የአውሮጳ ህብረትና የቱርክ ስምምነት የገጠመው ትችት | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 26.04.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የአውሮጳ ህብረትና የቱርክ ስምምነት የገጠመው ትችት

የአውሮጳ ህብረት እና ቱርክ ህገ ወጥ የሚሉትን ስደት ለመከላከል የተስማማበት ውል ማወዛገቡ ቀጥሏል ። ጀርመንና የአውሮጳ ህብረት ውሉ ተቀባይነት እንዲኖረው ለማግባባት እየጣሩ ነው ። የመብት ተሟጋቾች ግን የስደተኞችን መብት ይጋፋል የሚሉትን ይህን ውል ህገ ወጥ ሲሉ ይቃወሙታል ።

በርካታ ስደተኞች ወደ አውሮፓ የሚሻገሩባት ቱርክ ፣ስደተኞችን ወደ አውሮጳ እንዳታሳልፍ ከአውሮጳ ህብረት ጋር ስምምነት ላይ ከደረሰች አንድ ወር አለፋት ። ሆኖም ውሉ አሁንም ማነጋገሩ ማከራከሩ ቀጥሏል ። በሰብዓዊ መብት ረገጣ እና በፕሬስ ነጻነት አፈና ከምትወቀሰው ከቱርክ ጋር ህብረቱ የተስማማበት ውል ተቀባይነት እንዲያገኝ የአውሮጳ ህብረትና ቱርክ እየጣሩ ነው። ለዚሁ ዓላማም ባለፈው ቅዳሜ የጀርመን መራሄ መንግሥት አንጌላ ሜርክል የአውሮጳ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ቱስክ እና ሌሎችም የህብረቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ወደ ቱርክ በመጓዝ በዚያ የሚገኝ አንድ የስደተኞች መጠለያ ጎብኝተዋል ። በዚሁ ጋዝያንቴፕ በሚገኘው የኒዚፕ መጠለያ ወደ 5 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች ይገኛሉ ። ይሁንና ሜርክል እና የአውሮፓ ህብረት ባለሥልጣናት ከዚያ ይልቅ ቱርክ እንዳይገቡ የከለከለቻቸው በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ያሉበትን ስፍራ ቢጎበኙ ስደተኞች የሚገኙበትን ሁኔታ ይበልጥ መገንዘብ ይችሉ ነበር የሚሚሉ ትችቶች ተሰንዝረውባቸዋል ። በኢስታንቡል የጀርመኑ የሃይንሪሽ በል ተቋም ሃላፊና የቱርክ ጉዳዮች አዋቂ ክርስቲያን ብራክል ሜርክልና የአውሮጳ ህብረት ባለሥልጣናት አካባቢውን እንዲጎበኙ ት የተደረገበት ምክንያት አለ ይላሉ ።

«እንደሚመስለኝ ወደ ጋዝያንቴፕ መሄዳቸው ጥሩ ነበር ።ምክንያቱም ስፍራው ብዙ ስደተኞች የሚገቡበት ቦታ ነው ። ሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢዎች በሙሉ በዚያ ይገኛሉ ።እርግጥ ነው የቱርክ መንግሥት የተደራጀ መጠለያ ወደ ሌለበት ሰዎች በየጎዳናው ላይ ወደ ሚተኙበት ኢዚሚር ዙሪያ ወደ ሚገኝ አካባቢ ሊወስዳቸው አይፈልግም ።»
በቱርክና በአውሮጳ ህብረት ስምምነት መሠረት ከጎርጎሮሳዊው መጋቢት 20 ወዲህ በህገ ወጥ መንገድ ግሪክ ገብተዋል የሚባሉ ስደተኞች ግሪክ ውስጥ ተገን እንዲሰጣቸው ካላመለከቱ አለያም ማመልከቻቸው ተቀባይነት ካላገኘ ወደ ቱርክ ይባረራሉ ። በሌላ በኩል ከግሪክ ወደ ቱርክ በተመለሰ ሶሪያዊ ምትክ ቱርክ ውስጥ ህጋዊ ተቀባይነት ያገኘ ሌላ ሶሪያዊ ወደ አውሮጳ ህብረት አባል ሃገር ይወሰዳል ። ቱርክ ህገ ወጥ የሚባለውን በባህር የሚደረግ ስደት ለመከላከል አስፈላጊውን እርምጃ ስትወስድ ከአውሮፓ ህብረትም ትብብር ይደረግላታል ። በምትኩ ቱርክ በሃገርዋ ለሚገኙ ስደተኞች መርጃ የምታውለው 3 ቢሊዮን ዩሮ ይሰጣታል ። የቱርክ የአውሮጳ ህብረት አባልነት ጥያቄ እንደገና መታየት ይጀምራልም ተብሏል ።የቱርክ ዜጎች በአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ያለ ቪዛ መግባት የሚችሉበት መንገድ ይመቻቻል ። ከአንድ ወር አንስቶ መተግበር በጀመረው በዚህ ውል መሰረት ስደተኞች በግዳጅ ከግሪክ ወደ ቱርክ እየተወሰዱ ሲሆን ጥቂቶች ደግሞ በተወሰኑ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት

እንዲሰፍሩ ተደርጓል ። አንዳንዶቹ ከቱርክ እየተጠረዙ ነው ። የመብት ተሟጋቾች « ስደተኞች ወደ አውሮጳ እንዳይመጡ ለመከላከል ያለመ »የሚሉትን የቱርክ እና የአውሮፓ ህብረት ውል አጥብቀው ይቃወማሉ ። ከመካከላቸው መቀመጫውን ለንደን ያደረገው አመነስቲ ኢንተርናሽናል አንዱ ነው ። አምነስቲ ውሉን ህገ ወጥ ነው የሚለው ። በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የአውሮጳና እና የማዕከላዊ እስያ ክፍል ምክትል ሃላፊ ጋውሪ ቫን ጉሊክ ውሉን ህገ ወጥ የምንለው ሦስት የተሳሳቱ ሃሳቦችን መሠረት ያደረገ በመሆኑ ነው ይላሉ ።ይህም በርሳቸው አስተያየት ውሉን አደገኛ አድርጎታል ።
«በአንድ በኩል በግሪክ ሁሉም ነገር በትክክል እንደሚከናወን እዚያ ያሉ ስደተኞች በሙሉ ጉዳያቸው በተገቢው መንገድ ሁሉንም ደረጃ ተከትሎ እንደሚታይ ነው የሚታሰበው ። ይህ ግን ትክክል አይደለም ። ከጥቂት ሳምንታት በፊት እኔ በአይኔ እንዳየሁት በሌስቦስ በኪዮስ ለሰዎች በቂ እርዳታ ለመስጠት ፍፁም ዝግጁ አይደሉም ።ስደተኞች የተገን ጥያቄ ለማቅረብ የሚያስችላቸው አመቺ እድል የላቸውም ። ሁለተኛው ችግር ቱርክ ለስደተኞች ደህንነት አስተማማኝ ሃገር ናት ተብሎ ነው የሚገመተው ። ሆኖም በአሁኑ ሁኔታ ይሄ በፍፁም ትክክል አይደለም ሰዎች ከቱርክ ወደ ሶሪያ እንደሚባረሩ መረጃዎች አሉን ።ይሄ ፍፁም ህገ ወጥ ነው የመጨረሻው ትልቁ ችግር ይህ ውል ሰዎችን ከአውሮጳ ለማስወጣትና ለማራቅ የተደረሰበት ስምምነት መሆኑ ነው ። »
የቱርክ ጉዳዮች አዋቂው ክርስቲያን ብራክልም የጋውሪን ወቀሳ ይጋራሉ ።
«ከውሉ ውስጥ አደገኛ የምለው ዓለም አቀፍ ህጎችንና የስደተኞችን መብቶች የሚጥስውን ክፍል ነው ።ሰዎች ወደ ጦርነት ቀጣናዎቹ እንደማይላኩ ተነግሯል ። ይሁንና ቱርክ ይህን መብት እየጣሰች ነው ።ሆኖም ቱርክ ይህን አትቀበልም ።የጀርመን መንግሥትም እንዲሁ ። ይሁንና ይሄ እንደሚፈፀም እኔ ከሶሪያውያን ያገኘሁት ግልፅ ማስረጃ አለኝ ።ራሱን እስላማዊ መንግሥት ብሎ ከሚጠራው ከIS ወይም ከአሳድ የቦምብ ድብደባ መሸሽ የሚፈልጉ ሰዎች አልቻሉም ።መራሂተ መንግሥት

አንጌላ ሜርክል ቱርክ ሶሪያ ገብታ ስደተኞች መቀበያና የፀጥታ ቀጣና እንድትከልል አንጌላ ሜርክል ድጋፋቸውን ሰጥተዋል ። ይሄ ግን ሊተገበር የማይችል ቅዠት ነው ።
ቱርክ ስደተኞችን ወደ ሶሪያ ትልካለች መባሉን በማስተባበሉ ቀጥላለች ። የአምነስቲ እንተርናሽናሏ ጋውሪ ቫን ጉሊክ ግን ድርጅታቸው ሰዎች ጦርነት ወደ ሚካሄዳባት ወደ ሶሪያ በግዳጅ ለመመለሳቸው ማስረጃዎች አሉን ይላሉ ።
«ለምሳሌ በአንድ አጋጣሚ የተወሰኑ ወጣት ወንዶች ይጫወቱ ከነበረበት ስፍራ ታፍሰው ከወላጆቻቸው ተነጥለው በአውቶብስ ወደ ሶሪያ ተልከዋል ይህ ፍፁም ህገ ወጥ ነው ። ይታያችሁጦርነት ሸሽተው የመጡ ሰዎች በዚህ ዓይነት መንገድ ሲባረሩ ። ቱርክ ግን ይህን ታስተባብላለች ።እኛ ግን መረጃ አለን ። ሌሎች ቡድኖችም ይህን አረጋግጠዋል ።ጋዜጠኞችም ይህን አረጋግጠዋል ። ስለዚህ ይህ አላደርግኩም ከማለትዋም በላይ ጉዳዩን በቅጡም አልተከታተለችውም ። የአውሮጳ መንግሥትትም ተመሳሳይ ጨዋታ ነው የሚጫወቱት ።«ማጣራት አለብን ፣ ቱርክ ይህን አላደረግኩም ካለች ልናምናት ይገባል ይላሉ » ይህ ግን ተቀባይነት የለውም ።»
ዓለማችን በአስቸጋሪ የስደተኞች ቀውስ ውስጥ በምትገኝበት በአሁኑ ሰዓት ይላሉ ቫን ጉሊክ አውሮጳ የችግሩ ተጋሪ እንጂ ችግሩን የሚያርቅ መሆን የለበትም ። እንዲያውም አውሮጳ ተጨማሪ ስደተኞችን ሊቀበል ይገባል ብለዋል ። የምዕራባውያን ስልታዊ አጋር የሆነችው ቱርክ በርካታ የሶሪያ ስደተኞችን ካስጠጉ ሃገራት አንዷ ናት ። በሃገሪቱ ከሶስት ሚሊዮን በላይ ስደተኞች ይገኛሉ ። ለነዚህ ሁሉ ሰዎችደግሞ በቂ መጠለያ ምግብ የላትም ። የስደተኞችን አያያዝ እንድታሻሻልም ከአውሮፓ

ህብረት 3 ቢሊዮን ዩሮ ሊሰጣት ቃል ተገብቶላታል። ቫን ጉሊክ ይህ ድጋፍ የሚሰጣት ቱርክ የስደተኞችን መብትም ልታከብር ይገባታል ይላሉ ።
«ገንዘብ በርግጥ አስፈላጊ ነው ። ቱርክ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስደተኞችን ማስጠለልዋ የታወቀ ነው ። እናም ድጋፍ ያስፈልገዋል ገንዘቡ ለስደተኞች መኖሪያ ግንባታ እና ለመሳሰሉት ነው የሚውለው ሆኖም ቱርክ ገንዘብ ሊገዛው የማይችል ብዙ ነገሮችን ማድረግ አለባት ። ይህም የተገን አሰጣጥ ስርዓቷን ማስተካከል ለሶሪያዎች ብቻ ሳይሆን ዓለም ዓቀፍ ጥበቃ የማግኘት መብት ያላቸው ስደተኞችን በተገቢው መንገድ መብታቸው መጠበቅ አለበት ። ይህም የሶሪያ ስደተኞች በፍፁም የጦርነት ቀጣና ወደ ሆነችው ወደ ሶሪያ መመለስ የለባቸውም ። ይህ መሆን አለበት ። ይህ ደግሞ በገንዘብ የሚገኝ አይደለም ፤ በፖለቲካ ፈቃደኝነት እንጂ »
ቱርክ ውስጥ ብዙ ጊዜ የቆዩ ስደተኞች ህጋዊ ወረቀት ስለሌላቸው ሥራ ማግኘት አይችሉም ። ለደህንነታቸውም ይሰጋሉ ። ህጋዊ ፈቃድ ስለሌላቸው በማንኛውም ጊዜ ከቱርክ ሊባረሩ ይችላሉ ። ከዚህ ሌላ ስደተኞች በቱርክ ድንበር ጠባቂዎች እንደሚበደሉም ይናገራሉ ።በሌላ በኩል በቅርብ ጊዜው የአውሮጳ ህብረትና የቱርክ ውል ምክንያት ግሪክ ውስጥ በርካታ ስደተኞች እየተሰቃዩ ነው ። ቫን ጉሊክ የአውሮፓ ህብረት ለነዚህ ስደተኞች ጉዳይ መፍትሄ እንዲሰጥ አሳስበዋል ።
«በአሁኑ ጊዜ ከግሪክ መውጣት ያልቻሉትን ስደተኞች መከፋፈል አለባቸው እነዚህ ሰዎች ተረስተዋል ። ወደ 5o ሺህ የሚዎጠሩ ሰዎች መተላለፊያ ተዘግቶባቸዋል ። እነዚህ ወደ ሌሎች የአውሮጳ ሃገራት መላክ አለባቸው ።ይህም የአውሮጳ ሃገራት ከተስማሙባቸው ጉዳዮች አንዱ ነው ። ይህ በአፋጣኝ ተግባራዊ መሆን አለበት ። ሌላው ጉዳይ ሰፈራ ነው። ከቱርክ ጋር የተደረሰው ስምምነት አንድ በጎ ጎን መንግሥታት ከቱርክ የተወሰኑ ስደተኞች ወደ አውሮፓ በአስተማማኝና ህጋዊ መንገድ እንዲገቡ እየተደረገ ነው ። ይህን በአፋጣኝ ተግባራዊ ማድረግ አለባቸው ።ሰዎችን መጠረዝን ከማስቀደም ይልቅ በመልሶ ማስፈር ነው መጀመር ያለባቸው ።»

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic