የአውሮጳ ህብረት እና የአፍሪቃ ስደተኞች | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 20.12.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮጳ ህብረት እና የአፍሪቃ ስደተኞች

የአውሮጳ ህብረት ስደተኞች ወደ ክፍለ ዓለሙ እንዳይመጡ ለመከላከል እና በአውሮጳ ተገን ያላገኙትንም ለመመለስ የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛል ። በዚህ ረገድ ህብረቱ ከአፍሪቃ መንግሥታት ጋር የተፈራረማቸው ስምምነቶች ተጠቃሽ ናቸው ። የስምምነቶቹ ዓላማ ግን በይበልጥ  የአውሮጳ ኩባንያዎችን ተጠቃሚ ማድረግ ነው የሚል ትችት ይቀርባል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:57
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:57 ደቂቃ

የአውሮጳ ህብረት እና የአፍሪቃ የስደተኞች

 

የአውሮፓ ህብረት እና የአባል ሀገራት መንግሥታት ህገ ወጥ የሚሉትን ስደት ለማስቆም የስደተኞች  መሸጋገሪያ  ከሚባሉ ሀገራት ጋር በትብብር የመሥራት እንቅስቃሴ ከጀመሩ ጥቂት የማይባሉ ዓመታት ተቆጥረዋል ። በተለይ የሜዴትራንያንን ባህር አቋርጠው አውሮጳ ለመግባት የሚሞክሩ  የአፍሪቃ ሀገራት ስደተኞችን ለመግታት ከአፍሪቃ መንግሥታት ጋር የለያዩ ስምምነቶች ላይ ደርሰዋል ። ከመካከላቸው የዛሬ ዓመት ቫሌታ ማልታ ውስጥ የተካሄደው እና የአውሮጳ እና የአፍሪቃ ህበረት አባል ሀገራት  መሪዎች ይፋ ስምምነት ላይ የደሩሰበት ጉባኤ አንዱ ነው ።  ከ60 በላይ የመንግሥታት ተወካዮች እና ጉዳዩ የሚመለከታቸው የአውሮጳ ህብረት እና የአፍሪቃ ህብረት ተቋማት እንዲሁም አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች የተካፈሉበት ይኽውጉባኤ ችግሩን ይፈታሉ የተባሉ ውሳኔዎችን አሳልፎ ነበር ። ጉባኤው ፣ ሁለቱ ወገኖች በሀገር እና በአካባቢ ደረጃ ስደትን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ሃላፊነትን  በጋራ ለመወጣት ትብብሮችን ማጠናከር ፣በአጋር ሀገራት የስደትን ትክክለኛ ምንጮች ማድረቅ የሚያስችል እርዳታ መስጠት ህገ ወጥ ስደትን እና የሰው አሻጋሪዎችን ለመከላከል ትብብሮችን ማጠናከር  ፣ በመፍትሄነት ከተስማማባቸው እቅዶች መካከል ዋና ዋና ዎቹ ናቸው ። ለዚሁ ለቫሌታው የድርጊት መርሃ ግብር ማስፈፀሚያ «የአውሮጳ ህብረት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ» EU Emergency Trust Fund የ 1.88 ቢሊዮን ዩሮ መድቧል። በቅርቡ ታገስሳይቱንግ የተባለው ግራ ዘመሙ የጀርመን ጋዜጣ ባቀረበው የምርመራ ዘገባ ከአውሮጳ ህብረት በጀት እና ከአውሮጳ የልማት እርዳታ የሚገኘው የዚህ ገንዘብ  ዋነኛ ተጠቃሚዎች የአውሮጳ ኩባንያዎች መሆናቸውን አጋልጧል ። የጋዜጣው ዘጋቢ ዚሞነ ሽሊንድቫይን እና ሌሎች 24 ጋዜጠኞች ባካሄዱት ምርመራ የእርዳታው

ገንዘብ ግንባር ቀደም ተጠቃሚዎች የጀርመን እና የአውሮጳ ኢንዱስትሪዎች እንዲሁም የጦር መሣሪያ አምራች ኩባንያዎች መሆናቸውን ደርሰውበታል  ።

«እኛ በቀላሉ በብረት አጥር አምራቾች በኩል ነው መረጃ ያገኘነው ። ከነርሱም አብዛኛዎቹ የጦር መሣሪያ አምራቾች ናቸው ፤ ለጦርነት የሚያገለግሉ የተለመዱ ታንኮችን የሚሰሩ ። እንደራይን ሜታልና ዶቼ ኮንሰርን የመሳሰሉ አዳዲስ ተቋማት ተፈጥረዋል ። ይህን አጥር የማሳጠር ሀሳብ የጀርመን የቀድሞ የልማት ሚኒስትር ዲርክ ኒብል እንደ አንድ ደንብ አስቀምጠው እንደገና ደግሞ ሀሳቡ ተግባራዊ እንዲሆን አጥር ለሚገነቡ ኩባንያዎች ከፍተኛ ቀስቃሽ ሆኑ ።»

ዘገባውን ያወጣው የታገስሳይቱንግ የአፍሪቃ ዘጋቢ የ36 ዓመትዋ ዚሞነ ሽሊንድቫይን እና መርማሪ ጋዜጠኞቹ በ37 የአፍሪቃ እና የአውሮጳ ሀገራት ውስጥ ነው ፍተሻ ያካሄዱት ። የጋዜጣው የምርመራ ዘገባ ፕሮጀክት ሃላፊ ክርስቲያን ያኮብ  እንዳሉት ብዙ በተለፋበት በዚህ ምርመራ የአውሮጳ ህዝብ እንዳይሰማ እና እንዳያውቃቸው የተደረጉ ያልታተሙ ሰነዶችን አግኝተዋል ። ሰነዶቹን ያገኙትም መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች እና የአውሮጳ ህብረትን መርህ ከሚተቹ ውስጥ አዋቂዎች ነው ።

ጋዜጠኛ ሽሊንድቫይን እንደምትለው በርካታ የአውሮጳ ህብረት ፓርላማ አባላት መንግስቶቻቸው ከአፍሪቃ አምባገነኖች ጋር በድብቅ ስለ ሚፈጽሙዋቸው  ውሎች ምንም አያውቁም ። ከመካከላቸው አንዱ ህብረቱ ለሱዳኑ መሪ የገባው ቃል ነው  ። ሱዳን በአመዛኙ ኤርትራውያን እና ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ አውሮጳ ከሚሸጋገሩባቸው አገሮች አንዷ ናት ። ከዚህ ሌላ ባለፈው ዓመት ከ100 ሺህ በላይ ሱዳናውያን ስደተኞች አውሮጳ ገብተዋል ። ሽሊንድቫይን እንደምትለው  የአውሮጳ ህብረት በጦር እና በሰብዓዊነት ላይ በተፈፀሙ ወንጀሎች በዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች መዳኛ ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ለተቆረጠባቸው የሱዳኑ መሪ ኦማር አል በሽር ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ ሱዳን የሚገቡ ስደተኞች፣ ወደ አውሮጳ እንዳይመጡ የሚያስቆሙዋቸው ከሆነ ፣አውሮጳ ያሉ ተገን የተከለከሉ ሱዳናውያንንም ከወሰዱ የሀገሪቱን ብድር ለመሰረዝ ፣ቃል ተገብቶላቸዋል ። እናም ትላለች ጋዜጠኛዋ ህብረቱ የልማት እርዳታን ከመልካም አስተዳደር እና ከሰብዓዊ መብት አያያዝ ጋር ከማገናኘት ይልቅ አሁን ስደተኞች አውሮጳ እንዳይመጡ ለሚተባበሩት  እና የተገን ጥያቄአቸው ያልተሳካላቸውን ዜጎች ለሚወስዱት መንግሥታት የገንዘብ ሽልማት መስጠት ነው የተያያዘው ። ለተበደሉ ህዝቦች መብት የሚቆመው ገዜልሻፍት ፉር በድሮህተሜንሽን የተባለው የጀርመን ድርጅት የአፍሪቃ ጉዳዮች አማካሪ

ዩልሪሽ ዴልዩስ ይህን አሠራር በጥብቅ ይተቻሉ ። በርሳቸው አስተያየት ከአምባገነን መንግሥታት ጋር እነዚህ ስምምነቶች ላይ መድረሱ በየትኛውም መመዘኛ አግባብ አይደለም ።

«እንዴት ነው በነዚህ ሀገራት ዴምክራሲን ተግባራዊ ማድረግ የሚቻለው ። የሲቪክ ማህበራትንስ እንዴት ነው ማበረታታት የሚቻለው ? አሁን ከሁሉም በላይ ቅድሚያ የተሰጠው በየሀገራቱ ከፍ ብሎ የሚገነባው አጥር ጉዳይ ነው ።አጥሩ ከተገነባ ከነዚህ ሀገራት አንድም ሰው ወደ አውሮጳ እንዳይሸሽ ማድረግ እና በአውሮጳ የተገን ማመልከቻቸው ተቀባይነት ያላገኘ ስደተኞችንም መመለስ ላይ ብቻ ነው ትኩረቱ ።ይህ ነው የስምምነቱ መሥፈርት ። ይህን ካደረጉ እርዳታ ይሰጣቸዋል ። ገንዘብም ያገኛሉ ።ይህ ደግሞ በአፍሪቃ ልማት እና ዲሞክራሲ እንዲሰፍን የሚያደርጉ እና ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር የሚያስችሉ መርሆች ላይ በሙሉ የተፈፀመ ክህደት ነው  ።»

በጎርጎሮሳዊው 2015 ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ያስገባችው ጀርመን የአፍሪቃ ፖሊሲዋን የመቀየር ሂደት ላይ ናት ። የጀርመን የልማት ተራድኦ ሚኒስትር ጌርድ ምዩለር በጎርጎሮሳዊው 2016 የስደተኞች መነሻ እና መሸጋገሪያ የሆኑትን ሴኔጋል ኒዠር እና ሩዋንዳን ጎብኝተዋል ። ምዩለር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ኤኮኖሚያቸው በጦርነቱ ለደቀቀ የአውሮጳ ሀገራት ተግባራዊ የተደረገውን የማርሻል እቅድ መሰል ድጋፍ ለአፍሪቃ እንዲሰጥ ሃሳብ አቅርበዋል ። ዝርዝሩ ይፋ ያልተደረገው የምዩለር ሀሳብ በክፍለ ዓለሙ የመንግሥታትን ውስብስብ እና ጊዜ የሚፈጅ አሠራር ወደ ጎን ትቶ የሚተገበር የኤኮኖሚ ግንባታውን እውን ማድረግ ነው ። ኡልሪሽ ዴልዩስ ምዩለር ያቀዱት ማርሻል ፕላን ከአውሮጳው ምንም የሚያመሳስለው ነገር የለም ይላሉ ።

« እዚህ አውሮጳ ላለነው ማርሻል ፕላን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አውሮጳን መልሶ ለመገንባት  ተግባራዊ የተደረገው እቅድ ነው ። እዚህ (አፍሪቃ) ግን ምንም ዓይነት መልሶ መገንባት የለም ።ይልቁንም ከዚህ የባሰ ነው ። በስተመጨረሻ የአውሮጳን ኢንዱስትሪዎች እናየአውሮጳን የጦር መሣሪያ አምራቾች ለማጠናከር የታሰበ ነው ።»

ከዚሁ ጋርም ከአፍሪቃ ወደ አውሮጳ በህገ ወጥ መንገድ ይካሄዳል የሚባል ስደትን ለመግታት የሚተባበሩ ሀገራት በየድንበሮቻቸው ላይ ዘመናዊ የኢሚግሬሽን ቁጥጥር ስርዓት ተግባራዊ እንዲያደርጉም ነው የሚፈለገው ። እንደ ሽሊንድቫይን ስደተኞች የሚሰጣቸው መታወቂያ የማንኛውንም እንቅስቃሴያቸውን መረጃ ለመንግሥት ባለሥልጣናት አሳልፎ የሚሰጥ እንዲሆን ተደርጎ ነው የሚዘጋጀው ። ይህ የግል መረጃ ጥበቃን የሚጥስ እና ከመጠን ያለፈ የቁጥጥር እቅድ ነው ስትል ጋዜጠኛ ሽሊንድቫይን ተችታለች ።በአፍሪቃ ከአልጀሪያ እስከ ኬፕታውን ድረስ እንደ ኤር ባስ እና ራይን ሜታል የመሳሰሉ ታንኮችን እና ሌሎች የጦር መሣሪያዎችን የሚያመርቱ የአውሮጳ የመከላከያ ሥራ ተቋራጮች  በአፍሪቃ ሀገራት የተራቀቀ ቴክኖሎጂ የሚጠቀሙ የብረት የድንበር አጥሮችን ይሠራሉ ። በነሽሊንድንቫይን ምርመራ መሠረት ለእነዚህ ኩባንያዎች ገንዘብ የሚከፈለው በአፍሪቃ ድህነትን ለመቀነስ እና ለሰብዓዊ እርዳታ ከሚውለው የአውሮፓ ህብረት የእርዳታ ገንዘብ ላይ ነው ። አስፈላጊ የሆኑ የኢሚግሬሽን መረጃዎች አያያዝ ላይ የሚሰሩት ሁለት የጀርመኖቹ ኩባንያዎች አሁን ከበርካታ የአፍሪቃ አገሮች የሥራ ትዕዛዞች ደርሰዋቸዋል ። ድርጅቶቹ አብዛኛዎቹ ሥራዎች የተሰጧቸው ጨረታ ሳይካሄድ ለሊት በፕሬዝዳንታዊ ቤተ መንግሥቶች በተካሄዱ ስብሰባዎች ነው ብላለች ጋዜጠኛ ሽሊንድቫይን ። ታገስሳይቱንግ በምርመራ ዘገባው ስላጋለጣቸው ጉዳዮች ዶቼቬለ የጠየቃቸው የጀርመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ በሰጡት መልስ ጀርመን ከአፍሪቃ መንግሥታት ጋር በምታካሂዳቸው የትብብር ሥራዎች ፣የመልካም አስተዳደር የዴሞክራሲ የህግ የበላይነት እና የሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ ሁሌም ሳይታዩ ቀርተው አያውቁም ። ይህ የሚያጠራጥር አይደለም ብለዋል ።

በአሁኑ ጊዜ የስደተኞችን እንቅስቃሴ ለመገደብ አጥር እንዲገነባ የሚያደርጉት የአውሮጳ መንግሥታት ብቻ አይደሉም ። ራሳቸው የአፍሪቃ መንግሥታትም አጥር እየገነቡ ነው ። ከዓለም ትልቁ የሚባለውን  በአመዛኙ የሶማሊያ ስደተኞች የሚገኙበትን የዳዳብ ኬንያውን የስደተኞች መጠለያ መንግሥት ሊዘጋ ተዘጋጅቷል ። ከዚሁ ጋርም የኬንያ መንግሥት ከሶማሊያ ጋር በሚያዋስነው ድንበር ላይ ትልቅ የብረት አጥር ለመሥራት አቅዷል ። እቅዱ የወጣው ወደፊት ከዳዳብ ወደ ሀገራቸው የሚላኩ ሶማሌዎች ተመልሰው እንዳይመጡ ለማድረግ መሆኑን ሽሊንድቫይን ትናገራለች ።እናም በርስዋ አባባል አውጳውያን ስደተኞችን ለማባረር እና ለማስቆም ተግባራዊ የሚያደርጓቸው አሠራሮች ወደ አፍሪቃም እየተዛመቱ ነው ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች