የአውሮጳ ህብረት፤ የአፍሪቃ ቀንድ የስደት መርህ እና ትችቱ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 08.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮጳ ህብረት፤ የአፍሪቃ ቀንድ የስደት መርህ እና ትችቱ

ከአፍሪቃ በህገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች አማካይነት የሚካሄድ ስደትን ለማስቆም ያለመው የመርሁ ትኩረት የሰዎችን እንቅስቃሴ መግታት ላይ ብቻ መሆኑ ነው ችግሩ እንደዘገባው። ለምሳሌ የህብረቱ አጋር በሆነችው በሱዳን ስደተኞች በድንበር ጠባቂዎች ቁም ስቅል ያያሉ ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:29
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:29 ደቂቃ

የአውሮፓ ህብረት የስደት መርህ

«የአውሮጳ ህብረት የአፍሪቃ ቀንድ የስደት ጉዳይ መርህ» የተዛባ ነው ሲል ዛሬ ይፋ የተደረገ አንድ ዘገባ ተቸ።  ለስደተኞች እና ለአፍሪቃ ቀንድ ሴቶች መብቶች የቆሙ ሁለት ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች እና አንድ የትምህርት ተቋም በጋራ  ያወጡት ይኽው ዘገባ መርሁ መሻሻያ ሊደረግበት እንደሚገባ ጠቁሟል። ከዘገባው አዘጋጆች አንዱ ዶክተር ሉዝ ኦቴ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ፣መርሁ  ስደተኞችን ለከፍተኛ ጉዳት የሚዳርግ ነው ብለዋል። 
የአውሮጳ ህብረት እና የአፍሪቃ ቀንድ ሀገራት በጋራ አረቀቁት የተባለዉ መርሕ ከአፍሪቃ በረሃ እና ባህር አቋርጦ ወደ አውሮጳ የሚደረግ ስደትን ለመግታት ያስችላል ተብሏል። በእንግሊዘኛው ምህጻር IRRI የተባለው ለስደተኞች መብት የቆመው ዓለም አቀፍ ድርጅት፣ በአፍሪቃ ቀንድ ሴቶች ላይ አትኩሮ የሚሰራው በምህፃሩ SIHA የሚል መጠሪያ ያለው ሌላ ድርጅት እና  በለንደን ዩኒቨርስቲውስኩል ኦፍ ኦርየንታል ኤንድ አፍሪካን ስተዲስ የሰብዓዊ መብቶች ህግ ተቋም በጋራ እንደሚሉት ደንቡ ሰዎችን ይጎዳል።

ሰወስቱ ተቋማት በጋራ ያወጡት ዘገባ እንደሚለው የአፍሪቃ ቀንድ የስደት መስመሮችን ለመዝጋት ዓላማ ያለው ይህ መርህ ስደትን ከመግታት ይልቅ ስደተኞችን በእጅጉ እየጎዳ ነው። በለንደኑ ስኩል ኦፍ ኦርየንታል ኤንድ አፍሪካን ስተዲስ የሚያስተምሩት ዶክተር ሉትስ ኦኤተ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳሉት  መርሁ ችግሩን ለመፍታት የሚከተለው መንገድ ነው ዐብዩ ችግር።
«ዋነናው ችግር መርሁ የችግሩን ምንጮች ሳይሆን ምልክቶቹን ነው የሚከላከለው። ይህን የሚያደርገውም በአካባቢው ከሚገኙ ከባድ የአስተዳደር እና የሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ችግሮች

ካሉባቸው አጋር መንግሥታት ጋር ነው። እናም የችግሩ ምንጮች መፍትሄ ሳይገኝላቸው አሁን በተያዘው ሥልት ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ማሻገርን በተሳካ ሁኔታ መከላከል መቻሉ በጣም አጠራጣሪ ነው። »
«የካርቱም ሂደት» በመባልም የሚጠራው ይኽው መርህ  ከዛሬ 4 ዓመት በፊት በ37 የአውሮጳ እና የአፍሪቃ ሀገራት ነው የወጣው።  ከአፍሪቃ በህገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች አማካይነት የሚካሄድ ስደትን ለማስቆም ያለመው የመርሁ ትኩረት የሰዎችን እንቅስቃሴ መግታት ላይ ብቻ መሆኑ ነው ችግሩ እንደዘገባው። ለምሳሌ የህብረቱ አጋር በሆነችው በሱዳን ስደተኞች በድንበር ጠባቂዎች ቁም ስቅል ያያሉ ።የመርሁ አውጭዎች  ህገ ወጥ የሚሉትን ድንበር አቋራጭ የሰዎች ዝውውርን የህግ አስፈጻሚዎች ወይም የድንበር ጠባቂዎች ጉዳይ ብቻ አድርገው ከመመልከት ይልቅ የስደተኞች ምንጭ በሆኑ ሀገራት ውስጥ የሚታዩ የአስተዳደር ችግሮችን፤ የከፋ ድህነትን እና ሌሎች ሰዎችን ለስደት የሚገፋፉዋቸውን ምክንያቶች ከግምት ውስጥ እንዲያስገቡ ጠይቀዋል። ከዘገባ ፀሀፊዎች አንዱ ዶክተር ኦኤተ እንደሚሉት ደግሞ መርሁ ጀርመንን በመሳሰሉ የመርሁ አራማጅ እና ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ሰጭ በሆኑ የአውሮጳ ሀገራት ላይ ሊያሳድርባቸው የሚችለው ተጽእኖም አሳሳቢ ነው። 
«ጀርመን ለፕሮጀክቱ ተጨማሪ 6 ሚሊዮን ዩሮ አዋጥታለች። ከዚህም ሌላ ጀርመን ከሱዳን እና ከሌሎች ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነቶች አድርጋለች። እንደሚመስለኝ በስደተኞች ጉዳይ ላይ አጋር ነን ብለው ራሳቸውን የሚያዩ ሀገራት አሁን በሚፈጸመው የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በተመለከተ እንደ ከዚህ ቀደሙ ግልጽ ተቃዋሚ እና ተናጋሪ ይሆናሉ ተብለው አይጠበቁም።» 
እናም ይላሉ ዶክተር ኦኤተ የካርቱም ሂደት እንደገና መዋቀር አለበት። ከ60 የሚበልጡ ኤርትራውያን ስደተኞች ጋር የተደረጉ ቃለ ምልልሶችንም ያካተተው ዘገባ የአውሮጳ ህብረት እና የአፍሪቃ አጋሮቻቸው የስደት መንስኤ ለሆኑት ፖለቲካዊ ምክንያቶች መፍትሄ እንዲፈልጉ የስደተኞች መተላለፊያዎችን ደህንነት እንዲያስጠብቁ እና በአግባቡም እንዲይዟቸው አሳስቧል።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic