የአውሮጳ ህብረትና የቱርክ ስምምነት እጣ ፈንታ  | ኢትዮጵያ | DW | 10.03.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

የአውሮጳ ህብረትና የቱርክ ስምምነት እጣ ፈንታ 

የአውሮጳ ህብረት ገንዘቡን በቀጥታ ለአንካራ አይሰጥም።ይልቁንም ለተለያዩ ለስደተኞች ድጋፍ ለመስጠት የተቀረጹ ፕሮጀክቶችን በሚያካሂዱ አጋሮች በኩል እርዳታው ለሶሪያ ስደተኞች እንዲደርስ ነው የሚያደርገው።ገንዘቡ የሚውለውም ቱርክ ለሚገኙ ስደተኞች ሰብዓዊ እርዳታ ለትምሕርት ለጤና ለመሠረተ ልማት ግንባታ እና ማህበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ድጋፍ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:53

የአውሮጳ ህብረትና የቱርክ ስምምነት

ቱርክ ከዚህ ቀደም ስታስጠነቅቅ እንደቆየችው ከግሪክ ጋር የሚያዋስናትን ድንበሯን በመክፈት ስደተኞች ወደ ግሪክ እንዲገቡ መፍቀዷ የሰሞኑ የአውሮጳ ህብረት ራስ ምታት ሆኖ ከርሟል።ባለፈው ሰሞን 33 ወታደሮቿ ሶሪያ ውስጥ ከተገደሉ በኋላ ቱርክ በወሰደችው በዚህ እርምጃ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ቱርክና ግሪክ ድንበር ላይ ፈሰው ወደ አውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ለመሻገር እየተጠባበቁ ነው።ስደተኞቹ ቱርክና ግሪክ ድንበር ላይ በግሪክ ፖሊስ አስለቃሽ ጢስ እና ውሐ እየተረጨባቸው ና ሌሎችም ኢሰብዓዊ ድርጊቶች እየተፈጸመባቸው በሚንገላቱበት በአሁኑ ወቅት የአውሮጳ ህብረት ቱርክን ለማግባባት መጣሩን ቀጥሏል።ሁለቱም ወገኖች የዛሬ 4 ዓመት የተስማሙበትን የስደተኞች ውል ባለማክበር ርስ በርስ ሲወነጃጀሉ ከርመዋል።ህብረቱ ቱርክ ስደተኞችን እየለቀቀችብን ነው ሲል፣ቱርክ ደግሞ 27 አባል ሃገራትን ያቀፈው የአውሮጳ ህብረት በውሉ መሠረት ቃል የገባውን ገንዘብ አልሰጠኝም ስትል እየከሰሰች ነው።ሁለቱ ወገኖች መጋቢት 2016 በተፈራረሙት ውል መሠረት ቱርክ ወደ አውሮጳ ህብረት ድንበር የሚያቀኑ ስደተኞችን በሃገርዋ እንድታስቀር፣ የአውሮጳ ህብረት ደግሞ በፈንታው ለቱርክ 6 ቢሊዮን ዩሮ ለመስጠት ቃል ገብቷል። ገንዘቡ የሚሰጣትም በግዛቷ ለሚገኙ የሶሪያ ስደተኞች እርዳታ ነው።ከዚህ በተጨማሪም በውሉ የቱርክን የአውሮጳ ህብረት አባልነት ጥያቄ ማፋጠን እንዲሁም የቱርክ ዜጎች ቪዛ ሳያስፈልጋቸው ወደ አውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት እንዲገቡ ማድረግም ተካቶ ነበር።ከውሉ በኋላ በቱርክ በኩል ወደ ግሪክ ደሴቶች የሚጎርፈው ስደተኛ እጅግ መቀነሱ ነው የተነገረው።ሆኖም የቱርክ የአውሮጳ ህብረት አባልነት ድርድር አልተንቀሳቀሰም።ቱርክ ዜጎቿ ለአጭር ጉዞ እና ለሥራ ያለ ቪዛ በአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት መግባት እንዲችሉ ያቀረበችው ጥያቄም ተግባራዊ አልሆነም።ሁለቱን ወገኖች ከዚህ በላይ የሚያነታርከው ግን የገንዘብ ጉዳይ ነው። ባለፈው ሳምንት ለፓርቲያቸው አባላት ባሰሙት ንግግር ላይ ድንበሯን መክፈትዋ ሕጋዊ ነው ያሉት የቱርክ ፕሬዝዳንት ጠይብ ሬቼብ ኤርዶሃን የአውሮጳ ህብረት በስደኞች ለተጨናነቀችው ቱርክ ሰጥቶ የማያውቀው ያሉትን አፋጣኝ እርዳታ ለግሪክ መስጠቱን በእጅጉ ነቅፈው ነበር። 

«ለስደተኞች ድንበራችንን የመክፈት  ውሳኔያችን  ከዓለም ቀፍ ሕግ ጋር ሙሉ በሙሉ አብሮ የሚሄድ ነው።ግሪክ እና የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራትም በዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ  መሠረት በየሃገሮቻችሁ ጥገኝነት ማግኘት የሚፈልጉ ስደተኞችን መብቶች እንድታከብሩ ጥሪ አቀርባለሁ።የአውሮጳ ህብረት በአፋጣኝ 350 ሚሊዮን ዩሮ ሰጥቷል።ከዚህ በተጨማሪም ጀልባዎች የጦር መሣሪያዎች እና የምግብ እርዳታ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑንም አስታውቋል።ሆኖም እኛ ላለፉት 10 ዓመትት 4 ሚሊዮን የሶሪያ ስደተኞችን ተቀብለን አስተናግደናል።እንደዚህ ዓይነቱን ድጋፍ ሰጥታችሁን ታውቃላችሁ?በቀላሉ ውሳኔ ማሳለፍ ይችላሉ።ለኛ ግን ቃል የገቡልንን አልሰጡንም።ታማኝነት ይጎድላቸዋልና።» 
ኤርዶሀን ህብረቱን የወቀሱት ባለፈው ሳምንት የህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን ከግሪክ ጉብኝታቸው በኋላ የግሪክን የስደተኞች ጫና ለማቃለል ለድንበር ማስጠበቂያ እና ለስደተኞች አስተዳደር የሚውል የ700 ሚሊዮን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚሰጥ ካሳወቁ በኋላ ነበር። ፎን ዴር ላየን ግሪክ ውስጥ በሰጡት መግለጫ ከ700 ሚሊዮን ዩሮው ውስጥ 350 ሚሊዮን ዩሮው ወዲያውኑ የሚሰጥ መሆኑን ነበር የተናገሩት።
«በግሪክ ደሴቶች ባሉ የስደተኞች መጠለያዎች ከመጠን በላይ ስደተኞች ይገኛሉ። አሁን ደግሞ ተጨማሪ ስደተኞች እየገቡ ነው።እናም ተጨማሪ እርዳታ ያስፈልጋል።የአውሮፓ ህብረት በአፋጣኝ የሚሰጠው 350 ሚሊዮን ዩሮ በግሪክ ደሴቶች የሚታየውን ሁኔታ ለማሻሻል የተወሰደ የመጀመሪያ እርምጃ ነው።ሌላ 350 ሚሊዮን ዩሮ ደግሞ ይከተላል።»
 በኢድሊብ ሶሪያ ከተባባሰው ጦርነት በኋላ ተጨማሪ የሶሪያ ስደተኞች ይመጡብኛል ብለው የሰጉት የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬቼፕ ጠይብ ኤርዶሀን ተጨማሪ ገንዘብ ጠይቀዋል። የአውሮጳ ህብረት ቃል የገባውም ገንዘብ ቢሆን ቱርክ ሙሉ በሙሉ አልተሰጠኝም ነው የምትለው። የአውሮጳ ህብረት የፍልሰት ጉዳዮች ኮሚሽን እንደሚለው ግን ህብረቱ ለቱርክ የገባውን ቃል አላጠፈም።ለ1.7 ሚሊዮን ስደተኞች ጥሬ ገንዘብ መክፈሉን አላቆመም። 500 ሺህ ህጻናትን ለሚያስተምሩ መምህራንም እንዲሁ ገንዘብ መክፈሉን ቀጥሏል ሲሉ የአውሮጳ ህብረት የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ኮሚሽን ኮሚሽነር ኢልቫ ጆንሰን ህብረቱ ለስደተኞች የሚያደርገውን እርዳታ አለማቋረጡን አስረድተዋል ።አሁን እርዳታው እንዴት መቀጠል እንዳለበት መወያየቱ ይበጃል ሲሉ መፍትሄውን ጠቁመው ነበር። 

«የአውሮጳ ህብረት ከቱርክ ጋር የደረሰበትን ስምምነት ተግባራዊ እያደረገ ነው። አሁንም ቱርክ የሚገኙ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን እየረዳን ነው።ይህንንም ድጋፋችንን እንቀጥላለን።በእርግጥም ከዓለም እጅግ ብዙ ስደተኞችን ያስጠጋችው ጀርመን በአውሮፓ ህብረት ልትረዳ ይገባል።ስለዚህ አሁን ትኩረቱ ወደ ውይይት መመለስ መሆን አለት መሆን አለበት።ይኽውም እርዳታው እንዴት መቀጠል እንዳለበት መወያየት አለብን።»
የአውሮጳ ህብረት ገንዘቡን በቀጥታ ለአንካራ አይሰጥም።ይልቁንም ለተለያዩ ለስደተኞች ድጋፍ ለመስጠት የተቀረጹ ፕሮጀክቶችን በሚያካሂዱ አጋሮች በኩል እርዳታው ለሶሪያ ስደተኞች እንዲደርስ ነው የሚያደርገው።ገንዘቡ የሚውለውም ቱርክ ለሚገኙ ስደተኞች ሰብዓዊ እርዳታ ለትምሕርት ለጤና ለመሠረተ ልማት ግንባታ እና ማህበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ ድጋፍ ነው። ቱርክ አሁን በሃገርዋ የምታስተናግደው 4 ሚሊዮን ስደተኛ የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ካስጠጉት በጣም በብዙ የሚልቅ ነው።የሶሪያው ጦርነት ከተባባሰ የስደተኞቹ ቁጥር ከፍ እንደሚል ነው ቱርክ ትሰጋለች።የአውሮፓ ህብረት እንደሚለው ለቱርክ ቃል የተገባው ገንዘብ የተሰጠው በሁለት ተከፍሎ ነው።በ18 ወራት ውስጥ 3 ቢሊዮን ዩሮ የሚፈጁ ፕሮጀክቶች ተዘጋጅተዋል።ከ70 በላይ ፕሮጀክቶችም ሥራ ጀምረዋል። ላለቁ የኮንትራት ሥራዎችም ከ2 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ተከፍሏል። ቃል የተገባው 6 ቢሊዮን ዩሮ ሙሉ በሙሉ ሥራ ላይ ውሏል ይላል የአውሮጳ ህብረት ። ቱርክ በበኩሏ ከ6ቱ ቢሊዮን ግማሹ ብቻ ነው የተከፈል ነው የምትለው።ከዚህ በተጨማሪ ወደ 36 ቢሊዮን ዩሮ ወይም 40 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የራስዋን ገንዘብ ለስደተኞች ማውጣትዋንም ትናገራለች። ቱርክ ስደተኞችን እለቅባችኋለሁ ስትል ባለፈው ሰሞን ድንበሯን በመክፈት የወሰደችው የማስፈራራት እርምጃ የአውሮጳ ህብረትን ትኩረት ስቦ የህብረቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አንካራ ሲመላለሱ ነው የከረሙት። ህብረቱ ሰሞኑን ከቱርክ ባለሥልጣናት ጋር ሲወያይ መሰንበቱን ያስታወሱት የህብረቱ የውጭ ጉዳዮች ሃላፊ ጆሴፕ ቦሬል ህብረቱ ቱርክን መርዳቱ ይቀጥላል ብለዋል። 
« ከቱርክ ባለሥልጣናት ጋር በጣም ትኩረት የሚስቡ በርካታ ውይይቶችን አድርገናል።ከመከላከያ ሚኒስትሩ ከሃገር ውስጥ ጉዳይ እና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ከምክትል ፕሬዝዳንቱም ጋር ተነጋግረናል።የአውሮጳ ህብረት የመሪዎች ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ሻልርስ ሚሼልምአንካራ ድረስ ሄደው ከፕሬዝዳንቱ ጋርም ተወያይተዋል።እነርሱ እኛ የምንሰጠው እርዳታ በቂ ነው ብለው አያምኑም።እርግጥ ነው በ2016 በተዋዋልንበት ጊዜ የኢድሊብ ሁኔታ እንደ አሁኑ አልነበረም።ሆኖም በተቻለ መጠን እርዳታ መስጠታችንን እንቀጥላለን።ሰዎች ወደ ድንበሩ እንዲሄዱ መገፋፋት መፍትሄ እንደማይሆን ነግረናቸዋል።ሰዎችን ለአደጋ እያጋለጡ ነው።እኛ በትብብራችን እንቀጥላለን።ግን ትብብራችን የሰዎችን በሚያንቀሳቅሱበት ወቅት አይሆንም። ስደተኞቹን ወደ አውሮፓ የመሻገር እድል እንዳለ የማሳመን ሙከራ እየተደረገ ነው። ሆኖም ይህ ሁኔታ የለም።»

ቱርክ እና የአውሮጳ ህብረት የተስማሙበት የስደተኞች  ውል ወደ ህብረቱ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር በእጅጉ በመቀነስ የታሰበለትን ዓላማ አሳክቷል።ፍላጎታቸው ከዳር እንደማይደርስ የተረዱ በርካታ የሶሪያ ስደተኞች ጉዞውን ላለመጀመር ወስነዋል።ይህም ከጎርጎሮሳዊው 2016 ወዲህ ግሪክ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር በእጅጉ እንዲያንስ አድርጓል።በአንጻሩ ከህብረቱ በርካታ ድጋፍ የሚደረግላት ግሪክ ለሶሪያ ስደተኞችን የተገን ማመልከቻዎች ፈጣን መልስ መስጠት እንደተሳናት ነው። ሂደቱ ወራቶች ብቻ አይደለም ዓመትት ይወስዳል።በዚህ ምክንያትም ከዚህ ቀደም ይገመት ከነበረው በጣም ዝቅተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ናቸው ወደ ቱርክ የሚመለሱት ።በአሁኑጊዜ 20 ሺህ የሚሆኑ ስደተኞች ሌስቦስን በመሳሰሉት የምሥራቅ ግሪክ ደሴቶች አስቸጋሪ ሕይወት እየገፉ ነው።ችግሩን የሚያወሳስበው ሌላው ጉዳይ ደግሞ አብዛኛዎቹ የህብረቱ አባል ሃገራት ግሪክ የሚገኙ ስደተኞችን ለመከፋፈል ፈቃደኛ አለመሆናቸው ነው። የፍልሰት ጉዳዮች ተመራማሪ ጀራልድ ክናውስ ፣ የአውሮጳ ህብረት እነዚህን ጉድለቶች ካላስተካከለ የቱርክ እና የአውሮጳ ህብረት የስደት ውል የመፍረስ አደጋ ሊገጥመው እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
«የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ቱርክ ለሚገኙ ሶሪያውያን  የሚሰጡትን እርዳታ ለመቀጠል ዝግጁነታቸውን በግልጽ ማሳየት አለባቸው። 6 ቢሊዮኑ ዩሮ እስከ 2020 መጨረሻ ወጪ ሊደረግ የታሰበ ነው። በቱርክ የሶሪያ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመሄዱ ግልጽ ነው።ስለዚህ የአውሮጳ ህብረት አባል ሃገራት ቱርክ ለሚገኙ የሶሪያ ስደተኞች በትምሕርት በጤና እና በሌሎችም ማህበራዊ ዘርፎች ድጋፍ መስጠታቸውን መቀጠል አለባቸው።በግሪክ ደሴቶች ውስጥም ብዙ መሠራት አለበት።ግሪኮች ለስደተኞች የተገን ማመልከቻዎች መልስ የሚሰጡበትን ሂደት ለማፋጠን ቃል ገብተዋል።ሆኖም ተገን ሊሰጣቸው የማይገባውን መመለስ ሲኖርባቸው በሦስት ዓመት ውስጥ የመለሱት ቁጥር አነስተኛ ነው።የግሪክ የተገን ጉዳይ መስሪያ ቤት ሂደቱን ማፋጠን አልቻለም።ይህ የሚስተካከለው ደግሞ ግሪክን በመኮነን ሳይሆን ጀርመን ፈረንሳይ እና ሌሎች ሃገራት ሊተገበር የሚችል እቅድ በማውጣት ለግሪክ አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ነው።»     
የቱርክን ስጋት ለመስማት እና መፍትሄ ለመፈለግ ዝግጁነታቸውን ሲገልጽ የቆዩት የአውሮጳ ህብረት ባለሥልጣናት ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶሀን ጋር የዛሬ 4 ዓመቱን ውል ትናንት ብራሰልስ ውስጥ ገምግመዋል።የትናንቱ ንግግር የሁለቱ ወገኖች የመጀመሪያው እንጂ የመጨረሻው ውይይት እንዳልሆነ መሆኑን ነው የአውሮጳ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን የተናገሩት።

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች