1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአዉሮፓ ህብረት የፕሬዝደንትነት መንበርና ፖርቱጋል

ሰኞ፣ ሰኔ 25 1999

ትናንት ፖርቱጋል የቀጣዩን ስድስት ወራት የአዉሮፓ ህብረት የፕሬዝደንትነት መንበር ተረክባለች።

https://p.dw.com/p/E0c2
ሶቅራጥስ ከጀርመን የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሲረከቡ
ሶቅራጥስ ከጀርመን የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር ሲረከቡምስል AP
የአዉሮፓ ህብረት የፕሬዝደንትነት የስልጣን ዘመን ማለት በርካታ ሃላፊነቶችና የሚከወኑ ተግባራትን አጣምሮ የሚያሸክም ነዉ። 80ሚሊዮን ኗሪ ያላት ጀርመን ባሳለፈችዉ የስልጣን ዘመኗ ያከናወነችዉ ፍሬያማ ተብሏል። ከፖርቱጋል ደግሞ በተለይ በአዉሮፓና በአፍሪቃ ጋ መካከል የሚኖረዉ ግንኙነት ላይ ትኩረት ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል።
10ሚሊዮን ህዝብ ያላት ፓርቱጋል ነበረች በ16ና በ17ናዉ ክፍለ ዘመን ወደምድረ አፍሪቃ እግሯን ያስገባች አዉሮጳዊት አገር። ለዚህም ይመስላል በስድስት ወሩ የአዉሮጳ ህብረት የፕሬዝደንትነት የስልጣን ዘመኗ ሁለቱን አህጉሮች ይበልጥ ለማስተሳሰር ያለለመችዉ። በምዕራብ አፍሪቃ በሴኔጋልና ጊኒ ጀመራ መልክዓ ምድሩ በፈቀደላት ተንሰራፍታ ወደደቡብ አንጎላን ሁሉ አዳርሳለች። ይህ መልክዓ ምድራዊ ሁኔታ ዛሬም በፖሊሲ ረገድ የራሱን ሚና ይጫወታል።
ፓርቱጋል በአሁኑ ሰዓት ባለፈዉ ወደሌላ አህጉር በባህር ላይ ያደረገችዉን ጉዞ መቀኘት ጀምራለች። ሆኖም ህልሟን የሚከተል ተግባር ከፊቷ ተደቅኗል። የአገሪቱ ፕሬዝደንት ሆዜ ሶቅራጥስ በህብረቱ ፕሬዝደንትነት ስልጣናቸዉ የዉጪ ፖሊሲዉ ወደደቡብ የሚያቀናበትን መንገድ ይሞክራሉ። አፍሪቃ ይላሉ ሶቅራጥስ በህብረቱ ከተዘነጋች ከራርማለች፤
«ያ ትልቅ ስህተትና ሃላፊነት የጎደለዉ ነበር፤ ላለፉት ሰባት ዓመታት ከአፍሪቃ ጋ ጉባኤ አልተቀመጥንም፤ ያ ደግሞ ለአዉሮፓም ሆነ ለአፍሪቃ ፍላጎት በጣም አፍራሽ ነዉ። በዚያም ላይ በርካታ ልንነጋገርባቸዉ የሚገቡ ጉዳዮች አሉ።»
ይህን መሰሉ አስተያየት የስቅራጥስ ብቻ አይደለም። ስፓኝ፤ ጣሊያን፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ ፈረንሳይ ወደደቡብ እናቅና ባዮች ናቸዉ። እናም የቀድሞዋ ግንባር ቀደም የአፍሪቃ ቅኝ ገዢ ፓርቱጋል ይህን ለማቀናበር ይሳካላታል፣ በፖርቱጋል ኮይምብራ ዩኒቨርሲቲ የስነሰብ ምሁር የሆኑት ፓዉል ፓዮክሶቶ
«ከአዉሮፓ እይታ ብቻ ልንሰራ አንችልም። ከአፍሪቃና ከብራዚል ጋ የነበረንን የድሮ ግንኙነት ማደስ የግድ ይኖርብናል። ይህን የተለየ ነገር ነዉ ፖርቲጋል ወደአዉሮፓ ህብረት ልታመጣ የምትችለዉ።»
በዚህ የአዉሮፓ ዓመት መገባደጃ በሚካሄደዉ የአዉሮፓና የአፍሪቃ ጉባኤ ስደትና ምጣኔ ሃብትን የተመለከተ ዉይይት ይኖራል። በምጣኔ ሃብት ማሳደግ ረገድም ከቻይናና ሩሲያ ጋ የሚኖረዉን ፊክክር ለማሸነፍም ፓርቱጋል እንደአንጎላ፤ ሞዛምቢክና ጊኒ ካሉ የቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ ጋ የመሰረተችዉን መልካም ግንኙነትም ለአዉሮፓ ትከፍታለች። ይህ ሃሳቧ ጋ ግን ሁሉንም አላስደሰተም። በተለይም ምስራቅ አዉሮፓ ላይ ትኩረት እንዲደረግ የምትፈልገዉ ጀርመን አትስማማበትም። ታዋቂዉ ፓርቱጋላዊ የታሪክ ምሁር ፌርናንዶ ሮዛስ አሁን ህብረቱ ዉስጥ ዉጥረት መጣ ማለት እንደሆነ ነዉ የሚናገሩት፣
«ይህ ወደአፍሪቃ እንመለስ የሚለዉ አዝማሚያ ህብረቱ ያለዉን መሰረታዊ መነሻ የሚጎዳ ነዉ። ማዕከላዊዉንና የረዥም ጊዜንዉ ዕቅድ በመምረጡ ረገድ ዉጥረቱ ተፈጥሯል።»
የአዉሮፓ ህብረት የፕሬዝደንትነት የስልጣን ዘመን ለየባለተራዎቹ ለአህጉሪቱ በጋራ የሚበጅ ምጣኔ ሃብታዊም ሆነ ፖለቲካዊ ትርፍ ማስገኛ አጋጣሚ ነዉ። ጀርመን ስልጣኑን ተረክባ ፍሬያማ ተግባራት ማከናወኗን አስመልክቶ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ተወድሰዋል። ፖርቱጋል ሃላፊነቱን አሁን ትረከብ እንጂ ቀድሞ ስልጣኑን ይዞ ከነበረዉ ወገን ጋ በቅርብ አብሮ መስራት ስኬት እንዲቀጥል የአዉሮፓ ህብረት መለያ ነዉ።