የአዉቶሚክ ቦምብ ባለቤትዋ ዓለም | ዓለም | DW | 10.08.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

የአዉቶሚክ ቦምብ ባለቤትዋ ዓለም

ዛሬ ከዩናይትድ ስቴትስ እስከ ሩሲያ፤ ከፈረንሳይ እስከ ብሪታንያ፤ ከቻይና እስከ ሕንድ፤ እስከ ፓኪስታን ያሉ መንግሥታት በማጥፋት አቅሙ ከያኔዉም ቦምብ እጅግ የረቀቀ-የጠከረዉን የኒኩሌር ቦምብ ታጥቀዋል።ሰሜን ኮሪያ የኒኩሌር ቦምብ እንዳላት አምናለች።እስራኤልም በይፋ አትመን እንጂ ቦምቡን መታጠቋን ብዙዎች «የአደባባይ ሚስጥር» ይሉታል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:25
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
16:25 ደቂቃ

የአዉቶሚክ ቦምብ ባለቤትዋ ዓለም

የቀድሞዉ ዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሐሪ ኤስ ትሩማን ከተወሰኑ ጄኔራሎቻቸዉ የቀረበዉን ተቃዉሞ፤ ማንገራገርና ማቅማማት በዘዴም፤ በቁጣም፤ ካስወገዱ በኋላ-ጊዜ አላጠፉም።የመጨረሻዉን ትዕዛዝ ሰጡ።ትዕዛዙም ተፈፀመ።ነሐሴ 6-19145 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ።) የእስከዚያ ዘመኑ ዓለም አይቶ-ሰምቶት በማያዉቀዉ ቦምብ የጃፓኗ ከተማ ወደመች።ሔሮሺማ።በሳልስቱ ናጋሳኪ ተደገመች።ዘንድሮ ሰባ-ዓመታቸዉ።ብዙ መቶ ሺዎችን የፈጀዉ የአዉቶሚክ ቦምብ ድብደባ መነሻ፤ የያኔ-ምክንያት-ዉጤቱ ማጣቃሻ፤ ያሁን አስተጋብኦቱ መድረሻችን ነዉ።

ዩናይትድ ስቴትስን ከ1933 ጀምሮ የመሩት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዘቬልት ስልሳ-ሰወስተኛ ልደታቸዉ ለማክበር አስር ቀን ሲቀራቸዉ ጥር-20 1945 ያሳለፉት ዉሳኔ-በአራተኛ ወሩ ሚያዚያ የሚሆነዉን ተንብየዉ ነዉ ማለት ሰዉዬዉን ከነብይ ማስተካከል ሊሆን ይችላል።ሚያዚያ-አስራ-ሁለት 1945 የሆነዉ-ሲሆን ግን የኛን ብልሕ መሪ-አርቆ አስተዋይነት አለመቀበል ከባድ ነዉ።

ዩንይትድ ስቴትስን እንደ ምጣኔ ሐብት አዋቂ-ከትልቅ ኪሳራ አዉጥተዉ ሞልተ ለተረፈዉ ሐብታምነት ያበቁት፤ እንደ ቆራጥ የጦር መሪ ከትልቁ ድል ያቃረቡት፤ እንደ ሳይንቲስት የእስከዚያ ዘመኑ ሰዉ-ከማያዉቀዉ መሳሪያ ጋር ያስተዋወቁት፤ እንደ ሠላም አቀንቃኝ ፖለቲከኛ የዓለም ሰላም አስከባሪ የተባለዉ ድርጅት የመሰረቱት ፕሬዝደንት ሩዘቬልት-የትልቁን ድል ፍፃሜ፤የአዲሱን ጦር መሳሪያ ዉጤት፤ የትልቁን ድርጅት ቁመና ለማየት አልታደሉም።ሞቱ።ሚያዚያ 12 1945።

ሩዘቬልት ጥር 20 ለአራተኛ ዘመነ-ሥልጣን ቃለ መሐላ ሲፈፅሙ-በምክትል ፕሬዝደንትነት የሰየሟቸዉ ሐሪ ኤስ ትሩማን የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን ሲወርሱ- የሟች አለቃቸዉን ብልሐት፤ ግርማ ሞገስ፤ ሥም ዝና እንደ ሥልጣኑ መዉረስ አልቻሉም።አይችሉም ነበርም።የሩዘቬልትን ጅምር ከዳር ለማድረስ እንደሚጥሩ ግን ካንዴ በላይ ቃል መግባታቸዉ ግን አልቀረም።

ትሩማን የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን ሲረከቡ የሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ቆስቋሽ የነበረችዉ የናትዜ ጀርመን ከይፋ አዋጅ በስተቀር ተሸንፋለች።የአዶልፍ ሒትለርም የቀደኛ ጠላታቸዉን የሩዘቬልትን ሞት በሰሙ በሳምንቱ ሩዘቬልትን ተከትለዉ ሞተዋል።

ሰኔ 18፤ 1945 ፖስትዳም-ጀርመን ላይ በተደረገዉ የድል አድራጊ ሐገራት መሪዎች ጉባኤ ላይ አዲሱ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሐሪ ኤስ ትሩማን ከአንጋፋዉ የሶቬት ሕብረት መሪ ጆሴፍ ስታሊን ጋር የገጠሙት አተካራ-የሩዝቬልትን ጅምር ዳር ለማድረስ ካቀዱ-ዕቅዳቸዉን የሚያስፈፅሙት በራሳቸዉ መንገድ እንጂ በቀድሞ አላቃቸዉ ትልም እንዳልሆነ ፍንጭ የሰጠ ነበር።

አስከፊዉን ጦርነት ባንድ አብረዉ በመዋጋታቸዉ ለድል የበቁት ሐያላን መንግሥታት የወደፊቷን ዓለም በጋራ ከመምራት ይልቅ ዓለምን በርዕዮተ-ዓለም አጥር ለሁለት እንደሚገምሷት በፖስትዳሙ ጉባኤ የታየዉ ልዩነት ግልፅ ምልክት ነበር።የፖስትዳሙ ጉባኤ ባበቃ በወሩ ግን ሳንፍራንሲስኮ-ዩናይትድ ስቴትስ ዉስጥ የአዲሱ ዓለም አቀፍ ድርጅት የመተዳደሪያ ደንብ ሲፀድቅ ደግሞ ሐያላኑ ጥቅማቸዉ እኩል ሲከበር-ዓለም በአንድነት እንደሚመሩ ጥቅማቸዉ ሲበላለጥ ግን ዓለምን እንደሚያቃርኑ አስመሰከሩ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መተዳደሪያ ደንብ ሲፀድቅ ፕሬዝደንት ሐሪ ኤስ ትሩማን ያስተላለፉት መልዕክት የሐያላኑን ልዩነትን ሳይሆን አንድነትን፤ ጦርነትን ሳይሆን ሠላምን ሰባኪ ነበር።

«በነዚሕ በሐይማኖት፤ በዘር፤ በቋንቋና በባሕል ብዙ በሚለያዩ ሐምሳ ሐገራት መካከል ይሕ ስምምነት ይደረጋል ብለዉ የተጠራጠሩ ብዙዎች ነበሩ።እነዚሕ ልዩነቶች ግን ተረስተዋል።እነዚሕ ልዩነቶች ጦርነትን ለማቆም መፍትሔ በመፈለግ የማይናወጥ አንድነት ተለዉጠዉ ተረስተዋል።»

ትሩማን ከዚያ የኦፔራ አዳራሽ ለተሰበሰቡት የሐምሳ ሐገራት ተወካዮች ሥለአንድነትና-ሲናገሩ ፖስትዳም ላይ ከስታሊን ጋር የገጠሙትን ዉዝግብ የረሱ መስለዉ ነበር።ጦርነት እንዲቆም ሲያሳስቡ እስያ ላይ በአዋጅ ያልተጠናቀቀዉ ጦርነትን ለማስቆም የቀየሱትን ብልሐት በጣሙን ለጃፓን የደገሱትን የሚያዉቅ- አልነበረም።ተሰብሳቢዎች ከመቀመጫቸዉ ተነስተዉ ያጨበችባሉ።በደስታ።ትሩማንም ጦርነት ለሰቸዉ ዓለም የሠላም ንግግራቸዉን ያንቆረቁራሉ። ሐምሌ 26 ነዉ።

«ከጥቂት ዓመታት በፊት ይሕ መተዳደሪያ ደንብ፤ ከሁሉም በላይ ደንቡን የማይክበር ፍቃደኝነቱ ኖሮን ቢሆን ኖሮ ዛሬ የሞቱት ሚሊዮኖች በኖሩ ነበር። ደንቡን ለማክበር የገባነዉን ቃል ወደፊት ከጣስነዉ ደግሞ ዛሬ በሕይወት ያሉ ሚሊዮኖች ይሞታሉ።ዕቅድ የሚወጣበት ጊዜ አለ።እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ አለ።እርምጃ የሚወሰድበት ጊዜ-አሁን እዚሕ አለ።»

ሐምሌ ሃያ-ስድት።የዩናይትድ ስቴትሱ ዓለም አቀፍ የስልታዊ ጥናት ተቋም ባልደረባ ናታን ዶኖሁ እንደፃፉት ፕሬዝደንት ሐሪ ኤስ ትሩማን ሳንፍራንሲስኮ ላይ ሥለ ሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ እና ሥለ ሠላም ሲናገሩ አምስት ጉዳዮችን በዕምሯቸዉ ሳያሰላሰሉ አልቀሩም።እስያ ላይ ሙሉ በሙ ያልቆመዉን ጦርነት በተቻለ ፍጥነት ማጠናቀቅ-የመጀመሪያዉ ነዉ።

ሁለት ቢሊዮን ዶላር የወጣበትን የአቶሚክ ቦምብ ሥራን ተገቢነት ማስመከር-ሁለተኛዉ።እስከዚያ ዘመን ድረስ ያን ያሕል ገንዘብ የፈሰሰበት ፕሮጄክት ዓለም አታዉቅም።ቦምቡ የሆነ ቦታ ፈንድቶ የዩናይትድ ስቴትስን ኃያልነት ካላረጋገጠ በትሩማን እምነት በሳቸዉና በመስተዳድራቸዉ ላይ የሚነሳዉን ተቃዉሞ በቀላሉ ማብረድ የሚቻል አልመሰላቸዉም።ከፖስትዳሙ ጉባኤ በሕዋላ የዓለምን የልዕለ-ሐይልነት ሥፍራ ለመያዝ የሚንጠራሩትን ሥታሊንን ማስደንገጥ-ሰወስተኛዉ ምክንያት ነዉ።

ያን አዉዳሚ ቦምብ ላለማፈንዳት ምክንያት ማጣታቸዉ-ይቀጥላል።የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ጃፓንን ለማስገበር በአየርም፤በባሕርም እስያዊቱን ሐገር መደብደብ ከጀመረ ሰንብቷል።ትሩማን አዉቶሚክ ቦምቡ ሒሮሺማ ላይ እንዲጣል ከማዘዛቸዉ በፊት የዩናይትድ ስቴትስ ጦር በጣለዉ መደበኛ ቦምብ ና ሚሳዬል ከሰወስት መቶ ሺሕ በላይ ሰላማዊ ሕዝብ ተገድሏል።

ጃፓኖችን በሙሉ እንደ ጠላት እንዲያይ የተደረገዉ አብኛዉ አሜሪካዊ ይሁን የተቀረዉ ዓለም ሕዝብ ድብደባዉ በሰላማዊ ሰዎችና ተቋማት ላይ የሚያደርሰዉን ዉድመት እንደ ጥፋት ሥላልቆጠረዉ ተጨማሪ ሕዝብ ቢያልቅ ተቃዋሚ ይኖራል ብለዉ ትሩማን አልገመቱም።

ተመራማዊ ዶኖሑ አዉዳሚዉን ቦምብ ለመጣል አምስተኛ ምክንያት ያደረጉት ወይም ትሩማን ሳንፍራንሲስኮ ላይ ሥለ-ሠላም ሲናገሩ ሥለ ጦርነት ከሚያብሰለስሏቸዉ ጉዳዮች አንዱ የጃፓን ጦር ፐርል ሐርበር ወደብ ላይ አድርሶት የነበረዉን ጥፋት መበቀልን ነበር።ፕሬዝደንት ትሩማን የሚያወጥነጥኑት ሐሳብ ሲጨርሱ ጄኔራሎቻቸዉን አዘዙ።ከጄኔራሎቹ ቢያንስ አንዱ ቦምቡ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚያደርሰዉን ጥፋት እና ጃፓኖች እጅ እንዲሰጡ ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጣቸዉ በመዘርዘር ትዕዛዙ እንዲታጠፍ ጠይቀዉ ነበር።

ትሩማን ጄኔራላቸዉን ለማሳመን ብዙ አልተጨነቁም።ጃፓኖች ፐርል ወደብ ላይ ያደረሱትን ጥፋት ለጄኔራሉ አስታወሱት።«ለአዉሬ አፀፋ መስጠት ካለብሕ እንደአዉሬ ነዉ።»አከሉ ፕሬዝደንቱ።እና ኮሎኔል ፓዉል ቲቤስ በናታቸዉ ሥም ኢኖላ ጌይ ብለዉ በሰየሙት B-29 አዉሮፕላን ላይ ያን ቦምብ ጭነዉ ከጓዶቻቸዉ ጋር በአትላንቲክ ሰማይ ላይ ይከንፉ ያዙ።Littel boy አሉት አሜሪካኖች ትንሹ ልጅ፤ ትልቁን አጥፊ ቦምብ።ነሐሴ-ስድስት።1945 ጧት-አስደንጋጭ ፍንዳታ፤ ሐምራዊ ጢስ፤ ከፍተኛ ቃጠሎ---ሔሮሺማ----እልቂት።መቶ ሠላሳ ሺሕ ሕዝብ ረገፈ።በሰወስተኛዉ ቀን ሌላዋ የጃፕን ከተማ ተደገመች።ናጋሳኪ።ባንዴ ሰባ ሺሕ ሕዝብ አለቀ።ዘንድሮ-ሐሙስ ሄሮሺማ፤ ትናት ደግሞ ናጋሳኪ የዚያን ዕልቂት ሰለቦችን ሰባኛ ዓመት ዘከሩ።ያን ቦምብ የሠሩት ሳይቲስቶች ሎስ አልሞስ-ዩናይትድ ስቴትስ ሆነዉ የምርምር አጥፊ ዉጤታቸዉን በራዲዮ ይከታተሉ ነበር።ዊሊያም ሁድግንስ አንዱ ናቸዉ።የፊዝክስ አዋቂ።የዛሬ ሰባ ዓመቱን ስሜት አልረሱትም።ደስታም-ሐዘንም-ተስፋም ነበር ምስቅልቅል።ይሉታል

ደስታ አልነበረም።ብዙ ሕዝብ በተገደለበት እርምጃ የሚደሰቱበት ምክንያት አልነበረም።ከዉስጥ ያለዉ ዕዉነት ግን እርምጃዉ የጦርነቱን ጊዜ በማሳጠር ምናልባት የሚሊዮኖችን ሕይወት አድኗል የሚል ነዉ።እና እዚያ የነበረዉ (የሳይቲስቶቹ) ስሜት (ቦምቡ) በመሳካቱ እፎይታ እና ደስታ ነዉ።ዋናዉ ደግሞ ጃፓን ዉስጥ ብዙ ሰዎች ቢገደሉም ፤ ጦርነቱን በማሳጠር ብዙ ሕይወት መትረፉ ነዉ። በጣም የተወሳሰበ ነገር ነዉ።»

ባለፉት ሰባ ዓመታት ጃፓን ትቢያዋን አራግፋ-ከዓለም በምጣኔ ሐብት የሁለተኝነቱን ደረጃ ይዛለች።የሐብቱ ክምችት፤ የረቂቁ ቴክኖሎጂ ዕደገት፤ የምርምር ጥናቱ ሥርፀት፤ የዘመኑ እርቀትም ከዚያ ቦምብ የተረጨዉን መርዛማ ንጥረ ነገር ሙሉ በሙሉ ማጥፋት አልቻሉም።ዛሬም አካል-አዕምሯቸዉ የጎደለ ሕፃናት ይወለዳሉ።

የአጥፊዉን ቦምብም የጥፋት መጠን ዓለም ማወቁ-ጥፋቱ እንዳይደገም ከማድረግ ይልቅ የአጥፊዉ መሳሪያ ባለቤት ለመሆን ፖለቲከኞችን ማጣደፉ እንጂ ድንቁ።ዛሬ ከዩናይትድ ስቴትስ እስከ ሩሲያ፤ ከፈረንሳይ እስከ ብሪታንያ፤ ከቻይና እስከ ሕንድ፤ እስከ ፓኪስታን ያሉ መንግሥታት በማጥፋት አቅሙ ከያኔዉም ቦምብ እጅግ የረቀቀ-የጠከረዉን የኒኩሌር ቦምብ ታጥቀዋል።ሰሜን ኮሪያ የኒኩሌር ቦምብ እንዳላት አምናለች።እስራኤልም በይፋ አትመን እንጂ ቦምቡን መታጠቋን ብዙዎች «የአደባባይ ሚስጥር» ይሉታል።

ኢራን የኑክሌር ቦምብ እንዳታመርት የዩናይትድ ስቴትስና ተባባሪዎችዋ ሐገራት ፖለቲከኞች ከኢራን መሪዎች ጋር ያደረጉትን ስምምነት አጥብቃ የምትቃወም አንዲት ሐገር አለች።እስራኤል።የእስራኤልን አቋም በመደገፍ የኑክሌር ቦምብ እንዳይመረት የተደረገዉን ስምምነት የሚቃዉሙ በርካት የአሜሪካ ፖለቲከኞች አሉ።አብዛኞቹ የወግ አጥባቂ ፓርቲ አባላት ናቸዉ።

የእስራኤል መሪዎችና የዩናይትድ ስቴትስ ወግ አጥባቂ ፖለቲከኞች የሰላም ስምምነቱን መቃወማቸዉ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት እስካሁን የነበረዉ ፍጥጫ፤ ጠብ እና ቁርቁስ ይቀጥል፤ኢራንም የኑክሌር ቦምብ ለማምረት ማድባትዋን ትግፋበት ከማለት መለየቱ ሲበዛ አጠራጣሪ ነዉ።የጃፓኑ ጠቅላይ ሚንስትር ሺንዞ አቤ የሔሮሺማዉ እልቂት ባለፈዉ ሐሙስ ሲከበር እንዳሉት ዓለም ከኑክሌር ቦምብ ነፃ እንድትሆን መንግሥታቸዉ የሚያደርገዉን ጥረት ያጠናክራል።

«ዓለም ከኑክሌር ቦምብ እንድተፀዳ ጃፓን የጀመረችዉን ጥረት ለማጠናከር አቅዳለች።ኑክሌር በታጠቁት እና ኑክሌር በሌላቸዉ መንግሥታት መካከል ትብብር ከሌለ ኑኬሌር ቦምብን ማጥፋት አይቻልም።በሚቀጥለዉ መፅዉ የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንዲጠፋ የሚጠይቅ አዲስ ረቂቅ ሐሳብ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እናቀርባለን።»

የአቤ መልዕክት ከሰባ ዓመት በፊት የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ሐሪ ኤስ ትሩማን ሳንፍራንሲኮ ላይ ካደረጉት ጋር ይመሳሰላል።ትሩማን ሥለ ጦርነት መቆም፤ ሥለ ዓለም ሰላም የተናገሩት ያን አዉዳሚ ቦምብ ጃፓን ላይ የሚጥሉበትን ሥልት እያዉጠነጠኑ ነበር።አቤ የኒክሌር ቦምብ እንዲታገድ እንጠይቃለን ያሉትም የጃፓን ጦር ሌላ ሐገር ዘምቶ እንዳይዋጋ የሚያግደዉን ሕግ-አሽረዉ ጦሩ ዘምቶ እንዲዋጋ በሚፈቅድ ሕግ ለመተካት የሚያስችላቸዉን ዕቅድ ለምክር ቤታቸዉ ባቀረቡ ማግስት ነዉ።

አቤ ኑክሌር ቦምብ ለማሳገድ የያዙት ዕቅድ ከልብ ቢሆን እንኳ እስከ ዛሬ የኒኩሌርን ቦምብ በፍቃድዋ ያጠፋች-ሐገር አንድ ብቻ መሆንዋ መዘንጋት የለበትም።ደቡብ አፍሪቃ።የኑክሌር ቦምብ ለመስራት የነበራትን ዕቅድ፤ በግፊትም፤ በስምምነትም፤ በማባበልም የሠረዘችዉ ደግሞ የኮሎኔል ሙዓመር ቃዛፊዋ ሊቢያ ነበረች።ቃዛፊ አጥፊዉን ቦምብ ለመስራት የነበራቸዉን ዕቅድ መሠረዛቸዉ እራሳቸዉን፤ መንግሥታቸዉን፤ ሐገራቸዉንም ከማጥፋት አላዳናቸዉም።

የዩናይትድ ስቴትስ አዉቶሚክ ቦምብ የጃፓን ከተሞችን ከነ-ሕዝባቸዉ ያወደመበት ሰባኛ ዓመት ባለፈዉ ሳምንት ከመዘከሩ ከጥቂት ቀናት በፊት ቦምቡ የተሰራበትን ሥፍራ ጀርመናዊዉ የፊዚክስ ተማሪ ጎብኝቶ ነበር።ማርክስ ነዉ ስሙ።ሃያ አራት ዓመቱ።ፊዝክስን በጣም ይወዳል።እንደ ቦምብ ሠሪዎቹ ሳይንቲስቶች ሁሉ ፊዝክስን በጣም ለማወቅ ይታትራል።ጎበዝ ተማሪም ነዉ።ግን እንዲሕ አለ።«ቦምቡ ባይሰራ ጥሩ ነበር።አሁን ግን ተሠርቷል።እና እንደሚመስለኝ አስተማማኝ ወገኞች እጅ መሆን አለበት።(ኑኬሌር ያማዝዝ የነበረዉ) ቀዝቃዛዉ ጦርነት መቀዝቀዙም ጥሩ ነዉ።»

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic