የአዉሮጳ የስደተኞች ፖሊሲና ትችቱ | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 16.02.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

የአዉሮጳ የስደተኞች ፖሊሲና ትችቱ

በአደገኛ የባህር ጉዞ አዉሮጳ ለመግባት ከሚሞክሩ ስደተኞች የባህር ሲሳይ ሆነው የሚቀሩት ጥቂት የሚባሉ አይደሉም ። በዚህን መሰል ጉዞ የሚደርስ የስደተኞችን ሞት ለማስቀረት ወይም ለመቀነስ የአዉሮጳ ባለሥልጣናት የስደተኞች ጉዳይ መርሃቸውን እንዲቀይሩ ተጠይቀዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:00
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:00 ደቂቃ

የአውሮፓ የስደተኞች ፖሊሲ እና ትችቱ

ህይወታቸው የሚያልፍ ብዙዎች ናቸው ። ጎሮጎሮሳዊው 2016 ዓም ከገባበት ከዛሬ አንድ ወር ከአስራ አምስት ቀን ወዲህ ብቻ ከ400 በላይ ስደተኞች የተሳፈሩባቸው ጀልባዎች ሰጥመው ህይወታቸው አልፏል ። በቀደመው በ2015 ዓም ደግሞ 4ሺህ የሚጠጉ ስደተኞች ይህ እጣ ገጥሟቸዋል ። ወደ አዉሮጳ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞች ሞት እንዲቀር መወሰድ አለባቸው ያለውን እርምጃ የጠቆመው አንድ ጥናት በቅርቡ እንዳስታወቀው አውሮጳውያን እስካሁን ስደተኞች ወደ ክፍለ ዓለሙ እንዳይመጡ ለመገደብ የሚወስዷቸው እርምጃዎች ውጤት ሊያመጡ አለመቻላቸውን ያስረዳል ። ጀሲካ ሃገን ዜንከር ጥናቱን ያካሄዱ ፣የለንደኑ የባህር ማዶ የልማት ጥናት ተቋም Overseas Development Institute ባልደረባ ናቸው ። የአዉሮጳውያን መርሆች ውጤት አልባ የሆኑበትን ምክንያት ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ተናግረዋል ።
«ሰዎች ወደ አዉሮጳ ለመምጣት የሚወስኑት ምርጫ ስለሌላቸው ነው ። እዚህ ውሳኔ ላይ የሚደርሱትም እነርሱ በሚያምኑት መረጃ መሠረት ነው ። እነዚህን መረጃዎችም ከቤተሰብ አባላት እና ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ነው የሚያገኙት ። እናም በጥናታችን እንደደረስንበት በመጀመሪያ ደረጃ ወደ አውሮጳ የሚደረግ ስደትን ለመከላከል የሚወጡ ማናቸውም ፖሊሲዎች ፣ሰዎች ወደ አውሮጳ እንዳይመጡ ሊከላከሉ አይችሉም ።የስደቱን አቅጣጫ ግን ከአንዱ ሃገር ወደ ሌላው ያስቀይራሉ ።»
ለዚህም ሃገን ዜንክነር በምሳሌነት ያነሱት ከወራት በፊት ሃንጋሪ ድንበሯን ስታጥር ስደተኞች ወደ ሃንጋሪ መግባታቸው ይቁም

እንጂ ስደቱ ወደ በክሮኤሽያና ወደ በስሎቬንያ በኩል መቀጠሉን ነው ።
በቅርቡ ጀርመን ብሪታንያ እና ስፓኝ የገቡ 52 የሶሪያ የኤርትራ እና የሴኔጋል ስደተኞችን በማነጋገር የተካሄደው ጥናት እንዳስታወቀው ስደተኞቹ ከሃገራቸው የሚወጡት በተለያዩ ግን ተቀራራቢ በሆኑ ምክንያቶች ነው ። የሚጀምሩት አደገኛ ጉዞም በትንሽ ገንዘብም ይሁን በአጭር ጊዜ የሚወጡት አይደለም ።
Oton 2«ያነጋገርናቸው ሰዎች ግጭቶችን ግድያዎችን የሚሸሹ ናቸው ። አንዳንዶቹ ደግሞ በድህነት ምክንያት ነው የሚሰደዱት ። ወደ አውሮጳ ለመምጣት ብዙ ገንዘብ ያስፈልጋል ። አብዛኛዎቹ ለጉዞአቸው የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የሚያጠራቅሙት በመንገዳቸው ላይ በሚገቡባቸው አገራት እየሰሩ ነው ። ከጉዞዎቹ አብዛኛዎቹ አጭርና በቶሎ የሚደረሱ አይደሉም ። ዓመታት ሊወስዱ ይችላሉ ። በአንድ ሃገር መኖር ከጀመሩ በኋላ ጉዞአቸውን ለመቀጠል ይወስናሉ ። »
ለሞትና ለከፋ ስቃይ የሚዳርገውን ይህን መሰሉን ስደት ለማስቆም ሃገን ዜንክነር እንደሚሉት የአዉሮጳ ፖሊሲ አውጭዎች የተናጠል የስደት ፖሊሲን ወደ ጎን በመተው አካባቢያዊ ቀውስ የፈጠረውን ይህን ችግር ለመቋቋም በአውሮጳ ደረጃ የተቀናጀ እርምጃ መውሰድ አለባቸው ። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ደግሞ ሶስት ጉዳዮች ሊተኮርባቸው ይገባል ይላሉ ።
«በመጀመሪያ ደረጃ ፖሊሲ አውጭዎች የስደተኞች ጉዞ ከአደጋ ነፃ እንዲሆን ማደረግ አለባቸው ፣ ስደተኞችን የመታደግ ተልዕኮዎች ፣ ሰብዓዊ ቪዛ እንዲሁም ህጋዊ የስደት አማራጮችን ማስፋት ፣አውሮጳ አቀፍ ፈጣንና የተሻለ የተገን አሠጣጥ ስርዓት መዘርጋት አለባቸው ።የተገን ማመልከቻዎችን በፍጥነት በተመሳሳይ መንገድና በአውሮጳ በአጠቃላይ ሃላፊነትን በመጋራት ማስተናገድ ይገባቸዋል ።በመጨረሻም ፖሊሲ አውጭዎች ስደተኞች ከሚያስገኙት ማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ጥቅሞች ተቋዳሽ ለመሆን ለምሳሌ በኤኮኖሚያዊ የውህደት መርሃ ግብር ላይ መዋዕለ ንዋያቸውን በማፍሰስ ሃይማኖትን መሰረት ያላደረገ የስደት መርሃ ግብር መዘርጋት አለባቸው ።»
ስለዚህ ይላሉ በጉዳዩ ላይ ምርምር ያካሄዱት የODI ባልደረባ ሃገን ዜንክነር ለምሳሌ የአውሮጳ መንግሥታት ወደ አውሮጳ

ለመሻገር ያለሙ ስደተኞች በብዛት በሚገኙባቸው ቱርክና ሊቢያን በመሳሰሉ ሃገራት የቆንስላ ቢሮዎችን በመክፈት ተዓማኒ የሆነ የተገን ጥያቄ ለሚያቀርቡ ሰዎች ሰብዓዊ ቪዛ መስጠት ይችላሉ ። አንዳንድ የአውሮጳ መንግሥት ወደ አውሮጳ የሚሰደዱ ሰዎችን ቁጥር መቀነስ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ዜጎቻቸው በብዛት ከሚሰደዱባቸው ሃገራት መንግሥታት ጋር እየተደራደሩ ነው ። በተለይ ዜጎችን በመጨቆንና ነፃነታቸውን በመንፈግ ከሚተቹ መንግሥታት ጋር የሚካሄደው ይህን መሰሉ ድርድር ጠንካራ ወቀሳ እየተሰነዘረበት ነው ። ሃገን ዜንክነር ይህም ቢሆን አሁን ለተፈጠረው ችግር መፍትሄ እንደማይሆን ነው የገለፁት ።
«በርግጥም የስደትን መሠረታዊ ምክንያቶች ከምንጩ ማድረቅ አንድ የፖሊሲ እርምጃ አካል መሆን ይገባዋል ። እናም ይህ በጣም አስፈላጊ ነው ። መሠረታዊውን ችግር ማስወገድ ችግሩን በረዥም ጊዜ መከላከል የምንችልበት መንገድ ነው ። በአጭር ጊዜ ውስጥ ግን ያን ያህል የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም ። ስለዚህ ለአጭር ጊዜ መፍትሄ የሚሆነን የተሻሉ የስደት ፖሊሲዎችን ማካሄድ ያስፈልገናል ። »
በጥናቱ እንደተገለፀው ስደተኞች አውሮጳ እስኪደርሱ እያንዳንዳቸው በአማካይ እስከ 3,880 ዶላር አውጥተዋል ። መንገድ ላይም ለከፉ ችግሮች ይጋለጣሉ ። ከኤርትራውያኑ ስደተኞች ግማሽ ያህሉ ገንዘብ እንዲያመጡ ታግተዋል ። አንድ ሶስተኛው ደግሞ ተዘርፈዋል ። ስደተኞች ይህን መሰሉ በደል የሚፈፀምባቸው ደግሞ በህገ ወጥ ደላሎች ብቻ አይደለም ።
«ሰዎችን በህገ ወጥ መንገድ ከአንዱ ሃገር ወደ ሌላው የሚያሻግሩት ብቻ አይደሉም በሰዎች ስደት የሚያተርፉት ። በጥናታችን እንደደረስንበት ስደተኞች ለአደጋ የተጋለጡ እንደመሆናቸው መንገድ ላይ በሌሎች ሰዎችም የሚበዘበዙበት ብዙ አጋጣሚዎች ይፈጠራሉ ። በህገ ወጥ አሻጋሪዎች ብቻ ሳይሆን በታጠቁ ቡድኖችና በተራ ዜጎችም ይዘረፋሉ ። ካነጋገርናቸው መካከል አንድ ሶስተኛዎቹ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በኃይል ገንዘባቸውን ተቀምተዋል ። ህገ ወጥ አሻጋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ሾፌሮችም ድንበር ጠባቂዎችም ይህን ሊያደርጉ ይችላሉ ።»
በሃገን ዜንክነር አስተያየት ሰዎችን ለዚህ ሁሉ ችግር የሚዳርገውን ስደትንና ህገወጥ የሰዎች አሸጋጋሪዎችን መከላከያው መንገድ

አንድ ብቻ ነው ።
«ህገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎችን እንዴት እንዋጋ ለሚለው እነርሱን ከዚህ ሥራ ውጭ ለማድረግ የሚያስችል የተሻለው መንገድ በመጀመሪያ ደረጃ የሰዎችን ህገ ወጥ ጉዞን ማስቆም ነው ። ሰዎች ደህንነቱ በተረጋገጠ እና በህጋዊ መንገድ አውሮጳ መምጣት የሚችሉበት እድል ከተሰጣቸው ወደ ህገ ወጥ አሻጋሪዎች አይሄዱም ።ህገ ወጥ አሻጋሪዎችም ከነዚህ ለአደጋ ከተጋለጡ ስደተኞች ትርፍ ማጋበስ ባልቻሉም ነበር ።»
የሰሜን አትላንቲክ የጋራ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት በምህፃሩ ኔቶ በሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች የሚፈጽመውን ወንጀል ለማስቆም በሚደረገው ጥረት ቱርክና ግሪክን ለማገዝ ባለፈው ሳምንት መርከቦቹን ወደ አግያን ባህር አሰማርቷል። ኔቶ መርከቦቹን የላከውው በቱርክና በሶሪያ ድንበር ላይ የሚካሄደውን የሕገ ወጥ የሰዎች አሻጋሪዎች እንቅስቃሴንም ለመቆጣጠር መሆኑን አስታውቋል ። የODI ዋ ጀሲካ ሃገን ዜንከር ግን ይህ እርምጃው ችግሩ ሊያስወግድ አይችልም ይላሉ ።
«የሜዴቴራንያን ባህርን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር የሚቻል አይመስለኝም ። በርካታ የባህር ዳርቻዎች አሉ ። በግሪክም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች በርካታ ጥቃቅን ደሴቶች ይገኛሉ ። ኔቶ ወይም የቱርክ ባለሥልጣናት የህገ ወጥ ደላሎችን እንቅስቃሴ ከአንድ የባህር ዳርቻ ማስቆም ቢችሉ ደላሎቹ አንድ 20 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ ሌላ የባህር ዳርቻ ሆነው ይህንኑ ሥራቸውን ያከናውናሉ ። ሰዎችም በዚህ መንገድ ወደ አውሮጳ መምጣታቸው ይቀጥላል ።»
፣የለንደኑ የባህር ማዶ ልማት ጥናት ተቋም Overseas Development Institute በጥናቱ ማጠቃለያ በመፍትሄነት ከጠቆማቸው መካከል ፣ አውሮጳ አቀፍ ፍትሃዊ የተገን አሰጣጥ ስርዓት እንዲዘረጋ አባል ሃገራትም በዚህ ረገድ ሃላፊነታቸውን በጋራ እንዲወጡ ያቀረበው ጥሪ ይገኙበታል ።በሜዲቴራንያን ባህር ስደተኞች መታደግ የሚያስችሉ ተልዕኮዎችን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ እና ፖለቲከኞችም ሆኑ ህህቡ ስደተኞችን እንደ ችግር ፈጣሪ ሳይሆን እንደሃብት ሊያያቸው እንደሚገባ አሳስቧል ።

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሀመድ

Audios and videos on the topic