የአውሮጳ ህብረት አዲሱ የልማት መርህ መመሪያ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 30.05.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮጳ ህብረት አዲሱ የልማት መርህ መመሪያ

የአውሮጳ ህብረት የእርዳታ አሰጣጥ መስፈርት እና አተገባበሩ አሁንም አነጋጋሪ ሆኖ ቀጥሏል ።የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተቋሙንም ሆነ አባል ሀገራቱን ሰብዓዊ መብት በመጣስ ለሚወቀሱ አንዳንድ የአፍሪቃ አገራት የልማት እርዳታ በመስጠት አጥብቀው ይተቿቸዋል ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:41

የአውሮጳ ህብረት አዲሱ የልማት መርህ መመሪያ

የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት የልማት ሚኒስትሮች ከአስር ቀናት በፊት ብራሰልስ ቤልጂግ ውስጥ ባካሄዱት ስብሰባ በህብረቱ የልማት መርህ አዲስ መመሪያ ላይ ተስማምተዋል። አዲሱን የልማት መርህ መመሪያ የህብረቱ ፓርላማ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል። የአውሮጳ ህብረት በአሁኑ ጊዜ ከዓለማችን በልማት እርዳታ አቅርቦት የመሪነቱን ቦታ ይዟል። ከዚህ ቀደም በልማት እርዳታ ለጋሽነት ቀዳሚውን ስፍራ የምትይዘው ዩናይትድ ስቴትስ ነበረች ህብረቱ ከዓመት ወደ ዓመት በልማት ወደ ኋላ ለቀሩ ሀገራት የሚሰጠውን የገንዘብ እርዳታም እያሳደገ ነው ። ባለፈው ሚያዚያ ይፋ እንደተደረገው ህብረቱ እና አባል ሀገራት በጎርጎሮሳዊው 2016 ለልማት እርዳታ የለገሱት ገንዘብ 75.5 ቢሊዮን ዩሮ ደርሷል። ይህም በጎርጎሮሳዊው 2015 ከሰጠው ጋር ሲነፃፀር በ11 በመቶ ከፍ ያለ መሆኑ ነው የተገለፀው። የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት የልማት ሚኒስትሮች ከ10 ቀናት በፊት ባካሄዱት ስብሰባ ለህብረቱ የልማት መርህ በተዘጋጀው አዲስ መመሪያ ተስማምተዋል። አዲሱ የአውሮጳ ህብረት የልማት መርህ መመሪያ ትኩረት ዘላቂነትን እና አጋርነትን ይበልጥ ማጠናከር ነው። ህብረቱ ከጊዜያዊ እርዳታ ይልቅ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ፣

የሥራ እድል የሚፈጥሩ እና አስተማማኝ ድጋፍ የሚሰጡ ዘላቂ የልማት መርሃ ግብሮችን ነው የሚመርጠው። የህብረቱ ባለስልጣናት እንደሚሉት ህብረቱም ሆነ አባል ሀገራቱ ይህን የሚያደርጉት በሰብዓዊነት ብቻ አይደለም። የራሳቸውንም ጥቅም ለማስጠበቅ ጭምር እንጂ ። የተሻሻለው የህብረቱ የልማት ፖሊሲ መመሪያ ይፋ በተደረገበት ወቅት የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን የውጭ  እና የፀጥታ መርህ ጉዳዮች ከፈተኛ ተጠሪ ፌደሪካ ሞጎሮኒ ይህንኑ የህብረቱን ግብ ግልጽ አድርገዋል።
«በኛ እምነት ለልማት ፣ ለሰላም ማስከበር ለሰብዓዊ ተግባራት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ የደህንነታችን እና የውጭ ፖሊሲያችን እጅግ አስፈላጊ አካል ነው። እኛ ይህን ለራሳችን ደህንነት እና ብልጽግና መዋዕለ ንዋይ እንደማፍሰስ ነው የምናየው። ለዚህም ነው የተመ ሁል ጊዜ የአውሮጳ ህብረትን ከጎኑ የማያጣው ።»
የአውሮጳ ህብረት አሁን አዲስ የልማት መመሪያ ማውጣት ያስፈለገው መመሪያውን  ከወቅቱ የዓለማችን ፈተናዎች እና አጀንዳ 2030 ከተባለው የተመድ የዘላቂ ልማት ግቦች ጋር ለማጣጣም መሆኑ ተነግሯል። የዶቼቬለ የብራሰልስ ዘጋቢ ገበያው ንጉሴ እንደሚለው አዲሱን መመሪያ ከቀድሞው ከሚለዩት አንዱ የተቋሙ እና የአባል ሀገራቱ እርዳታ ትኩረት እና አቅጣጫ ወጥ እንዲሆን የሚያደርግ መሆኑ ነው ።
መመሪያው ከበፊቱ ጋር ሲተያይ ብዙም አዲስ ሊባል የሚችል እንዳልሆነ ተነግሯል ። ዓለም ዓቀፉ የፀጥታ ጥናት ተቋም ስለ መመሪያው ባወጣው ዘገባ ከአዲሱ መመሪያ ከማንም በላይ ተጠቃሚዋ አፍሪቃ ናት። ህብረቱ ከዓለም እጅግ ድሀ የሚባሉ ሀገራት ለሚገኙባት ለአፍሪቃ እርዳታ ትኩረት እንደሚሰጥ በልማት ፖሊሲ መመሪያው ላይ ጠቅሷል። የልማት እርዳታው

ትኩረት በልማት ወደ ኋላ ለቀሩ የአፍሪቃ ሀገራት መሆኑ በበጎ ቢታይም ትችት ግን አልተለየውም። እደንደገና ገበያው 
ጀርመንን የመሳሰሉ የአውሮጳ ህብረት አባል ሀገራት አዲሱ የልማት መርህ መመሪያ ላይ ስምምነት ላይ ሲደረስ ለእርዳታ ተቀባዮች ማሳሰቢያ መስጠታቸው አልቀረም። ተቀባይ ብቻ ከመሆን ችግሮችን ለመከላከል የበኩላችሁን ጥረትም አድርጉ የሚል። በብራሰልሱ ስብሰባ ላይ የተገኙት የጀርመን ተወካይ ከእስካሁኑ በተለየ አፍሪቃውያን የበኩላቸውን ሃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል ። የጀርመን የኤኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴታ ቶማስ ዚልበርሆርን  በተፈጥሮ ሀብት በበለጸጉ የአፍሪቃ ሀገራት የሚከሰተውን ረሀብ እንደምሳሌ በማንሳት ሀገራቱ ችግሩን አስቀድመው ለመከላከል በዚዘጋጁ እንደሚበጅ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረው ነበር  ።
« ረሀብ የተከሰተባቸው ሀገራት መንግሥታት የችግሩ ዋነኛ ተጠያቂዎች ናቸው። ለምሳሌ ናይጀሪያን ወይም ደቡብ ሱዳንን ተመልከቱ ፤ ሀብታም ሀገራት ናቸው። ስለዚህ በችግሩ የተጠቁ ሀገራት ለችግሩ መከላከያ ላይ ይበልጥ ወጪ እንዲያደርጉ መገፋፋት አለብን ።»
ለቀጣዮቹ ዓመታት ሥራ መሠረቱ ይህ መሆን አለበት ያሉት ሚኒስትሩ ውጊያ በሚካሄድባቸው የአፍሪቃ ሀገራት ሰብዓዊ እርዳታ እንዳይደርስ በመከልከል ረሀብን እንደ መሣሪያ መጠቀምም

ተቀባይነት እንደሌለውም ተናግረዋል። ለእርዳታ ተቀባዮች ይህን መሰሉን መልዕክት የሚያስተላልፉት የህብረቱ አባል ሀገራትም ሆኑ የአውሮፓ ህብረት የእርዳታ አሰጣጥ መስፈርት እና አተገባበሩ አሁንም አነጋጋሪ ሆኖ የቀጠለ ጉዳይ ነው።የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ተቋሙንም ሆነ አባል ሀገራቱን ሰብዓዊ መብት በመጣስ ለሚወቀሱ አንዳንድ የአፍሪቃ አገራት የልማት እርዳታ በመስጠት አጥብቀው ይተቿቸዋል  ። የአውሮጳ ህብረት በጎርጎሮሳዊው 2005 ዓም ያስቀመጣቸውን እስካሁን ሲሰራባቸው የቆዩትን ግቦች ለዘላቂ ልማት ትኩረት ከሚሰጠው አጀንዳ 2030 ከሚባለው የዘላቂ ልማት ግብ ጋር እንዲጣጣም አድርጎ አዘጋጀው የተባለው መመሪያ ታዲያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ትችት በሚሰነዘርበት የህብረቱ የልማት እርዳታ አሰጣጥ ላይ ያደረገው ለውጥ ይኖር ይሆን ?የድምጽ ማዕቀፉን በመጫን ሙሉውን ዝግጅት ማዳመጥ ይቻላል ።

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic