠናቃለች።

በሣምንቱ መጨረሻ የአውሮጳ ክለቦች የዋንጫ ጨዋታዎች ከባርሴሎና ካምፕ ኑ ስታዲየም እስከ በርሊኑ ኦሊምፒያ ስታዲየም፤ ከጁቬንቱስ ቱሪን ስታዲየም እስከ ውዌምብሌይ በደማቁ ተከናውነዋል።

የዋንጫ ፍልሚያ፦ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከባየርን ሙንሽን

የዋንጫ ፍልሚያ፦ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከባየርን ሙንሽን

76,000 ተመልካቾች በታደሙበት የበርሊኑ ኦሊምፒያ ስታዲየም የቡንደስ ሊጋው አሸናፊ ባየር ሙንሽን እና ተከታዩ ቦሩስያ ዶርትሙንድ ከትናት በስትያ ያከናወኑት ጨዋታ የተጠበቀውን ያህል አጓጊ አልነበረም። የጀርመን እግር ኳስ ማኅበር ዋንጫን ለመጨበጥ በተደረገው ግጥሚያ የመጀመሪያው አጋማሽ ኳስ በተንቀረፈፈ መልኩ ወዲያ ወዲህ ስትዋልል ነበር የተስተዋለው።

ከእረፍት መልስ 64ኛው ደቂቃ ላይ ግን የጨዋታውን ሁናቴ ሊቀይር ይችል የነበረ ክስተት ተስተውሏል። በቀጣዩ የእግር ኳስ ዘመን ለባየርን ሙንሽን ለመሰለፍ ባለፈው ጥር ወር የ5 ዓመት ውል የፈረመው የቦሩስያ ዶርትሙንዱ አጥቂ ሌቫንዶቭስኪ ያቀበለውን ኳስ የመሀከል ተከላካዩ ማትስ ሁመል በጭንቅላት ገጭቶ ወደ ግብ ይልካታል። ሆኖም የባየርኑ ጠንካራ ተከላካይ ዳንቴ ኳሷ መረብ ላይ ከማረፏ በፊት በፍጥነት በግራ እግሩ ሊያወጣት ችሏል። ይህች ኳስ በዝግታ ስትታይ ከግብ መስመሩ ያለፈች በመሆኗ ምናልባት የጨዋታውን መልክ ለመቀየር ትችል ነበር ተብሏል። ዳኛው ፍሎሪያን ማየር ግን ግቡን ሳያፀድቁ ጨዋታው እንዲቀጥል አድርገዋል። ይህ ውሳኔ የቦሩስያ ዶርትሙንድ ደጋፎዎችን፣ አሠልጣኙንና ተጨዋቾችን ሲበዛ አናዳለች። በተለይ ግቡ ለተሻረበት ማትስ ሁመል እጅግ የምታበሳጭ ነበረች።

«በጣም የሚያበሳጭ ነው። ግቡ ሊፀድቅልን በተገባ። ያ ቢሆን ኖሮ ምናልባት ሁሉም ነገር በቀለለን ነበር፤ ምክንያቱም ዕድላችን ይሰፋ ነበራ። ያ ባለመሆኑ ግን ጨዋታውን ማሸነፍ አንችልም ነበር ማለት አልነበረም። ብቸኛ ዕድላችን ያ ብቻ ነበር ብሎ መውሰድም አያስፈልግም። ዛሬ በእራሳችን ላይ የፈረድነው እራሳችኑ ነን።»

አሠልጣኞች፤ የቦሩስያ ጥቁር፣ የባየርን ቀይ ለብሰው

አሠልጣኞች፤ የቦሩስያ ጥቁር፣ የባየርን ቀይ ለብሰው

የዶርትሙንዱ አሠልጣኝ ዩርገን ክሎፕ ግቧ ባለመቆጠሯ ምንም ማድረግ ባይችሉም፤ በ83ኛው ደቂቃ ላይ ግን ፈጣኑ አጥቂያቸው ፒየር ኤመሪክ አውባሜየንግን ማስገባት ችለው ነበር። ፒየር ኤመሪክም ወደ ሜዳ ከመግባት ውጪ ግብ ማስገባት ሳይችል ቀርቷል። እናም 90 ደቂቃ ጨዋታው ያለምንም ግብ ተጠናቀቀ።

በነገራችን ላይ ባየር ሙንሽን እና ዶርትሙንድ ከእዚህ ቀደም ያልተለመደ አሰላለፍ ይዘው ነው ወደ ሜዳው የገቡት። የዶርትሙንዱ አሠልጣኝ ዬርገን ክሎፕ ባልተለመደ መልኩ 4-3-3 አሰላለፍን ሲመርጡ፤ የባየርኑ ፔፕ ጋርዲዮላ ከእዚህ ቀደም አድርገውት በማያውቁት የ3-4-2-1አሠላለፍ ነበር ወደ ሜዳ የገቡት። በእርግጥ ጨዋታው በሁለቱም በኩል የተጠበቀውን ያህል አጓጊ ባይሆንም ይህ አሰላለፍ ግን ባየርን ሙንሽኖች በተሻለ መልኩ እንዲንቀሳቀሱ አስችሏቸዋል። ከመደበኛው ሠዓት በላይ በተጨመረው የግማሽ ሠዓት ጨዋታ 107ኛው ደቂቃ ላይ ሆላንዳዊው አርየን ሮበን ወሳኟን የማሸነፊያ ግብ ከመረብ ሊያሳርፍ ችሏል። ሁለተኛዋን የማሳረጊያ ግብ ቶማስ ሙለር በድንቅ ሁናቴ ተከላካዩንና ግብ ጠባቂው በማታለል ከመረብ ሊያሳርፍ ችሏል። በእዚህም ባየር ሙንሽን ዶርትሙንድን 2 ለ0 አሸንፏል።

«የፍፃሜ ወሳኝ ፍልሚያ ነው፣ ዋንጫ ማግኘት ነው፣ ድል መቀዳጀት ነው። ስለእዚህ ምንም ይሁን ምንም ማሸነፍ ነበር የፈለግነው። ያ ደግሞ ሜዳ ላይ ታይቷል። ለቡድናችን አድናቆቴ ከፍተኛ ነው። ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት አድርገናል። እናም የመጣነው ለእዚያ ነበር፤ አሸንፈናል። ጣምራ ድል ነው፤ ድንቅ የጨዋታ ዘመን አሳልፈናል። አከተመ።»

ይህ ጨዋታ አርየን ሮበን ዳግም ታሪክ ያስመዘገበበት ነበር። የዛሬ ዓመት ለሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ እንግሊዝ ዌምብሌይ ውስጥ ከቦሩስያ ዶርትሙንድ ጋር ሲገጋጠሙ ወሳኟን የማሸነፊያ ሁለተኛ ግብ ለቡድኑ ባየር ሙንሽን ያስቆጠረው ሮበን ነበር። ዘንድሮም በዓመቱ እዛው ዶርትሙንድ ላይ ወሳኟን የማሸነፊያ የመጀመሪያ ግብ ያስቆጠረው ይኸው ራሰ-በረኻው የ30 ዓመቱ ሆላንዳዊ አጥቂ አርየን ሮበን ነው።

አርየን ሮበን ግብ ካስቆጠረ በኋላ

አርየን ሮበን ግብ ካስቆጠረ በኋላ

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የሦስት ጊዜያት የዋንጫ ባለድሉ፤ የወራጅ ቃጣና ጠርዝ ላይ ይገኝ የነበረው ሐምቡርግ የመጨረሻ ወሳኝ ጨዋታውን ያከናወነው ትናንት ነበር። ሐምቡርግ ቡንደስ ሊጋው በጀርመን መከናወን ከጀመረበት ከዛሬ 51 ዓመታት አንስቶ ከቡንደስ ሊጋው ሳይወርድ የቆየ ብቸኛ የእግር ኳስ ቡድን ነው። ሁለተኛ ዲቪዚዮን ውስጥ ከሚገኘው ግሬውተር ፉርትስ ጋር ያከናወነውን የትናትናውን ጨዋታ ቢሸነፍ ኖሮ የግማሽ ክፍለ-ዘመን በቡንደስ ሊጋ የመቆየት ታሪኩ በአዲስ አሳዛኝ ታሪክ ይተካ ነበር። ጨዋታው በተጀመረ በ14ኛው ደቂቃ ላይ ግን ፒየር ሚሼል ላሶጋ ብቸኛዋን ግብ በማስቆጠር ቡድኑን ከውረደት ታድጎታል።

«ወሳኝ ጨዋታ ነበር። በአንድ ሣምንት ውስጥ ሦስት ጨዋታዎችን ነው ያደረግነው። የመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች እጅግ ሲበዛ አስጨናቂ ነበሩ። ምንም ይሁን ምን ብቻ አሁን በቡንደስ ሊጋው በመቆየታችን በጣም ነው የተደሰትነው። በጨዋታው አቻ ነው የወጣነው። በእርግጥ የፍፃሜውን ዋንጫ አልጨበጥንም። ሆኖም በቡንደስሊጋው መቆየት መቻላችን እራሱን የቻለ ደስታ ነው የፈጠረብን። »

በተጠናቀቀው ቡንደስ ሊጋ ከ1 እስከ ሦስት የወጡት፤ ባየር ሙንሽን፣ ቦሩስያ ዶርትሙንድ እና ሻልካ ለሻምፒዮንስ ሊግ ሲያልፉ፤ በአራተኛ ደረጃ የጨረሰው ባየር ሌቨርኩሰን ለማጣሪያ አልፏል። በ5ኛነት ያጠናቀቀው ዎልፍስቡርግ ለአውሮጳ ሊግ ሲያልፍ፤ 6ኛ እና 7ኛ ደረጃ ይዘው የጨረሱት ቦሩስያ ሞንሽንግላድባኅ እና ማይንስ ለማጣሪያው አልፈዋል። ቡንደስ ሊጋው ከወራቶች በኋላ እንደ አዲስ የሚጀምረው የዓለም ዋንጫ ጨዋታ ከተጠናቀቀ ከስድስት ሣምንታት ገደማ በኋላ ነሐሴ 16 ነው።

አርሰናል የFA Cup ዋንጫ አሸናፊ

አርሰናል የFA Cup ዋንጫ አሸናፊ

በእንግሊዝ «FA-Cup» ዋንጫ የእግር ኳስ ፍልሚያ መድፈኞቹ አርሰናሎች ከ9 ዓመታት ቆይታ በኋላ ከትናንት በስትያ ለ11ኛ ጊዜ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን በቅተዋል። ጨዋታው እንደተጀመረ በሁል ሲቲ 2 ለዜሮ የተመሩት አርሰናሎች ሦስት ተከታታይ ግቦችን በማስቆጠር ነው ለድል የበቁት። ትናንት የሰሜን ለንደን ጎዳናዎች በሺህዎች በሚቆጠሩ የአርሰናል ደጋፊዎች ተጨናንቀው ነው የዋሉት። የአርሰናል ድል በአርሴን ቬንገር የ18 ዓመታት የቡድኑ አሠልጣኝነት ዘመን 5ኛው የ«FA-Cup» ዋንጫ ድል ሆኖ ተመዝግቦላቸዋል። የአርሠናልን ድል አስመልክቶ Sunday Times እንዲህ ሲል አስነብቧል፦ «በ8ኛው ዓመት፣ በ11ኛው ወር፣ በ26ኛው ቀን፣ በ38ኛው ደቂቃ፣ በ20ኛው ሠከንድ ላይ አርሠናል የ«FA-Cup» ባለድል ሆነ» ሲል ዘግቧል።

የስፔኑ አትሌቲኮ ማድሪድ ከ96 ሺህ ተመልካች በላይ በታደመበት የባርሴሎናው ካምፕ ኑ ስታዲየም ከትናንት በስትያ ከኃያሉ ባርሴሎና ጋር አንድ እኩል ቢለያይም የላሊጋውን ዋንጫ በእጁ ለማስገባት ችሏል። በዕለቱ አቻ መውጣትን ጨምሮ ሁለት ዕድል ይዞ ከገባው አትሌቲኮ ማድሪድ አንፃር ባርሴሎና የዋንጫ ባለቤት ለመሆን ጨዋታዋን የግድ ማሸነፍ ይጠበቅበት ነበር። በእርግጥም ባርሳ በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ እንደ ብረት የጠጠረውን የአትሌቲኮ ማድሪድ ተከላካይ ጥሶ ግብ ለማስቆጠር ቀዳሚ ሆኖ ነበር። አሌክሲስ ሣንቼዝ በ34ኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም ቅጣት ክልል ውስጥ ከግብ ጠባቂው በስተግራ በኩል ከሁለት ተከላካዮች ፊት ለፊት የነጠረችውን ኳስ አክርሮ በመታት ነበር ግብ ያስቆጠረው።

የስፔን ላሊጋ ዋንጫን በእጁ ለማስገባት ለ18 ዓመታት መጠበቅ ግድ የነበረበት አትሌቲኮ ማድሪድ ዕኩል ለዕኩል በመውጣት ባለድል የመሆን የመጀመሪያ ዕድሉ ተጨናገፈ። ሁለተኛ ዕድሉን ግን በጨዋታው ሁለተኛ አጋማሽ ላይ በሚገባ ሊጠቀምበት ችሏል። ከእረፍት መልስ ጨዋታው ከተጀመረ 5 ደቂቃም ሳይሞላ ነበር አትሌቲኮ ግብ ማስቆጠር የቻለው። በ49ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ በኩል የተሻገረለትን ኳስ ዲዬጎ ጎዲን በጭንቅላቱ በመግጨት ከመረብ አሳርፎ ለ18 ዓመታት ሙሉ የዋንጫ ባለቤት ለመሆን ሲጨነቅ የነበረውን ደጋፊ እፎይ ማስባል ችሏል። በእዚህ ጨዋታ የስፔኑ ዳኛ ማቴዎ ላሆዝ 9 የቢጫ ካርዶችን ለመምዘዝ ተገደዋል።

የአትሌቲኮ ማድሪድ ደጋፊዎች በከፊልመንገድ ላይ

የአትሌቲኮ ማድሪድ ደጋፊዎች በከፊልመንገድ ላይ

በጣሊያን ሴሪኣ ትናንት ጁቬንቱስ ካጊላሪን 3 ለባዶ በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል። በጣሊያን ሴሪኣ ታሪክ በ38 ጨዋታዎች 102 ነጥቦችን በመሰብሰብ ጁቬንቱስ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል። በትናንትናው ጨዋታ የካጊላሪ ተከላካዮች ደካማ ሆነው ታይተዋል። የመጀመሪያዋን ግብ ፒርሎ በ8ኛው ደቂቃ ላይ ያገኘውን ቅጣት በመጠቀም በድንቅ ሁናቴ ለማስቆጠር ችሏል። በተደረደሩት የካጊላሪ ተከላካዮች አናት መጥኖ የላካት ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭታ በመንጠር ከመረብ አርፋለች። የተቀሩት ሁለት ግቦች ግን ሙሉ ለሙሉ በተከላካዮች ድክመት የተቆጠሩ ናቸው ማለት ይቻላል።

በ14ኛው ደቂቃ ላይ ሊዮሬንቴ ከበረኛው በስተግራ በኩል ከማዕዘን የተላከለትን ኳስ በቀላሉ ማስገባት ችሏል። 39ኛው ደቂቃ ላይ የተቆጠረው ሦስተኛ ግብም የማርኪዚዮ ብቃት የታየበት ቢሆንም አራት ተከላካዮች በአቅራቢያው የነበሩ ከመሆናቸው አንፃር የተከላካዮች ድክመት ጎልቶ ታይቷል። የካጊላሪ አጥቂዎች ያገኙዋቸውን ወደ ሦስት የሚጠጉ ጥሩ አጋጣሚዎች ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል። በ36ኛው ደቂቃ የጁቬንቱሱ አሣሞዋ ከርቀት በግራ እግሩ አክርሮ የመታት ኳስ ድንቅ ሙከራ ነበረች።

የሦስት ጊዜያት የዓለም ባለድሉ ጃክ ብራብሐም

የሦስት ጊዜያት የዓለም ባለድሉ ጃክ ብራብሐም

በFormula one የመኪና ሽቅድምድም የሦስት ጊዜያት የዓለም ባለድሉ ጃክ ብራብሐም በ88 ዓመቱ ከእዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። በመኪና ሽቅድምድም ዝናው sir የሚል የክብር ስያሜ የተሰጠው አውስትራሊያዊው አሽከርካሪ ያረፈው ለረዥም ጊዜያት በጉበት በሽታ ሲሰቃይ ቆይቶ እንደነበር ተዘግቧል።

ጣሊያን ሮም ውስጥ በተከናወነው የሜዳ ቴኒስ ጨዋታ ሠርቢያዊው ኖቫክ ጆኮቪች የስፔኑ ኃያል የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች ራፋኤል ናዳልን በተደጋጋሚ 6 ለ3 አሸንፎታል።

በሴቶች የሜዳ ቴኒስ ውድድር የዩናይትድ ስቴትሷ ሴሬና ዊሊያምስ ሣራ ኤራኒን በሜዳዋ 6 ለ3 እና 6 ለ0 በሆነ ሰፊ ልዩነት ልትረታት ችላለች።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዓርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic