የአውሮጳ ህብረት እና ቡድን አምስት ሳህል | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 27.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮጳ ህብረት እና ቡድን አምስት ሳህል

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህን ጥረት ለማገዝ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ለመለገስ ቃል ሲገባ የአውሮጳ ህብረት ከዚህ ቀደም ለቡድኑ ማጠናከሪያ ሊሰጥ ቃል የገባውን ገንዘብ በእጥፍ አሳድጎ 116 ሚሊዮን ዩሮ አድርሷል። ህብረቱ እርዳታውን ያሳደገው የራሱን ወታደሮች ህይወት ለአደጋ ከማጋለጥ የአካባቢውን ኃይሎች አሰልጥኖ ለውጊያ ማዘጋጀቱን በመምረጥ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:49

ቡድን አምስት የሳህል ኃይል

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ብራሰል ቤልጂግ ውስጥ የተካሄደው ዓለም አቀፍ የለጋሽ ሀገራት ጉባኤ ከአምስት የሳህል አካባቢ ሀገራት ለተውጣጣው «ቡድን 5 ሳህል» ለተባለው ኃይል ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ለመለገስ ቃል ገብቷል። በሳህል አካባቢ አሸባሪነትን ለመዋጋት ለተቋቋመው ለዚህ ኃይል የአውሮጳ ህብረት ደግሞ እርዳታውን በእጥፍ አሳድጓል። ለቡድኑ የተገባው ቃል እና ፋይዳው የዛሬው አውሮጳ እና ጀርመን ዝግጅታችን ትኩረት ነው።

ባለፈው ሳምንት አርብ «የቡድን አምስት አካባቢያዊ ኃይል» ተብሎ ለሚጠራው ከአምስት የምዕራብ አፍሪቃ ሀገራት ለተውጣጣው ሠረዊት እርዳታ ለማሰባሰብ በተካሄደው የለጋሽ ሀገራት ጉባኤ ላይ የተካፈሉት ወደ  50 የሚጠጉ ሀገራት ናቸው።  ዩናይትድ ስቴትስ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት ጃፓን ኖርዌይ እና ሳውዲ አረብያ በጉባኤው ላይ ከተካፈሉ ገንዘብ እና የተለያዩ እርዳታዎችን ለመስጠት ቃል ከገቡ ሀገራት መካከል ይገኙበታል ። ከነዚህ ውስጥ ሳውዲ አረብያ 100 ሚሊዮን ዩሮ ለመለገስ ቃል ገብታለች። የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳዮች ሃላፊ ፌደሪካ ሞገሪኒ በአርቡ ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ እንደተናገሩት በለጋሽ ሀገራት ቃል የተገባው አጠቃላይ ገንዘብ መጀመሪያ ከተጠበቀው በላይ ነው።

«ዛሬ ለናንተ በደስታ ላጋራችሁ የምፈልገው ዋናው ቁጥር በአጠቃላይ 404 ሚሊዮን ዩሮ ማግኘታችንን ነው። እደግመዋለሁ 414 ሚሊዮን ዩሮ። በአውሮጳ ህብረት እና በአባል ሀገራቱ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ አጋሮቻችን ጭምር በስፋት ለተካሄደው ዘመቻ ምስጋና ይግባውና የተገኘው በፊት ከጠበቅነው በላይ ነው።»

በሳህል ሀገራት ሽብርን ለመከላከል የተመሰረተው የቡድን አምስት ሳህል ኃይል በጎርጎሮሳዊው 2018 ዓም መጨረሻ ላይ ሥራውን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።  ከማሊ ኒዠር ቻድ ቡርኪናፋሶ እና ሞሪቴንያ ለተውጣጣው ለዚህ ኃይል እርዳታ ማሰባሰቢያ ጉባኤ የተካሄደው ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ የሚጠራው በምህጻሩ አይኤስ የተባለው ቡድን በኢራቅ እና በሶሪያ ከገጠመው ሽንፈት በኋላ ምዕራብ አፍሪቃን ጨምሮ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም የመግባት ሙከራ ያደርጋል የመባሉ ስጋት ነው። በአካባቢው ሀገራት  የሳህል ኃይልን በማጠናከር አይ ኤስ ወደ አካባቢው እንዳይገባ ለመከላከል የሚደረገው ጥረትም በደቡባዊ ድንበሩ በኩል ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞች እና ታጣቂ ኃይሎች ዝር እንዳይሉበት በተለያዩ ስልቶች በመከላከል ላይ ላለው ለአውሮጳ ህብረትም አንዱ ጠቃሚ እና ተመራጭ እርምጃ ሆኗል። በአርቡ ጉባኤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይህን ጥረት ለማገዝ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ለመለገስ ቃል ሲገባ የአውሮጳ ህብረት ደግሞ ከዚህ ቀደም ለቡድኑ ማጠናከሪያ ሊሰጥ ቃል የገባውን ገንዘብ በእጥፍ አሳድጎ 116 ሚሊዮን ዩሮ አድርሷል። ህብረቱ እርዳታውን ያሳደገው የራሱን ወታደሮች ህይወት ለአደጋ ከማጋለጥ የአካባቢውን ኃይሎች አሰልጥኖ ለውጊያ ማዘጋጀቱን በመምረጥ ነው። ያም ሆኖ በአርቡ የሳህል ቡድን አምስት ኃይል ፣ የለጋሽ ሀገራት ጉባኤ ላይ ቃል የተገባው ግማሽ ቢሊዮን

ዶላር በዚህ ጉባኤ ላይ የተገኙት የ«የሳህል ቡድን አምስት» ሊቀ መንበር እና የኒዠር ፕሬዝዳንት ሞሀማዱ ኢሶኡፉ እንደተናገሩት በቂ አይደለም።

«ውጤቱ ይፋ ሆኗል። ጉባኤው በርግጥ የተሳካ ነበር። ሆኖም እንዳለ መታደል ሆኖ የተነገረው ገንዘብ የሚሸፍነው የቡድን 5 የሳህል የጋራ ኃይሎች የመጀመሪያውን ዓመት ዘመቻ ወጪዎች ነው። በኛ እና በአሸባሪዎች መካከል የሚካሄደው ውጊያ በአንድ ዓመት ማለቁን እርግጠኛ አይደለም።»
በአሁኑ ጊዜ  ስደተኞች ወደ ህብረቱ አባል ሀገራት እንዳይገቡ ለመከላከል የአውሮጳ ህብረት ከሚሰጣቸው እነዚህን ከመሰሉ ድጋፎች ጎን ለጎን በአውሮጳ ተገን የተከለከሉ ስደተኞችንም ወደ የመጡበት ለመመለስ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የአፍሪቃ ሀገራት ጋር በመደራደር ላይ መሆኑ ባለፈው ሰሞን ሾልከው የወጡ ዘገባዎች ጠቁመዋል።  ፕሬዝዳንት ማሃማዱ ኢሶኡፉ  የስደተኞች መነሻ እና መተላለፊያ የሆኑት የሳህል ሀገራት ወጣቶች ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው የሚሰደዱት ያለ ምክንያት እንዳይደለ ለጉባኤተኞቹ ባሰሙት ንግግር አስረድተዋል።
«ዛሬ በርካታ የሳህል ህጻናት የተሻለ እድል የማግኘት ህልም አላቸው። ይህ ግን ብዙውን ጊዜ ቅዠት ሆኖ ነው የሚቀረው። በርግጥ ለብዙዎቹ ሁለት አማራጮች ብቻ ናቸው ያሉት። አንዱ አንድ ስደተኛ እንዳለው እናቶቻቸው ፊት ከመሞት በባህር ላይ መሞት ወይም ደግሞ በተለያዩ የወንጀል እንቅስቃሴዎች፣ በጦር መሣሪያ እና በአደንዛዥ እጽ ዝውውር ውስጥ የሚሳተፉ የአሸባሪ ቡድኖች መሰሬ እና አደገኛ ጥሪን መቀበል ነው።»

የቡድን አምስት የሳህል ዘመቻ የእዝ ማዕከል ማሊ ናት።  ጽንፈኛ ሙስሊሞች ሰሜን ማሊን በጎርጎሮሳዊው 2012 ለአስር ወራት ከተቆጣጠሩ በኋላ በዚህ ኃይል እና በፈረንሳይ ድጋፍ የማሊ መንግሥት አካባቢውን መልሶ መቆጣጠር ችሏል። ቁጥሩን ወደ አምስት ሺህ ለማሳደግ የታሰበው ይህ ኃይል አሁን ከፈረንሳዩ የባርካኔ ተልዕኮ እና ከ6 ዓመት በፊት ማሊን ለማረጋጋት ከተሰማራው የተባበሩት መንግሥታት ሰላም አስከባሪ ኃይል ጋር አብሮ እንዲሰራ ነው የታሰበው። ባለፈው ጥቅምት የአይ ኤስ ተባባሪ የተባሉ ሚሊሽያዎች ኒዠር እና ማሊ ድንበር ላይ ከሚገኙ የአሜሪካን እና የኒዠር ወታደሮች ጋር ተጋጭተው አራት አሜሪካውያን እና አምስት የኒዠር ወታደሮች ከተገደሉ ወዲህ ስጋቱ አይሏል። ወታደሮቿን በሳህል ያጣችው ዩናይትድ ስቴትስ ፣ አይ ኤስ በአፍሪቃ ከዚህም በላይ እርምጃዎችን ሊወስድ ይችላል የሚል ስጋት አላት።  ፕሬዝዳንት ማሃማዱ ኢሶኡፉ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዳስረዱት በአካባቢው አሁን የተፈጠረው

የፀጥታ ስጋት መንስኤ እስካሁን መፍትሄ ያላገኘው የሊቢያው ቀውስ ነው። ስለዚህ የሊቢያን ቀውስ በማስወገድ በዚህ ሰብብ ችግር ውስጥ የወደቁትን ሀገራት እንታደግ ሲሉ ጠይቀዋል። ማሃማዱ እንዳሉት ከአካባቢው ሀገራት የወጣቶችን ስደት ለመግታት ለዘላቂ ልማት ትኩረት መስጠት ይገባል ።

« የሊቢያ ቀውስ የሳህልን የፀጥታ ችግር ያባባሰ ዋነኛው ምክንያት ነው። ይበልጥ እየተባባሰ እንዲሄድም አስተዋጽኦ ያደርጋል። ስለዚህ የሊቢያ መንግሥት በመላው ግዛቱ አስተዳደሩ እንዲረጋገጥ በማድረግ፣ የችግሩን መንስኤ በማስወገድ፣ በሳህል ግዛት ግጭትን የሚያባብሱትን ከስረ መሰረታቸው በማጥፋት ይህን ቀውስ ማስቆም አለብን። ከአካባቢው ህገ ወጥ ፍልሰትን እና የሚያስከትላቸውን መዘዞች  ለማስወገድ ዘላቂ ልማት እውን እንዲሆን መሥራት አለብን። ይህን በማድረግም ሥራ ፍለጋ ላይ ላሉ በርካታ ወጣቶች ተስፋ መስጠት አለብን።»

ለዚህ የፕሬዝዳንቱ ማሃማዱ ጥሪ የአውሮጳ ህብረት መልስ ሰጥቷል። ህብረቱ የሳህል ሀገራትን መሠረታዊ የፀጥታ እና የድህነት ችግሮች ለመፍታት የበኩሉን እገዛ ለማድረግ  ቃል በጉባኤው ላይ ቃል ገብቷል። የህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ዦን ክሎድ ዩንከር ህብረቱ ከሳህል ሀገራት ጎን እንደሚቆም አረጋግጠዋል።

«እኛ አውሮጳውያን ፀጥታችሁ እንዲረጋገጥ በመርዳት  ለአለመረጋጋት እና ለህገ ወጥ ስደት መንስኤ ለሆኑ መሠረታዊ ምክንያቶች መፍትሄ ለመፈለግ ለኤኮኖሚ እድገት አመቺ ሁኔታን ለመፍጠር  እና ድህነትንም ለመቀነስ  በዚህ አስቸጋሪ ጉዞ ከጎናችሁ ለመቆም እንወዳለን።»

የአውሮጳ ህብረት የአምስቱን የሳህል አካባቢ ሃገራት ልማት እና ፀጥታ የማስጠበቅ ሥራን ለመደገፍ ቃል እንደገባው ሁሉ ጀርመንም ከፀጥታው ትብብር በተጨማሪ በተለይ በልማት እርዳታው የበኩሏን  እንደምትወጣ አስታውቃለች። የጀርመን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ህብረቱ ህገ ወጥ ስደትን የመከላከል ሥራ እየተካሄደ መሆኑን አስታውሰው ፀጥታ ከምንም በላይ አስፈላጊ ቢሆንም ለሀገራቱ ልማትም የዚያኑ ያህል አስፈላጊ  እንደሆነ አስረድተዋል። ጀርመን ለአምስቱ የሳህል ሀገራት  እስከ ዛሬ 2 ዓመት ድረስ 1,7 ቢሊዮን ዩሮ  መመደቧን ገልጸው ሆኖም ከዚህ በላይ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።  እንደ ሜርክል ሁሉ በጉባኤው ላይ የተገኙት የአፍሪቃ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሙሳ ፋኪ ማሀማትም በአካባቢውን ልማትን እውን ለማድረግ ይበልጥ መሥራት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
«ማንኛውም ዓለም አቀፍ እርምጃ ምንም ያህል ጠንካራ ይሁን የአካባቢውን ሀገራት ጥረቶች ሊተካ አይችልም። በሳህል ቡድን 5 ኃይል በኩል ዓለም አቀፋዊ ራእይ ይዘን በቡድኑ ውስጥ የታቀፉ ሀገራት ያጋጠሟቸውን ዘርፈ ብዙ ፈተናዎችን በመጋፈጥ ሽብርን በመዋጋት ረገድ ጠቃሚ ተግባር እናከናውናለን። የአካባቢው ሀገራት ፖለቲካዊ ፈቃደኝነት እና ቁርጠኝነት የትግሉ ምሶሶዎች ናቸው። ሆኖም  በመንግሥት አስተዳደር በኩል የማሻሻያ ጥረቶችን ለማፋጠን እና ሁሉን አካታች ልማት ለማራመድ ይበልጥ መሥራት ያስፈልጋል።»

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሳህል ሀገራት ካልተረጋጉ በዚያ መስመር ወደ አውሮጳ የሚካሄደው ስደት  ተባብሶ ይቀጥላል የሚል ስጋት አለው።  አካባቢው በምዕራቡ ዓለም ላይ ሊሰነዘሩ  የሚችሉ ጥቃቶች መነሻ ሊሆን ይችላልም እየተባለ ነው። ችግሩ በወታደራዊ እርምጃ ብቻ ሊቃለል አለመቻሉ የልማት እርዳታዎችንም እንዲያካትቱ አስገድዷል። ይሁን እና አሁንም ይህ የአካባቢው ወጣቶች ከሀገራቸው እንዳይሰደዱ አለያም በአሸባሪዎች ጥሪ እንዳይማረኩ የሚያደርግ ዘላቂ መፍትሄ መሆኑ እንዳጠያየቀ ነው። 

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic